Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 1፡ ሐጢያት

[1-2] ሰዎች ሐጢያተኞች ሆነው የተወለዱ ናቸው፡፡ ‹‹ ማርቆስ 7፡20-23 ››

ሰዎች ሐጢያተኞች ሆነው የተወለዱ ናቸው፡፡
‹‹ ማርቆስ 7፡20-23 ››
‹‹እርሱም አለ፡- ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው፡፡ ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸውና፡፡ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል፤ ሰውንም ያረክሰዋል፡፡››
 
 

ሰዎች ግራ ተጋብተው በራሳቸው ምናቦች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ 

 
ይበልጥ የመዳን ዕድል ያለው ማነው? 
ራሱን የከፋ ሐጢያተኛ እንደሆነ አድርጎ የሚያስብ ሰው ነው፡፡ 

ከሁሉ በፊት አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ እወዳለሁ፡፡ ራሳችሁን የምታዩት እንዴት ነው? በጎ ወይም መጥፎ እንደሆናችሁ ታስባላችሁን? ምን ይመስላችኋል?
ሰዎች ሁሉ የሚኖሩት በራሳቸው ምናቦች ውስጥ ነው፡፡ እንደምታስቡት መጥፎ ላትሆኑ ትችላላችሁ፡፡ እንደምታስቡትም ጥሩዎች አትሆኑ ይሆናል፡፡   
የተሻለ የእምነት ሕይወትን የሚመራ ማን ይመስላችኋል? ራሱን/ራስዋን ጥሩ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡት? ወይስ ራሱን/ራስዋን መጥፎ አድርገው የሚያስቡት? 
የኋለኞቹ ናቸው፡፡ ሌላ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ይበልጥ የመዳን ዕድል ያለው ማነው? ብዙ ሐጢያቶችን የሰራ ወይስ ጥቂት ሐጢያቶችን ብቻ የሰራ? በርካታ ሐጢያቶችን እንደሰራ የሚያምን እርሱ/እርስዋ ብዙ የመዳን ዕድል አለው፡፡ ምክንያቱም ግለሰቡ እርሱ/እርስዋ  የከፋ ሐጢያተኛ መሆኑን አምኖዋልና፡፡ ይህ ግለሰብ እርሱ/እርስዋ ኢየሱስ ለእርሱ ያዘጋጀለትን የቤዛነት ቃል በተሻለ መንገድ መቀበል ይችላል፡፡ 
ራሳችንን በትክክል ስንመለከት የሐጢያት ክምችቶች ብቻ እንደሆንን የተረጋገጠ ነው፡፡ ሰዎች ምንድናቸው? ሰው ‹‹የክፉ አድራጊዎች ዘር›› ብቻ ነው፡፡ በኢሳይያስ 59 ላይ በሰዎች ልቦች ውስጥ ሁሉም አይነት በደሎች እንደሚገኙ ተጠቅሶዋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች የሐጢያት ክምችቶች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም የሰውን ዘር እንደ ሐጢያት ክምችት የምንገልጠው ከሆነ ብዙዎች አይስማሙም፡፡ ነገር ግን ሰውን ‹‹የክፉ አድራጊዎች ዘር›› አድርጎ መግለጡ ትክክለኛ መግለጫ ነው፡፡ ራሳችንን በቅንነት ከተመለከትን ክፉዎች መሆናችን ግልጽ ነው፡፡ ለራሳቸው እውነተኞች የሆኑ ሰዎች ወደዚህ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ መድረስ አለባቸው፡፡   
ነገር ግን አብዛኛው ሰው በእርግጥም የሐጢያት ክምችት መሆኑን ለማመን አሻፈረኝ የሚል ይመስላል፡፡ ብዙዎች ተመችቶዋቸው ይኖራሉ፡፡ ምክንያቱም ራሳቸውን ሐጢያተኛ አድርገው አይቆጥሩምና፡፡ እኛ ክፉዎች ስለሆንን በሐጢያት የተሞላ ስልጣኔን ፈጥረናል፡፡ ይህ እውነት ባይሆን ኖሮ ሐጢያት ለመስራት እጅግ ባፈርን ነበር፡፡ ሆኖም ብዙዎቻችን ሐጢያቶችን ስንሰራ አናፍርም፡፡  
ሕሊናቸው ግን ያውቃል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ‹‹ይህ አሳፋሪ ነው›› ብሎ የሚነግረው ሕሊና አለው፡፡ አዳምና ሔዋን ሐጢያት ከሰሩ በኋላ በዛፎች መካከል ተሸሸጉ፡፡ ዛሬ ብዙ ሐጢያተኞች የሐጢያት ባህል ከሆነው ብልሹ ባህላችን በስተ ጀርባ ይደብቃሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ፍርድ ለመሸሽ አብረዋቸው ባሉ ሐጢያተኞች መካከል ይደብቃሉ፡፡  
ሰዎች በራሳቸው ምናቦች የተታለሉ ናቸው፡፡ ከሌሎች ይልቅ በጣም ሰናይ እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ያስባሉ፡፡ ስለዚህ አንዳንድ መጥፎ ዜናዎችን ሲሰሙ በቁጣ ‹‹ሰው እንዴት እንዲህ ያሉ ነገሮችን ያደርጋል? ሰው እንዴት ያንን ያደርጋል? በማለት ይጮሃሉ፡፡ እነርሱ ራሳቸው እነዚህን ነገሮች እንደማያደርጉ ያምናሉ፡፡ 
የተወደዳችሁ ወዳጆች ራሳችሁን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ራሳችንን በትክክል ለማወቅ በመጀመሪያ የሐጢያቶችን ስርየት መቀበል አለብን፡፡ ሰዋዊ ባህሪያችንን በትክክል ለማወቅ ረጅም ጊዜ ይወስድብናል፡፡ እስከ ዕለተ ሞታችንም ድረስ ይህንን ፈጽሞ የማናውቅ ብዙዎች እንኖራለን፡፡  
 
 
ራሳችሁን እወቁ፡፡
 
ራሳቸውን የማያውቁ ሰዎች የሚኖሩት እንዴት ነው?
ሐጢያተኛ ማንነታቸውን ለመደበቅ በመሞከር የግብዝነትን ኑሮ ይኖራሉ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን በትክክል የማያውቁ ሰዎች ያጋጥሙናል፡፡ ሶቅራጥስ ‹‹ራስህን እወቅ›› አለ፡፡ ነገር ግን ብዙዎቻችን በልባችን ውስጥ ምን እንዳለ አናውቅም፡፡ መግደል፣ ስርቆት፣ ስስት፣ ክፋት፣ ማታለል፣ ብልሹነት፣ መመቅኘት…፡፡
ራሱን የማያውቅ ሰው በከንፈሮቹ ላይ የእባብ መርዝ እያለ ስለ በጎነት ይናገራል፡፡ ምክንያቱም ሰውየው የማያመልጥ ሐጢያተኛ ሆኖ መወለዱን ስለማያውቅ ነው፡፡ 
በዚህ ዓለም ላይ እውነተኛ ባህሪዎቻቸውን የማያውቁ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ራሳቸውን አታለዋል፡፡ ሕይወታቸውንም በራሳቸው መታለሎች ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሸፍነው ይኖራሉ፡፡ ራሳቸውን በማታለላቸው ማንነታቸውን ወደ ሲዖል እየወረወሩ እንደሆኑ አይረዱም፡፡   
 
 

ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ያለ ማቋረጥ ሐጢያትን ያንጠባጥባሉ፡፡

 
እነርሱ ሲዖል የሚገቡት ለምንድነው?
ራሳቸውን ስለማያውቁ ነው፡፡

ማርቆስ 7፡21-23ን እንመልከት፡- ‹‹እርሱም አለ፡- ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው፡፡ ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸውና፡፡ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል፤ ሰውንም ያረክሰዋል፡፡›› የሰዎች ልቦች ከተጸነሱበት ዕለት አንስቶ በሐጢያት የተሞሉ ናቸው፡፡  
የሰው ልብ ከብርጭቆ የተሰራና እስከ አፍ ገደፉ ድረስ በቆሻሻ ፈሳሽ ማለትም በሐጢያቶቻችን የተሞላ ነው ብለን እናስብ፡፡ ይህ ሰው ወደኋላና ወደፊት ሲንቀሳቀስ ምን ይፈጠራል? ቆሻሻው ፈሳሽ (ሐጢያት) በተደጋጋሚ በየቦታው ይንጠባጠባል፡፡ 
እኛ የሐጢያት ክምችቶች የሆንን ሰዎች ሕይወታችንን የምንኖረው ልክ እንደዚያ ነው፡፡ በየሄድንበት ሁሉ ሐጢያትን እናንጠባጥባለን፡፡ የሐጢያት ክምችቶች ስለሆንን በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ሐጢያት እንሰራለን፡፡ 
ችግሩ እኛ የሐጢያት ክምችቶች ወይም በሌላ አነጋገር የሐጢያት ዘሮች መሆናችንን አለማወቃችን ነው፡፡ እኛ የሐጢያት ክምችቶችና ከተወለድንበት ቀን አንስቶም በልቦቻችን ውስጥ ሐጢያት ያለብን ነን፡፡  
የሐጢያት ክምችቶች ሊፈስሱ ተዘጋጅተዋል፡፡ ነገር ግን ሰዎች በተፈጥሮዋቸው ሐጢያተኞች መሆናቸውን አያምኑም፡፡ ሌሎች ወደ ሐጢያት እንደሚመሩዋቸው ስለሚያስቡ መጥፎዎቹ እነርሱ እንዳልሆኑ ያስባሉ፡፡ 
ሰዎች ሐጢያቶችን ከሰሩ በኋላ እንኳን ራሳቸውን ንጹህ አድርገው ለማጠብ የሚያስፈልገው ብቸኛው መጠይቅ ሐጢያትን መጥረግ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ሐጢያት በሰሩ ቁጥር ለራሳቸው ስህተቶቹ የእነርሱ እንዳልሆኑ በመናገር ራሳቸውን በመጥረግ መቀጠል ነው፡፡ ራሳችንን ስላነጻን ብቻ እያንጠባጠቡ መቀጠል ትክክል ነው ማለት ነው? ደጋግመን ያለ ማቋረጥ መጥረግ ይኖርብናል፡፡ 
ብርጭቆው በሐጢያት ሲሞላ መፍሰሱን ይቀጥላል፡፡ ውጭውን መጠራረግ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ውጭውን በሰናይ ምግባሮቻችን አዘውትረን ብንጠርገውም ብርጭቆው በሐጢያት እስከተሞላ ድረስ ጥቅም የለውም፡፡
እኛ ብዙ ሐጢያት ይዘን ስለተወለድን ምንም ያህል ሐጢያት በየመንገዱ ብናንጠባጥብ ልቦቻችን ከቶውኑም ባዶ አይሆኑም፡፡ ስለዚህ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ሐጢያቶችን እንሰራለን፡፡
ሰው በእርግጥም የሐጢያት ክምችት እንደሆነ የማያውቅ ከሆነ ሐጢያተኛ ባህሪውን በመደበቅ ይቀጥላል፡፡ ሐጢያት በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ ያለ ስለሆነ ውጭውን በማጽዳት አይወገድም፡፡ ትንሽ ሐጢያት ስናንጠባጥብ በጨርቅ እንጠርገዋለን፡፡ እንደገና ስናንጠባጥብ በትልቅ ጨርቅ…በፎጣ ከዚያም በመወልወያ…እንጠርገዋለን፡፡ ቆሻሻውን ደጋግመን የምንጠርገው ከሆነ ይጸዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ደጋግሞ መንጠባጠቡን ይቀጥላል፡፡  
ይህ የሚቀጥለው እስከ መቼ ይመስላችኋል? ሰውየው እስከሚሞትበት ቀን ድረስ ይቀጥላል፡፡ ሰዎች እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ ሐጢያትን ያደርጋሉ፡፡ ለመዳን በኢየሱስ ማመን የሚኖርብን ለዚህ ነው፡፡ ለመዳን በመጀመሪያ ራሳችንን ማወቅ ያስፈልገናል፡፡
 
የኢየሱስን ፍቅር በምስጋና የሚቀበል ማነው?
ብዙ ስህተቶችን መስራታቸውን ያመኑ ሐጢያተኞች ናቸው፡፡

ከሁለቱ ቆሻሻ የተሞሉ ብርጭቆዎች ጋር ሊነጻጸሩ የሚችሉ ሁለት ሰዎች አሉ እንበል፡፡ ሁለቱም ብርጭቆዎች በሐጢያት የተሞሉ ናቸው፡፡ አንዱ ራሱን ተመልክቶ ‹‹ኦ! እኔ እንዲህ ያለሁ ሐጢያተኛ ሰው ነኝ›› ይላል፡፡ ከዚያም ተስፋ ይቆርጥና ሊረዳው የሚችል ሰው ለመፈለግ ይሄዳል፡፡  
ሌላው ግን በእርግጥ ክፉ ሰው እንዳልሆነ ያስባል፡፡ በውስጡ ያለውን የሐጢያት ክምችት ማየት ስለማይችል ብዙም ሐጢያተኛ እንዳልሆነ ያስባል፡፡ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የተንጠባጠበውን መጥረጉን ይቀጥላል፡፡ በአንድ ጎን ያለውን ያጸዳል፤ ከዚያም በሌላ ጎን ያለውን ያጸዳል፡፡…ወዲያው ደግሞ ወደ ሌላው ወገን ይሄዳል…፡፡ 
መንጠባጠብን ለማስወገድ ሲሉ በተቻላቸው መጠን ትንሽ ሐጢያት ለመስራት በመሞከር ሕይወታቸውን በጥንቃቄ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም ድረስ በልባቸው ውስጥ ሐጢያት ስላለባቸው ይህ ምን ጥሩ ነገር ያመጣል? ጠንቃቃ መሆን ወደ ሰማይ አያቀርባቸውም፡፡ ‹ጠንቃቃ መሆን› በምትኩ ወደ ሲዖል በሚወስደው ጎዳና ላይ ያስቀምጣቸዋል፡፡  
ውድ ወዳጆች ‹ጠንቃቃ መሆን› የሚመራው ወደ ሲዖል ብቻ ነው፡፡ ይህንን ትምህርት በልባችን ውስጥ ማኖር ይገባናል፡፡ ሰዎች ጠንቃቆች ሲሆኑ ሐጢያቶቻቸው ብዙ አይንጠባጠቡ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሁንም ሐጢያተኞች ናቸው፡፡
በሰው ልብ ውስጥ ምን አለ? ሐጢያት? ብልሹነት? አዎ! ክፉ አሳቦች? አዎ! ስርቆት አለ? አዎ! ዕብሪት? አዎ!
በተለይ እንደዚያ ማድረግ ሳንማር ሐጢያት ስናደርግና ክፉ ነገር ስንሰራ የሐጢያት ክምችቶች የመሆናችንን እውነታ ከማመን በቀር ምንም ማድረግ አንችልም፡፡
ወጣት ሳለን ይህ አይታወቀን ይሆናል፤ ነገር ግን በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ እንዴት ነው? ወደ ከፍተኛ ትምህርት፣ ወደ ኮሌጅና ወ.ዘ.ተ ስንገባ በውስጣችን ያለው ነገር ሁሉ ሐጢያት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ይህ እውነት አይደለምን? እውነት ለመናገር ሐጢያተኛ ተፈጥሮዎቻችንን መደበቅ አንችልም፡፡ ትክክል? ምክንያቱም እያንዳንዳችን የሐጢያት ክምችት ሆነን ስለተወለድን ነው፡፡ 
ጠንቃቆች በመሆን ብቻ ንጹህ አንሆንም፡፡ ሙሉ በሙሉ ለመዳን እኛ ማወቅ የሚያስፈልገን የሐጢያት ክምችቶች መሆናችንን ነው፡፡ መዳን የሚችሉት ኢየሱስ ያዘጋጀውን ቤዛነት በምስጋና የሚቀበሉ ብቻ ናቸው፡፡
‹‹ብዙ ስህተት አልሰራሁም ወይም በጣም ብዙ ሐጢያት አልሰራሁም›› ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኢየሱስ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ እንደወሰደና ለሲዖል የታጩ እንደነበሩ የማያምኑ ናቸው፡፡ እያንዳንዳችን ከሐጢያት ጋር ስለተወለድን በውስጣችን ይህ የሐጢያት ክምችት እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ 
ሰው ‹‹ከዚህች ትንሽ ሐጢያት መዳን ብችል ኖሮ ብዙ ስህተት ባልሰራሁ ነበር›› ብሎ የሚያስብ ከሆነ በኋላ ላይ ከሐጢያት ነጻ ይሆናልን? ነገሩ ከቶውኑም ይህ ሊሆን አይችልም፡፡
መዳን የሚችል ሰው የሐጢያት ክምችት መሆኑን ያውቃል፡፡ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደና ስለ እኛ በሞተ ጊዜም የሐጢያቶችን ደመወዝ እንደከፈለ ከልቡ ያምናል፡፡
ብንድንም ባንድንም ሁላችንም በምናብ ውስጥ ለመኖር ያዘነበልን ነን፡፡ እኛ የሐጢያት ክምችቶች ነን፡፡ እንደዚያ ነን፡፡ ልንድን የምንችለው ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደ ስናምን ብቻ ነው፡፡
 
 
እግዚአብሄር ‹ቅንጣት ታህል› ሐጢያት ያለባቸውን ሰዎች አልተቤዣቸውም፡፡
 
ጌታን የሚያታልለው ማነው?
በየቀኑ ለሚሰራቸው ሐጢያቶች  ይቅርታን የሚለምን ሰው ነው፡፡

እግዚአብሄር ‹ቅንጣት ሐጢያት› ብቻ ያለባቸውን ሰዎች አያድንም፡፡ እግዚአብሄር ‹‹አምላኬ ያለብኝ እኮ ቅንጣት ሐጢያት ነች›› የሚሉትንም ቢሆን ትኩረት አያደርግባቸውም፡፡ እርሱ የሚራራላቸው ‹‹አምላኬ ሆይ እኔ የሐጢያት ክምችት ነኝ፤ እባክህ አድነኝ›› የሚሉትን ሰዎች ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ሐጢያተኞች የሆኑ ሰዎች ‹‹አምላኬ ሆይ አንተ ብታድነኝ እድናለሁ፤ በተደጋጋሚ ሐጢያት ከመስራት መቆጠብ እንደማልችል ስለማውቅ ከእንግዲህ ወዲያ ለንስሐ አልጸልይም፡፡ እባክህ አድነኝ›› ይላሉ፡፡
እግዚአብሄር ሙሉ በሙሉ በእርሱ የሚታመኑትን ያድናቸዋል፡፡ እኔም ራሴ በየቀኑ የንስሐ ጸሎቶችን ለመጸለይ ሞከርሁ፡፡ ነገር ግን የንስሐ ጸሎቶች ከቶውኑም ከሐጢያት ነጻ አላወጡኝም፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ፊት ተንበርክኬ ‹‹አምላኬ ሆይ እባክህ ራራልኝ›› በማለት ጸለይሁ፡፡ እንዲህ የሚጸልዩ ሰዎች ይድናሉ፡፡ በእግዚአብሄር ቤዛነትና በአጥማቂው ዮሐንስ በተከናወነው የኢየሱስ ጥምቀት ወደ ማመን ይመጣሉ፡፡ ይድናሉም፡፡    
እግዚአብሄር የሚያድነው ራሳቸውን የሐጢያት ክምችቶች፤ የክፉ አድራጊ ዘሮች አድርገው የሚያውቁትን ሰዎች ብቻ ነው፡፡ ‹‹እኔ የሰራሁት ይህችን ቅንጣት ሐጢያት ብቻ ነው፡፡ እባክህ ለዚህ ሐጢያት ይቅር በለኝ›› የሚሉ ሰዎች አሁንም ድረስ ሐጢያተኞች ስለሆኑ እግዚአብሄር ሊያድናቸው አይችልም፡፡ እግዚአብሄር የሚያድናቸው ፍጹም የሐጢያት ክምችቶች መሆናቸውን አምነው የሚቀበሉትን ሰዎች ብቻ ነው፡፡   
በኢሳይያስ 59፡1-2 ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፎዋል፡- ‹‹እነሆ የእግዚአብሄር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤ ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም፡፡ ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፤ እንዳይሰማም ሐጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል፡፡›› 
እኛ የሐጢያት ክምችቶች ሆነን ስለተወለድን እግዚአብሄር በፍቅር ሊመለከተን አይችልም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት እጁ ስላጠረች፣ ጆሮው ስለከበደች ወይም ይቅርታውን ስንጠይቀው ሊሰማን ስለማይችል አይደለም፡፡ 
እግዚአብሄር እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፤ እንዳይሰማም ሐጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል፡፡›› በልቦቻችን ውስጥ ብዙ ሐጢያት ስላለ በሮቹ ምንም ያህል ወለል ብለው ቢከፈቱም ሰማይ ልንገባ አንችልም፡፡    
እኛ የሐጢያት ክምችቶች የሆንን ሰዎች ሐጢያት በሰራን ቁጥር ይቅርታን ብንጠይቅ እግዚአብሄር ልጁን በተደጋጋሚ መግደል ሊኖርበት ነው፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ማድረግ አይፈልግም፡፡ እርሱ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹በየቀኑ ሐጢያቶቻችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ አትምጡ፡፡ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ያድናችሁ ዘንድ ልጄን ላኩላችሁ፡፡ እናንተ መረዳት የሚገባችሁ ነገር ቢኖር እርሱ ሐጢያቶቻችሁን መውሰዱንና ያም እውነት መሆኑን መቀበል ብቻ ነው፡፡ ከዚያም ለመዳን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እመኑ፡፡ እኔ ለእናንተ ለፍጡራኖቼ የሰጠኋችሁ እጅግ ታላቁ ፍቅር ይህ ነው፡፡››  
እርሱ የነገረን ይህንን ነው፡፡ ‹‹በልጄ እመኑና የሐጢያቶቻችሁንም ስርየት ተቀበሉ፡፡ እኔ የእናንተ አምላክ ለሐጢያቶቻችሁና ለበደሎቻችሁ ስርየት የገዛ ልጄን ላክሁ፡፡ በልጄ አምናችሁ ዳኑ፡፡››
ራሳቸውን የሐጢያት ክምችቶች እንደሆኑ አድርገው የማያውቁ ሰዎች ለእያንዳንዱ ትንሽ ሐጢያታቸው የእርሱን ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡ የሐጢያቶቻቸውን አስከፊ ክብደት ሳያውቁ በፊቱ ቀርበው ‹‹እባክህ ይህችን ትንሽ ሐጢያት ይቅር በለኝ፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ይህችን ሐጢያት አልሰራም›› ብለው ይጸልያሉ፡፡  
እግዚአብሄርን በእነዚህ ጸሎቶች ሊያታልሉት ይሞክራሉ፡፡ እኛ ሐጢያት የምንሰራው አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን እስክንሞት ድረስ በየጊዜው ሐጢያትን እንሰራለን፡፡ እስከ መጨረሻው የሕይወታችን ቀን ድረስ በየጊዜው ሐጢያትን እንሰራለን፡፡ እስከ መጨረሻው የሕይወታችን ቀን ድረስ ይቅርታን በመጠየቅ እንቀጥላለን፡፡ ምክንያቱም ሐጢያት መስራትን ማቆም አንችልምና፡፡ ሥጋችንም እስክንሞት ድረስ የሐጢያትን ሕግ ያገለግላልና፡፡ 
ለአንዲት ትንሽ ሐጢያት ይቅርታን ማግኘት የሐጢያትን ችግር አይፈታም፡፡ ምክንያቱም በየቀኑ በርካታ ሐጢያቶችን እንሰራለንና፡፡ ስለዚህ ከሐጢያት ነጻ መሆን የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወደ ኢየሱስ ማስተላለፍ ነው፡፡
 
የሰው ተፈጥሮ ምንድነው?
የሐጢያቶች ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሐጢያቶች ይዘረዝራል፡- ‹‹እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፡፡ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮዋል፡፡ ምላሳችሁም ሐጢአትን አሰምቶዋል፡፡ በጽድቅም የሚጠራ በእውነትም የሚፈርድ የለም፡፡ በምናምንቴ ነገር ታምነዋል፤ ሐሰትንም ተናግረዋል፤ ጉዳትን ጸንሰዋል፤ በደልንም ወልደዋል፡፡ የእባብን እንቁላል ቀፈቀፉ፤ የሸረሪትንም ድር አደሩ፡፡ እንቁላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፤ እንቁላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል፡፡ ድሮቻቸውም ልብስ አይሆኑላቸውም፡፡ በሥራቸውም አይሸፈኑም፡፡ ሥራቸውም የበደል ሥራ ነው፡፡ የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው፡፡ እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፤ የንጹሁንም ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፡፡ አሳባቸው የሐጢያት አሳብ ነው፡፡ ጉስቁልናና ቅጥቃጤ በመንገዳቸው አለ፡፡ የሰላምን መንገድ አያውቁም፤ በአካሄዳቸውም ፍርድ የለም፡፡ መንገዳቸውንም አጣመዋል፡፡ የሚሄድባትም ሁሉ ሰላምን አያውቅም፡፡›› (ኢሳይያስ 59፡3-8)    
የሰዎች ጣቶች በበደል የረከሱ ናቸው፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የሚያደርጉትም ነገር ሐጢያት ነው፡፡ እነርሱ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ክፉ ነው፡፡ ምላሶቻችንም ‹‹ሐሰትን ተናግሮዋል፡፡›› ከአፋችን የሚወጡት ነገሮች ሁሉ ውሸቶች ናቸው፡፡
‹‹ዲያብሎስ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፡፡›› (ዮሐንስ 8፡44) ዳግም ያልተወለዱ ሰዎች ‹‹የምነግርህ እውነቱን ነው፡፡…በእርግጠኝነት እየነገርኩህ ነው፡፡ የምናገረው እውነት ነው…›› ማለት ይወዳሉ፡፡ ነገር ግን እነርሱ የሚናገሩት ሁሉ ውሸት ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ ተጽፎዋል፡- ‹‹ዲያብሎስ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፡፡›› 
ሰዎች በባዶ ቃሎች ይታመኑና ውሸቶችን ይናገራሉ፡፡ ሰዎች ክፋቶችን ጸንሰው በደሎችን ይወልዳሉ፡፡ የእባብን እንቁላሎች ይቀፈቅፋሉ፡፡ የሸረሪት ድሮችንም ያደራሉ፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንቁላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፤ እንቁላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል፡፡›› በልባችሁ ውስጥ የእባብ እንቁላሎች እንዳሉ ይናገራል፡፡ የእባብ እንቁላሎች! በልባችሁ ውስጥ ክፋት አለ፡፡ በውሃውና በደሙ ወንጌል በማመን መዳን የሚኖርብን ለዚህ ነው፡፡  
ስለ እግዚአብሄር መናገር በምጀምርበት ጊዜ ሁሉ ‹‹ኦ ውዴ እባክህ ስለ እግዚአብሄር አትንገረኝ፡፡ አንድ ነገር ለማድረግ በምሞክርበት ጊዜ ሁሉ ሐጢያት ከውስጤ ይንጠባጠባል፡፡ እንደ ጎርፍ ይፈስሳል፡፡ በየቦታው ሐጢያት ሳላንጠባጥብ አንዲት እርምጃ አልራመድም፡፡ ምንም ላደርገው አልችልም፡፡ እኔ እጅግ በሐጢያት ተሞልቻለሁ፡፡ ተስፋ የለኝም፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ አትንገረኝ›› የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ 
ይህ ሰው የሐጢያት ክምችት እንደሆነ በእርግጠኝነት ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር በፍቅሩ ወንጌል አማካይነት ሙሉ በሙሉ እንዳዳነው ግን አያውቅም፡፡ መዳን የሚችሉት ራሳቸውን የሐጢያት ክምችቶች እንደሆኑ አድርገው የሚያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ 
ሁሉም ሰው እንደዚያ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ሁሉም ሰው በየሄደበት ስፍራ ሁሉ ያለ ማቋረጥ ሐጢያትን ያንጠባጥባል፡፡ ሰዎች ሁሉ የሐጢያት ክምችቶች ስለሆኑ ሐጢያት እንደ ጎርፍ ይፈስሳል፡፡ እኛ እንደዚህ ካለው ኑባሬ መዳን የምንችልበት ብቸኛው መንገድ የእግዚአብሄር ሐይል ነው፡፡ ይህ የሚያስገርም አይደለምን? በተበሳጩ፣ በተደሰቱ ወይም በተመቻቸው ቁጥር ሐጢያትን የሚያንጠባጥቡ ሰዎች መዳን የሚችሉት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ  እኛን ለማዳን መጣ፡፡  
እርሱ ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ ፈጽሞ ደምስሶዋቸዋል፡፡ የሐጢያት ክምችቶች መሆናችሁን አምናችሁ ተቀበሉና ዳኑ፡፡