Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 12] በእግዚአብሄር ፊት አእምሮዋችሁን አድሱ፡፡

‹‹እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ሰውነታችሁን እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው፣ ቅዱስም፣ መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሄር ርህራሄ እለምናችኋለሁ፡፡ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው፡፡›› (ሮሜ 12፡1) 
 
ለእግዚአብሄር ልንሰጠው የሚገባውና በኒው ኢንተርናሽናል ትርጉም ‹‹መንፈሳዊ የአምልኮ ምግባር›› ተብሎ የተተረጎመው ይህ ‹‹ለአእምሮ የሚመች አገልግሎት›› ምንድነው? ለእግዚአብሄር ለአእምሮ የሚመች አገልግሎት መስጠት ማለት የጽድቅ ሥራውን ይሰራ ዘንድ ሰውነታችንን ለእርሱ መስጠት ማለት ነው፡፡ እኛ ስለዳንን ሰውነታችንን ማቅረብና የጽድቅ ወንጌልን ለማስራጨትም ለእግዚአብሄር የምንመች መሆን ያስፈልገናል፡፡ ለእግዚአብሄር ልንሰጠው የሚገባው ለአእምሮ የሚመች አገልግሎት ሰውነታችንን ለእርሱ መስጠት እንችል ዘንድ በቅድስና መለየት ነው፡፡ 
 
ጳውሎስ በምዕራፍ 12 ላይ መንፈሳዊ አገልግሎታችን ምን እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው የእግዚአብሄር ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትነን እናውቅ ዘንድ በአእምሮዋችን መታደስ መለወጥ እንጂ ይህንን ዓለም መምሰል አይደለም፡፡
 
ለአእምሮ የሚመች አገልግሎት ሰውነታችንንና ልባችንን ሁሉ ለእግዚአብሄር መቀደስ ነው፡፡ ጻድቃን በእግዚአብሄር ፊት እንዲህ ያለ ሕይወት መኖር የሚችሉት እንዴት ነው? ጳውሎስ ሰውነታችንን ለእግዚአብሄር የጽድቅ ሥራዎች ለማቅረብ በአእምሮዋችን መታደስ መለወጥ እንጂ ይህንን ዓለም መምሰል እንደሌለብን ይናገራል፡፡ ልባችንንና ሰውነታችንን በማቅረብ በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን ለእግዚአብሄር የሚመች አገልግሎት ነው፡፡
          
ይህ ምንባብ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ዓለም ጋር መመሳሰል እንደሌለበን በፈንታው የእግዚአብሄርን ሥራዎች መስራትና በአእምሮዋቸውን መታደስ መለወጥ እንዳለብን ይነግረናል፡፡
 
በመጀመሪያ ልባችንን ሳናድስ መንፈሳዊ አምልኮ ማቅረብ አንችልም፡፡ ጻድቃኖችም ቢሆኑ በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን ካቆሙ ሰውነታቸውን ወይም ልባቸውን ለእግዚአብሄር መስጠት አይችሉም፡፡
 
በጳውሎስ ትውልድ እንደሆነው እኛም በዚህ ትውልድ ተጽዕኖ ያድርብን ይሆናል፡፡ የምንኖረው በዚህ ሐጢያተኛ ተንሳፋፊ ትውልድ መካከል በመሆኑ በእግዚአብሄር ጽደቅ ባናምን ኖሮ የዚህን ዘመን ፍሰት መከተላችን አይቀሬ ነበር፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ጻድቃን እንኳን ሕይወታቸውን ከዓለም ሰዎች ጋር በሚኖሩበት ጊዜ በዓለማዊ ፍሰት ተጽዕኖ ስር ከመሆን ፈጽሞ ማምለጥ አይችሉም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ዓለም እንዳንመስል የነገረን ለዚህ ነው፡፡
 
ታዲያ ጻድቃን ለዚህ ዓለም ተጋልጠው እያሉ በሙሉ ልባቸውና ሰውነታቸው ለአእምሮ የሚመች አምልኮ፣ ቅዱስ መስዋዕት ማቅረብ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህ የሚሆነው አእምሮዋችንን የሚያድሰውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሁልጊዜም በማመን ብቻ ነው፡፡ ጻድቃን አእምሮዋቸውን ሲያድሱና በእርሱ ጽድቅ ሲለወጡ በጎና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሄር ፈቃድ በማወቅና በመከተል ነው፡፡
 
ጳውሎስ ይህንን የሚናገረው ዓለማዊ ጉዳዮችን ስለማያውቅ አይደለም፡፡ ያሉባቸውን ሁኔታዎችና ብቃቶቻቸውን ሳያውቅ ‹‹እስቲ በጎ እንሁን›› በማለት ለምዕመናን የሃይማኖት ትምህርት እየሰጠ አይደለም፡፡ ጳውሎስ እግዚአብሄርን እናገለግል ዘንድ ልባችንን እንድናድስ የሚያደፋፍረን ምዕመናኖችም በዚህ ዓለም መንገዶች ተጠርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ በሚገባ ስላወቀ ነው፡፡
 
ዳግም ቢወለድ ወይም ባይወለድ ሥጋዊ ሰውነት አንዱ ከሌላው በጣም የተለየ ነው፡፡ ነገር ግን ዳግም በተወለዱና ዳግም ባልተወለዱ መካከል አንድ ትልቅ ልዩነት ያለ ሲሆን እርሱም በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ያለ መታከት አእምሮዋቸውን በማደስ ጌታን መከተል የሚችሉት ጻድቃን ብቻ ናቸው፡፡
ታዲያ አእምሮዋችንን ማደስ የሚችለው ምንድነው? ሙሉ በሙሉ ከሐጢያታችን መዳናችንን በሚያውጀው የወንጌል ቃል ማመን ልባችንን ያድሰዋል፡፡ በሥጋ ድክመታችን፣ ልፍስፍስነታችን፣ በሰውነታችንና በአእምሮዋችን የሰራናቸውን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ይቅር በማለቱ የጻድቃን አእምሮ ሊታደስ ይችላል፡፡ በሌላ አነጋገር በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመናችን አእምሮዋችን ታድሶዋል፡፡
 
አሁን በእግዚአብሄር ፊት ስለምናደርገው ነገር ትክክለኛ መረዳት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ የእርሱ ፍጹም ፈቃድ ምን እንደሆነ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ምን ተልዕኮዎችን እንደሰጠንና ዳግም የተወለዱ ጻድቃንም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማወቅ አለብን፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች አእምሮዋችንን ማደስና እርሱን ማገልገል አለብን፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ሰውነታችንንና አእምሮዋችንን ለእርሱ በማቅረብ ራሳችንን ቅዱስ መስዋዕት አድርገን ለእርሱ መቀደስ ነው፡፡ አእምሮዋችንን ማደስ የሚመጣው እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደ በማመን ነው፡፡
ዳግም በተወለዱና ዳግም ባልተወለዱ ሰዎች መካከል ልዩነት አለ፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን አእምሮዋቸውን ማደስ የሚችሉት ጻድቃን ብቻ ናቸው፡፡ እኛ ጻድቃኖች ልባችንን በማንጻትና በማደስ እንደዚሁም የሥጋን ዓለማዊ ምኞቶች በመካድ ሁልጊዜም እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኙትን ነገሮች በእምነት ማድረግ እንችላለን፡፡
   
 

ልባችሁን በእምነት ማደስ አለባችሁ፡፡ 

 
በቴሌቪዥን የሚታዩ ብዙ ታዋቂ ሰዎች አሉ፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች የእነዚህን ታዋቂ ሰዎች ቄንጦችና ፋሽኖች ለመቅዳት በመሞከር ይባትላሉ፡፡ ቴሌቭዥን በማየት የቅርብ ጊዜ ፋሽኖችን በቀላሉ ማግኘት እንችላለን፡፡ ዓለምን በርቀት መቆጣጠሪያ መሳርያ መክፈት እንችላለን፡፡ ሕይወታችሁ ይህንን ዓለም አልመሰልምን?
ይህ ዓለም በፍጥነት እየተለወጠ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ አሁን የወረቀት ገንዘቦችን የያዝን ብንሆንም ውሎ አድሮ የአሌክትሮኒክ ገንዘብና የኤሌክትሮኒክ ካርዶችን እንይዛለን፡፡ እነዚህን የኤሌክትሮኒክ ካርዶች መጣል ችግር ሆኖብን ከሆነ የተሻለ ይሆን ዘንድ በእጆቻችን ወይም በግምባሮቻችን ላይ ባር ኮዶችን እንድንቀበል ይነግረናል፡፡ በዚያን ወቅት ብዙ የተፈጥሮ ጥፋቶች እንደሚሆኑ አስባለሁ፡፡ እኛ ጻድቃኖች ይህንን ዓለምን እንዳንመስል የዚህ አይነቱ ጊዜ ከመምጣቱ በፊት አእምሮዋችንን ለማደስ ልባችንን አዘጋጅተን የእግዚአብሄርን ወንጌል እናሰራጭ፡፡
 
እኔ በእያንዳንዱ ቀን የማስበው እግዚአብሄርን ስለ ማገልገል ነው፡፡ የእርሱን ጽድቅ የያዘውን ወንጌል አሁኑኑ በትጋት ማሰራጨት እመኛለሁ፡፡ ምክንያቱም በእጆቻችን ወይም በግምባሮቻችን ላይ ባር ኮዶችን የምንቀበልበት ጊዜ ሲመጣ ቃሉን ማሰራጨት አይቻልምና፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመከተል ያለ መታከት እየሰራሁ ነው፡፡ ምናልባት ማረፍ የምችለው ዳግመኛ መስራት የማልችልበት ቀን ሲመጣ ብቻ ነው፡፡ ያቺ ቅጽበት ስትመጣ ያለኝን ሁሉ ለድሆች እለግስ ይሆናል፡፡
 
አሁን ግን ከዓለም ተለይቼና ዓለምን ሳልመስል የእግዚአብሄርን ፈቃድ ብቻ እከተላለሁ፡፡ ጳውሎስ በሰበከው ወንጌል የዳኑትና በሮሜ የነበሩት ብዙዎቹ ጻድቃኖች በጊዜ ሒደት ውስጥ ከዓለም ጋር ተመሳስለው ከጌታ እየራቁ ነበር፡፡ የእነርሱን ዱካዎች እንዳንከተል መጠንቀቅ አለብን፡፡ 
 
ጳውሎስ ይህንን ምንባብ የጻፈው የሮሜ ምዕመናን ይህንን ዓለም እየመሰሉ ነው ከሚል ስጋት ነው፡፡ ‹‹ሰውነታችሁ ይህንን ዓለም እየመሰለ ነው፡፡ ነገር ግን ልታደርጉት የምትችሉት አንድ የከበረ ነገር አለ፡፡ አእምሮዋችሁን አድሱ፡፡ ጌታ ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ አልዋጀምን? የእግዚአብሄርን የጽድቅ ወንጌል አስታውሱ፡፡ እርሱ ደስ የሚሰኝበትንም አስቡ፡፡ አእምሮዋችሁን አድሱ፡፡ ስለ ሥጋ ሳይሆን ሰለ መንፈስ በማሰብ ‹‹ፍጹምና ደስ የሚያሰኙ ምግባሮችን አድርጉ፡፡›› ጳውሎስ ለሮሜ ምዕመናንና ዛሬም ለእኛ የሚመክረው ይህንን ነው፡፡
 
ከውጪ ይህንን ዓለም እንደማንመስል ብናስመስልም እንመስላለን፡፡ እንደዚያም ቢሆን አእምሮዋችንን በማደስ አሁንም ጌታን ማገልገል እንችላለን፡፡ በድካማችን ይህንን ዓለም አለመምሰል አስቸጋሪ መሆኑን ብናውቅም ጌታችን በእግዚአብሄር ጽድቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደ ዛሬም እናምናለን፡፡ በእርሱ ጽድቅ ባለን እምነታችን ሁልጊዜም የእግዚአብሄርን የጽድቅ ሥራዎች መስራት የምንችለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በእርሱ በማመን የእግዚአብሄርን በጎና ፍጹም ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መከት እንችላለን፡፡
 
በየቅጽበቱ አእምሮዋችንን ማደስ አለብን፡፡ ለዚህ ዓለም የሞቱት ጻድቃን ከዓለማዊ ሰዎች ይልቅ ንጹህ በመሆናቸው ከዓለማዊ ሰዎች ይልቅ ወደተሳሳቱ አስተሳሰቦች፣ አእምሮና ሰውነት የመዝቀጥ አደጋ ይገጥማቸዋል፡፡ ሁልጊዜም በእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ ባለን እምነታችን ልባችንን መጠበቅ የሚገባን ለዚህ ነው፡፡
 
ክርስቶስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስለወሰደ ከእኛ የሚፈልገው እምነታችን ፍጹም የመደረጉን እውነታ ለራሳችን በማረጋገጥ በእምነት ጸንተን መቆም ብቻ ነው፡፡ ጌታችን በእግዚአብሄር ጽድቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደ ታምናላችሁን? የምታምኑ ከሆነ ያለፈው ዓመጻችሁ ምንም ቢሆንም የጌታችንን ሥራ በእምነት መስራት ትችላላችሁ፡፡ ምክንያቱም ጌታ የሐጢያቶቻችሁን ፍርድና ኩነኔ በሙሉ ከእናንተ አስወግዶዋልና፡፡
 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን አእምሮዋችንን ማደስ አለብን፡፡ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ በመጨረሻው ዘመን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን አእምሮዋችንን ካላደስን ውሎ አድሮ ሁላችንም ቤተክርስቲያንን ትተን እንሞታለን፡፡ 
 
በማያቋርጥ ተሐድሶ የእምነት ሕይወት መኖር ማለት በብስክሌት ተራራን መውጣት ነው፡፡ አእምሮን አለማደስ ወደ ተራራ እየወጡ መንገድ ላይ መቆምና ፔዳሎቹን አለማሽከርከር ነው፡፡ ፔዳሎቹን ካላሽከረከራችሁ መቆም ብቻ ሳይሆን ወደኋላ ተመልሳችሁ ወደታች ትወድቃላችሁ፡፡ 
 
በእግዚአብሄር ጽድቅ ለሚያምነው እምነታችንም ተመሳሳይ መርህ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ እኛም በብስክሌት ወደ ተራራው እየወጣን ነው፡፡ በራሳችን ጉልበትና ውዴታ ብቻ ጫፍ ላይ መድረሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ገናም በሥጋ ስላለን የእግዚአብሄርን ጽድቅ አጥብቀን መያዝ አለብን፡፡ ስለ ሥጋ ሳይታሰብ አንዲትም ሰከንድ አታልፍም፡፡
 
የሥጋ ፈቃዳችን ጉልበታችን ሲደክም በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጥ ነው፡፡ ‹‹ይህንን ማድረግ አልችልም፡፡ ከዚህ ጋር መጣጣም አልችልም፡፡ የፈቃድ ሐይሌ በጣም ደካማ ነው፡፡ የዚያ ወንድም የፈቃድ ሐይል ግን በእርግጥም ብርቱ ነው፡፡ እኔ አቅም የለኝም፡፡ ያቺ እህት ግን ታላቅ አቅም አላት፡፡ እኔ ከእነዚያ ወንድሞችና እህቶች ጋር ስነጻጸር በጣም ደካማ ነኝ፡፡ እነርሱ ጌታን ለማገልገል ብቁ ይመስላሉ፡፡ እኔ ግን አይደለሁም፡፡›› የእግዚአብሄርን ጽድቅ የማያምንና አጥብቆ የማይዝ ማንኛውም ሰው ውሎ አድሮ ፔዳሎቹን ማሽከርከር ያቆምና ወደታች ይወድቃል፡፡ 
ይህ የሚመለከተው ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነውን? አይደለም፡፡ ይህ ሁሉንም የሚመለከት ነው፡፡ በሚገባ የሰለጠነ ብስክሌት ነጂ ተራራውን በቀላሉ ሊወጣው ይችላል፡፡ ደካማ ሰው ግን ይቸገራል፡፡ ሆኖም የጻድቃን ችግር ያለው አካላዊ ጉልበታቸው ላይ አይደለም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በእምነታቸው አጥብቀው በመያዙ ላይ ነው፡፡ በሥጋዊ ጉልበት ብቻ መንፈሳዊ ጫፍ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ በሥጋ ደካማ ወይም ብርቱ መሆን ከዚህ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡
 
ሰው ብርቱ የፈቃድ ሐይል ስላለው ብቻ የእምነትን ሕይወት መኖር እንደማይችል ይታወስ፡፡ ራሳችሁን ከሌሎች ጋር በማነጻጸር ተስፋ መቁረጥ የለባችሁም፡፡ የጌታን ጸጋ ብቻ አጥብቃችሁ ያዙ፡፡ ያለ መታከት በእግዚአብሄር ጽድቅ አእምሮዋችንን ብናድስ ጌታ ያግዘናል፡፡ እኛ የተቀበልነው የደህንነት ወንጌል በልባችን ውስጥ ይተከላል፡፡ በየቀኑ ልባችንን ብንመረምር ጌታ ይደግፈናል፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመንና የጌታን ሥራ በመስራት የቆሸሸውን አእምሮዋችንን ማጽዳት አለብን፡፡
 
አእምሮዋችንን በማደስ እርሱን እናገለግለው ዘንድ የፈቀደልንን ጌታችንን ስለ ጸጋው አመሰግነዋለሁ፡፡ አምላካችን አእምሮዋችንን በማደስ ሁልጊዜም በእምነታችን በፊቱ እንድንሮጥ ፈቅዶልናል፡፡
 
 

በእኔ አንዳች በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፡፡

 
ጳውሎስ በሮሜ 7፡18 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም፡፡›› ጳውሎስ በሥጋው ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደሌለ በሚገባ አውቋል፡፡ ሕጉ በሥጋ ውስጥ አንዳች በጎ ነገር የለም የሚል ነው፡
 
ጳውሎስ በሥጋው ምንም በጎ ነገር እንደሌለ ተረድቷል፡፡ ሕጉን ምንም ያህል ቢወድና በእርሱ ለመኖር ቢሞክር ያንን ማድረግ አልቻለም፡፡ ልብ ጌታን ለመከተል ራሱን ማደስ ይሻል፡፡ ሥጋ ግን ያለ መታከት ከመንፈሳዊው አውደ ውጊያ መሸሽ ይፈልጋል፡፡
 
ጳውሎስ በሮሜ 7፡21-24 ላይ የጮኸው ለዚህ ነው፡- ‹‹እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ፡፡ በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሄር ሕግ ደስ ይለኛልና፡፡ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በሐጢያት ሕግ የሚማረከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን፡፡ እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሄር ሕግ በሥጋዬ ግን ለሐጢያት ሕግ እገዛለሁ፡፡››
 
ጳውሎስ ሰውነቱን ያብራራው እንዴት ነው? ‹‹ለሞት የተሰጠ›› ሥጋ አድርጎ አብራራው፡፡ የእናንተስ ሰውነት? ለሞት የተሰጠ ሰውነት አይደለምን? በእርግጥም ነው! ሰውነት ራሱ ለሞት የተሰጠ ሰውነት ነው፡፡ የሚፈልገውም ሐጢያትን መስራትና ሐጢያት ወደሚበዛበት ሥፍራ ሁሉ መሄድ ብቻ ነው፡፡ ‹‹እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?›› ጳውሎስ ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን፡፡ እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሄር ሕግ በሥጋዬ ግን ለሐጢያት ሕግ እገዛለሁ›› (ሮሜ 7፡25) ያለው ለዚህ ነው፡፡ 
 
ጳውሎስ ሁለት ሕጎች እንዳሉ ጠቁሞዋል፡፡ አንደኛው የሥጋ ሕግ ነው፡፡ የሚሻውም የሥጋን ምኞቶች ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ከሚያስደስተው ፈጽሞ ተቃራኒ የሆኑትንም ሥጋዊ አስተሳሰቦች ያስባል፡፡
 
ሁለተኛው የሕይወት መንፈስ ሕግ ነው፡፡ የመንፈስ ሕግ እግዚአብሄር እንድንከተለው በሚፈልገው ትክክለኛ ጎዳና ላይ ሊመራን ይፈልጋል፡፡ የመንፈስ ሕግ የሥጋ ሕግ ከሚፈልገው በተቃራኒ ፍላጎት አለው፡፡ እኛ ክርስቲያኖችም ወዴት እንደምንሄድ ለመወሰን በመሞከር በሁለቱ መካከል ተጣብቀናል፡፡ 
 
አንዳንድ ጊዜ ሥጋችን የሚፈልገውን በመከተል እንቀጥላለን፡፡ አእምሮዋችንን ስናድስ ግን መንፈስ የሚሻውን የእግዚአብሄር ሥራ እንከተላለን፡፡ ይህንን የምናደርገው ማለትም ሰውነታችንን ለእግዚአብሄር መስዋዕት አድርገን የምናቀርበውና ወዲያው ደግሞ የሥጋን ነገሮች የምናደርገው ሁላችንም ሥጋ ስላለን ነው፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም አእምሮዋችንን በመንፈስ ቅዱስ ማደስ አለብን፡፡
 
ብንድንም በቀላሉ ይህንን ዓለም እንመስላለን፡፡ ምክንያቱም አሁንም በሥጋ ነንና፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ያለው ሌላው ሰው ሁሉ ከዓለም ጋር በመመሳሰል ሕይወቱን ስለሚኖር በቀላሉ በእነርሱ ተጽዕኖ ስር እንወድቃለን፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄርን መከተል የምንችልበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፡፡ ያም አእምሮዋችን ማደስ ነው፡፡ ሁልጊዜም አእምሮዋችንን በእምነት እያደስን መኖር እንችላለን፡፡ ጌታችን ዳግም እስኪመጣ ድረስ ሁልጊዜም እየተከተልነው መኖር የምንችለው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡
 
ሥጋችንን ብቻ ብንመለከት ማናችንም የጌታን የጽድቅ ሥራዎች መስራት አንችልም፡፡ ሁላችንም ለጥፋት እንኮነናለን፡፡ ነገር ግን አእምሮዋችንን በማደስና የእርሱን ጽድቅ ከሙሉ ልባችን አጥብቀን በመያዝ ጌታን መከተል እንችላለን፡፡ ጳውሎስ በሮሜ 8፡2 ላይ እንዲህ ያለው ለዚህ ነው፡- ‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከሐጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡››
 
በሥጋ የተነሳ ስለደከመ ሕግ ሊያደርግ ያልቻለውን ነገር ክርስቶስ በእግዚአብሄር ጽድቅ ፈጸመው፡፡ ሮሜ 8፡3 እንዲህ ይላል፡ ‹‹ከሥጋ የተነሳ ስለደከመ ለሕግ ያልተቻለውን እግዚአብሄር የገዛ ልጁን በሐጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በሐጢአትም ምክንያት አድርጎ ልኮአልና፡፡ ሐጢአትን በሥጋው ኮነነ፡፡›
 
እግዚአብሄር አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም ልኮ ሐጢያቶቻችንን በሥጋው ኮነነ፡፡ ‹‹ሐጢያትን በሥጋው ኮነነ›› ማለት ሐጢያቶቻችን በሙሉ ተወስደው እኛም ሐጢያት አልባ ሆንን ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ከሐጢያቶቻችን ድነናል፡፡ የሕጉን የፍትህ ጥያቄ ለመመለስ እግዚአብሄር በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወስዶ ከዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ያድነን ዘንድ ልጁን ላከ፡፡
 
ይህንን ደህንነት ከተቀበሉ በኋላ ሁለት ዓይነት ሰዎች ብቅ ይላሉ፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩና አሳባቸውን በሥጋ ነገሮች ላይ ያደረጉ ሰዎችና እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚመላለሱና አሳባቸውን በመንፈስ ነገሮች ላይ ያደረጉ ሰዎች ናቸው፡፡ የሥጋ አሳቦች ወደ ሞት ሊነዱዋችሁ እንደሚችሉ የመንፈስ አሳቦች ግን ወደ ሕይወትና ሰላም ሊመሩዋችሁ እንደሚችሉ መረዳት አለባችሁ፡፡
 
ለእግዚአብሄር ሕግ አንገዛም፡፡ ይህንን መቼም ቢሆን ልናደርገው አንችልም፡፡ (ሮሜ 8፡7) ዳግም የተወለዱ ጻድቃኖች እንኳን አእምሮዋቸውን ካላደሱ በሥጋ አሳቦች ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደ የማናምንና አእምሮዋችንን የማናድስ ከሆንን በቀላሉ በሥጋ ሥራዎች ውስጥ ስለምንወድቅ ጌታን መከተል አንችልም፡፡ ሁልጊዜም አእምሮዋችንን ማደስ የሚገባን ለዚህ ነው፡፡
 
ጳውሎስ እኛ ዳግም የተወለድን ጻድቃን የሥጋን አሳቦች በመከተል በሥጋ ውስጥ እንደምንወድቅ ወይም አእምሮዋችንን በማደስ የመንፈስን አሳቦች እንደምንከተል ተናግሮዋል፡፡ በሁለቱ መካከል እየተወዛወዝን ነው፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ እንዲህም ብሎዋል፡- ‹‹እናንተ ግን የእግዚአብሄር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም፡፡ የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም፡፡›› (ሮሜ 8፡9)
እኛ የእግዚአብሄር መንፈሳዊ ሕዝቦች ነን፡፡ በሌላ አነጋገር እኛ የእርሱ ሕዝብ ነን፡፡ የዓለምን ፍትወቶች ብንከተልና በድክመታችን ከእነርሱ ጋር ብንመሳሰልም አሁንም ዳግም የተወለድን ሰዎች ነን፡፡ የሥጋን ነገሮች ስናስብ በሥጋ ውስጥ እንወድቃለን፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ስለሚኖር እኛ የክርስቶስ ሰዎች ነን፡፡ በሌላ አነጋገር ጻድቃን የእግዚአብሄር ሕዝብ ሆነናል፡፡
 
ጳውሎስ ‹‹ሰውነታችን በክርስቶስ እንደሞተ›› ተናግሮዋል፡፡ ጨምሮም ‹‹ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በሐጢአት ምክንያት የሞተ ነው፡፡ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው›› (ሮሜ 8፡10)  ይላል፡፡ መንፈሳዊ አስተሳሰቦቻችን መንቃት አለባቸው፡፡ እኛ አሁንም ደካሞች ነን፡፡ እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስም ሰውነታችን በቀላሉ ይስታል፡፡ ነገር ግን አእምሮዋችንና አስተሳሰቦቻችን ሁልጊዜም በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን መታደስ አለባቸው፡፡
 
በውስጣችን ያለውን የሐጢያት ፍላጎት በምንረዳበት ጊዜ ሁሉ ዓይኖቻችንን በእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ እናድርግ፡፡ ያን ጊዜ የእግዚአብሄር ጽድቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደ ማወቅ እንችላለን፡፡ ወደ እግዚአብሄር ጽድቅ ተመልከቱና እመኑ፡፡ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስለወሰደ አመስግኑት፡፡ የእግዚአብሄርንም ሥራዎች አስቡ፡፡ ፍጹምና እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘው የእርሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስቡ፡፡ ያን ጊዜ አእምሮዋችሁ ሁልጊዜም የታደሰ ይሆናል፡፡
 
አእምሮዋችንን በእምነት ማደስና አእምሮዋችን እግዚአብሄርን ደስ በሚያሰኙ ነገሮች ላይ እንዲጸና ማድረግ አለብን፡፡ ጻድቅ ሊኖር የሚገባው እንደዚህ ነው፡፡ ጌታን እስከ ምጽዓቱ ድረስ ልንከተለው የምንችለው ይህንን በማድረግ ብቻ ነው፡፡ በቀን ተቀን ሕይወታችን ሁላችንም እንደታከትን አውቃለሁ፡፡ ሥራ መስራት አስቸጋሪ ነው፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ችግሮች እየገጠሙት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስ በሞቱ ወቅት ‹‹ተፈጸመ›› ብሎ በመጮሁ እቀናለሁ፡፡ እኛም ደግሞ ‹‹ተፈጸመ›› ማለት እንደምንችልና ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች ነጻ እንደምንወጣ እተማመናለሁ፡፡
የጌታችን ዳግመኛ ምጽዓት ቀርቦዋል፡፡ እስከዚያ ድረስ ሳንመሳሰል አእምሮዋችንን እናድስ፡፡ ምከንያቱም ጌታን ለመከተል ልባችን የእግዚአብሄርን ጽድቅ አጥብቆ መያዝ ስለሚያስፈልገው አእምሮዋችን በየጊዜው መታደስ አለበት፡፡ ጌታን እስኪመጣ ድረስ የምንከተለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ጊዜው ቀርቦዋል፡፡
 
በቅርቡ የአንታርቲክ የኦዞን ሽንቁር ከአህጉራዊቷ አሜሪካ በሦስት ዕጥፍ ትልቅ እንደሆነ የዘገበ አንድ ጋዜጣ አነበብሁ፡፡ ስለ ሚሳኤል መከላከያ ዕቅድ የሚያትት ሌላ ጋዜጣም አንብቤያለሁ፡፡ ይህ ሲስተም ባለስቲክ ሚሳኤሎችን በአየር ላይ ሳሉ ለመምታት የታለመ ነው፡፡ ቀደምት ሙከራዎችም የተሳኩ ሆነዋል፡፡ የእነዚህ ፈጠራዎች አንደምታ ግልጽ ነው፡፡ የወታደራዊ ሐይል አጥፊ አቅም በብዙ ዕጥፎች ሲበዛ ሥነ አካባቢም በስፋት ይወድማል፡፡
 
አንድ አገር ወታደራዊ ሐይሉን ሲያጠናክር ይህን ሐይል ለመቋቋም የእርሱ ተቀናቃኞችስ ወታደራዊ ጡንቻዎቻቸውን አያፈረጥሙምን? የዓለም መንግሥታት በሙሉ አንድ አገር አቅሙን ሲያፈረጥም ሥራ ፈተው በመቀመጥ ሊያዩ አይችሉም፡፡ በእነዚህ ታላላቅ ሐይሎች መካከል ጦርነት ቢነሳ ምን ይፈጠራል?
 
አንዳንድ አገሮች የኒውክሌር ጦር መሳርያዎችን ለመስራት ሲሞክሩ ታላላቆቹ ሐይሎች የኒውክሌር አቅም እንዳያዳብሩ አጥብቀው ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ያሉት የመከላከያ ጥረቶች ባይሳኩና በጥያቄ ውስጥ ያለው አገር ሕዝብ ጨራሽ የጦር መሳርያዎችን አግኝቶ እነርሱን ለመጠቀም ቢዝትስ እንበል፡፡ ያን ጊዜ የቀረው ዓለም ይህንን ሁኔታ ለመቋቋም አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን ለመፍጠር እንደሚሞክር የታወቀ ነው፡፡
 
እነዚህ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ከኒውክሌር የጦር መሳሪያዎች እጅግ በላቀ መልኩ ይህችን ዓለም ያወድሙዋታል፡፡ ጦርነቶች ባለፉት ጊዜያት እንደተደረጉት በጠመንጃዎች አይደረጉም፡፡ ሰዎችን መግደል ምንም ማለት የማይሆንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ሙሉ ከተሞች ወይም ጠቅላላ አገሮች በቅጽበት ውስጥ ይወድማሉ፡፡ የኒውክሌር ጦርነት በአንድ ክልል ብቻ አይወሰንም፡፡ ነገር ግን ወደ አለም ጦርነት ያመራል፡፡ አስቀድሞ እንደዚህ ባለው ጦርነት የወደመችው ዓለም በተፈጥሮ ጥፋቶች መልክም ከዚህ የበለጠ ጥፋት ይጠብቃታል፡፡ የኦዞን ንጣፍ በበለጠ ፍጥነት ይወድማል፡፡ ማዕበሎችና የባህር ወጀቦችም ከደን ጭፍጨፋ የተነሳ በየጊዜው ይጨምራሉ፡፡ ያን ጊዜ የክርስቶስ ተቃዋሚ በታላቅ ሐይል  ይገለጥና ይህንን ዓለም ያሸንፋል፡፡
 
እኔ ይህንን አጽመ ታሪክ ለጥጬ የወሰድሁት ይመስላችሁ ይሆናል፡፡ የሰው ተፈጥሮ ግን ከስር መሰረቱ ክፉ ነው፡፡ መንግሥታቶች ወታደሮችን ያከማቻሉ፡፡ ለበጎ ዓላማ የማይጠቅሙ አዳዲስ መሳሪያዎችንም ይፈበርካሉ፡፡ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ሕዝብ ጨራሽ ከሆኑ የጦር መሳሪያዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አንዳቸው ብቻ ለመኖር ስለሚፈልጉ እርስ በርሳቸው ይቆራቆሳሉ፡፡ ሌሎች አገሮችም ዓለምን ለመግዛት የሚሻ ማንኛውንም አንድ አገር ለመቃወም ይሞክራሉ፡፡ አሳባቸው ምንም ይሁን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችና ወታደራዊ አቅሞች አንድ ጊዜ ከተገነቡ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉት ለክፉ ዓላማዎች ብቻ ነው፡፡
 
ጳውሎስ ጥንት በሮሜ የሚገኙትን ምዕመናን ልባቸውን በማደስ ጌታን እንዲከተሉ እንጂ ይህንን ዓለም እንዳይመስሉ ነገራቸው፡፡ ይህ በዚህ ዘመን ለምንኖር ለእኛ በጣም ተስማሚ ምንባብ ነው፡፡ በዚህ በመጨረሻው ዘመን የእግዚአብሄር በጎ፣ ፍጹምና ደስ የሚያሰኝ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅና ጌታን በእምነታችን መከተል አለብን፡፡
 
ብዙ ጉድለቶች ቢኖሩብንም ጌታችን ሁሉን የሚችል አምላክ ነው፡፡ ሁሉን ቻዩ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ መልክ በውስጣችን ይኖራል፡፡ ሥጋዊ ሰውነታችን ደካማ ቢሆንም በውስጣችን ያለው መንፈስ ቅዱስ በጣም ብርቱ ነው፡፡ ጌታን መከተል እንችል ዘንድ ይህ መንፈስ ቅዱስ በቃሉ ላይ ባለን እምነት አእምሮዋችንን ያድሳል፡፡
ሁላችንም በመንፈስ ቅዱስ ሐይል ላይ እንደገፍ፡፡ አእምሮዋችንን እናድስ፡፡ ጌታንም እናገልግል፡፡ እርሱን እያገለገልነው ሳለን ጌታ ቢመለስልን ያን ጊዜ ከእርሱ ጋር አብረን እንሂድ፡፡ ክርስቶስ እስከሚመለስበት እስከዚህ ቀን ድረስ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማሰራጨት እንኖራለን፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን አእምሮዋችሁን አድሱ፡፡