Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 6-1] የሮሜ መግቢያ ምዕራፍ 6

የኢየሱስን ጥምቀት ምስጢር መረዳት አለብን፡፡

 
ኢየሱስ ከዮሐንስ ስለተቀበለው የጥምቀት ምስጢር አውቃችሁ ታምናላችሁን? ስለዚህ ነገር ከሮሜ 6፡1-4 ልነግራችሁ እወዳለሁ፡- ‹‹እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በሐጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም፡፡ ለሐጢአት የሞትን እኛ ወደፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሳ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡››
 
ይህንን ጥቅስ ለመረዳትና እውነቱን ቆፍረን ለማግኘት ከሁሉ በፊት በገላትያ 3፡27 ላይ የታየውን የጳውሎስን እምነት መረዳትና እኛም የእርሱ አይነት እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ እርሱ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡›› ይህ ጥቅስ ምን ማለት ነው? አሁን እነዚህን ቃሎች በማቴዎስ 3፡13-17 አማካይነት መረዳት እንችላለን፡፡
 
ጳውሎስ በእግዚአብሄር ጽድቅ ለአንዴና ለመጨረሻ የሐጢያቶችን ስርየት ስለተቀበልን በሐጢያት ጸንተን ስለመኖር ይጠይቃል፡፡ የጳውሎስ መልስ አይሆንም የሚል ነው፡፡ ይህ በእርግጥ በእግዚአብሄር ጽድቅ ለሚያምኑ ሰዎችም የተሰጠ መልስ ነው፡፡ ይህ ማለት ጻድቃን በሥጋቸው ፈጽሞ ሐጢያት አይሰሩም ማለት አይደለም፡፡
 
ሐጢያቶቻችን ይቅር ስለተባሉም ይበልጥ ሐጢያት ለመስራት ማቀድ አለብን ማለትም አይደለም፡፡ ጻድቃን ቀደም ብለው በእርሱ ሞት ውስጥ ተጠምቀዋል፡፡ በእርሱ ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች እንዴት በሐጢያቶች ውስጥ ይኖራሉ? ይህ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ጳውሎስ ምክንያቱን እንዲህ በማለት በገላትያ 3፡27 ላይ ያብራራል፡- ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡››
 
በሌላ አነጋገር ኢየሱስ በእርሱ ያመኑ ሰዎች በእምነት ‹‹በክርስቶስ ውስጥ ይጠመቁ›› ዘንድ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በጥምቀቱ ወስዶ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ስለዚህ የዚህ አይነቱ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡
 
 

ከኢየሱስ ጥምቀት ጋር የተጣመረ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡

 
ከኢየሱስ ጥምቀትና ከሞቱ ጋር የተባበረ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ እንዲህ ተብሎዋል፡- ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡›› ይህ ጥቅስ ኢየሱስ በዮርዳኖስ በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ በአንድ ጊዜ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወስዶዋል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞቱ ለሐጢያቶቻችን ሁሉ ስርየት ነው ማለትም ነው፡፡ ምክንያቱም በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወስዶዋልና፡፡ ይህንን እውነት መረዳትና ማመን ከጌታችን ጋር የተባበረ እምነት መያዝ ነው፡፡
 
በበደሎቻችን ምክንያት ከእግዚአብሄር ጽድቅ ተለይተን ነበር፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ ሐጢያቶቻችንንና መተላለፎቻችንን በሙሉ እንደወሰደ ታውቃላችሁን? ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በአንድ ጊዜ ወስዶ የሐጢያቶችን ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ እኛ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያቶችን ከመስራት መቆጠብ የማንችል ሰዎች ነን፡፡ ስለዚህ የእምነታችንን መሰረቶች በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ላይ በመመስረት ከክርስቶስ ጋር በተባበረ እምነት ልንይዝ ይገባናል፡፡ ከክርስቶስ ጋር የምንተባበረው ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንደፈጸመ ስናምን ብቻ ነው፡፡
የአብን ፈቃድ የጽድቁን ፍጻሜ የታዘዘው ማነው? ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በአንድ ጊዜ ፈጸመ፡፡ ኢየሱስ የሐጢያትን ዋጋ በሞቱ መክፈል የቻለው ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በመውሰድ ነው፡፡ ከክርስቶስ ጋር መተባበር የምንፈልግ ከሆንን ሐጢያቶቻችንን ለአንዴና ለመጨረሻ በወሰደው ጥምቀቱ ማመን ይገባናል፡፡
 
እርሱ በጥምቀቱ አማካይነት ዘላለማዊ አዳኛችን በመሆኑ ከጌታችን ጋር መተባበርና በእርሱ ማመን አለብን፡፡ አሁን ለእናንተ የቀረላችሁ ብቸኛው አማራጭ ይህንን እውነት መቀበል ወይም አለመቀበል ነው፡፡ በእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን የእግዚአብሄር ልጅ መሆን ወይም እውነትን በመግፋት በሲዖል ውስጥ ለዘላለም ሞት መኮነን ሙሉ በሙሉ የእናንተ ምርጫ ነው፡፡ ሐጢያቶቻችን ይወሰዱ ዘንድ ኢየሱስ ተጠመቀ፡፤ (ማቴዎስ 3፡13-15)
 
ማቴዎስ 3፡15ን ስንመለከት ‹‹እንዲህ›› የሚለው ሐረግ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሁሉ የመፈጸሚያ መንገድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ‹‹እንዲህ›› የሚለው ሐረግ በግሪክ ‹‹ሁ-ቶስ ጋር›› ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹በዚህ መንገድ›› ‹‹እጅግ ተስማሚ›› ወይም ‹‹ከዚህ ውጭ ሌላ መንገድ የለም›› ማለት ሆኖ የእርሱ ጥምቀት ሐጢያቶቻችንን ለማስረከብ እጅግ እርግጠኛው መንገድ መሆኑን ያወሳል፡፡ ይህ ቃል ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት የሰውን ዘር ሐጢያቶች ለዘላለም እንደወሰደ ያብራራል፡፡
 
ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ሐጢያቶቻችን ወደ እርሱ እንደተላለፉ ኢየሱስ የተጠመቀው ሐጢያቶቻችን እንዲወገዱና በመስቀል ላይ የሞተውም የሰውን ዘር ለማዳን መሆኑን በሚናገረው የሮሜ 6፡5-11 እውነት ማመን አለብን፡፡
 
ለሰው ብድራችሁን ለመክፈል ከፈለጋችሁ ከዕዳችሁ ጋር እኩል የሆነውን ደመወዛችሁን መክፈል ይኖርባችኋል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ጌታችን ሐጢያቶቻችንን ለማስወገድ በምን መንገድና ምን ያህል እንደከፈለ ማወቅ አለብን፡፡
 
ኢየሱስ ሲጠመቅ ከተወለድን ጊዜ ጀምሮ 10 ዓመት እስኪሆነን ድረስ ከዚያም ከ10 እስከ 20፤ 30፤ 40፤ 50፤ 60፤ 70፤ 80፤ 90 ዓመት ድረስ የተሰሩትን ሐጢያቶች ሁሉና እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሳችን ድረስ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች ወስዶዋል፡፡ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በጥምቀቱ ወስዶ ዋጋውን ከፈለ፡፡ ኢየሱስ አውቀን ወይም ሳናውቅ የሰራናቸውን በደሎቻችንን ሁሉ በአንድ ጊዜ ወሰደ፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ለማንጻት ተጠመቀ፡፡ በመስቀል ላይም የሐጢያቶችን ዋጋ ከፈለ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ ያለውና ቅዱሳት መጻህፍትም የሚናገሩለት እውነት ይህ ነው፡፡
 
እዚህ ላይ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የተናገረለትን ‹‹የጥምቀት›› ምስጢር ባለመረዳታቸው ምክንያት የቅድስናን ትምህርት በማጽናትና በመደገፋቸው ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው ለመቀበል በብዙ ይሞክራሉ፡፡ ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ ዮሐንስ የሰጠውን ‹‹ጥምቀት›› ባይቀበል ኖሮ የሰው ዘር ሐጢያቶች ለዘላለም እዚህ ይቆዩ ነበር፡፡ ስለዚህ ልቦቻችንና አካሎቻችን በጊዜ ሒደት ሊቀደሱ ይችላሉ ብሎ የሚያስተምረውን ይህንን የሐሰት ትምህርት ልናምነው አይገባንም፡፡
 
በዚህ ምድር ላይ ብቸኛውና ዘላለማዊው እውነት ኢየሱስ መጠመቁና ሐጢያቶቻችንን በሙሉ መውሰዱ ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን የሐሰት ትምህርቶችን ሁሉ እንድናሸንፍና ለሚያምኑ ሰዎችም ማሸነፍን እንድናመጣ ይረዳናል፡፡ ስለዚህ በዚህ እውነት ማመን ይኖርብናል፡፡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ጥምቀት ጋር ባለመተባበራቸው ዳግም ስላልተወለዱ ሲዖል ይወርዳሉ፡፡
 
በሳንጃ የተወጋ የልብ ስዕል አይታችሁ ታውቃላችሁን? ይህ የሚያሳየው የእግዚአብሄርን መስዋዕታዊ ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሄር አብዝቶ ስለወደደን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነን፡፡ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሄር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡›› (ዮሐንስ 3፡16)
 
ኢየሱስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሁሉ የሰጠንን ፍቅሩን መቀበል አለባችሁ፡፡ ልባችን ከእግዚአበሄር ጽድቅ ጋር መተባበር ይኖርበታል፡፡ ከኢየሱስ ጋር በሕብረት መኖር አለብን፡፡ ከክርስቶስ ጽድቅ ጋር አንድ በመሆን የሚኖር የታመነ ሕይወት ውብ ነው፡፡ ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 6 ላይ ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር በመተባበር በእምነት መኖር እንደሚገባን አበክሮ ተናግሮዋል፡፡
 
ጳውሎስ በሮሜ 7፡25 ላይ እንደተናገረው በአእምሮዋችን ለእግዚአብሄር ሕግ በሥጋችን ግን ለሐጢያት ሕግ እገዛለንን? አዎ እንገዛለን፡፡ እኛም እንደ ጳውሎስ ሁልጊዜም ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር የሚተባበር ልብ ሊኖረን የሚገባን ለዚህ ነው፡፡ ልባችንን ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር የማናስተባብር ከሆነ ምን ይፈጠራል? ፍጹም ጥፋት ይሆናል፡፡
 
ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር የሚተባበሩ ሰዎች ከእርሱ ቤተክርስቲያን ጋር የተባባረ ሕይወት ይኖራሉ፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የምታምኑ ከሆነ ከእርሱ ቤተክርስቲያንና ከእርሱ አገልጋዮች ጋር መተባበር ይገባችኋል፡፡ ሥጋ ሁልጊዜም የሐጢያትን ሕግ ማገልገል ይሞክራል፡፡ ስለዚህ በተደጋጋሚ የእግዚአብሄርን የሕይወት ሕግ እያሰላሰልን በእምነት መኖር ይገባናል፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በአእምሮዋችን ይዘን በየቀኑ የምናሰላስለው ከሆነ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያመነዥኩ እንስሶች ንጹህ ናቸው የሚለው ለዚህ ነው፡፡ (ዘሌዋውያን 11፡2-3)
 
ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር ተባበሩ፡፡ አዲስ ጉልበት ሲንቀሰቀስ ይሰማችኋል ወይስ አይሰማችሁም? አሁኑኑ ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር ለመተባበር ሞክሩ! ልባችሁን ከኢየሱስ ጥምቀት ጋር አስተባብራችኋል እንበል፡፡ እንግዲያውስ አሁንም ድረስ በልባችሁ ውስጥ ሐጢያት አለ ወይስ የለም? --የለብንም፡፡-- ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞቷል፡፡ ይህንን በልባችሁ እመኑት፡፡ ልባችሁን ከዚህ እውነት ጋር አቀናጅታችኋልን? እንግዲያውስ ሞተናል ወይስ አልሞትንም? --ሞተናል፡፡-- ክርስቶስ ከሙታን ተነስቷልን? --አዎ፡፡-- ስለዚህ እኛም ደግሞ ከሙታን ተነስተናል፡፡ ልባችንን ከክርስቶስ ጋር ስናስተባብር ሐጢያቶቻችን ይነጻሉ፡፡ በመስቀል ላይ ከእርሱ ጋር አብረን ሞተናል፡፡ ከክርስቶስም ጋር ከሙታን ተነስተናል፡፡
 
ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ባንተባበር ምን ይፈጠራል? ‹‹ምንድነው የምታወራው? አዎ ስለ ኢየሱስ ጥምቀት እያወራህ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ነገሩ እጆችን በእንስሳው ላይ መጫን ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀት ነው ማለትህ ነው፡፡ ምናልባት ያ ትክክል ነው! ነገር ግን ሰው ሁሉ ስለዚህ ነገር የሚንጫጫው ይህ ምን የተለየ ነገር ስለሆነ ነው?››
 
የኢየሱስን ጥምቀት በጽንሰ አሳብ ደረጃ ብቻ የሚያምኑ ሰዎች እውነተኛ እምነት ስለሌላቸው በመጨረሻ ኢየሱስን ትተውት ይሄዳሉ፡፡ በጽንሰ አሳብ ላይ የተመሰረተ እምነት ተማሪዎች በትምህርት ቤት ከአስተማሪዎቻቸው እንደሚማሩት አይነት መረጃ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማግኘት በቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን አስተማሪዎቻቸውን ከልብ የሚያከብሩና የአስተማሪዎቻቸውን ጠባይና የአመራር ብቃት ለመማር የሚሞክሩ ተማሪዎች አሉ፡፡ እኛ የእግዚአብሄርን ቃሎች እንደ ተራ እውቀት ልንቀበላቸው አይገባንም፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ጠባይ፣ ፍቅር፣ ምህረትና የጽድቅ ቃሎች ጋር አብረን በልባችን ውስጥ መሰንቀር አለብን፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ስንማር እውቀትን ብቻ የመማር ፍላጎታችንን መጣል አለብን፡፡
 
ቀደም ብሎ አእምሮዋቸው በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ የጠለቀላቸው ሰዎች ጌታን ለማገልገልና ከእርሱ ጋር ሕብረት ለማድረግ የቆረጡ ስለሆኑ በቀላሉ በሁኔታዎች አይናወጡም፡፡ ታላቁን ተልዕኮ ለመፈጸም ሲሉ በጥንቃቄ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ነገር ግን ልባቸውን ገና ከእርሱ ጋር ያላቀናጁ ሰዎች ጥቃቅን ነገሮች በቀላሉ ያሰናክሉዋቸዋል፡፡
 
እምነቶቻችን ከጌታ ጽድቅ ጋር እንዲተባበሩ ማድረግ አለብን፡፡ ልቦቻችን በዓለም ጥቃቅን ነገሮች እንዲናወጡ መፍቀድ አይኖርብንም፡፡ ልባቸውን ከክርስቶስ ጋር ያቀናጁ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ተጠምቀዋል፡፡ ከእርሱም ጋር በመስቀል ላይ ሞተዋል፡፡ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ለመዳንም ከእርሱ ጋር ዳግመኛ ተነስተዋል፡፡ እኛ የዚህ ሥጋዊ ዓለም ሰዎች ስላይደለን ማመን አለብን፡፡ የእርሱ ጽድቅ አገልጋዮች እንሆን ዘንድ የጠራንን እርሱን ለማስደሰት ከእርሱ ጽድቅ ጋር መተባበር አለብን፡፡
 
ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር ስትተባበሩ ልባችሁ ሁልጊዜም ሰላም ይሆናል፡፡ በደስታም ይሞላል፡፡ ምክንያቱም የጌታ ሐይል ከእኛ ጋር ይሆናልና፡፡ እግዚአብሄር በረከቶቹንና መለኮታዊ ሐይሉን በእኛ ላይ አትረፍርፎ በመለገሱ በአያሌው የተባረከ ሕይወትን መኖር እንችላለን፡፡
 
ልባችሁ ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር ይተባበር፡፡ ያን ጊዜ ልክ እንደ እኔ ከእግዚአብሄር ባሮች ጋር መተባበርና በጋራ ሕብረት አማካይነትም በቃሉ ላይ ጠንካራ እምነት ይኖራችኋል፡፡ የእርሱንም ሥራ በትኩስ ሐይል ትሰሩታላችሁ፡፡ እምነታችሁ እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ትንሽ ብትሆንም ጌታ ሐጢያቶቻችሁን አንጽቷል፡፡ ብቁ ባትሆኑም ከእርሱ ጋር በተለይም ከጥምቀቱ ጋር ተባብራችሁ ቆዩ፡፡
 
በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ አማካይነት ከጌታ ጋር የምንተባበርበትን እምነት ስለሰጠን እግዚአብሄርን እናመሰግናለን፡፡ ከአሁን ጀምሮ ጌታችንን እስከምንገናኝበት ቀን ድረስ ልባችንን ከጌታ ጋር ማቀናጀት ይኖርብናል፡፡ በራሳችን ደካሞች ስለሆንን መተባበር ይኖርብናል፡፡ ልባችሁን ኢየሱስ ከፈጸመው ጽድቅ ጋር የምታቀናጁበትን እምነት ተምራችኋልን? ከኢየሱስ ጥምቀት ጋር የተባበረውን እምነት አግኝታችኋልን? አሁን ከኢየሱስ ጥምቀትና ከፈሰሰው ደሙ ጋር የተባበረውን እምነት መያዝ አለባችሁ፡፡ እንዲህ ያለውን እምነት ያልያዙ ሰዎች ከመዳን ይጎድላሉ፡፡ ያልታመነ ሕይወትንም ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄር ጽድቅ ለሕይወታችሁ አስፈላጊ ነው፡፡
 
ከጌታ ጋር መተባበር የሐጢያቶችን ስርየት ባርኮቶችና በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን የእግዚአብሄር ልጆች ሆኖ የመኖርን ሕይወት ያመጣል፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ የእናንተው ጽድቅ ይሆን ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእምነታችሁ ጌታና የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡ እመኑ! የእግዚአብሄርንም ጽድቅ ተቀበሉ፡፡ ያን ጊዜ የእግዚአብሄር በረከቶች ከእናንተ ጋር ይሆናሉ፡፡
  
 
ለእግዚአብሄር ታማኝነታችንን ብቻ ማቅረብ አይገባንም፡፡
 
አንዳንድ ክርስቲያኖች በእግዚአብሄር ጽድቅ ሳያምኑ ‹‹♫አምላኬ ሆይ የእኔን ወስደህ የራስህ አድርገው፡፡ ♪ትንሽዋ ታማኝነቴን ሕይወቴን መስዋዕቴን ♫ትንሽ ቢሆንም ያለኝን ሁሉ ለአንተ ለንጉሤ እሰጣለሁ፡፡ ♪ጌታዬ ለአንተ ብቻ እኖራለሁ! ♫ኦ መንፈስ ቅዱስ እንደ እሳት ወረደ›› በመለት ብቻ ጌታን ያመሰግናሉ፡፡ እንደ እነዚህ አይነት ክርስቲያኖች መሆን የለብንም፡፡ እነርሱ በየቀኑ ያመሰግናሉ፡፡ በእግዚአብሄርም ፊት ታማኝነታቸውን በማቅረብ ስለሚቀጥሉ እግዚአብሄር ለእነርሱ አንዳች ነገር የሚያደርግበት ዕድል የለውም፡፡
 
ሰዎች በጣም ታማኞች በመሆን እግዚአብሄርን እያስቸገሩት ነው፡፡ እግዚአብሄር በእውር ድንብር በምናደርጋቸው ታማኝነቶቻችን ተሰላችቷል፡፡ እግዚአብሄር ‹‹ሰብዓዊ›› ጽድቃቸውን እንዲቀበልላቸው ይለምኑታል፡፡ ወለሉን ሲያጸዱ፣ መተላለፊያውን ሲጠርጉ፣ ሲጸልዩ፣ ሲያመሰግኑና ሲበሉም እንኳን ‹‹አምላካችን ሆይ! ለአንተ ያለንን ታማኝነት ተቀበል!›› እያሉ ያለማቋረጥ ወደ ጌታ ይጮሃሉ፡፡ ዛሬ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሳያውቁና ሳያምኑበት ኢየሱስ የሥጋ ታማኝነቶቻቸውን እንዲቀበል መጠየቃቸው አሳፋሪ ነው፡፡ ታማኝነቶቻችንን ለጊዜው ዘወር ማድረግና የኢየሱስን ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን የያዘውን የእግዚአብሄርን ጽድቅ መቀበል አለብን፡፡
 
የሥጋ ታማኝነቶቻችን በእግዚአብሄር ፊት ምንም ውጤት የላቸውም፡፡ ሰዎች ግን አሁንም ድረስ እግዚአብሄር ታማኝነቶቻቸውን እነዲቀበልላቸውና በምትኩም ሐጢያቶቻቸውን ይቅር እንዲላቸው ይጠይቁታል፡፡ ይህ አንድ ጎስቋላና ደሃ ለማኝ ያለውን ንብረት ሁሉ ለአንድ ቢሊኒየር ከሰጠ በኋላ ዋጋ ለሌለውና ቆሻሻ ለሆነው ስጦታው ካሳ ይሆንለት ዘንድ ግርማ ሞገስ ባለው ቤተመንግስት ውስጥ ለመኖር የመጠየቅን ያህል ሞኝነት ነው፡፡ እግዚአብሄር በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ በማመን እምነት እንዲኖረን ይፈልጋል፡፡
 
ክርስትና ሰዎች በዚህ ዓለም ላይ እንደፈጠሩት አይነት ሃይማኖት አይደለም፡፡ ክርስትና ሰው ያለ ማቋረጥ እንዲጸልይ፣ እንዲያጎነብስና ራሱን እንዲያነጻ ከሚጠይቀው እንደ ቡዲዝም አይነት ካሉ ሌሎች የዓለም ሃይማኖቶች ጋር ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ለዓለማዊ ሃይማኖት መስራች በመስገድና በመጸለይ በረከት ይገኛል የሚል የዚህ አይነት እምነት ሊኖረን አይገባም፡፡ ታማኝነታችንን መስጠትና በምላሹም የእርሱን ባርኮት መጠየቅ አይገባንም፡፡ ነገር ግን በፋንታው የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማወቅና መቀበል ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እርሱ ይህንን ሊሰጠን ይፈልጋልና፡፡
 
ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ስናምን የሐጢያቶችን ስርየት እንቀበላለን፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች ለመውሰድ ተጠመቀ፡፡ ሐጢያቶቻችንንም ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድ ሞተ፡፡ ስለዚህ ጥምቀቱንና ሞቱን መድገም አያስፈልገውም፡፡
 
ዕብራውያን 10፡18 እንዲህ ይላል፡- ‹‹የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ ከዚህ ወዲያ ስለ ሐጢአት ማቅረብ የለም፡፡›› ኢየሱስ አንድ ጊዜ በመጠመቅና በመሞት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወስዶ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሁሉ ፈጸመ፡፡ አሁን በክርስቶስ ጥምቀትና ደም ላይ ያለን እምነት ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት መልሶልናል፡፡
 
ጳውሎስ መናገሩን ይቀጥላል፡- ‹‹እንግዲህ ለምኞቱ እንዳትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ሐጢአት አይንገስ፡፡›› (ሮሜ 6፡12) እኛ ጌታችንና ዘላለማዊ የነገሥታት ንጉሥ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንነግሳለን፡፡ ሐጢያት በእናንተ ላይ ነግሶ የነበረባቸው ወቅቶች አብቅተዋል፡፡ የሥጋችንን ክፉ ምኞት ወይም ፍላጎቶች መከተል የለብንም፡፡ እግዚአብሄር ፍጹም የሆነውን ጽድቁን ስለሰጠን እነዚህን ነገሮች ሁሉ በብቃት ማሸነፍ እንችላለን፡፡
 
 

ልባችሁንና ሰውነታችሁን ለእግዚአብሄር የዕቃ ጦር አድርጋችሁ አቅርቡ፡፡

 
‹‹ብልቶቻችሁንም የአመጻ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለሐጢአት አታቅርቡ፡፡ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሄር አቅርቡ፡፡ ሐጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና፡፡›› (ሮሜ 6፡13)
 
ጳውሎስ ሐጢያትን ለመቋቋም ስለ ሦስት ዋና ዋና እውነታዎች ተናግሮዋል፡፡ በመጀመሪያ የሚሞተውን ሥጋችንን ምኞት መታዘዝ የለብንም፡፡ አሮጌው ማንነታችን በምኞቱ ማድረግ የሚሞክረውን መቃወም አለብን፡፡ ሁለተኛ ብልቶቻችን ማለትም አቅሞቻችን የአመጻ ዕቃ ጦር የመሆን ልማዳቸውን ማስቆም አለብን፡፡ ሦስተኛ ብልቶቻችንን የእግዚአብሄር ዕቃ ጦር አድርገን ማቅረብ አለብን፡፡
 
በኢየሱስ ከማመናችን በፊት እጆቻችንን፣ እግሮቻችንን፣ አፋችንንና ዓይኖቻችንን ለሐጢያት አቅርበን ነበር፡፡ የሐጢያት ዕቃ ጦር ሆነን እርሱ ወደሚመራን ሁሉ ሄደናል፡፡ አሁን ግን ብልቶቻችንን ለሐጢያት አመጻ ዕቃ ጦር አድርገን ከማቅረብ ለመቆጠብ ወስነናል፡፡ ሐጢያት ያለ ምንም ተቃውሞ በእኛ ላይ እንዲነግሥ መፍቀድ የለብንም፡፡ የሐጢያት ፈተና ሲመጣ ‹‹ሐጢያት ሆይ በክርስቶስ ሞተሃል›› ብለን መናገር ይገባናል፡፡ እግዚአብሄር የኑሮዋችን ሁሉ ጌታ መሆኑን ማወጅ አለብን፡፡
 
በእምነት ሕይወት ውስጥ መደረግ ያለባቸውንና መደረግ የሌለባቸውን ነገሮች ማሰብ አለብን፡፡ ብልቶቻችንን ለእግዚአብሄር እንጂ ለሐጢያት ማቅረብ የለብንም፡፡ የምናደርገው ነገር ማድረግ እንደማይገባን ነገር ሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ምንም የማናቀርብ ከሆንን ይህ ማለት ለሐጢያት እያቀረብን ነው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ጊዜያችንን ለእግዚአብሄር የምናቀርብ ከሆነ ለሐጢያት የምናቀርብበት ጊዜ አይኖረንም፡፡ የሐጢያት ጠላቶች መሆንና ከእግዚአብሄር ጋርም አንድ ቤተሰብ መሆን አለብን፡፡
 
በአጋጣሚ ‹‹ሐጢያትን የማሸንፍበት ድፍረት የለኝም›› ልንል እንችላለን፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ በሮሜ 6፡14 ላይ እንደዚያ ማሰብ እንደሌለብን ነግሮናል፡፡ ‹‹ሐጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና፡፡›› አሁንም በሐጢያት አገዛዝ ስር ያለን ከሆንን ዳግመኛ ሐጢያት እንደምናደርግ የታወቀ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጸጋ በታች ከሆንን ግን ጸጋው ደግፎ ድልን ይሰጠናል፡፡ የመዝሙር ጸሐፊው እንዲህ በማለት ጸልዮዋል፡- ‹‹አካሄዴን እንደ ቃልህ አቅና፡፡ ሐጢአትም ሁሉ አይግዛኝ፡፡›› (መዝሙረ ዳዊት 119፡113)
 
በዚህ ምድር ላይ እስከኖርን ድረስ ሐጢያት ወደ እኛ ያቀናል፡፡ ቀደም ብሎ በክርስቶስ እንደሞትን ከመሰከርን በኋላም ቢሆን ሐጢያት ሊጥለንና ሊገዛን ይሞክራል፡፡ ከሕግ በታች ሆነን በራሳችን ጻድቃን ለመሆን ብንሞክር ከሐጢያት አገዛዝ ነጻ መሆን አንችልም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምን እምነት እንዳለን በአእምሮዋችን መያዝ ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ሐጢያት ሊገዛን አይችልም፡፡ ይህንን ማወቅና ማስተጋባት ይኖርብናል፡፡
 
ሁላችሁም በእግዚአብሄር ጽድቅ ልታምኑና በአንደበታችሁም ልትመሰክሩ ይገባችኋል፡፡ ‹‹ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና፤ በአፉም መስክሮ ይድናልና፡፡›› (ሮሜ 10፡10) የእግዚአብሄርን ጽድቅ በልባችሁ ማመንና በአንደበታችሁ መመስከር ለእናንተ በእርግጥም አስፈላጊ ነው፡፡
 
ስለዚህ ሐጢያት በእኛ ላይ ለመንገስ በሚፈልግበት ጊዜ ሁሉ --ቁጣ አእምሮዋችንን ለመግዛት በሚሞክርበት ጊዜ ሁሉ፣ ምንዝርናና መዳራት ሊገዛን በሚሞክርበት ጊዜ ሁሉ፣ ኑሮዋችንን ለማሻሻል ሲባል ስስት ገብቶ ሌሎችን እንድናታልል ሲፈትነን፣ ጥላቻና ጥርጣሬም ሲያድግ ወይም ቂም ልባችንን አንቆ ሲይዝ-- ‹‹ኢየሱስ እነዚህን ሐጢያቶች በሙሉ አስወግዶዋል›› ብለን መጮህ አለብን፡፡ ‹‹ሐጢያት! ልትነግስብኝ አትችልም፡፡ እግዚአብሄር በጽድቁ ሙሉ በሙሉ ከሐጢያቶቼ፣ ከጥፋት፣ ከእርግማኖችና ከሰይጣን አድኖኛል›› በማለት በእምነት መጮህ አለብን፡፡
 
‹‹ለእግዚአብሄር እንኖራለን›› የሚለው ሐረግ በእርሱ ጽድቅ ባለን እምነታችን በጽድቅ እንኖራለን ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ በኢየሱስ ጥምቀትና ደም የሚያምኑ ሰዎችን ፍጹማን አድርጎዋቸዋል፡፡ በእርሱ ጽድቅ በማመን ለሐጢያት ሞተን ለእግዚአብሄር ሕያው የሆንነው ለዚህ ነው፡፡ እኛ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመናችን መንፈሳዊ ትንሳኤን ያገኘን መሆናችንን እንደ ማወቅና መመስከር ያለ አስፈላጊ ነገር የለም፡፡
 
ጳውሎስ ሐጢያት በበዛበት ጸጋ ከመጠን ይልቅ እንደበዛ ተናግሮዋል፡፡ (ሮሜ 5፡20) በጊዜው ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ተረድተውት ሰው ብዙ ጸጋ እንዲበዛለት ሐጢያት በመስራት መቀጠል አለበት አሉ፡፡ ጳውሎስ ግን ተቃወማቸው፡፡ በእርሱ ጥምቀትና ደም ካመኑ በኋላ ነገሮች አሁንም ድረስ በእንጥልጥል ላይ ናቸው፡፡ የዓለም ሐጢያቶች ከበው ልቦቻችንን ለመማረክ ይሞክራሉ፡፡
 
ነገር ግን ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ በእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ መደገፍና ድካሞቻችንን ማሸነፍ እንችላለን ወይም እምነታችንን እንጠራጠረዋለን፡፡ እግዚአብሄር የሚደሰትብን ልጆች ሆነን መኖር እንችላለን፡፡ በዚህ እምነት ለሐጢያት ሞተን ለእግዚአብሄር መኖር መቻል ነበረብን፡፡ ቀሪ ዘመናችንን የእግዚአብሄርን ጽድቅ በማመንና በመከተል መኖር እንችላለን፡፡ አንድ ጊዜ እዚያ ከደረስን በኋላም ለዘላለም በመንግሥቱ ውስጥ እንኖራለን፡፡
 
ሮሜ 6፡23 እንዲህ ይላል፡- ‹‹የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሄር ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው፡፡›› አሜን፡፡ ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው የመሰከሩ ሰዎች በጥምቀቱ ሐይልና በመስቀል ላይ ፍርዱ ውጤት ያምናሉ፡፡ አሜን!
 
ሃሌሉያ! ጌታ ይመስገን!