Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 7-1] የምዕራፍ 7 መግቢያ

የምዕራፍ 7 መግቢያ
 
 
ሐዋርያው ጳውሎስ ከመዳኑ በፊት ሥጋው በእግዚአብሄር ሕግ ለሞት የተኮነነ የነበረ የመሆኑን እውነታ ሲያሰላስል በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ለሐጢያት እንደሞተ ምስክርነትን ሰጥቷል፡፡ ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር  ከመገናኘታችን በፊት በክርስቶስ የምናምን ሰዎች በሕግ አገዛዝና እርግማን ሥር መኖርን ለምደን ነበር፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ካመጣልን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመገጣጠም ከሐጢያቶቻችን ቤዛነትን ባናገኝ ኖሮ ሕጉ በእኛ ላይ ይሰለጥን ነበር፡፡ 
 
ጳውሎስ በሥጋ በቀላሉ ሊስተዋሉ ስለማይችሉ መንፈሳዊ ጉዳዮች ተናግሮዋል፡፡ እነዚያ ጉዳዮችም ባልዋ የሞተባት ሴት ለባልዋ ካለባት ግዴታ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንደወጣች ሁሉ ለሐጢያት የሞትን ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲያ ሐጢያት የማይገዛን መሆኑ ነው፡፡ ይህ ምንባብ ቀላል ይመስል ይሆናል፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ መልኩ ወሳኝ ምንባብ ነው፡፡ ወደዱም ጠሉም ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር ያልተገናኙ ሰዎች ዕጣ ፈንታቸው ከእግዚአብሄር እርግማን በታች ሆነው መኖር መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው የሐጢያቶቻቸውን ችግር ገናም ያልፈቱ በመሆናቸው ነው፡፡ 
ሮሜ 6፡23 ‹‹የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነው›› በማለት ይነግረናል፡፡ ይህ ማለት ሐጢያት የሚከስመው ዋጋው ሲከፈል ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ሰው በኢየሱስ አምኖ በኢየሱስ የተሰጠውን የእግዚአብሄር ጽድቅ የማያውቅ ከሆነ አሁንም በሐጢያት እየኖረ ስለሆነ የሐጢያትን ደመወዝ መክፈል አለበት፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መገናኘት የሚኖርብን ለዚህ ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን በመሞት ከሕግ ነጻ መውጣትና ከአዲሱ ሙሽራችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር መጋባት የምንችለው የእግዚአብሄርን ጽድቅ በመገናኘት ብቻ ነው፡፡
 
የእግዚአብሄርን ጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ማግኘት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው በዚህ የእግዚአብሄር ጽድቅ ሳያምን ከሕግ አርነት መውጣት አይችልም፡፡ ከሕግ እርግማን ለመላቀቅ ብቸኛው መንገድ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማወቅና ማመን ነው፡፡ ይህንን የእግዚአብሄር ጽድቅ በኢየሱስ በኩል አግኝታችኋልን? ካላገኛችሁ የራሳችሁን ጽድቅ ትታችሁ ራስን በማዋረድ ወደ እግዚአብሄር ቃል የምትመለሱበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ 
  
 

ለሐጢያት ከሞትን በኋላ የክርስቶስ መሆን፡፡ 

 
ጳውሎስ በሮሜ ላሉት ወንድሞቹ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ በኩል ለሕግ ተገድላችኋል፡፡›› ‹‹በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ መገደል›› ምን እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ ማንም ሰው በክርስቶስ ሥጋ ለሐጢያት ሳይሞት ወደ ክርስቶስ መቅረብ አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ሐጢያቶቻችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መሞት አለባቸው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ሰው በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ ሲያምን ብቻ ነው፡፡ 
ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት በማመን ከክርስቶስ ጋር ለሐጢያት መሞት እንችላለን፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ ጥምቀት የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በሥጋው ወስዶ በመሞቱ በዚህ ስናምን ሐጢያቶቻችንም ከእርሱ ጋር ሞተዋል፡፡ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ኢየሱስ በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ ወደ እርሱ መተላለፋቸው እውነት ነው፡፡ ይህ እውነት መታወቅ ብቻ ሳይሆን በእምነት በልባችን ውስጥ መታተም አለበት፡፡ ይህንን እምነት ወደ እግዚአብሄር መንግሥት እስክንገባ ድረስ ይዘነው ልንቆይ ይገባናል፡፡ ጳውሎስ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ እንደተገደልን የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ እውነት የሚያምኑ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መቅረብ፣ ከእርሱ ጋር መኖርና ለእግዚአብሄርም የጽድቅ ፍሬዎችን ማፍራት ይችላሉ፡፡ 
 
በአዲሱ የመንፈስ እውነት እንጂ በአሮጌው ፊደል ማመን የለብንም፡፡ ሐጢያተኞች በሕጉ ምክንያት ብዙ ሐጢያቶች እንደሚሰሩ የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህ የሆነው ሕጉ በውስጣቸው የተደበቁትን ብዙ ሐጢያቶች በመግለጥ ይበልጥ ስለ ሐጢያቶቻቸው እንዲያውቁ ስለሚያደርጋቸውና ይበልጥ ሐጢያት እንዲሰሩም ስለሚፈቅድላቸው ነው፡፡ ከሕግ ተግባራቶች አንዱ ሐጢያቶቻችንን እንድናውቅ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ሕጉ የሐጢያትን ባህርይ አብዝቶ በመግለጥና ተጨማሪ ሐጢያቶችን እንድናደርግ በመስራት ይንቀሳቀሳል፡፡ እግዚአብሄር በሰጠን ሕግ ባይሆን ኖሮ በውስጣችን በጣም ብዙ ሐጢያት እንደተደበቀ አናውቅም ነበር፡፡ እግዚአብሄር ግን ሕጉን ሰጠን፡፡ ይህ ሕግ ሐጢያትን ይበልጥ ሐጢያት ከማድረጉም በላይ ተጨማሪ ሐጢያቶችንም  እንድናደርግ አድርጎናል፡፡
 
ስለዚህ ጳውሎስ በክርስቶስ ስጋ ለሐጢያት ስለሞትን አሁን በእግዚአብሄር ጽድቅ በሚያምነው እምነት ጌታን ማገልገል እንደሚኖርብን ይናገራል፡፡ ጌታን በፊደል ቃል ከማገልገል ፋንታ በልባችን ጥልቅ ውስጥ ባለው እምነታችንና በመንፈስ እርዳታና በተሰጠን የቤዛነት ስጦታ እንድናገለግለው ይነግረናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል›› ብሎ እንደሚነግረን የእግዚአብሄር ጽድቅ የሆነውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እውነተኛ ትርጉም በመረዳት ጌታን መከተል አለብን፡፡ በሌላ አነጋገር በእግዚአብሄር ቃል ስናምን በተጻፈው ቃል ውስጥ የተደበቀውን እውነተኛ ትርጉም ማወቅና ማመን ይኖርብናል፡፡ 
 
 

ታዲያ ሕግ ሐጢያት ነውን? በእርግጥም አይደለም! 

 
ጳውሎስ በእግዚአብሄር ሕግ ላይ በማተኮር ተግባራቶቹን አብራርቷል፡፡ ይህም የሕጉን ተግባር በትክክል በመረዳት ማመን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ጳውሎስ ቀደም ብሎ የገዛ ራሱን ሐጢያቶች በራሱ መንገድ ተመለከተ፡፡ በዚህ ምክንያት የራሱን ሐጢያቶች አላወቀም፡፡ ነገር ግን በውስጡ ምኞት እንዳለ በእግዚአብሄር ሕግ አማካይነት መረዳት ቻለ፡፡ 
 
ዛሬም በኢየሱስ የሚያምኑ ምዕመናኖች ስለ ሕጉ ጳውሎስ የደረሰበት ተመሳሳይ መረዳት ላይ መድረስ ይችላሉ፡፡ የሕጉን እውነት ሳይረዱ ሕይወታቸውን በሕጉ ለመኖር የሚጥሩ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ጥቂት ቢጥሩ ሕጉን በሙሉ መጠበቅ እንደሚችሉ በማሰብ ወደ ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ፡፡ በተጨባጭ ግን እነዚህ ሰዎች ፈጽሞ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማግኘት አይችሉም፡፡ 
 
በእግዚአብሄር የተሰጠውን የሕጉን ጥልቅ ትርጉም አልተረዱም፡፡ ስለዚህ ሕግ አጥባቂዎች ይሆናሉ፡፡ እነርሱ የራሳቸውን ልብ እንኳን ማየት የማይችሉ ግብዝ ዕውሮች ናቸው፡፡ በክርስትና ማህበረሰብ ውስጥም የእግዚአብሄርን ጽድቅ የተቃወሙ መሆናቸውን አያውቁም፡፡ በዘመኑ ክርስትና ውስጥ እንደዚህ ያሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በውኑ የማያውቁና በሕግ ላይ በተመሰረተ እምነት ኢየሱስን ተራ አዳኛቸው አድርገው የተቀበሉ ሰዎች ከዘላለም ሞት ቅጣት አያመልጡም፡፡ 
 
ጳውሎስ በእግዚአብሄር ትዕዛዛት አማካይነት በልቡ ውስጥ ያለውን ምኞት ወደ መረዳት ደረሰ፡፡ ጳውሎስ በትዕዛዛቶቹ አማካይነት ሐጢያቶቹን ሲያውቅ የእግዚአብሄርን ሕግ መጠበቅ እንደነበረበት የሚያስብ ሕግ አጥባቂ ነበር፡፡ የእግዚአብሄር ትዕዛዛት በጳውሎስ ልብ ውስጥ ያለውን ምኞት ገልጠው የጳውሎስን ሐጢያቶች ያለ ልክ ሐጢያት አደረጉዋቸው፡፡ ጳውሎስ የከፋ ሐጢያተኛ መሆኑን ወደ መረዳት የደረሰው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ 
 
በሰው ልቦና ውስጥ አስራ ሁለት የሐጢያት ባህሪዎች አሉ፡፡ ጳውሎስ የሕግን ትክክለኛ ተግባራቶች ያውቅ ባልነበረበት ጊዜ ምን ያህል ሐጢያተኛ እንደነበር ሳይገነዘብ ራሱን ጥሩ ሰው አድርጎ ያስብ ነበር፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ትዕዛዛት ለመኖር ያደረገው ጥረት ውጤቱ የእግዚአብሄርን ትዕዛዛት መጠበቅ ከመቻል በጣም የራቀ እንደሆነ አሳዩት፡፡ እነዚህ ትዕዛዛቶችም ሐጢያቶቹን ይበልጥ ገለጡበት፡፡ 
 
ሰዎች በኢየሱስ ሲያምኑ እንዴት ናቸው? ለመጀመሪያ በኢየሱስ ማመን ስትጀምሩ በእምነታችሁ የጋላችሁ ነበራችሁ፡፡ ነገር ግን ጊዜ እየነጎደ ሲሄድ በውስጣችሁ ብዙ ሐጢያቶች እንዳሉ አወቃችሁ፡፡ እነዚህን ሐጢያቶች ያገኛችሁት በምን አማካይነት ነው? ልባችን በአስራ ሁለት አይነት ሐጢያት የተሞላ መሆኑን የተረዳነው በተጻፈው ቃልና ትዕዛዛት አማካይነት ነው፡፡ በሕጉ ፊት ሐጢያተኛውን ማንነታችንን በማየትም እንሸማቀቃለን፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በሕጉ አማካይነት በእርግጥም የከፋን ሐጢያተኞች ስለሆንን ነው፡፡ 
 
አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን ለማጽናናት ሲሉ የመንጻትን ትምህርት የፈጠሩት ለዚህ ነው፡፡ ይህ ትምህርት በልባችን ውስጥ ሐጢያት ቢኖርብንም በኢየሱስ በማመናችን ምክንያት እግዚአብሄር ጻድቃን አድርጎ ይመለከተናል ይላል፡፡ ይህ ሰው ሰራሽ ትምህርት ነው፡፡ ሰዎች ከዚህ ትምህርት ጋር ተስማምተው ለመኖር በመሞከር ሐጢያቶቻቸውን ለመደበቅ እንዲህ ያለውን ትምህርት ፈጠሩ፡፡ አመኑበትም፡፡ ነገር ግን አሁነም በሕጉ ፊት ሐጢያተኞች መሆናቸው ስለተገለጠ ሐጢያቶቻቸው በልቡናቸው ላይ ይበልጥ እየከበዱ መጥተዋል፡፡ እኛ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለመዳን ብቸኛው መንገድ ይህ ነው፡፡ 
 
ጳውሎስ ባለፈው ሕይወቱ እግዚአብሄር ትዕዛዛትን የሰጠው እንዲጠበቁ ነው ብሎ በማሰቡ ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ መሞከሩ የተለመደ ነው ብሎ አሰበ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ እነዚህ ትዕዛዛቶች በሐጢያት ምክንያት ነፍሱን ገደሉበት፡፡ በመጨረሻም ጳውሎስ የእግዚአብሄርን ትዕዛዛቶች በተሳሳተ መንገድ እንደተረዳቸውና በስህተት መንገድ እንዳመነባቸው ተገነዘበ፡፡ 
 
ሰው ሁሉ በማርቆስ 7፡21-23 ውስጥ የተጠቀሱት አስራ ሁለት አይነት ሐጢያቶች በልቡ ውስጥ አሉበት፡፡ ‹‹ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው፡፡ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል፤ ሰውንም ያረክሰዋል፡፡›› 
 
ጳውሎስና ሌሎች ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሄር ትዕዛዛቶች አማካይነት ሐጢያቶቻቸውን ወደ ማወቅ ደርሰዋል፡፡ በሕጉ በኩል ሐጢያቶቻቸውን ተረድተው ተገድለዋል፡፡ ከዚያም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የእግዚአብሄርን ጽድቅ አግኝተው አምነውበታል፡፡ ስለ እግዚአብሄር ጽድቅ ያላችሁ መረዳት ምንድነው? ሁሉንም ልትጠብቁ እንደምትችሉ በማሰብ ትዕዛዛቱን አሁንም ድረስ ለመጠበቅ እየሞከራችሁ ነውን? እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን አውቀን ወደ እርሱ እንድንመለስ ማለትም በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ከሐጢያት እንድንድን ሕጉን ሰጠን፡፡ እግዚአብሄር ለምን ትዕዛዛቱን እንደሰጠን ትክክለኛ መረዳት ሊኖረን ይገባል፡፡ በእነርሱም በትክክል ማመን አለብን፡፡ አንድ ጊዜ ይህንን እውነት ከተረዳችሁ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ምን ያህል ክቡር እንደሆነ ታውቃላችሁ፡፡ 
 
በእግዚአብሄር ትዕዛዛት የሚያምኑ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት ምንኛ ታላቅ ሐጢያተኞች እንደሆኑ መረዳት ይችላሉ፡፡ የትዕዛዛቱን ሚና የማያምኑና በእግዚአብሄር ጽድቅ የማያምኑ ሰዎች በሃይማኖታዊ ሕይወታቸው ታላላቅ ችግሮች ይገጥሙዋቸዋል፡፡ በመጨረሻም ወደ ጥፋታቸው ይነጉዳሉ፡፡ ምክንያቱም ሐጢያቶችን በተሞላ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ከሐጢያት መራቅ የማይቻል ነውና፡፡ ሰዎች በጣም ራቅ ባሉ ተራሮች ውስጥ በመኖርና ከዓለም ሐጢያቶች ርቀው በመገለል ሐጢያቶችን ከመስራት እንደሚታቀቡ ያስባሉ፡፡ ጉዳዩ ግን ይህ አይደለም፡፡ 
 
በዚህ ዓለም ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ሐጢያት የሚሰራና በልቡ ውስጥም ሐጢያት ያለበት መሆኑ እውነት ቢሆንም ከዚህ ሁሉ ሐጢያት ቤዛነትን ማግኘት የሚቻለው የእግዚአብሄርን ጽድቅ በማወቅና በማመን መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ከሐጢያቶቹ ለማምለጥ ስንል ከዓለም መሸሽ ቢኖርብንም በልባችን ውስጥ ካሉት ሐጢያቶች ማምለጥ ግን አንችልም፡፡ ምክንያቱም ሐጢያቶቻችን በልባችን ውስጥ ይገኛሉና፡፡ ራሳችንን በተጨባጭ ከሐጢያት ለመገላገል በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን አለብን፡፡ የእግዚአብሄር ሕግና ትዕዛዛቶቹ ሐጢያቶቻችንን ያለ ልክ ሐጢያተኛ ያደርጉዋቸዋል፡፡ የሐጢያቶቻቸውን ከባድነት የሚያውቁ ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በኩል የተገለጠውን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማወቅና ማመን አለባቸው፡፡ 
 
‹‹ለሕይወትም የተሰጠችውን ትዕዛዝ እርስዋን ለሞት ሆና አገኘኋት፡፡ ሐጢአት ምክንያት አግኝቶ በትዕዛዝ አታሎኛልና፡፡ በእርስዋም ገድሎኛል፡፡›› (ሮሜ 7፡10-11) ሕጉን በትክክል መረዳት አለብን፡፡ ሕጉን በትክክል ያልተረዱ ሰዎች እስከ መጨረሻው ቀናቸው ድረስ ከሕግ ለማምለጥ እየሞከሩ ዘመናቸውን በሙሉ በሕግ አክራሪነት ውስጥ ተዘፍቀው ያሳልፉታል፡፡ በኢየሱስ የተፈጸመውን የእግዚአብሄር ጽድቅ የሚወድዱና የሚያምኑ ሰዎች የሕጉን እውነተኛ ሚና የሚያውቁ ብቻ ናቸው፡፡ እንግዲያውስ ይህንን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ታውቁታላችሁን?
 
ሐዋርያው ጳውሎስ ባለፈው ዘመኑ ዳግም ስላልተወለደ የሥጋው ተገዢ እንደነበርና ለሐጢያት እንደተሸጠ ተናግሮዋል፡፡ በእግዚአብሄር ሕግ ለመኖር ቢፈልግም ማድረግ የማይፈልገውን እንዳደረገ ማለትም ሐጢያትን እንደፈጸመም መስክሮዋል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የእግዚአብሄር ጽድቅ ስላልነበረው በውስጡ መንፈስ ቅዱስ ስለሌለ ነው፡፡ ከዚያም ጳውሎስ ያለ ፍላጎቱ ሐጢያት የሰራው በልቡ ውስጥ ከሚገኙት ሐጢያቶች የተነሳ እንደነበርም አምኖዋል፡፡ በወቅቱ ገና የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማግኘት ነበረበትና፡፡ 
 
ሆኖም ጳውሎስ አንድ ሕግ ተረድቷል፡፡ ያም ሕግ የሐጢያት ሕግ ነበር፡፡ በልቡ ውስጥ ሐጢያት ያለበት ሰው ሐጢያት ከመስራት መሸሽ የማይችል የመሆኑን መሰረታዊ እውነታ ተገንዝቦዋል፡፡ ውስጣዊው ሰው ሁልጊዜም በእግዚአብሄር ሕግ መሰረት መኖር እንደሚፈልግም ተረድቷል፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ የሐጢያት ዛፍ የሐጢያት ፍሬዎችን እንደሚያፈራ ሁሉ እርሱም በሐጢያት በመኖር የሚቀጥል ሐጢያተኛ ብቻ እንደነበርም መስክሮዋል፡፡ እርሱ ገና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስላልተገናኘ የሐጢያቶቹን ቤዛነት አላገኘም፡፡ በሌላ አነጋገር በሐጢያቶቹ ምክንያት እንዲሞት መደረጉ ትክክል ነበር፡፡ 
 
‹‹ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?›› (ሮሜ 7፡24) ብሎ በመጮህ ጎስቋላ ሰው እንደነበር የተናዘዘው ለዚህ ነው፡፡ ጳውሎስ ሐጢያተኛ በነበረ ጊዜ ስለ ራሱ የነበረው ትዝታ ይህ ነበር፡፡ ይህንን የጳውሎስን ኑዛዜ የራሳችሁ ስለማድረግ ልታስቡ ይገባችኋል፡፡ እናንተስ ብትሆኑ ሕጉን መጠበቅ በማይችል ለዚህ ለሞት በተሰጠ ሥጋ ውስጥ አሁንም ድረስ የታሰራችሁ አይደላችሁምን? በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን ይገባናል፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ጽድቅ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ ተሰውሮዋል፡፡ በዚህ ወንጌል በማመን ወደ እርሱ ጽድቅ መድረስ እንችላለን፡፡ 
 
ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ በማመን ከጉስቁልናው ሁሉ ነጻ መውጣት ቻለ፡፡