Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 2፡ ሕጉ

[2-1] ነገሮችን በሕጉ መሰረት ብናደርግ ሕጉ ሊያድነን ይችላልን? ‹‹ ሉቃስ 10፡25-30 ››

ነገሮችን በሕጉ መሰረት ብናደርግ ሕጉ ሊያድነን ይችላልን?
‹‹ ሉቃስ 10፡25-30 ››
‹‹እነሆም አንድ አዋቂ ሊፈትነው ተነስቶ፡- መምህር ሆይ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው፡፡ እርሱም፡- በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? አለው፡፡ እርሱም፡- በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው፡፡ እርሱም መልሶ፡- ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ አለው፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው፡፡ ኢየሱስም፡- እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ አለው፡፡ እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን፡- ባልንጀራዬስ ማነው? አለው፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፡- አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፡፡ በወንበዴዎች እጅም ወደቀ፡፡ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ደበደቡትም፤ በሕይወትና በሞት መካከልም ጥለውት ሄዱ፡፡››
 

የሰዎች እጅግ ትልቁ ችግር ምንድነው?
በብዙ የተሳሳቱ ውዥንብሮች ውስጥ መኖራቸው ነው፡፡

ሉቃስ 10፡28 ‹‹ይህን አድርግ፤ በሕይወትም ትኖራለህ፡፡››
ሰዎች በብዙ የተሳሳቱ ውዥንብሮች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በተለይ በዚህ ረገድ የተጋለጡ ይመስላሉ፡፡ አዋቂዎች ይመስላሉ፤ ነገር ግን በቀላሉ ይታለላሉ፡፡ ክፉ ጎኖቻቸውንም አያውቁዋቸውም፡፡ የተወለድነው ራሳችንን ሳናውቅ ነው፤ ነገር ግን አሁንም ድረስ ራሳችንን እንደምናውቅ ሆነን እንኖራለን፡፡ ሰዎች ራሳቸውን ስለማያውቁ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ሐጢያተኞች እንደሆንን ይነግረናል፡፡ 
ሰዎች ስለ ሐጢያቶቻቸው ኑባሬነት ይናገራሉ፡፡ ሰዎች ጥሩ ነገር ማድረግ ያቃታቸው ይመስላሉ፡፡ ሆኖም ራሳቸውን ጥሩ ሰው አድርገው ለመግለጥ ያዘነብላሉ፡፡ በአንደበታቸው ሐጢያተኞች እንደሆኑ ቢናገሩም ስለ በጎ ስራዎቻቸውና ስለ ምግባራቸው ይመጻደቃሉ፡፡
በውስጣቸው ምንም መልካም ነገርም ሆነ መልካም የማድረግ አቅም እንደሌላቸው አያውቁም፡፡ ስለዚህ ሌሎችን ለማታለል ይሞክራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ራሳቸውን ያታልላሉ፡፡ ‹‹ፈጽሞ ክፉዎች ልንሆን አንችልም፡፡ በውስጣችን አንድ ጥሩ ነገር መኖር አለበት፡፡››  
ስለዚህ ሌሎችን ተመልክተው ለራሳቸው ‹‹ያንን ባያደርግ እመኛለሁ፤ ባያደርገው ጥሩ ይሆንለት ነበር፡፡ እንደዚህ ተናግሮ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ይሆንለት ነበር፡፡ ወንጌልን በዚህና በዚህ መንገድ ቢሰብክ የሚሻለው ይመስለኛል፡፡ ከእኔ በፊት የዳነው እርሱ ነው፡፡ ልክ እንደዳነ ሰው መንቀሳቀስ ይገባው ነበር፡፡ እኔ የዳንኩት በቅርቡ ነው፡፡ ሆኖም ብዙ ተምሬ ቢሆን ኖሮ ከእርሱ ይበልጥ ብዙ የተሻለ ነገር አደርግ ነበር›› ይላሉ፡፡    
እነርሱ በተጎዱ ጊዜ ሁሉ በልባቸው ቢላዋ ይስላሉ፡፡ ‹‹ጠብቅ ብቻ፤ እኔ እንደ አንተ እንዳልሆንኩ ታያለህ፡፡ አሁን ከእኔ የቀደምህ መስሎ ይሰማህ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጠብቅ ብቻ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ ተብሎ ተጽፎዋል፡፡ ይህ እኔን እንደሚመለከት አውቃለሁ፡፡ ጠብቅ አሳይሃለሁ፡፡›› ሰዎች ራሳቸውን ያታልላሉ፡፡   
እርሱ በሌላው ሰው ቦታ ቢሆን ኖሮ በተመሳሳይ መንገድ ምላሽ ቢሰጥም አሁንም ይፈርዳል፡፡ ምስባክ ላይ ሲቆም ስለ ለበሰው ልብስ አብዝቶ ስለሚያስብ ድንገት ሲኮላተፍ ራሱን ያገኘዋል፡፡ ሰዎች ጥሩ ነገር የማድረግ አቅም እንዳላቸው ሲጠየቁ አብዛኞቹ ሰዎች በአንደበታቸው እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ በልባቸው ግን እነርሱ ራሳቸው አቅሙ እንዳላቸው ይቀባዥራሉ፡፡ ስለዚህ እስኪሞቱ ድረስ ሰናይ ለመሆን አብዝተው ይሞክራሉ፡፡  
እነርሱ በልባቸው ውስጥ ‹‹በጎነት›› እንዳለና በጎ ነገር የማድረግ አቅም እንዳላቸው ያስባሉ፡፡ እነርሱ ራሳቸው ጥሩዎች እንደሆኑም ያምናሉ፡፡ ምንም ያህል ለረጅም ጊዜ ሐይማኖተኞች ሆነው ቢቆዩም በተለይ በእግዚአብሄር አገልግሎት ውስጥ የላቀ እመርታ ላይ በደረሱት ሰዎች መካከል ‹እኔ ለጌታ ይህንንና ያንን ማድረግ እችላለሁ› ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡    
ነገር ግን ጌታን ከሕይወታችን ካስወጣነው በእርግጥ ጥሩ ነገር ማድረግ እንችላለን? በሰዎች ውስጥ ጥሩ ነገር አለ? በጎ ስራዎችን እያደረግን በእርግጠኝነት መኖር እንችላለን? ሰዎች በጎ ነገር የማድረግ አቅም የላቸውም፡፡ ነገሮችን በራሳቸው መንገድ ለማድረግ በሞከሩ ቁጥር ሐጢያት ይሰራሉ፡፡ አንዳንዶች በኢየሱስ ካመኑ በኋላ በራሳቸው ጥረት ጥሩዎች ለመሆን ሲሞክሩ ኢየሱስን ገለል ያደርጉታል፡፡ በሁላችንም ውስጥ ያለው ክፋት ነው፡፡ ስለዚህ የምንተገብረውም ክፋትን ብቻ ነው፡፡ በራሳችን (የዳኑትም ቢሆኑ) ልናደርግ የምንችለው ነገር ሐጢያትን ብቻ ነው፡፡ ይህ የስጋችን ተጨባጭ ሁኔታ ነው፡፡

እኛ ሁልጊዜ የምንሰራው ምንድነው? በጎ ነገር ነው ወይስ ክፋት?
ክፋት፡፡

‹የኢየሱስን ስም አመስግኑ› በሚለው የመዝሙር መጽሐፋችን ውስጥ እንዲህ የሚል መዝሙር አለ፡- ‹‹♪ያለ ኢየሱስ ተሰናክለን እንወድቃለን፤ እኛ ባህርን ያለ መቅዘፊያ እንደምታቋርጥ መርከብ ዋጋ ቢሶች ነን♪›› ከኢየሱስ ውጪ ከሆንን መስራት የምንችለው ሐጢያትን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ክፉዎች ነንና፡፡ የጽድቅ ስራዎችን የመስራት አቅም የሚኖረን ከዳንን በኋላ ብቻ ነው፡፡ 
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና፤ ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም፡፡›› (ሮሜ 7፡19) ሰው ከኢየሱስ ጋር ከሆነ አሳሳቢ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከኢየሱስ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር ከሌለ በእግዚአብሄር ፊት በጎ ምግባሮችን ለማድረግ ይሞክራል፡፡ ነገር ግን ሰውየው አብዝቶ በሞከረ ቁጥር ይበልጥ ክፋትን ያደርጋል፡፡  
ንጉሥ ዳዊትም እንደዚሁ ተመሳሳይ የሆነ የውርስ ተፈጥሮ ነበረው፡፡ አገሪቱ ሰላማዊና የለማች በሆነች ጊዜ አንድ ምሽት በሰገነቱ ላይ ለመንሸራሸር ወጣ፡፡ እዚያም አንድ ፈታኝ ምስል አየና በፍትወት ደስታ ወደቀ፡፡ ጌታን በረሳ ጊዜ ምን ይመስል ነበር? በእርግጥም ክፉ ሰው ሆኖ ነበር፡፡ ከቤርሳቤህ ጋር አመነዘረ፤ ባልዋን ኦርዮንንም አስገደለ፡፡ ነገር ግን በራሱ ውስጥ ያለውን ክፋት ማየት አልቻለም፡፡ በፋንታው ለድርጊቶቹ ማማኻኛዎችን አቀረበ፡፡  
አንድ ቀን ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፡- ‹‹በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሃ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው፡፡ ለድሃው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፡፡ አሳደጋትም፡፡ ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፡፡ እንጀራውንም ትበላ፣ ከዋንጫውም ትጠጣ፣ በብብቱም ትተኛ ነበር፡፡ እንደ ልጁም ነበረች፡፡ ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፡፡ የዚያንም የድሃውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ፡፡›› (2ኛ ሳሙኤል 12፡1-14)    
ዳዊትም ‹‹ይህን ያደረገው ሰው በእርግጠኝነት መሞት አለበት›› አለ፡፡ እጅግም ተቆጣ፡፡ ስለዚህም እንዲህ አለ፡- ‹‹እርሱ የራሱ የሆነ ብዙ እያሉት ከእነርሱ መውሰድ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ለእንግዳው ማዕድ ለማቅረብ ሲል የደሃውን ሰው ጠቦት ወሰደ፡፡ እርሱ መሞት ይገባዋል!›› ያን ጊዜ ናታን እንዲህ አለው፡- ‹‹ያ ሰው አንተ ነህ፡፡›› ኢየሱስን ካልተከተልነውና አብረነው ካልሆንን ዳግም የተወለዱትም ቢሆኑ እነዚህን ክፉ ነገሮች ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡  
ነገሩ ለሰው ሁሉ ለታማኞቹም ሳይቀር ተመሳሳይ ነው፡፡ ከኢየሱስ ውጭ ከሆንን ሁልጊዜም እንሰናከላለን፡፡ ክፋትንም እናደርጋለን፡፡ በውስጣችን ክፋት ቢኖርም ኢየሱስ ስላዳነን ዛሬም እንደገና እናመሰግነዋለን፡፡ ‹‹♪ከመስቀሉ ጥላ ስር ማረፍ እፈልጋለሁ♪›› ልቦቻችን በክርስቶስ ቤዛነት ጥላ ስር ያርፋሉ፡፡ ነገር ግን ጥላውን ብንተውና ራሳችንን ብንመለከት በጭራሽ ማረፍ አንችልም፡፡
 


እግዚአብሄር በሕጉ ፊት የእምነትን ጽድቅ ሰጥቶናል፡፡


ከእምነትና ከሕግ ለመከተል ቀዳሚው የትኛው ነው? እምነት ወይስ ሕግ?
እምነት ነው፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሄር ከመጀመሪያውም የእምነትን ጽድቅ እንደሰጠን ተናገረ፡፡ ይህንኑ ለአዳምና ለሔዋን፣ ለአቤልና ለቃየን፣ ለሴትና ለሔኖክ፣ ለኖህ፣ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ በመጨረሻም ለያዕቆብና ለአስራ ሁለቱ ልጆቹ ሰጠ፡፡ ሕግ ሳይኖር እንኳን ከቃሉ ውስጥ በተገኘው የእምነት ጽድቅ አማካይነት በእግዚአብሄር ፊት ጸድቀዋል፡፡ በቃሉ ላይ ባላቸው እምነት አማካይነት ተባርከው ዕረፍትን አግኝተዋል፡፡
ዘመን አለፈ፡፡ የያዕቆብ ዘሮችም በዮሴፍ ምክንያት ለ400 አመታት ባሪያዎች ሆነው በግብጽ ኖሩ፡፡ ከዚያም እግዚአብሄር በሙሴ አማካይነት ወደ ከንዓን ምድር መራቸው፡፡ ሆኖም በ400 የባርነት አመታት ወቅት የእምነትን ጽድቅ ረሱ፡፡
ስለዚህ እግዚአብሄር በሰራው ተዓምር ቀይ ባህርን እንዲሻገሩ ፈቀደላቸው፡፡ ወደ ምድረ በዳም መራቸው፡፡ ወደ ሲን ምድረ በዳ ሲደርሱም በሲና ተራራ ሕግን ሰጣቸው፡፡ አስርቱን ትዕዛዛትና 613 ዝርዝር አንቀጾችን የያዘውን ሕግ ሰጣቸው፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ አለ፡- ‹‹እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሄር ነኝ፡፡ ሙሴ ወደ ሲና ተራራ ይምጣ፤ ሕጉንም እሰጣችኋለሁ፡፡›› 
‹‹ሐጢአትን እንዲያውቁ›› (ሮሜ 3፡20) ሕጉን ሰጣቸው፡፡ ይህንን ያደረገው ምን እንደወደደና ምን እንደጠላ እንደዚሁም ጽድቁንና ቅድስናውን ሊያስታውቃቸው ነው፡፡ 
ለ400 አመታት በግብጽ ባሪያዎች የነበሩ የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ቀይ ባህርን ተሻገሩ፡፡ እነርሱ የአብርሃምን አምላክ፣ የይስሐቅን አምላክና የያዕቆብን አምላክ ከቶውኑም አልተገናኙትም፤ አላወቁትምም፡፡ 
በእነዚያ 400 አመታት ባሮች ሆነው ሲኖሩ ሳሉ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ረስተው ነበር፡፡ በወቅቱ መሪ አልነበራቸውም፡፡ መሪዎቻቸው ያዕቆብና ዮሴፍ ነበሩ፤ እነርሱ ግን ከረጅም ጊዜ በፊት ሞተው ነበር፡፡ ዮሴፍ እምነቱን ለልጆቹ ለምናሴና ለኤፍሬም ማስተላለፍ የተሳነው ይመስላል፡፡  
ስለዚህ ጽድቁን ስለረሱ ጌታቸውን እንደገና ፈልገው ማግኘት አስፈለጋቸው፡፡ እግዚአብሄር አስቀድሞ የእምነትን ጽድቅ ከዚያም ሕጉን የሰጣቸው እምነታቸውን ከረሱ በኋላ እንደነበር በአእምሮዋችን መያዝ ይኖርብናል፡፡ ሕጉን የሰጣቸው ወደ እርሱ እንዲመለሱ ነበር፡፡ 
እርሱ እስራኤልን ለማዳንና የራሱ ሕዝቦች ለማድረግ እንዲገረዙ ነገራቸው፡፡
እነርሱን የጠራበት አላማ ሕጉን በማጽናት እየኖረ እንዳለ እንዲያውቁና ሁለተኛም በፊቱ ሐጢያተኞች እንደነበሩ እንዲያውቁ ነበር፡፡ እግዚአብሄር በሰጣቸው የመስዋዕት ስርዓት አማካይነት ድነው ወደፊቱ እንዲቀርቡና የእርሱ ሕዝቦች እንዲሆኑ ፈለገ፡፡ የራሱ ሕዝብም አደረጋቸው፡፡ 
የእስራኤል ሕዝብ የዳነው በሚመጣው መሲህ በማመን በሕጉ የመስዋዕት ስርዓት በኩል ነበር፡፡ ነገር ግን የመስዋዕቱ ሕግም በጊዜ ሒደት ውስጥ ደብዝዞ ነበር፡፡ ያ መቼ እንደሆነ እንመልከት፡፡
በሉቃስ ወንጌል 10፡25 ላይ ኢየሱስን የፈተነ አንድ ሕግ አዋቂ ተጠቀሰ፡፡ ይህ ሕግ አዋቂ ፈሪሳዊ ነበር፡፡ ፈሪሳውያን በእግዚአብሄር ቃል ለመኖር የሚጥሩ ከልክ በላይ ወግ አጥባቂ ሰዎች ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ አገራቸውን ለመጠበቅ ከዚያም በእግዚአብሄር ሕግ ለመኖር ሞከሩ፡፡ እስራኤልን ከሮም ነጻ የማውጣት ራዕያቸውን ለማሳካት ሲሉ በስሜት የሚነዱና አመጽን ወደ ማድረግ የሚያዘነብሉ ቀናተኞችም ደግሞ ነበሩ፡፡

ኢየሱስ ማግኘት የሚፈልገው ማንን ነው?
እረኛ የሌላቸውን ሐጢያተኞችን ነው፡፡

ዛሬም እነርሱን የሚመስሉ አንዳንድ የሐይማኖት ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱ ‹የዓለምን ጭቁን ሕዝቦች አድኑ› በሚሉ መፈክሮች ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎችን ይመራሉ፡፡ እነርሱ ኢየሱስ የመጣው ድሆችንና ጭቁኖችን ለማዳን እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ስለዚህ በሴሚናሪዎች ውስጥ የስነ መለኮትን ትምህርት ከተማሩ በኋላ በፖለቲካ ውስጥ ይሳተፋሉ፡፡ በእያንዳንዱ የማሕበራዊ መስክ ‹የተጨቆኑትን ለማዳን› ይሞክራሉ፡፡  
እነርሱ ‹‹ሁላችንም በቅዱሱና በመሐሪው ሕግ እንኑር፡፡…በእርሱ ቃሎች በሕጉ እንኑር›› ይላሉ፡፡ ነገር ግን የሕጉን ትክክለኛ ትርጉም አይረዱትም፡፡ የሕጉን መለኮታዊ መገለጥ ሳይገነዘቡ በሕጉ ፊደል ለመኖር ይሞክራሉ፡፡
ስለዚህ ከክርስቶስ በፊት ለ400 አመታት በእስራኤል ነቢያቶች፤ የእግዚአብሄር አገልጋዮች አልነበሩም ማለት እንችላለን፡፡ ከዚህ የተነሳ እረኛ የሌላቸው የበጎች መንጋ ሆኑ፡፡
እነርሱ ሕግም ሆነ እውነተኛ መሪ አልነበራቸውም፡፡ እግዚአብሄርም በወቅቱ በነበሩት ግብዝ የሐይማኖት መሪዎች በኩል ራሱን አልገለጠም፡፡ አገሪቱም የሮም መንግሥት ቅኝ ግዛት ሆነች፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በምድረ በዳ ሲከተሉት ለነበሩት ለእነዚያ የእስራኤል ልጆች ተርበው እንደማይሰዳቸው ነገራቸው፡፡ በወቅቱ ይሰቃዩ የነበሩት ብዙዎች ስለነበሩ እረኛ ለሌላቸው መንጎች ራራላቸው፡፡
መብቶች የነበሩዋቸው እንዲህ ባሉ ሥልጣኖች ላይ የተቀመጡ ሕግ አዋቂዎችና ሌሎች ሰዎች ነበሩ፡፡ ፈሪሳውያን ከወግ አጥባቂው የይሁዲነት የዘር ግንድ የሚመደቡ ነበሩ፡፡ በጣም ኩሩዎች ነበሩ፡፡
ይህ ሕግ አዋቂ በሉቃስ 10፡25 ላይ ኢየሱስን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- ‹‹የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?›› በእስራኤል መካከል ከእርሱ የተሻለ ሰው እንዳልነበር ያሰበ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ይህ የሕግ አዋቂ (ቤዛነትን ያላገኘ ሰው) ኢየሱስን ‹‹የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?›› በማለት ተገዳደረው፡፡   
የሕግ አዋቂው የእኛ ነጸብራቅ ነው፡፡ ኢየሱስን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- ‹‹የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድረግ?›› ኢየሱስም እንዲህ  ሲል መለሰለት፡- ‹‹በሕግ የተጻፈው ምንድነው? እንዴትስ ታነባለህ?››
እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፡- ‹‹ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ፡፡ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ፡፡››
ኢየሱስም መልሶ፡- ‹‹እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ፡፡››
እርሱ ፈጽሞ ጥሩ ነገር ማድረግ የማይችል የሐጢያት ክምር ክፉ ሰው መሆኑን ሳያውቅ ኢየሱስን ተገዳደረው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- ‹‹በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው፡፡››

በሕግ የተጻፈውን የምታነቡት እንዴት ነው?
እኛ ሕጉን ልንጠብቅ የማንችል ሐጢያተኞች ነን፡፡

‹‹እንዴትስ ታነባለህ?›› ኢየሱስ በዚህ ምንባብ ውስጥ ሰው እናንተንና እኔን ጨምሮ ሕጉን እንዴት እንደሚያውቅና እንደሚረዳ ይጠይቃል፡፡ 
በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች እንደሚያደርጉት ይህም የሕግ አዋቂ እንደዚሁ እግዚአብሄር ሕጉን የሰጠው እንዲጠብቀው እንደነበር አሰበ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ሲል መለሰ፡- ‹‹ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ፡፡ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ፡፡››
ሕጉ እንከን የለበትም፡፡ እርሱ ፍጹም ሕግ ሰጠን፡፡  ጌታን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ሐይላችንና በፍጹም አሳባችን እንድንወደውና ባልንጀራዎቻችንንም እንደ ራሳችን እንድንወዳቸው ነገረን፡፡ አምላካችንን በፍጹም ልባችንና ሐይላችን መውደዳችን ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ፈጽሞ ሊጠበቅ የማይችል ቅዱስ ትዕዛዝ ነው፡፡  
‹‹እንዴትስ ታነባለህ?›› ማለት ሕጉ ትክክል ነው፤ አንተ ግን እንዴት ትረዳዋለህ? ማለት ነው፡፡ ሕግ አዋቂው እግዚአብሄር ሕጉን የሰጠው እንዲታዘዘው እንደሆነ አሰበ፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄር ሕግ የተሰጠን ጉድለቶቻችንን ሙሉ በሙሉ በማጋለጥ በደሎቻችንን መገንዘብ እንችል ዘንድ ነው፡፡ ‹‹ሐጢያት ሰርታችኋል፤ አትግደሉ ስላችሁ ገድላችኋል፡፡ ለምን አመጻችሁብኝ?››  
ሕጉ በሰዎች ልቦች ውስጥ ያሉትን ሐጢያቶች ያጋልጣል፡፡ ወደዚህ እየመጣሁ ሳለሁ በአንድ እርሻ ላይ የበሰሉ ሃብሃቦችን አየሁ እንበል፡፡ እግዚአብሄር በሕጉ አማካይነት ‹‹እነዚህን ሃብሃቦች ቀጥፈህ እንዳትበላ፤ እንደዚያ ካደረግህ ታዋርደኛለህ›› ብሎ አስጠነቀቀኝ፡፡ ‹‹አዎ አባት ሆይ›› ‹‹እርሻው የአቶ እከሌና እከሌ ስለሆነ ፈጽሞ መቅጠፍ አይገባህም፡፡›› ‹‹አዎ አባት ሆይ፡፡››  
እነርሱን መቅጠፍ እንደሌለብን በሰማንበት ቅጽበት የመቅጠፍ ስሜት ይሰማናል፡፡ አንድን ስፕሪንግ ወደታች ብንወጥረው ተመልሶ ይነጥራል፡፡ የሰዎችም ሐጢያቶች ልክ እንደዚያ ናቸው፡፡
እግዚአብሄር ፈጽሞ ክፉ ምግባሮችን ማድረግ እንደሌለብን ነግሮናል፡፡ እግዚአብሄር ቅዱስ፣ ፍጹምና ያንን የማድረግ አቅም ያለው ስለሆነ እንደዚያ ማለት ይችላል፡፡ በሌላ በኩል እኛ ‹በጭራሽ› ሐጢያት አለመስራት አንችልም፡፡ ‹በጭራሽ› ሙሉ በሙሉ ጥሩዎች መሆን አንችልም፡፡ በልባችን ውስጥም ‹በጭራሽ› ጥሩ ነገር የለም፡፡ ለምን? ምክንያቱም ሰዎች በልቦቻቸው ውስጥ ፍትወቶች አሉባቸውና፡፡ ፍትወቶቻችንን ከመተግበር ውጭ ልናደርገው የምንችለው ነገር የለም፡፡ የምናመነዝረው በልቦቻችን ውስጥ ምንዝርና ስላለ ነው፡፡  
መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማንበብ አለብን፡፡ በመጀመሪያ ሙከራዬ ቃሉን ከፊደሉ ጋር አገናዘብሁ፡፡ ኢየሱስ ለእኔ በመስቀል ላይ እንደሞተ አንብቤ ዕንባዎቼን መቆጣጠር አልቻልሁም፡፡ እኔ እንዲህ ያለሁ ክፉ ሰው ነበርሁ፡፡ እርሱም ለእኔ በመስቀል ላይ ሞተልኝ፡፡…ልቤ ክፉኛ ስለቆሰለ በእርሱ አመንሁ፡፡ ከዚያም እንዲህ ብዬ አሰብሁ፡- ‹ማመን የሚኖርብኝ ከሆነ በቃሉ መሰረት አምናለሁ፡፡›  
ዘጸአት 20ን ሳነብ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በፊቴ ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ፡፡›› በዚህ ትዕዛዝ መሰረት የንስሐ ጸሎት ጸለይሁ፡፡ በፊቴ ሌሎች አማልክቶች የነበሩ ስለመሆናቸው፣ ስሙን በከንቱ ጠርቼ እንደሆነ ወይም ለሌሎች አማልክቶች ሰግጄ እንደሆነ ለማስታወስ ትውስታዬን ፈተሸሁ፡፡ ለቅድመ አያቶቼ ክብር በሚደረጉ ስርዓቶች ወቅት ብዙ ጊዜ ለሌሎች አማልክቶች እንደሰገድሁ ተገነዘብሁ፡፡ ሌሎች አማልክቶችን የመቆራኘት ሐጢያት ሰርቼ ነበር፡፡    
ስለዚህ ‹‹ጌታ ሆይ ለጣዖታት ሰግጃለሁ፤ ለዚህም ፍርድ ይገባኛል፡፡ እባክህ ሐጢያቶቼን ይቅር በለኝ፡፡ ደግሞ ከቶውኑም እንዲህ አላደርግም›› የሚል የንስሐ ጸሎት ጸለይሁ፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ ሐጢያት የተወገደ መሰለኝ፡፡   
በመቀጠል ስሙን በከንቱ የጠራሁበት ጊዜ ይኖር እንደሆነ ለማስታወስ ሞከርሁ፡፡ ያን ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ በእግዚአብሄር ማመን ስጀምር አጨስ እንደነበር አስታወስሁ፡፡ ጓደኞቼ ‹‹ሲጋራ በማጨስ እግዚአብሄርን እያዋረድከው አይደለምን? ክርስቲያን እንዴት ያጨሳል?›› ብለው ነገሩኝ፡፡  
ይህ ስሙን በከንቱ ከመጥራት ጋር ተመሳሳይ ነው አይደል? ስለዚህ ደግሜ እንዲህ ስል ጸለይሁ፡- ‹‹ጌታ ሆይ ስምህን በከንቱ ጠርቻለሁ፤ እባክህ ይቅር በለኝ፡፡ ማጨስ አቆማለሁ፡፡›› ስለዚህ ሲጋራ ማጨስን ለማቆም ሞከርሁ፡፡ ነገር ግን ለአመት ያህል ገባ ወጣ እያልሁ ማጨሴን ቀጠልሁ፡፡ ሲጋራ ማጨስ ማቆም በእርግጥም አስቸጋሪ እንዲያውም አዳጋች ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ሙሉ በሙሉ ሲጋራ ማጨስ አቆምሁ፡፡ ሌላ ሐጢያት እንደተወገደ ታወቀኝ፡፡   
ቀጣዩ ‹‹የሰንበትን ቀን ቀድሰው›› የሚለው ነበር፡፡ ይህ ማለት በየእሁዶቹ ሌሎች ነገሮችን ማድረግ ወይም ገንዘብ ማግኘት አይገባኝም ማለት ነው፡፡…ያንንም ደግሞ አቆምሁ፡፡
‹‹አባትህንና እናትህን አክብር›› የሚል ደግሞ ነበር፡፡ ርቄ ሳለሁ ላከብራቸው ችዬ ነበር፡፡ ቅርባቸው መሆኔ ግን የበሽታ ምንጭ ነበር፡፡ ‹‹ኦ እንዴት ያለ ነገር ነው፤ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት ሰርቻለሁ፡፡ ጌታ ሆይ እባክህ ይቅር በለኝ፡፡›› በንስሐ ጸለይሁ፡፡
ነገር ግን ዳግመኛ ወላጆቼን ማክበር አልቻልሁም፡፡ ምክንያቱም ያን ጊዜ ሁለቱም ሞተው ነበርና ምን ላደርግ እችላለሁ? ‹‹ጌታ ሆይ እባክህ ይህንን ከንቱ ሐጢያተኛ ይቅር በለው፡፡ ለእኔ በመስቀል ላይ ሞተሃል፡፡›› እንደምን አመስጋኝ ነበርሁ! 
በዚህ መንገድ ሐጢያቶቼን አንድ በአንድ እንደፈታሁ አሰብሁ፡፡ አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትመኝ…የሚሉ ሌሎች ሕጎችም ነበሩ፡፡ አንዱንም ሕግ እንኳን እንዳልጠበቅሁ እስከተረዳሁበት ቀን ድረስ ሌሊቱን ሁሉ ጸለይሁ፡፡ ነገር ግን በንስሐ መጸለይ በእርግጥም የሚያስደስት እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፡፡ እስቲ ስለዚህ እናውራ፡፡   
ስለ ኢየሱስ ስቅለት ባሰብሁ ጊዜ ምንኛ ስቃይ የተሞላበት እንደነበር ሐዘኑ ተሰማኝ፡፡ እርሱም ቃሎቹን ማክበር ላልቻልነው ለእኛ ሞተ፡፡ እንዴት እንደወደደኝ በማሰብና እውነተኛ ደስታ እንደሰጠኝ በማመስገን ሌሊቱን ሁሉ ሳለቅስ አደርሁ፡፡
ቤተክርስቲያን አዘወትር የነበረበት የመጀመሪያው አመት በጥቅሉ በጣም አመቺ ነበር፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ግን በንስሐ ማልቀስ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነብኝ ሄደ፡፡ ምክንያቱም ለብዙ ጊዜ ዕንባዎቼን አፍስሼ ስለነበር ዕንባዎቼ እንዲወርዱ በጣም ማሰብ ነበረብኝ፡፡   
ዕንባዎቼ የማይወርዱ ከሆኑም ብዙውን ጊዜ ለጸሎት ወደ ተራሮች ሄጄ ለ3 ቀናት እጦማለሁ፡፡ ያን ጊዜ ዕንባዎች ተመልሰው መጡ፡፡ በዕንባዎቼ ታጠብሁ፤ ወደ ማሕበረሰቡም ተመለስሁ፤ በቤተክርስቲያን ውስጥም አለቀስሁ፡፡
በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችም ‹‹በተራሮች ላይ በምታደርጋቸው ጸሎቶች በጣም ቅዱስ ሆነሃል›› ይሉኛል፡፡ ዕንባዎቼ ግን እንደገና መድረቃቸው አልቀረም፡፡ ሦስተኛው አመት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በጓደኞቼና አብረውኝ ባሉት ክርስቲያኖች ላይ የሰራሁዋቸውን ስህተቶች እያሰብሁ እንደገና አለቀስሁ፡፡ ይህ ከሆነ ከ4 አመታት በኋላ ዕንባዎቼ እንደገና ደረቁ፡፡ በዓይኖቼ ውስጥ የዕንባ ዕጢዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ዳግመኛ መስራት አልቻሉም፡፡ 
ከ5 አመታት በኋላ ምንም ያህል በርትቼ ብሞክርም ማልቀስ አልቻልሁም፡፡ ንፍጤ መዝረብረብ ጀመረ፡፡ ከሁለት ተጨማሪ አመታት በኋላ ራሴን ስለጠላሁ እግዚአብሄር እንደገና ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንድመለስ አደረገኝ፡፡
 


ሕጉ ለሐጢያት እውቀት ነው፡፡


ስለ ሕጉ ማወቅ ያለብን ምንድነው?
ሕጉን በጭራሽ መጠበቅ አንችልም፡፡

በሮሜ 3፡20 ላይ እንዲህ እናነባለን፡- ‹‹ሐጢአት በሕግ ይታወቃልና፡፡›› በመጀመሪያ ይህ ጥቅስ ለሐዋርያው ጳውሎስ የተላከ የግል መልዕክት ብቻ እንደሆነ አጤንሁና እኔ በመረጥኋቸው ቃሎች ብቻ ለማመን ሞከርሁ፡፡ ዕንባዎቼ ከደረቁ በኋላ ግን ሐይማኖታዊ የሆነውን የእምነት ሕይወቴን መቀጠል አልቻልሁም፡፡    
ስለዚህ በተደጋጋሚ ሐጢያትን ሰራሁ፡፡ በልቤም ውስጥ ሐጢያት እንዳለና በሕጉ መኖርም እንደማይቻል ተረዳሁ፡፡ ልሸከመው አልቻልሁም፡፡ ነገር ግን ሕጉንም ደግሞ መተው አልቻልሁም፡፡ ምክንያቱም ሕጉ የተሰጠው እንድታዘዘው ነው ብዬ አምኜ ነበርና፡፡ 
ሕጉን ስጠብቅ ደስተኛ ነበርሁ፡፡ ሕጉን መጠበቅ ባልቻልሁ ጊዜ ግን ጭንቀታም፣ ብስጩና ሐዘንተኛ ሆንሁ፡፡ ውሎ አድሮም በሁሉም ነገር ላይ ተስፋ ቆረጥሁ፡፡ ከመጀመሪያው ‹‹አይደለም፤ ሕጉ ሌላ ትርጉም አለው፡፡ ሕጉ የሚያሳይህ የሐጢያት ክምር መሆንህን ነው፡፡ ገንዘብን፣ ተቃራኒ ፆታንና ውብ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ትወዳለህ፡፡ ከእግዚአብሄር አስበልጠህ የምትወዳቸው ነገሮች አሉህ፡፡ የዓለምን ነገሮች መከተል ትፈልጋለህ፡፡ ሕጉ የተሰጠህ እንድትጠብቀው ሳይሆን በልብህ ውስጥ ክፋት ያለብህ ሐጢያተኛ መሆንህን ራስህን እንድታውቅ ነው›› የሚለውን የሕጉን እውነተኛ እውቀት እንዲህ ተምሬ ብሆን ኖሮ ነገሩ እንዴት ቀላል መሆን በቻለ ነበር፡፡    
ያን ጊዜ አንድ ሰው እውነቱን አስተምሮኝ ቢሆን ኖሮ ለ10 አመታት ያህል ባልተሰቃየሁ ነበር፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ግንዛቤ ከመምጣቴ በፊት ለ10 አመታት ያህል ከሕግ በታች ሆኜ ስኖር ነበርሁ፡፡
አራተኛው ትዕዛዝ ‹‹የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ›› የሚል ነው፡፡ ያ ማለት በሰንበት መስራት አይገባንም ማለት ነው፡፡ እነርሱ በእሁድ ቀን ረጅም ርቀቶችን በመኪና ሳይሆን በእግራችን መጓዝ እንደሚገባን ያስተምራሉ፡፡ ወደምሰብክበት ስፍራ በእግር መሄድ በጣም ተገቢና ተወዳሽ እንደሆነ አሰብሁ፡፡ እኔም የምሄደው ሕጉን ለመስበክ ነበር፡፡ ስለዚህ የምሰብከውን መተግበር እንደሚገባኝ ተሰማኝ፡፡ ይህንን ለመተው መዘጋጀት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡  
እዚህ ላይ ‹‹እንዴትስ ታነባለህ?›› ተብሎ እንደተጻፈ ይህንን ጥያቄ ስላልተረዳሁት ለ10 አመታት ያህል ተሰቃየሁ፡፡ የሕግ አዋቂውም እንደዚሁ ይህንኑ ነገር የተረዳው በተሳሳተ መንገድ ነበር፡፡ ሕጉን ቢታዘዝና ተጠንቅቆ ቢኖር በእግዚአብሄር ፊት እንደሚባረክ አሰበ፡፡
ኢየሱስ ግን፡- ‹‹እንዴትስ ታነባለህ?›› አለው፡፡ ሰውየው መልሱን የሰጠው በሕግ ላይ በተመሰረተው እምነቱ መሰረት ነበር፡፡ ያን ጊዜ ኢየሱስ ለሰውየው ‹‹አዎ በትክክል መልሰሃል፡፡ ሕጉን እንደተጻፈው ተቀብለኸዋል፡፡ ልትጠብቀው ሞክር፤ ብትጠብቀው በሕይወት ትኖራለህ፡፡ ባትጠብቀው ግን ትሞታለህ፡፡ የሐጢያት ደመወዝ ሞት ነው፡፡ ባትጠብቀው ትሞታለህ›› አለው፡፡ (የሕይወት ተቃራኒ ሞት ነው አይደል?)  
የሕግ አዋቂው ግን አሁንም ድረስ አልተረዳም፡፡ ይህ የሕግ አዋቂ እንደ እናንተና እንደ እኔ እንደ ማናችንም ነው፡፡ እኔ የስነ መለኮትን ትምህርት ለ10 አመታት ያህል አጥንቻለሁ፡፡ ሁሉን ሞከርሁ፤ ሁሉን አነበብሁ፤ ሁሉን አደረግሁ፡፡ ጾምሁ፤ ራዕዮችን አይቻለሁ፤ በልሳንም ተናግሬአለሁ፡፡…መጽሐፍ ቅዱስን ለ10 አመታት ያህል አንብቤአለሁ፡፡ አንዳች ነገርም ለመፈጸም ጓጉቼ ነበር፡፡ በመንፈሳዊ ሁኔታ ግን አሁንም ድረስ እውር ሰው ነበርሁ፡፡  
ሐጢያተኛ ዓይኖቹን ሊከፍትለት የሚችል ሰው ማግኘት ያለበት ለዚህ ነው፡፡ ያም ሰው ጌታችን ኢየሱስ ነው፡፡ ሰዎች ‹‹አሃ! ሕጉን በጭራሽ መጠበቅ አንችልም፡፡ ምንም ያህል ጠንክረን ብንሞክርም እየሞከርን ብቻ እንሞታለን፡፡ ኢየሱስ ግን በውሃውና በመንፈሱ ሊያድነን መጥቶዋል! ሐሌሉያ!›› ብለው ሊገነዘቡ ይችላሉ፡፡ ውሃውና መንፈሱ ሊያድነን ይችላል፡፡ ይህ ጸጋ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታን እናመሰግነዋለን፡፡  
እኔ ተስፋ ቢስ ከሆነው ሕግ አጥባቂነት መስመር ለመመረቅ በመብቃቴ ዕድለኛ ነኝ፡፡ አንዳንዶች ግን እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ ዕድሜ ዘመናቸውን በሙሉ ስነ መለኮትን በከንቱ ያጠናሉ፡፡ እውነትንም ፈጽሞ አይገነዘቡም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለአስርተ አመታት ድረስ ወይም ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ ያምናሉ፤ ነገር ግን በጭራሽ ዳግም አይወለዱም፡፡    
ሕጉን በፍጹም መጠበቅ እንደማንችል ስንገነዘብ ሐጢያተኛ ከመሆን ተመርቀን በኢየሱስ ፊት እንቀርብና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንሰማለን፡፡ ኢየሱስን ስንገናኝ ከፍርዶችና ከኩነኔዎች ሁሉ ተመርቀን እንለወጣለን፡፡ እኛ እጅግ የከፋን ሐጢያተኞች ነን፡፡ ነገር ግን እርሱ በውሃና በደም ስላዳነን ጻድቃን ሆነናል፡፡  
ኢየሱስ በእርሱ ፈቃድ ውስጥ በጭራሽ መኖር እንደማንችል ነገረን፡፡ ይህንኑም ለሕግ አዋቂው ነገረው፡፡ እርሱ ግን አልገባውም፡፡ ስለዚህ እንዲገባው ለማገዝ አንድ ታሪክ ነገረው፡፡

ሰዎችን ከእምነት ሕይወት እንዲወድቁ የሚያደርጋቸው ምንድነው?
ሐጢያት፡፡

‹‹አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፡፡ በወንበዴዎች እጅም ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም፤ በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ፡፡›› (ሉቃስ 10፡30) ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ለሕግ አዋቂው የነገረው ይህ ሰው በወንበዴዎች እንደተደበደበና በሞትና በሕይወት መካከል እንደነበረ ሁሉ እርሱም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንዲህ እንደተቸገረ እውነቱን እንዲያውቅ ነው፡፡   
አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፡፡ ኢያሪኮ ሥጋዊውን ዓለም ስታመላክት ኢየሩሳሌም ደግሞ የሐይማኖትን ከተማ ማለትም በሕግ የሚመጻደቁ ሰዎች የሞሉባትን የእምነት ከተማ ታመለክታለች፡፡ ይህ ታሪክ በኢየሱስ የምናምነው በሐይማኖታዊ መንገድ ብቻ ከሆነ እንደምንጠፋ ይነግረናል፡፡ 
‹‹አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፡፡ በወንበዴዎች እጅም ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ ደበደቡትም፤ በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ፡፡›› (ሉቃስ 10፡30) ኢየሩሳሌም ብዙ ሕዝብ ያለባት ትልቅ ከተማ ነበረች፡፡ በዚያ ሊቀ ካህኑ፣ ካህናቶች፣ ሌዋውያንና ብዙ ታዋቂ የሐይማኖት ሰዎች ነበሩ፡፡ ሕጉን በደምብ የሚያውቁ ብዙዎች ነበሩ፡፡ እነርሱ በሕጉ ለመኖር ሞከሩ፤ ነገር ግን ውሎ አድሮ ወደቁና በዓለም (ኢያሪኮ) ውስጥ መውደቃቸውን ቀጠሉ፡፡ ወንበዴዎችን ከመገናኘት ማምለጥ አልቻሉም፡፡      
ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ የሄደው ሰው ወንበዴዎች ያገኙትና ልብሱን ይዘርፉታል፡፡ ‹‹ልብሶቹን መግፈፍ›› ማለት ጽድቁን አጥቶዋል ማለት ነው፡፡ እኛ በሕጉ መኖርና ለሕጉም መኖር አይቻለንም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 7፡19-20 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና፤ ዳሩ ግን የምወደውን በጎውኑ ነገር አላደርገውም፡፡ የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፤ በእኔ የሚኖር ሐጢያት ነው እንጂ፡፡››   
እኔ በጎ ነገር ማድረግና በእርሱ ቃሎች መኖር ብችል እመኛለሁ፡፡ በሰው ልብ ውስጥ ግን ክፉ አሳቦች፣ ምንዝርና፣ ዝሙት፣ ነፍስ መግደል፣ መስረቅ፣ ክፉ ምኞት፣ ማታለል፣ መጎምጀት፣ መዳራት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ተንኮል፣ ስንፍና አሉ፡፡ (ማርቆስ 7፡21-23) 
እነዚህ ነገሮች በልባችን ውስጥ ስላሉና በየጊዜው ስለሚወጡ ማድረግ የማንፈልገውን እናደርጋለን፡፡ ማድረግ የሚገባንንም አናደርግም፡፡ በልቦቻችን ውስጥ ያሉትን እነዚያን ክፋቶች ደጋግመን እናደርጋቸዋለን፡፡ ዲያብሎስ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ሐጢያት እንድንሰራ ትንሽ ግፊት ማድረግ ብቻ ነው፡፡
 


በሰው ዘር ሁሉ ልብ ውስጥ ያሉት ሐጢያቶች፡፡

 
በሕጉ መኖር እንችላለን?
አንችልም፡፡

በማርቆስ 7 ላይ እንዲህ ተብሎዋል፡- ‹‹እርሱም አለ፡- ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው፡፡ ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ፣ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸውና፡፡ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል፤ ሰውንም ያረክሰዋል፡፡››   
ኢየሱስ በሰው ልብ ውስጥ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና እንዳሉ ይነግረናል፡፡  
ሁላችንም በልባችን ውስጥ ነፍስ መግደል አለ፡፡ ነፍስ የማይገድል ማንም የለም፡፡ እናቶች በልጆቻቸው ላይ ‹‹አይደለም፤ ያንን እንዳታደርግ! ያንን እንዳታደርግ ደጋግሜ ነግሬሃለሁ አንተ የማትረባ፡፡ ዳግመኛ ያንን ብታደርግ እገድልሃለሁ፤ ያንን እንዳታደርግ ብያለሁ›› በማለት ይጮሃሉ፡፡ ያ ነፍስ መግደል ነው፡፡ ሳታስቡ በምትናገሩዋቸው ቃሎች ልጆቻችሁን በአእምሮዋችሁ ውስጥ ትገድሉዋቸው ይሆናል፡፡     
ልጆቻችን በሕይወት መኖር አለባቸው፡፡ ምክንያቱም በፍጥነት ከእኛ ያመልጣሉና፡፡ ነገር ግን ቁጣችንን በሙሉ በእነርሱ ላይ የምናፈስስ ከሆነ ልንገድላቸው እንችል ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን እናስጨንቃለን፡፡ ‹‹ኦ አምላኬ! ለምንድነው ያንን ያደረግሁት?›› ልጆቻችንን ከመታናቸው በኋላ ጠባሳዎቹን ተመልክተን ያንን በማድረጋችን ወፈፌዎች እንደሆንን እናስባለን፡፡ ያንን ከማድረግ አንመለስም፡፡ ምክንያቱም በልባችን ውስጥ ነፍስ መግደል አለና፡፡ 
ስለዚህ ‹‹የማልወደውን አደርጋለሁና›› ማለት ክፉዎች ስለሆንን ክፉ ነገር እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ ሰይጣን እኛን ሐጢያት እንድንሰራ ለመፈተን በጣም ይቀለዋል፡፡
አንድ ያልዳነ ሰው በቅርቡ የሞተው ታላቁ የኮርያ መነኩሴ ሱንግቹል እንደሚያደርገው ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ በማሰላሰል ለ10 አመታት በአንድ ጎጆ ውስጥ ተቀመጠ እንበል፡፡ ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ እስከተቀመጠ ድረስ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ምግብ የሚያመጣለትና ሰገራውን የሚጠርግለት ሰው ያስፈልገዋል፡፡  
እርሱ ከሰው ጋር መገናኘት ይኖርበታል፡፡ ወንድ ከሆነ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ውብ ሴት ናት እንበል፡፡ በአጋጣሚ ካያት በመቀመጥ ያጠፋው ጊዜ ሁሉ ከንቱ ይሆናል፡፡ ‹‹ማመንዘር የለብኝም፤ ይህ በልቤ ውስጥ አለ፤ ነገር ግን ላስወግደው ይገባኛል፡፡ ላባርረው ይገባኛል፡፡ አይሆንም ከአእምሮዬ ውጣ!›› ብሎ ያስብ ይሆናል፡፡  
ነገር ግን እርስዋን ባየበት ቅጽበት ውሳኔው በሙሉ ይተናል፡፡ ሴቲቱ ከሄደች በኋላ ልቡን ይመለከታል፡፡ የ5 አመት የምንኩስና ልምምዶቹ ሁሉ ከንቱና ፍሬ ከርሲ ሆነዋል፡፡ 
ለሰይጣን የሰውን ጽድቅ መንጠቅ በጣም ቀላል ነው፡፡ ሰይጣን ማድረግ ያለበት ነገር እርሱን/እርስዋን ጥቂት ገፋ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ሰው ሳይድን ሐጢያት ላለመስራት ቢታገል በሐጢያት ውስጥ መውደቁን ይቀጥላል፡፡ ያ ሰው በየእሁዱ አስራትን በታማኝነት ይከፍል፣ 40 ቀን ይጾም፣ የ100 ቀን የንጋት ጸሎቶችን ይጸልይ ይሆናል፡፡…ሰይጣን ግን በሕይወት ውስጥ ጥሩ በሚመስሉ ነገሮች ይፈትነውና ያስተዋል፡፡  
‹‹በካምፓኒ ውስጥ ቁልፍ ቦታ ልሰጥህ እወዳለሁ፡፤ አንተ ክርስቲያን ስለሆንህ እሁድ አትሰራም፡፡ መስራት ትችላለህ እንዴ? ቦታው ትልቅ ቦታ ነው፡፡ ለ3 እሁዶች ሰርተህ በወር አንድ ጊዜ ብቻ ቤተክርስቲያን መሄድ ትችላለህ፡፡ ያን ጊዜ እንዲህ ባለው ከፍተኛ ክብር ትደሰታለህ፡፡ ወፍራም ደመወዝም ይኖርሃል፤ እንዴት ነው?›› በዚህ ከ100ዎቹ ሰዎች ምናልባትም 100ዎቹም ይገዙ ይሆናል፡፡ 
ይህ የማይሰራ ከሆነ ሰይጣን በሴቶች ፍትወት በቀላሉ በሚጠመዱ ሰዎች ላይ ብልሃት ይጠቀማል፡፡ ሰይጣን በፊቱ አንዲት ሴት ያቆምለታል፡፡ እርሱም እግዚአብሄርን ወዲያውኑ ረስቶ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ በፍቅር ይወድቃል፡፡ የሰው ጽድቅ የሚገፈፈው በዚህ መንገድ ነው፡፡  
በሕጉ ለመኖር የምንሞክር ከሆንን በመጨረሻ የሚተርፈን ነገር ቢኖር የሐጢያት ቁስል፣ ስቃይና መንፈሳዊ ድህነት ብቻ ነው፡፡ ጽድቅን ሁሉ እናጣለን፡፡ ‹‹አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፡፡ በወንበዴዎች እጅም ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ ደበደቡትም፤ በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ፡፡›› (ሉቃስ 10፡30)   
ይህ ማለት በቅዱስ አምላክ ፈቃድ እየኖርን በኢየሩሳሌም ለመቆየት ብንሞክር ከድክመቶቻችንና የተነሳ በየጊዜው እንሰናከላለን፤ ውሎ አድሮም እንጠፋለን ማለት ነው፡፡
በእግዚአብሄር ፊት በንስሐ ትጸልዩ ይሆናል፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ ሐጢያት ሰርቻለሁ፤ እባክህ ይቅር በለኝ፡፡ ዳግመኛ ይህንን በጭራሽ አላደርግም፡፡ ይህ በእርግጥ የመጨረሻ እንደሆነ ቃል እገባልሃለሁ፡፡ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ፤ እማጸንህማለሁ፡፡  
ይህ ግን ፈጽሞ ማለቂያ የለውም፡፡ ሰዎች ሐጢያት ሳይሰሩ በዚህ ዓለም ላይ መኖር አይችሉም፡፡ ለአንድ ሁለት ጊዜ ያህል ሐጢያትን ማስወገድ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዳግመኛ ሐጢያት አለመስራት የማይቻል ይሆናል፡፡ ስለዚህ በተደጋጋሚ ሐጢያቶችን ከመስራት በቀር ማድረግ የምንችለው ነገር የለም፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ እባክህ ይቅር በለኝ፡፡›› ይህ የሚቀጥል ከሆነ ከቤተክርስቲያንና ከሐይማኖታዊ ሕይወታቸው ያፈነግጣሉ፡፡ በሐጢያቶቻቸው ምክንያትም ከእግዚአብሄር ይርቃሉ፡፡ ውሎ አድሮም መጨረሻቸው ሲዖል ነው፡፡    
ወደ ኢያሪኮ መጓዝ ማለት ወደ ዓለም ይበልጥ በመቅረብና ከኢየሩሳሌም በመራቅ በሥጋዊው ዓለም ውስጥ መውደቅ ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያ ኢየሩሳሌም ገናም ቅርብ ነበረች፡፡ ነገር ግን ሐጢያትን የመስራትና ንስሐ የመግባት ዑደት ሲደጋገም ራሳችንን ሙሉ በሙሉ በዓለም ውስጥ ወድቀን በኢያሪኮ የቀለጠ ከተማ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡

መዳን የሚችሉት እነማን ናቸው?
የራሳቸውን ጽድቅ ማቆም የተዉ ሰዎች ናቸው፡፡

ወደ ኢያሪኮ የሄደውን ሰው እነማን አገኙት? ወንበዴዎች አገኙት፡፡ ሕጉን የማያውቅና በሕጉ የሚኖር ሰው ልክ ያበደ ውሻ የሚኖረውን አይነት ሕይወት ይኖራል፤ ይጠጣል፤ የትም ቦታ ይተኛል፤ የትም ቦታ ይሸናል፡፡ ይህ ውሻ በነጋታው ይነሳና የራሱን ዕዳሪ ይበላል፡፡ እንዲህ አይነት ሰው ውሻ ተብሎ የሚጠራው ለዚህ ነው፡፡ እርሱ መጠጣት አያውቅም፡፡ ነገር ግን ይጠጣና በነጋታው ንስሐ ይገባል፡፡ ይህንን ሒደት ደጋግሞ ያደርገዋል፡፡      
ነገሩ ወደ ኢያሪኮ ሲሄድ ወንበዴዎች የተገናኙትን ሰው ይመስላል፡፡ ቆስሎ በሞትና በሕይወት መካከል ቆየ፡፡ ይህ ማለት በልቡ ውስጥ ያለው ሐጢያት ብቻ ነበር ማለት ነው፡፡ ሰው ማለት ይህ ነው፡፡ 
ሰዎች የሐይማኖት ማህበረሰብ በሆነችው በኢየሩሳሌም ውስጥ በሕጉ ለመኖር እየሞከሩ በኢየሱስ ያምናሉ፡፡ ነገር ግን በልባቸው ውስጥ ሐጢያቶች አሉባቸው፡፡ በሐይማኖታዊ ሕይወታቸው የሚያሳዩት ነገር ሁሉ የሐጢያትን ቁስል ብቻ ነው፡፡ በልባቸው ውስጥ ሐጢያት ያለባቸው ሰዎች በመጨረሻ ወደ ሲዖል ይወረውራሉ፡፡ ይህንን ያውቁታል፤ ነገር ግን ምን እንደሚያደርጉ አያውቁም፡፡ እናንተና እኔም ተመሳሳይ በሆነችው ሐይማኖታዊ ከተማ ውስጥ ያለን አይደለንምን? አዎ ሁላችንም በተመሳሳይ መንገድ እዚያው ነበርን፡፡
የእግዚአብሄርን ሕግ በተሳሳተ መንገድ የተረዳው የሕግ አዋቂ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ቢታገልም ቆስሎ መጨረሻው ሲዖል ይሆናል፡፡ እርሱም እንደ እናንተና እንደ እኔ ከእኛ እንደ አንዱ ነው፡፡ 
ሊያድነን የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ በዙሪያችን በጣም አዋቂ የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ሁልጊዜም ስለሚያውቁት ነገር ይመጻደቃሉ፡፡ ሁሉም በእግዚአብሄር ሕግ እንደሚኖሩና ለራሳቸውም እውነተኞች እንደሆኑ ያስመስላሉ፡፡ አካፋን አካፋ ብለው አይጠሩትም፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜም ታማኝ ለመምሰል ውጫዊ ገጽታዎቻቸውን ያሰማምራሉ፡፡ 
በእነርሱ መካከል ወደ ኢያሪኮ ሲሄዱ በወንበዴዎች የተደበደቡና በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው የተተዉ ሐይማኖተኞች አሉ፡፡ እኛ በእግዚአብሄር ፊት ተሰባሪዎች መሆናችንን ማወቅ ይኖርብናል፡፡
እኛ በእርሱ ፊት ‹‹ጌታ ሆይ አንተ ካላዳንከኝ ሲዖል እወርዳለሁ፡፡ እባክህ አድነኝ፡፡ እውነተኛውን ወንጌል ብቻ መስማት ብችል በረዶም ይሁን ማዕበል ወደምትፈልገው ሁሉ እሄዳለሁ፡፡ ብቻዬን ከተውከኝ ሲዖል እወርዳለሁ፤ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ›› በማለት ማመን አለብን፡፡ 
መዳን የሚችሉት ወደ ሲዖል እየነጎዱ መሆናቸውን የሚያውቁና በጌታ ላይ ተንጠላጥለው የራሳቸውን ጽድቅ መከተልን ለመተው የሚሞክሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በራሳችን ጥረቶች ፈጽሞ መዳን አንችልም፡፡ 
እኛ በወንበዴዎች መካከል የወደቀውን ሰው እንደምንመስል መረዳት አለብን፡፡