Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 8-1] የምዕራፍ 8 መግቢያ፡፡

ምዕራፍ 8 ምናልባትም የሮሜ መጽሐፍ እጅግ አስፈላጊ ምዕራፍ ተብሎ ሊገለጥ ይችላል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ በቀረቡት በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች አማካይነት ጳውሎስ የእግዚአብሄር የጽድቅ ሥራ ምንኛ ድንቅ እንደሆነ ይገልጥልናል፡፡
የመጀመሪያው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም›› (ሮሜ 8፡1) የሚለው ነው፡፡ ይህ ማለት እኛ በሥጋችን ምንም ያህል ባለጌና ወራዶች ብንሆንም የእግዚአብሄር ጽድቅ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አርነት አውጥቶናል ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹ከሥጋ የተነሳ ስለደከመ ለሕግ ያልተቻለውን እግዚአብሄር አድርጓልና›› (ሮሜ 8፡3) የሚለው ነው፡፡ ይህ ማለት ሰዎች በሥጋቸው እግዚአብሄር የሰጠውን ሕግ መከተል ስላልቻሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ሞቱ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ በራሱ ላይ በመውሰድ ከሐጢያቶቻቸውና ከፍርዶቻቸው አዳናቸው ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በመስቀሉ ላይ መሸከም የቻለው የተሰቀለውና በዚህ እውነት የሚያምኑትን ሁሉ በማዳን ከሙታን የተነሳው ወደዚህ ምድር መጥቶ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት የሰውን ዘር ሐጢያቶች  በሙሉ በአንድ ጊዜ ስለወሰደ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የጌታችን ሥራዎች ለእግዚአብሄር አብ ፈቃድ በመታዘዝ ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን ሲባል የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለመፈጸም የተከወኑ ናቸው፡፡
ሦስተኛው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ›› (ሮሜ 8፡5) የሚለው ነው፡፡ ይህ ማለት በእግዚአብሄር ለማመን ስንወስን አስተሳሰቦቻችንን በመከተል ሳይሆን የእግዚአብሄርን ቃል በመከተል በእርሱ ማመን ይገባናል ማለት ነው፡፡
አራተኛው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹እናንተ ግን የእግዚአብሄር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም›› (ሮሜ 8፡9) የሚለው ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን በልባቸው ተቀብለው የእግዚአብሄር ልጆች ሆነዋል፡፡ ይህ ማለት ወደ ቤተክርስቲያን በትጋት ስለምትሄዱ ብቻ የእግዚአብሄር ልጅ መሆን አትችሉም ማለት ነው፡፡
አምስተኛው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም›› (ሮሜ 8፡12) የሚለው ነው፡፡ ይህ ርዕሰ ጉዳይ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በፈጸመው የጌታችን ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው በሙሉ የዳኑ ሰዎች ለሥጋ ዕዳ ሊኖርባቸውና የእርሱ ባርያ ሊሆኑ እንደማይችሉ ይነግረናል፡፤
ስድስተኛው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና›› (ሮሜ 8፡15) የሚለው ነው፡፡ በእግዚአብሄር የሚያምኑ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ስለተቀበሉ አሁን እግዚአብሄር አብን ‹‹አባ አባት›› ብለው መጥራት ይችላሉ፡፡
ሰባተኛው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹የእግዚአብሄር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡ ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን ማለት የእግዚአብሄር ወራሾች ነን›› (ሮሜ 8፡16-17) የሚለው ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ሰዎች ናቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ሰዎችም ከክርስቶስ ጋር አብረው መንግሥተ ሰማይን የሚወርሱ ናቸው፡፡
ስምንተኛው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹ፍጥረት ሁሉ እስካሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና›› (ሮሜ 8፡22) የሚለው ነው፡፡ ይህም በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎችም ቢሆኑ ከሌሎቹ ፍጥረታቶች ጋር አብረው በዚህ ዓለም ላይ መከራ እንደሚገጥማቸው ይነግረናል፡፡ ነገር ግን በቀጣዩ ዓለማቸው መቃተትም ሆነ ስቃይ እንደማይኖርም ይነግረናል፡፡
ዘጠነኛው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፡፡ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፡፡ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው›› (ሮሜ 8፡30) የሚለው ነው፡፡ ይህም እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደጠራቸውና በጽድቁም ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ በአንድ ጊዜ በመውሰድ ልጆቹ እንዳደረጋቸው ይነግረናል፡፡
በመጨረሻም አስረኛውና የመጨረሻው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹እግዚአብሄር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሄር ነው›› (ሮሜ 8፡33) የሚለው ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ከሐጢያት ለመዳናቸው ስጦታ እንዲሆናቸው መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉትን የእግዚአብሄር ልጆች ማንም ሊከሳቸው አይችልም፡፡
እነዚህ አስሩ ርዕሰ ጉዳዮች የሮሜ ምዕራፍ 8 መሰረታዊ ዝርዝሮች ናቸው፡፡ አሁን በዋናው ውይይታችን እነዚህን በስፋት እንመረምራለን፡፡