Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-27] በሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች ውስጥ የተደበቁት መንፈሳዊ ትርጉሞች፡፡ ‹‹ዘጸዓት 28፡1-43››

በሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች ውስጥ የተደበቁት መንፈሳዊ ትርጉሞች፡፡
‹‹ዘጸዓት 28፡1-43›› 
‹‹አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፡፡ አሮንን፣ የአሮንንም ልጆች ናዳብን፣ አብዩድንም፣ አልዓዛርንም፣ ኢታምርንም አቅርብ፡፡ የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለጌጥ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት፡፡ አንተም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ አሮን ቅዱስ ይሆን ዘንድ ልብስ እንዲሠሩለት የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር፡፡ የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ፣ ኤፉድም፣ ቀሚስም፣ ዝንጉርጉር ሸሚዝም፣ መጠምጠሚያም፣ መታጠቂያም፡፡ እነዚህም ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ፡፡ ወርቅንም፣ ሰማያዊና ሐምራዊ፣ ቀይም ግምጃ፣ ጥሩም በፍታ ይወስዱ፡፡ ኤፌዱንም በብልሃት የተሠራ በወርቅና በሰማያዊ፣ በሐምራዊውም፣ በቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ያድርጉ፡፡ ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ጫንቃ ላይ የሚጋጠም ጨርቅ ይሁን፡፡ በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉድ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ይሁን፤ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ግምጃም፣ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም የተሠራ ይሁን፡፡ ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ስማቸውን ቅረጽባቸው፤ እንደ አወላለዳቸው ስድስት ስም በአንድ ድንጋይ የቀረውንም ስድስቱን ስም በሌላው ቅረጽ፡፡ በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማህተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ፤ በወርቅም ፈርጥ አድርግ፡፡ የእስራኤል ልጆችም የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቁዎች በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ ለመታሰቢያ ስማቸውን በእግዚአብሄር ፊት ይሸከማል፡፡ የወርቅም ፈርጦች ሁለትም ድሪዎች ከጥሩ ወርቅ ሥራ፤ እንደ ተጎነጎነም ገመድ አድርግ፤ የተጎነጎኑትንም ድሪዎች በፈርጦቹ ላይ አንጠልጥል፡፡ ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ የፍርዱን የደረት ኪስ ሥራው፤ እንደ ኤፉዱም አሠራር ሥራው፤ ከወርቅና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊውም፣ ከቀይ ግምጃም፣ ከጥሩ በፍታም ሥራው፡፡ ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር ሆኖ ትክክልና ድርብ ይሆናል፡፡ በአራት ተራ የሆነ የዕንቁ ፈርጥ አድርግበት፤ በፊተኛው ተራ ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮን፣ የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ በሁለተኛውም ተራ በሉር፣ ሰንፔር፣ አልማዝ፤ በሦስተኛውም ተራ ያክንት፣ ኬልቄዶን፣ አሜቴስጢኖስ፤ በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፣ መረግድ፣ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ይደረጋሉ፡፡ የዕንቆቹም ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች አሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ይቀረጹ፤ ስለ አሥራ ሁለቱ ነገዶችም ይሁኑ፡፡ ለደረቱ ኪስም የተጎነጎኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገህ ከጥሩ ወርቅ ሥራቸው፡፡ ለደረቱ ኪስም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አድርጋቸው፡፡ የተጎነጎኑትንም ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች ታገባቸዋለህ፡፡ የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው ታደርጋቸዋለህ፡፡ ሁለት የወርቅ ቀለበቶችም ሥራ፤ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለቱ ጫፎች ላይ ታደርጋቸዋለህ፡፡ ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፤ በኤፉዱም ፊት ከጫንቃዎቹ በታች በብልሃት ከተጠለፈ ኤፉድ ቋድ በላይ በመያዣው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ፡፡ የደረቱም ኪስ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉድ ቋድ በላይ እንዲሆን ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያስሩታል፡፡ አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ በእግዚአብሄር ፊት ለዘላለም መታሰቢያ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ በደረት ኪስ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም፡፡ በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፤ በእግዚአብሄርም ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በእግዚአብሄር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል፡፡ የኤፉዱንም ቀሚስ ሁሉ ሰማያዊ አድርገው፡፡ ከላይም በመካከል አንገትጌ ይሁንበት፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ይሁንበት፡፡ በታችኛው ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊውም፣ ከቀይም ግምጃ ሮማኖች አድርግ፤ በዚያ መካከል በዙሪያው የወርቅ ሻኩራዎች አድርግ፤ የወርቅ ሻኩራ ሮማንም ሌላም የወርቅ ሻኩራ ሮማንም በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ይሆናሉ፡፡ በማገልገል ጊዜም በአሮን ላይ ይሆናል፤ እርሱም እንዳይሞት ወደ መቅደሱ በእግዚአብሄር ፊት ሲገባና ሲወጣ ድምጹ ይሰማል፡፡ ከጥሩ ወርቅም ቅጠል የሚመስል ምልክት ሥራ፤ በእርሱም ላይ እንደ ማህተም ቅርጽ አድርገህ፡- ቅድስና ለእግዚአብሄር የሚል ትቀርጽበታለህ፡፡ በሰማያዊም ፈትል በመጠምጠሚያው ፊት ላይ ታንጠለጥለዋለህ፡፡ በአሮንም ግምባር ላይ ይሆናል፤ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀደሱት በቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ሐጢአት ይሸከም፤ በእግዚአብሄርም ፊት ሞገስ እንዲሆንላቸው ቅጠል የሚመስለው ምልክቱ ሁልጊዜ በግምባሩ ላይ ይሁን፡፡ ሸሚዙንም ከጥሩ በፍታ ዝንጉርጉር አድርገህ መጠምጠሚውንም ከበፍታ ትሠራለህ፤ በጥልፍ አሠራር መታጠቂያም ትሠራለህ፡፡ ለአሮንም ልጆች ሸሚዞችን፣ መታጠቂያዎችንም፣ ቆቦችንም ለክብርና ለጌጥ ታደርግላቸዋለህ፡፡ ይህንም ሁሉ ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፤ ትክናቸዋለህ፤ ትቀድሳቸውማለህ፡፡ ሐፍረተ ሥጋቸውንም ይከድኑበት ዘንድ የበፍታ ሱሪ ታደርግላቸዋለህ፤ ከወገባቸውም እስከ ጭናቸው ይደርሳል፤ ሐጢአትም እንዳይሆንባቸው እንዳይሞቱም ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገቡ በመቅደሱም ያገለግሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ በአሮንና በልጆቹ ላይ ይሆናል፤ ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል፡፡›› 


የሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች፡፡


ዛሬ በሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች ውስጥ የተደበቁትን መንፈሳዊ ትርጉሞች እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ልብሰ ተክህኖዎች በአሮንና በልጆቹ መለበስ ነበረባቸው፡፡ በሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች አማካይነት እኛን ከሐጢያት ያዳነንን የእግዚአብሄር ዕቅድ በእምነት እንገነዘባለን፡፡ 
እግዚአብሄር ወንድሙን አሮንንና የአሮንን ልጆች ካህናት ሆነው እግዚአብሄርን ያገለግሉት ዘንድ እንዲቀድሳቸው ሙሴን አዘዘው፡፡ እግዚአብሄር ሙሴን በተመለከተው ምሳሌ መሠረት ልብሰ ተክህኖዋቸውን እንዲሠራም አዘዘው፡፡
በቁጥር 4 ላይ እግዚአብሄር እንዲህ አለ፡- ‹‹የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ፣ ኤፉድም፣ ቀሚስም፣ ዝንጉርጉር ሸሚዝም፣ መጠምጠሚያም፣ መታጠቂያም፡፡ እነዚህም ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ፡፡››
በቅድሚያ ሊቀ ካህኑ ራቁትነቱን ለመሸፈን ሸሚዙንና ሱሪውን ይለብሳል፡፡ እነዚህ ልብሶች የተሠሩት አየር በሚገባ እንዲሰራጭና ብዙ ላብ እንዳያልበው ለመከላከል ሲባል ከጥሩ የበፍታ ግምጃ ነው፡፡ የዚህ መንፈሳዊ ትርጉም ሊቀ ካህኑ የራሱን ሰጋዊ ጥረቶች አስወግዶ ቀደም ብሎ እግዚአብሄር በሰጠው እምነትና ጸጋ መሠረት ማገልገል ያለበት መሆኑን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የእግዚአብሄር ፈቃድ ሊፈጸም የሚችለው ሊቀ ካህኑ የራሱን አስተሳሰቦችና ቀናዒነት አስወግዶ በእግዚአብሄር በተመሠረተው የመሥዋዕት ስርዓት መሠረት በእምነት የስርየት መሥዋዕትን ሲያቀርብ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሊቀ ካህኑን ሸሚዞችና ሱሪዎች የሠራውና ያለበሰው ይህንን አስቦ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሊቀ ካህኑን በእነዚህ ልብሶች ካለበሰው በኋላ ከበላዩ ሰማያዊ ቀሚስ አለበሰው፡፡ ከሰማያዊው ቀሚስ በላይም ኤፉዱን ለበሰ፡፡ ከዚያም የደረቱን ኪስ አደረገ፡፡ በሊቀ ካህኑ ደረት ላይ ያለው የደረት ኪስ ሁለት ዕጥፋት ካለው ጠንካራ ማግ የተሠራና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ግምጃና ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አሠራር የተጠለፈ ነበር፡፡ ርዝመቱና ስፋቱም አንድ ስንዝር ነበር፡፡ በዚህ የደረት ኪስ ላይ አሥራ ሁለቱ የከበሩ ድንጋዮች ተደርገውበታል፡፡ በእነዚህ የከበሩ ድንጋዮች ላይም የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስሞች ተቀርጸውበታል፡፡
ከዚያም ከጥሩ በፍታ የተሠራ መጠምጠሚያ ያደርጋል፡፡ የተቀረጸበትና በመጠምጠሚያው ፊት ላይ በሰማያዊ ፈትል የተያያዘ ‹‹ቅድስና ለእግዚአብሄር›› የሚል ቃሎች ያሉበትን ከንጹህ ወርቅ የተሠራ ምልክት ያደርጋል፡፡ እነዚህ ሊቀ ካህናቱ የሚለብሱዋቸውን ልብሰ ተክህኖዎች፣ መጠምጠሚያና የወርቅ ምልክት በአጭሩ የሚያብራሩ ማብራሪያዎች ናቸው፡፡
አብዛኞቹ የሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተሠሩ ነበሩ፡፡ የሊቀ ካህኑ የደረት ኪስ የተሠራውም ከእነዚህ ነበር፡፡ በዚህ የደረት ኪስ ላይ አሥራ ሁለት የከበሩ ድንጋዮች ነበሩበት፡፡ በእነዚህ የከበሩ ድንጋዮች ላይም የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ሕዝበ ነገዶች ስሞች ተቀርጸውባቸው ነበር፡፡
የሊቀ ካህኑ ተግባር የሚከተሉትን የያዘ ነው፡፡ ከእስራኤል ልጆች ጉባኤ የመሥዋዕት እንስሶቻቸውን በመውሰድ፣ የእነርሱ ወኪል ሆኖ እጆቹን በራሳቸው ላይ በመጫን ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ ወደ እነዚህ መሥዋዕቶች ያሻግራል፤ ያርዳቸዋል፡፡ የእነዚህን መሥዋዕቶች ደም ለእግዚአብሄር ያቀርባል፡፡ በሌላ አነጋገር ሊቀ ካህኑ የሚያገለግለው በእግዚአብሄር ሕግ መሠረት መሥዋዕትን በማቅረብ የሕዝቡን ሐጢያቶች ለማስወገድ ነው፡፡ ሊቀ ካህኑ በእስራኤል ሕዝበ ፋንታ በእግዚአብሄር ፊት እጆቹን በመሥዋዕቱ እንስሳ ራስ ላይ በመጫን ያርደውና ደሙን ያፈስሰዋል፡፡ ይህንንም ደም በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ቀንዶች ላይ ይቀባዋል፡፡ ከዚያም ደሙን ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ይዞ በመግባት በስርየት መክደኛው ላይና ፊት ይረጨዋል፡፡ የሞተው መሥዋዕት ሬሳ ከሰፈሩ ውጪ ተወስዶ ሙሉ በሙሉ ይቃጠላል፡፡ (ዘሌዋውያን 16፡3-28) ሊቀ ካህኑ መሥዋዕትን የሚያቀርበው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ሊቀ ካህኑ በዚህ መንገድ እግዚአብሄር የሚደሰትበትን መሥዋዕት በማቅረብ የእግዚአብሄርን ቁጣ የማለዘብ ሚናውን ይፈጽማል፡፡ በሌላ አነጋገር ሊቀ ካህኑ በሕዝቡና በእግዚአብሄር መካከል የአስታራቂነትን ሚና ይፈጽማል፡፡
ልክ እንደዚሁ መሲሁ ኢየሱስ የመንግሥተ ሰማይ ሊቀ ካህን፣ በእግዚአብሄርና በሰው መካከልም አስታራቂ ሆነ፡፡ በስጋው ላይ የሰውን ዘር ሐጢያቶች የተሸከመበትን ጥምቀት ከአጥማቂው ዮሐንስ በመቀበልና ስጋውን በመስቀል ላይ አሳልፎ ሰጥቶ መሥዋዕት በመሆን መሲሁ የሰውን ዘር በሙሉ ከሐጢያትና ከሞት አዳነ፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን የሕዝቡን ሐጢያት የሚያስወግደውን መሥዋዕት ያቀረበው ሊቀ ካህኑ ነበር፡፡ በአዲስ ኪዳን ግን የሰውን ዘር ሐጢያቶች ሁሉ ለመደምሰስ ኢየሱስ የሚለውን ስም ይዞ የመጣውና የዘላለሙን ሊቀ ካህን አገልግሎት የፈጸመው መሲሁ ነው፡፡ (ዕብራውያን ምዕራፍ 7-9)
በዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን እግዚአብሄር የሊቀ ካህኑን አገልግሎት በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ውስጥ በተደበቀው እውነት ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ለታጠቡት ጻድቃን ሰጥቷል፡፡ በሊቀ ካህኑ መጠምጠሚያ ላይ ያለው የወርቅ ምልክት ‹‹ቅድስና ለእግዚአብሄር›› የሚል ቅርጽ የተቀረጸበት ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ የሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ያስወገደውን ወንጌል በግልጥ ያሳያሉ፡፡
የሊቀካህኑ ልብስ ከሰማያዊ ማግ የተፈተለ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ ሰማያዊ ቀሚስ ኢየሱስ ከተቀበለው ጥምቀት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሊቀ ካህኑ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ እንደዚሁም ከወርቅ ግምጃ የተሠሩ ልብሰ ተክህኖዎችን ስለሚለብስ ልብሰ ተክህኖዎቹ ዕጹብ ድንቅና አራቱ ቀለማቶችም በግልጥ የሚታዩ ነበሩ፡፡ በሰማያዊው ቀሚስ ዘርፍ ላይ የወርቅ ሻኩራዎች (ቃጭሎች) ዙሪያውን ተያይዘው ሮማኖች ተደርገውባቸዋል፡፡ ዋናው ምንባባችን በቁጥር 33 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በታችኛው ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊውም፣ ከቀይም ግምጃ ሮማኖች አድርግ፤ በዚያ መካከል በዙሪያው የወርቅ ሻኩራዎች አድርግ፤›› ስለዚህ ሊቀ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ገብቶ ለሕዝቡ መሥዋዕትን ሲያቀርብ ከውጪ የቆሙት የእስራኤል ሕዝቦች የሻኩራዎቹን (የቃጭሎቹን) ድምጽ በመስማት መሥዋዕት እያቀረበ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ ከአዲስ ኪዳን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ እርስ በርሳቸውም ይስማማሉ፡፡ ሊቀ ካህኑ የሚያደርገው የሕዝቡን ሐጢያት ማንጻት ነበር፡፡ እርሱ እነዚህን ልበሰ ተክህኖዎች እንዲለብስና ይህንን ተግባሩን እንዲፈጽም ያደረገው የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንድናውቅ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን የዘመኑ ካህናት የሆኑት የእግዚአብሄር ሕዝቦች ሌሎች ከሐጢያቶቻቸው እንዲነጹ ለማድረግ ምን ያደርጋሉ? እነርሱ ይህንን ተግባር ለማከናወን በቅድሚያ ራሳቸው በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ መገለጥ በተገለጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያቶቻቸውን ስርየት መቀበል አለባቸወ፡፡ ስለዚህ የሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የሚያነጻንን ወንጌል በግልጥ ያሳዩናል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ እኛ ጻድቃኖች በዚህ በአሁኑ ዘመን የሰዎችን ሕሊና ከሐጢያቶቻቸው የማንጻትንና ቅድስናን የመስጠትን የክህነት ተግባሮቻችንን መፈጸም ይኖርብናል፡፡ በሊቀ ካህኑ መጠምጠሚያ ላይ የወርቅ ምልክት ተሠርቶ በምልክቱ ላይ ‹‹ቅድስና ለእግዚአብሄር›› የሚል የተቀረጸበት ለዚህ ነው፡፡
ይህ ‹‹ቅድስና ለእግዚአብሄር›› የሚል ቅርጽ የተቀረጸበት የወርቅ ምልክት ሊቀ ካህኑ በራሱ ላይ በሚጠመጥመው መጠምጠሚያ ላይ በሰማያዊ ፈትል ተያይዞዋል፡፡ ሰዎች ሊቀ ካህኑን በመጀመሪያ ዕይታ አይተውት ራሱን ሲመለከቱ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ ከተሠሩት ውብ ውጫዊ ልበሰ ተክህኖዎች ጋር የወርቅ ምልክቱንና ሰማያዊውን ፈትል በግልጥ ማየት ይችላሉ፡፡ ይህም ሊቀ ካህኑ ሁልጊዜ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ሐጢያትን የማንጻት ሥራ እንደሚሠራ ያሳየናል፡፡ 


የእግዚአብሄርን ባሮች የጽድቅ ፍርድ መታዘዝ ይገባናል፡፡

ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በሚገባበት ጊዜ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በልቡ በፍርዱ የደረት ኪስ ላይ ይሸከማል፡፡ እኛም እንደዚሁ እግዚአብሄርን መቀበል የሚሹ የዓለም ሐጢያተኞችን ነፍስ በልቦቻችን ውስጥ መሸከምና ለእነርሱም መጸለይ ይገባናል፡፡ እግዚአብሄር ሙሴን ሊቀ ካህኑ በሚለብሰው የደረት ኪስ ውስጥ ኡሪምና ቱሚም ተብለው የሚጠሩትን ሁለቱን የከበሩ ድንጋዮች እንዲያደርግ አዞት ነበር፡፡ የዛሬው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ቁጥር 30 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፤ በእግዚአብሄርም ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በእግዚአብሄር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል፡፡›› 
እነዚህ የኡሪምና የቱሚም ክቡር ድንጋዮች ቃል በቃል ‹‹ብርሃንና ፍጽምና›› ማለት ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ሊቀ ካህኑ የእስራኤልን ሕዝብ በጽድቅና በትክክል ይፈርድ ዘንድ እግዚአብሄር ብሩህ ልብ ሰጥቶታል ማለት ነው፡፡ ሊቀ ካህኑ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ያለውን ትክክለኛና የተሳሳተ ነገር ይፈርድ ዘንድ እግዚአብሄር ሥልጣንና ጥበብ ሰጥቶታል፡፡ ሊቀ ካህኑ በእስራኤሎች መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ትክክለኛውንና የተሳሳተውን እንዲወስን ሐላፊነት ነበረበት፡፡
በዚህ ዘመንም እንደዚሁ የትኛው ትክክል እንደሆነና የትኛው ስህተት እንደሆነ ለመፍረድና እንደዚሁም አንድ ሰው የሐጢያቶቹን ስርየት ተቀብሎ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለመለየት እግዚአብሄር ያንኑ ችሎታ ለእያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ ሰጥቶዋል፡፡ የእርሱ ባሮች በሰጣቸው ችሎታ እውነተኛው ወንጌል ምን እንደሆነ፣ ትክክለኛው የሐጢያት ስርየት ምን እንደሆነ፣ የእግዚአብሄር ልጆች ሊኖሩበት ያላቸው የጽድቅ መንገድ ምን እንደሆነና አንድ ሰው ዳግመኛ የተወለደ ወይም ያልተወለደ እንደሆነ ትክክለኛ ፍርድ መስጠት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄር ሕዝቦች በሙሉ የእርሱን ፍርዶችና አመራር መታዘዝ ነበረባቸው፡፡ የእግዚአብሄርን ባሮች ትክክለኛ ፍርድ ለመቀበል እምቢተኛ መሆን የእግዚአብርን ፈቃድ ለመቀበል እምቢተኛ ከመሆን ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ መገንዘብ አለባቸው፡፡ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ልክ እንደ ዛሬዎቹ ሊቀ ካህናት ለእግዚአብሄር ባሮች ፍርድ መገዛት ነበረባቸው፡፡
ልክ እንደዚሁ በዚህ በአሁኑ ዘመንም እግዚአብሄር ‹‹ትክክለኛውንና ስህተቱን›› የመፍረድን ሐላፊነት ለባሮቹ በአደራ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ የእርሱ ቤተክርስቲያን መሪዎች እያደረጉ ያሉትን ማክበርና ከሥራዎቻቸው ጋር ልባችንን ማስማማት አለብን፡፡ ለእኛ ተገቢው ነገር በእምነት ትክክለኛ ፍርዶቻቸውንና አመራራቸውን ከልባችን መከተል መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ‹‹ያንን የማደርገው ሊቀካህን ሆኖ ስለተሾመ ነው፡፡ ነገር ግን በፍጻሜው ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ነው›› ብለን ማሰብ አይገባንም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹የመጋቢዬን ጠባይ አልወደውም! ስብዕናው በትዕቢት የተሞላ ነው፡፡ ውሳኔውም እንደዚሁ አምባገነናዊ ይሆናል፡፡ በሚሰብከው ወንጌል ባምንም በአስተሳሰቦቹ በሚወስናቸው ወሳኔዎች መስማማት አልችልም፡፡ እኔም እንደዚሁ ከእርሱ የተለየ ዓላማ ያለኝ ሰው ነኝ›› ብለው ያስቡ ይሆናል፡፡ ሰዎች ሊቀ ካህናትን ከስጋዊ አመለካከታቸው አንጻር በመመልከት የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ላይ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ያለ የተሳሳተ ውሳኔ መወገድ አለበት፡፡
እኛ እግዚአብሄርን እንደምንታዘዝ ለደህንነታቸው በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ የሚያምኑትን የእግዚአብሄር ባሮች ልንታዘዝ ይገባል፡፡ ለምን? ምክንያቱም ውሳኔያቸው ከራሳቸው አስተሳሰቦች የፈለቀ ሳይሆን እግዚአብሄርን በሚያስደስተው እምነታቸው መሠረት የተደረገ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የዘመኑ ሊቀ ካህናት ውሳኔ በእግዚአብሄር ብርሃንና እውነት የተደረገ ስለሆነ የእግዚአብሄር ፍርድና ውሳኔ ነው፡፡ ውሳኔዎቻቸው የተመሠረቱት ከራሳቸው ሚጢጢ አስተሳሰቦች በፈለቀ አላስፈላጊ ተጽዕኖ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሄር ቃልና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ባላቸው እምነት መሠረት ላይ ከሆነ የደረሱበት ውሳኔ ትክክል ነው፡፡ እነዚህ ወሳኔዎች ከእግዚአብሄር ቃልና ከፈቃዱ ካላፈነገጡ ውሳኔዎቻቸው የእግዚአብሄር ውሳኔዎች መሆናቸውን ማመን አለብን፡፡ 
ስለዚህ የሊቀ ካህኑ አገልግሎት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደሆነው በዚህ በአሁኑ ዘመንም የእግዚአብሄርን ሕዝብ የሚመራው ሊቀ ካህኑ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ በእስራኤል ከሊቀ ካህኑ ውጭ ሕዝቡን መምራት የሚችል ንጉሥ አልነበረም፡፡ የእስራኤል ፖለቲካዊ ስርዓት በእርግጥም አምላካዊ አስተዳደር ስለነበር ሕዝቡ በሙሉ በሊቀ ካህናቱ የተወሰኑትን ውሳኔዎች ይከተሉ ነበር፡፡ የእግዚአብሄር ሕዝብ በመንፈሳዊ ጉዳዮች እግዚአብሄር በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የእግዚአብሄር ቃል በሚያዘው መሰረት በሾማቸው ባሮች ምሪት ማመንና ያንንም መከተል አለባቸው፡፡ ሊቀ ካህናቱም በቃሉና በመለኮት ጣልቃ ገብነቱ ላይ በተመሠረተው የእግዚአብሄር ፈቃድ መሰረት እያንዳንዱን ነገር መወሰን አለባቸው፡፡
የሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች በእርግጥም ብዙ ትምህርቶችን ያስተምሩናል፡፡ በቅድሚያ እነዚህን ልብሰ ተክህኖዎች ለመሥራት ጥቅም ላይ የዋሉት ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና የወርቅ ማግ መንፈሳዊ ትርጉሞች ማወቅ አለብን፡፡ ቀደም ብሎ የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውንና የቀዩን ማግ እውነት ተምረናል፡፡ እግዚአብሄር በሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች አማካይነት በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ውስጥ የተደበቀው እውነትና በዚህ የሚያምነውም እምነት ምን ያህል አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ እነዚህ ማጎች የሕዝቡን ሐጢያቶች ስርየት የሚያሳዩ ጥሬ ዕቃዎች ናቸው፡፡ ጌታ ወደዚህ ምድር መጥቶ መጠመቁና ደሙን ማፍሰሱ በመላው ዓለም የእያንዳንዱን ሰው ሐጢያቶች በሙሉ የሚያስወግደው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ብቻ እንደሆነ ይገልጣል፡፡ ሰማያዊው፣ ሐምራዊውና ቀዩ ማግ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ፍጹም ስርየታችንን የሰጠን እውነት መሆኑን ስላስተማሩን ሁላችንም ወደዚህ ትክክለኛ ትርጉም ዕውቀት ላይ መድረስ አለብን፡፡ ይህንን ከልባችን በትክክል አውቀን ስናምንበት ለዘላለም ከሐጢያቶቻችን ነጽተን የዘላለምን ሕይወት እንቀበላለን፡፡ ስለዚህ በውሃው፣ በደሙና በመንፈሱ ወንጌል በተፈጸመው በዚህ እጅግ ግልጥ እውነት የሚያምን እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ 


በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ላይ ያለንን እምነት መደገፍ አለብን፡፡ 


በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ እንዲህ ያለ ትክክለኛ ዕውቀትና የማይናወጥ እምነት ከሌለን ለእውነተኛው ወንጌል ጠበቃ ሆነን መቆም አንችልም፡፡ የከፋው ደግሞ ይህ ወንጌል ሊበረዝ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ሐይማኖቶች ጊዜ እየነጎደ ሲሄድ ራሳቸውን ሊለውጡ ይችላሉ፡፡ እግዚአብሄር ግን የሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች ባላቸው ቀለማቶች አማካይነት ፈጽሞ የማይለወጠውን የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውንና የቀዩን ማግ እውነት አሳይቶናል፡፡ በሊቀ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖዎች አማካይነት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በሚገኙት ዕቃዎች ሁሉ አማካይነትና እንደዚሁም በመገናኛወ ድንኳን ውስጥ በሚቀርበው መሥዋዕት ምሳሌ አማካይነት እግዚአብሄር ፍጹም የሆነውን ፍቅሩንና ዕቅዶቹን ለእኛ እየገለጠልን ነው፡፡ ስለዚህ የሰማያዊው፣ የሐምራዊውና የቀዩ ማግ ወንጌል ሆኖ ወደ እኛ በመጣው በዚህ ዘላለማዊ እውነት ላይ ያለንን እምነት በትጋት መከላከል አለብን፡፡ ዘመን ሲለወጥ ፈጽሞ የማይለወጠው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለን እምነት ነው፡፡ ይህ እምነት በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጠው ዘላለማዊ ደህንነት የሚያምን እምነት ነው፡፡
ይህ የምናምንበት የሰማያዊ፣ የሐምራዊና የቀይ ማግ ወንጌል ይለወጥ ዘንድ እንዴት ልንፈቅድ እንችላለን? እግዚአብሄር ከሐጢያት ያዳነን በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ወንጌል መሆኑን ከነገረን እንግዲያውስ እውነቱ ይህ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሄር በእጆች መጫንና በሚፈስሰው ደም የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች ደመሰሰ፡፡ ዛሬም በዚህ ዘመን ደግሞ ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀትና (ማቴዎስ 3፡15) በመስቀል ላይ በሆነው ሞቱ ስለ እኛ ፍጹም የሆነውን የሐጢያት ስርየት ፈጸመ፡፡ እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የመላውን ዓለም ሐጢያተኞች በሙሉ ሐጢያቶች ደምስሶዋል፡፡
ይህ ምንኛ ተስፋ የሚሰጥ ነው! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወርቅ ‹‹እምነትን›› ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ ከተሠሩት የሊቀ ካህኑ ልበሰ ተክህኖዎች ጋር አብሮ ጥቅም ላይ የዋለው የወርቅ ድሪ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለንን የእምነታችንን ወሳኝነት ይጠቁማል፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችን ሁሉ የሚደመሰሱበትን ዘዴ ስላቋቋመና እንዲቀየሩም ስለማይፈቅድ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሙንም ሰላማችን የተጠበቀ ነው፡፡ ይህ የሆነው እግዚአብሄር ባሳየን በሰማያዊ፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጠው እውነት የተነሳ ነው፡፡ 

 
የሊቀ ካህኑ መታጠቂያ፡፡


ከሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች መካከል መታጠቂያም ይገኝበታል፡፡ ሊቀ ካህኑ በኤፉዱ ላይ የሚታጠቀው ይህ መታጠቂያም እንደዚሁ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተሠራ ነበር፡፡ የኤፉዱ መታጠቂያ የጥንካሬ ተምሳሌት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፤›› (ኤፌሶን 6፡14) የሊቀ ካህኑ መታጠቂያ የወንጌልን እውነት ከማመን የሚመጣውን ሐይል ያመለክታል፡፡ በሌላ አነጋገር በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ እውነት የሚያምነው እምነት ከሐጢያቶቻችን በሙሉ እንድንድን ያስቻለን መሆኑን ይነግረናል፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩ በፍታ ከተገለጠው ውጭ በሌሎች አስመሳይ ወንጌሎች ማመን ከንቱ ነው፡፡
በስጋ ጎዶሎዎች የሆኑ ሰዎችም በጌታ በተሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ፈጽመው መንጻት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ በእግዚአብሄር በተፈጸመው የሐጢያት ስርየት እውነት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሻግረዋልና፡፡ (ማቴዎስ 3፡15፤ ዘሌዋውያን 16፡1-22) ስለዚህ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጡት የኢየሱስ ሥራዎች እንዳዳኑዋቸው የሚያምኑ ስጋቸውና የፈቃድ ሐይላቸው ደካማ ቢሆኑም ሊበረቱ ይችላሉ፡፡ የሰማይ ሊቀ ካህን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ላይ ዕርፍ ስንል ከክርስቶስ ፍቅር ማን ሊለየን ይችላል? የእርሱ ፍጹም ደህንነት የእኛ ሊሆን የሚችለው በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩ በፍታ በተገለጠው እውነት ስናምን ብቻ ነው፡፡ 
ካህናቶች የክህነት ተግባሮቻቸውን ሲፈጽሙ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከተገለጠው የመስዋዕት ስርዓት ውጭ አንዳች ሌላ ሰው ሰራሽ ትምህርቶችን መከተል የለባቸውም፡፡ ልክ እንደዚሁ የዘመኑ የእግዚአብሄር ባሮችም ከእውነተኛው ወንጌል ያፈነገጡ ልዩ ወንጌሎች በጠፉት ነፍሳቶች ውስጥ ሥር እንዲሰዱ መፍቀድ አይገባቸውም፡፡ (ገላትያ 1፡6,9) እንደ እነዚህ ያሉ አስመሳይ ወንጌሎችን የሚሰብኩ ስብከቶቻቸውን ምንም ያህል በሚገባ ቢያቀርቡም የጠፉ ነፍሳቶችን ማገዝ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የተገለጠውን የእግዚአብሄርን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በትክክል አልመሰከሩምና፡፡ እነርሱ አስመሳዮችና ሐሰተኛ አስተማሪዎች ናቸው፡፡ የሰማዩን ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን አድርገን ወደ ማመኑ ስንመጣ በመገናኛው ድንኳን ስርዓት ውስጥ የተገለጠውን የመሥዋዕቱን ስርዓት የእጆች መጫንና የፈሰሰውን ደም ከመቀበል መጉደል የለብንም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ሐሰተኛ ወንጌሎች እንዳሉ ማወቅ አለብን፡፡ ወንጌልን የሚሰብክ ማንም ይሁን በእግዚአብሄር ቃል ላይ ተመሥርቶ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እውነት ለሚሰብክ ሁሉ ጆሮዋችንን መስጠትና ማመን አለብን፡፡
የዘመኑ ክርስትና በብዙ ችግሮች ከተተበተበባቸው ምክንያቶች አንዱ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳያውቁ ክህነታዊ ሐላፊነቶቻቸውን እየፈጸሙ እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ መንፈሳዊ አስመሳዮች መኖራቸው ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት እውነተኛ ካህናቶች ለመሆን የመጀመሪያው ደረጃ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ተገቢውን መሥዋዕት ማቅረብ የሚችሉት ይህ እምነት ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሚያውቁና የሚያምኑበት ሰውን ሁሉ ከልባቸው መውደድ ይችላሉ፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የተቋቋመችበት ምክንያት ምንድነው ብላችሁ ታስባላችሁ? የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የተቋቋመችው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለሐጢያተኞች ለመስበክ ነው ማለት እችላለሁ፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጠው የሰማያዊ፣ የሐምራዊና የቀይ ማግ እውነት ከሙሉ ልባችን ስናምን ከሐጢያቶቻችን ድነን ሐጢያት አልባ እንሆናለን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን በልቦቻችን ውስጥ እውነተኛ ሰላም ይኖራል፡፡ በዚህ ሰላም ውስጥ ስለምንኖር ከእግዚአብሄር በጭራሽ አንርቅም፡፡ ፍጹም በሆነው ወንጌል እናምናለን፡፡ በእምነት እንኖራለን፡፡ ከዚያም ወደ ጌታ መንግሥት ገብተን በዚያ እንኖራለን፡፡ ጌታችን ወደ ሰላም መርቶናል፡፡ በሊቀ ካህኑ መጠምጠሚያ ፊት ላይ ‹‹ቅድስና ለእግዚአብሄር›› የሚለው ቅርጽ በወርቁ ምልክት ላይ እንደተቀረጸ ሁሉ የዓለምን ሕዝብ በሙሉ ወደ እግዚአብሄር በመምራት በእውነተኛው የሐጢያቶች ስርየት ብርሃን ያበራቸዋል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር የሐጢያቶቻቸውን ስርየት እንዲቀበሉ የሚያስችሉዋቸውን ሥራዎች በአደራ ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሄር በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ወንጌል ለምናምነውም ለብሉይ ኪዳን ካህናት ከሰጣቸው ሐላፊነቶች ጋር የሚመሳሰል ሐላፊነት በአደራ ሰጥቶናል፡፡
እነዚህን ክቡር የሆኑ ሥራዎች ፍጹም በሆነው የእውነት ብርሃኑ እንድንሠራ ስለፈቀደልን እግዚአብሄርን እናመሰግነዋለን፡፡ ይህንን የወንጌል ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ከእግዚአብሄር በሰማሁት ጊዜ በደስታ ተጥለቅልቄ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብም ይህ ወንጌል ግልጥ ሆኖ ታየኝ፡፡ ከዚያ በኋላ መንፈሳዊ ዓይኖቼ ተከፈቱ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የእግዚአብሄርን ቃል በዝርዝር አስተማረኝ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች ሁሉ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እግዚአብሄር የሰጠን ብቸኛው ወንጌል እንደሆነ በግልጥ እንደሚመሰክር ተረዳሁ፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ይህ ወንጌል ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ ሆኖ ተገልጦዋል፡፡ በአዲስ ኪዳንም እንደዚሁ ሐዋርያቶችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በሙሉ እኛን ፈጽሞ ከሐጢያት ለማዳን ጥምቀትን እንደተቀበለና ደሙን እንዳፈሰሰ ነግረውናል፡፡ ከጌታ ዘንድ የሐጢያት ስርየትን መቀበል የምንችለው የንስሐ ጸሎት በመጸለይ አይደለም፡፡ ብቸኛው እውነተኛ ፍጹም ወንጌል የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡
ሊቀ ካህኑ እግዚአብሄር ባዘዘው መሠረት ሆነ ተብሎ የተሠራውን ልብሰ ተክህኖ መልበስ ነበረበት፡፡ ሊቀ ካህኑ ብርድ ቢያስቸግረውና እግዚአብሄር ያዘጋጀለትን ሸሚዝ መልበስ እንደማያስፈልገው በማሰብ በገዛ ፈቃዱ ወፈር ያለ ሸሚዝ ቢለብስ ወዲያውኑ ይሞት ነበር፡፡ ሊቀ ካህኑ ከጥሩ በፍታ የተሠራውን ሸሚዝ ብቻ ለብሶ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ቢገባም እንደዚሁ ይገደላል፡፡ ሰማያዊውን ቀሚስና ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ የተፈተለውን ኤፉድም መልበስ ነበረበት፡፡ 
እግዚአብሄር ያቀደውን መንገድ በትክክል ስንከተል ጌታ በፊታችን ይሄድና ይመራናል፡፡ በእያንዳንዱ የሕይወታችን ነገርም ይሠራል፡፡ እግዚአብሄር መሲሁን ሊልክልን አቀደ፡፡ ይህንን ዕቅድም ለእኛ ገለጠልን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ብናምንና የእግዚአብሄርን ዕቅድ ብንከተል በሕይወታችን ውስጥ ይሠራል፡፡ የሐጢያትን ስርየት የምንቀበለው በእኛ በኩል አንዳንድ ምግባሮችን በማድረግ ያልሆነው ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን የሐጢያቶቻችንን ስርየት መቀበል ያለብን ለሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች ጥቅም ላይ በዋሉት በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ በተገለጠው የእግዚአብሄር የደህንነት ዕቅድ በማመን ነው፡፡ 
እኛ የእግዚአብሄር ካህናት ማድረግ ያለብን ነገር እግዚአብሄር ያቀደልንን ማመንና ያንኑ መከተል ነው፡፡ እውነተኛው እምነት ይህ ነው፡፡ በራሳችን መንገድ ሁሉንም ዓይነት ያማሩ ዕቅዶች በማቀድ እግዚአብሄርን ማገልገል በእግዚአብሄር የማመን ትክክለኛው መንገድ አይደለም፡፡ የውሃውን የመንፈሱን ወንጌል በሌሎች አገሮች የማሰራጨት ጥረቶቻችንን በሚመለከት ይህም ቢሆን በራሳችን ሰው ሰራሽ ዕቅዶችና መንገዶች አማካይነት አንዳች የተለየ ነገር በማድረግ የሚከናወን ሳይሆን በእምነታቸው አማካይነት ለሕዝቡ በሰጠው በራሱ ረድኤት የሚከናወን ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ይህ ነው፡፡ አንድን ነገር በእምነት ስናደርግ ቀሪውን እግዚአብሄር ያከናውነዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አውቀን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ስናሰራጭ እግዚአብሄር መጽሐፎቻችንን የሚያነቡትን ሰዎች ልቦች ይነካና ያነቃቸዋል፡፡ በዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እንዲያምኑም ያደርጋቸዋል፡፡ ማመን ይችሉ ዘንድም የተሳሳቱትን አስተሳሰቦቻቸውን ያርማል፡፡ እነርሱም ደግሞ በተራቸው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ያሰራጫሉ፡፡
 

እኛ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለማሰራጨት በቅድሚያ ከሙሉ ልባችን በእርሱ ማመን አለብን፡፡

የእውነተኛው ወንጌል ስርጭት የሚከናወነው እኛ በምናደርገው አንዳች ነገር ሳይሆን ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር በመስማማት በእምነት ስናገለግለው ብቻ እንደሆነ ተናግሬያሁ፡፡ ነፍሳቶች የሚለወጡት በእኛ ጥረቶችና ቀናዒነት አይደለም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄር ቸርነት ይፈጸም ዘንድ በእርሱ ሥራዎችና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ስንሻ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማገልገል ያለብን በእምነት ነው፡፡ በዚህ በአሁኑ ዘመንም እንደዚሁ የእግዚአብሄር ልጆች የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውንና የቀዩን ማግ እምነት ማሰራጨት አለባቸው፡፡
በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ማመንና እርሱንም ማሰራጨት አለብን፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያ በሰማያዊው ማግ የተገለጠውን ማለትም መሲህ ኢየሱስ የተቀበለውን ጥምቀት ማወቅ አለብን፡፡ የሰማያዊውን ማግ እውነት ለጠፉት ሰዎች ስናሰራጭ ሙሉውን የእውነት ስዕል ይበልጥ በቀላሉ ስለሚረዱት በእርግጠኝነት እንደሚያምኑበት እንረዳለን፡፡ ለምን? ምክንያቱም መሲሁ ኢየሱስ በጥምቀቱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በስጋው ተሸክሞዋልና፡፡ ሰዎች በኢየሱስ ጥምቀት በማመን ኢየሱስ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ እንዳስወገደላቸው ሲያውቁ የሐጢያቶቻቸውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ እንደሞተም መገንዘባቸው አይቀሬ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሰዎች በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ወደ ማመን የሚመጡት የሰማያዊው ማግ እውነተኛ አካል በሆነው በመሲሁ ኢየሱስ የጥምቀት ምስጢር ሲያምኑ ነው፡፡ ‹‹አሃ በጥምቀቱ ሐጢያቶቼን ሁሉ ወስዶዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክና የሰው ዘር ሁሉ አዳኝ ነው፡፡ ይህ ልዩ እውነት ነው!›› በማለት በእርግጠኝነት ይረዳሉ፡፡
ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ራሱ አምላክ መሆኑ ን የሚያሳየውን የሐምራዊውን ማግ እምነት የሚገነዘቡት በኋላ ነው፡፡ ኢየሱስን አዳኝ አድርገን ማመን በምንጀምርበት ቅጽበት ‹‹ኢየሱስ ፍጹም አምላክ ነው›› ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ግን የማይጨበጥ ዕሳቤ ብቻ ነው፡፡ በልባችን ውስጥ እንዲህ ወዳለ ተጨባጭ እምነት የመጣነው ከጊዜ በኋላ ብቻ ነው፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና ደም በማመን የሐጢያት ስርየትን ስንቀበል ያን ጊዜ ኢየሱስ ራሱ እኛን የሚያግዘንና በሕይወታችን ውስጥም የሚሠራ ሕያው አምላክ እንደሆነ ወደሚያምን እምነት መጣን፡፡ በኢየሱስ ላይ ያለን እምነትም ቀስ በቀስ አደገ፡፡ ስለዚህ ሰዎች የሐጢያት ስርየትን ለማግኘት እግዚአብሄር ባስቀመጠው የሰማያዊው፣ የሐምራዊውና የቀዩ ማግ ወንጌል ማመን አለባቸው፡፡
 

የዘመኑ ካህናት ማገልገል ያለባቸው ምንን ነው? 

ሊቀ ካህናቱ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚያከናውኑት ምን ነበር? በመሥዋዕቱ ስርዓት አማካይነት ምን ይገልጡ ነበር? መሲሁ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ እንደሚደመስስ የሚናገረውን እውነት ገልጦዋል፡፡ በዚህ ዘመን ያሉት የእግዚአብሄር ባሮችም እንደዚሁ ይህንን ሐላፊነትና አገልግሎት መተካት ይገባቸዋል፡፡ እነርሱ የሕዝቡን ሐጢያቶች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እየደመሰሱ ነው፡፡
እጅግ ብዙ ሰዎች የራሳቸውን የወንጌል ትርጉም ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ እንደዚህ ያለ ወንጌል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመሠረተ ትክክለኛ ወንጌል አይሆንም፡፡ ማንንም አያድንም፡፡ እነርሱ ከዚህና ከዚያ ሰው ሰራሽ ትምህርቶችን ተበድረው በአንድ ላይ በማቆራኘት የተካኑ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ግን የተለያዩ የክርስቲያን ትምህርቶችን በአንድ ላይ በማቆራኘት የተፈጠረ ነገር አይደለም፡፡
ሰዎች ያለ ምንም ማመንታት የሐጢያት ስርየት የሚያገኙት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ብቸኛው የደህንነት መለኪያ ቃሉ ነው፡፡ የሰዎችን ሐጢያት ማንጻት የሚቻለው እግዚአብሄር ባስቀመጠው መለኪያ ብቻ ነው፡፡ ይህ መለኪያ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ ከእውነተኛው የደህንነት ወንጌል ውጪ ማንም ከሐጢያቶቹ ነጽቶ ቅድስናን ሊቀበል አይችልም፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ከሐጢያቶቻችን መንጻትና ቅድስናን መቀበል የምንችለው በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀውና አዳኝ ሆኖ ደሙን በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ኢየሱስ በማመን ብቻ ነው፡፡ ሰዎች የሐጢያቶቻቸውን ሁሉ መንጻት ያገኙ ዘንድ ልክ እንደዚህ በትክክል በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን አለባቸው፡፡ የሐጢያቶችን ስርየት ለመቀበል ሌላ መንገድ የላቸውም፡፡
የእርሱ ካህናት የሆኑት የእግዚአብሄር ባሮችም ለሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች ጥቅም ላይ በዋሉት በወርቅ፣ በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ የተሠራውን እውነተኛ ወንጌል ማመን አለባቸው፡፡ በዚህ እውነት የማያምኑ ከሆኑ የእርሱ ባሮች ለመሆን አይበቁም፡፡ እንዲያው ተራ የዚህ ዓለም ሐይማኖተኞች ሆነው ይቀራሉ፡፡ እጅግ ብዙ ከሆኑት የዓለም ሐይማኖቶች ውስጥ የኢየሱስን ስም በመበደር የተቋቋሙትን የገዛ ራሳቸውን ሐይማኖቶች ብቻ ያገለግላሉ፡፡ የእግዚአብሄር እውነተኛ ባሮች አዳኝ ሆኖ በውሃው፣ በደሙና በመንፈሱ በመጣው በኢየሱስ የሚያምን እምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ እምነታቸው በይፋ እንዲታይና የእግዚአብሄርም የእውነት ብርሃን በግልጥ እንዲያበራ የእርሱን ጥምቀት መመስከር አለባቸው፡፡ የእግዚአብሄር ባሮችና በፊቱም የዳኑት ይህንን የሚያደርጉት ብቻ ናቸው፡፡
የኢየሱስን ጥምቀት፣ መስቀሉን ወይም እርሱ ራሱ አምላክ የመሆኑን እውነት የማይቀበሉና ይህንን ዕውቀት ያለ እምነት እንዲያው በጽንሰ አሳብ ደረጃ የሚሰብኩት ከእግዚአብሄር ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የዲያብሎስ አገልጋዮች ናቸው፡፡
ዛሬ በዚህ ዓለም ላይ እጅግ ብዙ ‹‹ወንጌላውያን ተብዬዎች›› አሉ፡፡ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ በእምነት ከሐጢያቶቹ ሁሉ መንጻትና ሐጢያት አልባ መሆን ይችላል ይላሉ፡፡ መጀመሪያ ላይ እነርሱም እንኳን የሰማያዊውን፣ የሐምራዊንና የቀዩን ማግ እውነት እየሰበኩ ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ነገሩ እንደዚህ እንዳልሆነ ተረዳሁ፡፡ እነርሱ በራሳቸው አስተሳሰቦች የተፈጠሩት ትምህርቶች እውነተኛ ወንጌል እንደሆኑ በማሰባቸውና በማመናቸው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እየሰበኩ አይደለም፡፡ ራሳቸውን ‹‹ወንጌላውያን›› ብለው ቢጠሩም የሚከተሉት ግን የራሳቸውን ራስ ወዳድና ምድራዊ ምቾት ብቻ ነው፡፡ ዓላማቸውም ፍላጎታቸውን ማርካት ነው፡፡
አሁንም ቢሆን በዚህች ምድር ላይ ብዙ ካህናት ተብዬዎች አሉ፡፡ በተጨባጭ ቅዱሳን መሆን የሚያስችላቸውን እውነተኛ ወንጌል ለመቀበል እምቢተኛ የሚሆኑት ግን ለምንድነው? ወግ አጥባቂዎች በራሱ በቃሉ ላይ ባላቸው እምነት ይኮራሉ፡፡ እውነታው ግን እንደዚህ ዓይነት ሰዎችም ቢሆኑ በተጨባጭ ወግ አጥባቂዎች አለመሆናቸው ነው፡፡ ቃሉ በግልጥ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ገልጦ ሳለ የኢየሱስን ጥምቀት ከእምነታቸው ያወጡት ለምንድነው? ናዳብና አብዩድ የሞቱት በእግዚአብሄር ፊት እንግዳ እሳት በማቅረባቸው እንደሆነ ይታወስ፡፡ እነዚህ ካህናት እግዚአብሄር ባስቀመጠላቸው መንገድ መሠረት ቁርባኑን ባለማቅረባቸው ከእግዚአብሄር ዘንድ እሳት ወጥታ በማቃጠል ገደለቻቸው፡፡ (ዘሁልቁ፡26፡61) 
ሊቀ ካህኑም ቢሆን እግዚአብሄር ባዘዘው መሠረት ቀሚሱን ባይለብስ ኖሮ (ቁጥር 43) ይሞት ነበር፡፡ ሐጢያተኞች ምንም ያህል ተግተው የመሥዋዕቶቻቸውን ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ቢያቀርቡም በመጀመሪያ እጆቻቸውን በእንስሶች ራሶች ላይ እስካልጫኑ ድረስ መሥዋዕቶቻቸው ምንም ማለት ናቸው፡፡ ሐጢያቶቻቸውን ተናዘው ወደ መሥዋዕቶቻቸው ላይ የሚያሻግሩበት ይህ እጆችን በመጫን ላይ ያለ እምነት ሳይኖራቸው በመሥዋዕቶቹ ደም ምንም ያህል ቢያምኑም እምነታቸው ከንቱ ነወ፡፡ ሊቀ ካህናቱ ምንም ያህል ደጋግመው ደሙን ቢያቀርቡ፣ መጋረጃውን ቢገልጡ፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ቢገቡና ደሙን በስርየት መክደኛው ላይ ቢረጩ እግዚአብሄር ያዘጋጀውን ‹‹ሰማያዊ›› ቀሚስ ለብሰው ካልቀረቡ ይሞታሉ፡፡ ስለዚህ አፈንጋጮች ሁሉ አሮጌዎቹን የእምነት መንገዶቻቸውን ወደዚያ ጥለው ወደ ‹‹ብርሃንና ፍጽምና›› ማለት ወደ ‹‹ኡሪምና ቱሚም›› (ዘጸዓት 28፡30) ሊመራቸው ወደሚችለው ወደ እውነተኛው ወንጌል መመለስ ይገባቸዋል፡፡
እግዚአብሄር ደካሞች ቢሆኑም ቃሉንና ፈቃዱን አምነው በሚከተሉት ይደሰታል፡፡ እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ የምናምነውን የጠራን ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሄር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በአደራ ሰጥቶናል፡፡ በአንድነት ተባብረን በእምነት ወንጌልን ስናሰራጭ እግዚአብሄር አስደናቂ ሥራዎችን በየጊዜው እንድናከናውን ይፈቅድልናል፡፡
በቅርቡ የእግዚአብሄር ፈቃድ በሙሉ እንደሚፈጸም እናምናለን፡፡ በእርግጥ እኛ በእግዚአብሄር ፊት ደስተኞች ነን፡፡ በስጋችን ብዙ ጉድለቶች አሉብን፡፡ እኔ ከሁሉም የከፋሁ እንደሆንሁ አስባለሁ፡፡ እኔ ራሴን በግልጥ በፊታችሁ ብናዘዝ ሰው በመሆኔ እጅግ ብዙ ጉድለቶች ስላሉብኝ ፊቴ በሐፍረት ይቀላል፡፡ ድካሞቼ ጊዜያዊ አይደሉም፡፡ ጊዜ እየነጎደ ሲሄድ ወንጌልን አብዝቼ ባገለገልሁ መጠን በእግዚአብሄር ፊት ምን ያህል ደካማ እንደሆንሁ እገነዘባለሁ፡፡ አብረውኝ የሚሠሩትን ሠራተኞች ስመለከትም እነርሱም እንደ እኔ ደካሞች መሆናቸውን እመለከታለሁ፡፡ ነገር ግን ለእግዚአብሄር ጸጋ ምስጋና ይድረሰውና አሁንም ወንጌልን እያገለገልን ነው፡፡ እግዚአብሄር በአምላክ ወንጌልና በዕቅዶቹ በማመን የእርሱን ሥራ እንድናገለግለውና እንድንከተለው በእኛ ውስጥ የሚሠራ መሆኑን እንድናምን አድርጎናል፡፡
ጌታችን የሚከብረው በእኛ በደካሞቹ አማካይነት ነው፡፡ በብዙ ድካሞች እንደሆንን መጠን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌልም የዚያኑ ያህል በልቦቻችን ውስጥ ያበራል፡፡ እግዚአብሄር የሚከብረው ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ራሳችንን እንከን የለሽ አድርገን ስንቆጥርና ይበልጥ ኩሩዎች ስንሆን ያን ጊዜ እግዚአብሄር ጥሩ ስሜት አይሰማውም፡፡ ከእኛ ከደካሞቹ ምስጋናን ለመቀበል የሚሻው አምላክ ፈቃዱ ይህ ነው፡፡
እናንተና እኔ በጣም ደካሞች ነን፡፡ ምን ያህል ደካሞች ነን? ቃላት ሊገልጠው ከሚችለው በላይ ደካሞች ነን! ነገር ግን የውቅያኖስ ወይም የወንዝ ጥልቀት በመታጠቢያ ሳህን ውስጥ ካለው ጥልቀት የተለየ እንደሆነ ሁሉ እያንዳንዱ ሰውም የራሱ ድካሞች የሚታወቁት በተለየ መንገድ ነው፡፡ ከመጠን በላይ ደካሞች መሆናቸውን ከልባቸው የሚያውቁ ጌታን አብዝተው ይወዱታል፡፡ ምክንያቱም ለጌታ ከፍተኛ ዕዳ እንዳለባቸው ያውቃሉና፡፡ ድካሞቻቸውን በሚገባ የሚያውቁና ከመጠን በላይ የሆኑት ዕዳዎቻቸው እንደተሰረዙላቸው የሚያምኑ ጌታን አብዝተው ይወዱታል፡፡ በጌታ ወንጌል በአያሌው በመኩራራትና አብዝተው በመከተል የሚወዱት ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን ድካሞቻቸውን የማያውቁ ጌታን የሚወዱት በመጠኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የተሰረዙላቸው ዕዳዎች ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑና ጌታም እነዚህን ጥቂቶች ዕዳዎች ለመሰረዝ ከአነርሱ ብዙ እንደሚፈልግ ያስባሉና፡፡
ስለ ጉድለቶቻቸው በጣም በጥቂቱ የሚያውቁት እነዚህ ሰዎች ድካሞቻቸው በእርግጥም ምን ያህል ታላቅ እንደሆኑ መገንዘብ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህንን በእነርሱ ላይ በግዴታ መጫን አይቻልም፡፡ ነገር ግን ደካሞች ቢሆኑም ወንጌልን ማገልገል ለእነርሱ የእግዚአብሄር መንገድ መሆኑን በማመን ይህንን ሲያደርጉ ጉድለቶቻቸው ጊዜውን ጠብቀው ይገለጣሉ፡፡ አብዝተው በተገለጡ መጠንም ለእግዚአብሄር ያላቸው ፍቅር ይበልጥ እየጠለቀ ይሄዳል፡፡
ድካሞቻችንን በጽንሰ አሳብ ደረጃ ማወቅ ብቻውን አይጠቅመንም፡፡ ድካሞቻችንን ወደ ማወቅ መምጣት የምንችለው ወንጌልን በእርግጥ ለመስበክ እየሞከርን ሳለ አስቸጋሪ ወቅት በሚገጥመን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ጌታን አብዝተን ባገለገልነው ቁጥር እርሱም ለእኛ አብዝቶ ክቡር የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ደፋሮች የምንሆነው ከጌታ የተነሳ ነው፡፡ የምንከብረውም ከጌታ የተነሳ ነው፡፡ ከጌታ የተነሳ በእምነት መኖርና ራሳችንን ለተባረኩት ሥራዎቹ ቀድሰን መስጠት እንችላለን፡፡ በጌታ ባይሆን ኖሮ እናንተና አኔ ምናምን ነበርን፡፡
አጥማቂው ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- ‹‹እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባኛልና፡፡›› (ዮሐንስ 3፡30) እግዚአብሄር የሐጢያት ስርየትንና ይህንን ወንጌል የምናገለግልባቸውን የተባረኩ ዕድሎች ሰጥቶናል፡፡ የምንኖረው ወንጌልን ለማሰራጨት መገልገያ መሣርያዎች ለመሆን ብቻ ነው፡፡ ክብሩን የሚወስደው ጌታ ብቻውን ነው፡፡ ጌታ እኛን መሣርያዎቹ አድርጎ የሚጠቀምብን የመሆኑ እውነታ በራሱ ለእኛ እጅግ አስደሳች ነገር ነው፡፡
እግዚአብሄር የሊቀ ካህኑን ተግባራቶች የምናከናውንበትን ይህንን በረከት ስለሰጠን ከልባችን እናመሰግነዋለን፡ ኢየሱስ ለእኛ ሰማያዊ ሊቀ ካህንና ታላቅ እረኛ ነው፡፡ የእርሱ አገልጋዮች ትንንሽ እረኞች ናቸው፡፡ እናንተና እኔ ታላቁ እረኛ ለእኛ ያደረገውን የምንከተል ትንንሽ እረኞች ሆነናል፡፡ እናንተና እኔ ልክ እንደተጸፈው በትክክል በእግዚአብሄር ቃል ማመን በተጻፈው ቃል መሠረት መጓዝ፣ ይህንንም በተጻፈው መሠረት መከተል አለብን፡፡ ጌታ እንዳደረገው በትክክል ማገልገል፣ ማመንና እርሱንም መከተል አለብን፡፡ እኛ ማድረግ የሚገባን ነገር ቢኖር እርሱ ባዘዘንና ለእኛ ባቀደው መሠረት ማመንና መከተል፣ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌልም ማሰራጨት ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ትክክለኛው እምነት ቃሉን በንጽህና መቀበልና በእርሱ በማመንም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ ነው፡፡
ሊቀ ካህናችን ለሆነው ጌታችን ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡