Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-14] የተቀደደው መጋረጃ፡፡ ‹‹ ማቴዎስ 27፡50-53 ››

የተቀደደው መጋረጃ፡፡
‹‹ ማቴዎስ 27፡50-53 ››
‹‹ኢየሱስም ሁለተኛ በታለቅ ድምጽ ጮሆ ነፍሱን ተወ፡፡ እነሆም የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፡፡ ምድርም ተናወጠች፡፡ አለቶችም ተሰነጠቁ፡፡ መቃብሮችም ተከፈቱ፡፡ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሱ፡፡ ከትንሳኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ፡፡››
 
 
ቅድስተ ቅዱሳኑ እግዚአብሄር የሚያድርበት ስፍራ ነው፡፡ ለእስራኤላውያን ሐጢያቶች ስርየት ለመስዋዕት የቀረበውን ፍየል ደም ይዞ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችለው ሊቀ ካህኑ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ያደረገው የመገናኛው ድንኳን ቅድስተ ቅዱሳን የሆነው የእግዚአብሄር ቤት የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች ለመደምሰስ እጆቹን በራሱ ላይ ጭኖ የመስዋዕቱን ደም ካልያዘ በስተቀር ሊገባበት የማይችልበት ቅዱስ ስፍራ ነበርና፡፡ በተለየ መንገድ ለማስቀመጥ ሊቀ ካህኑ ወደ እግዚአብሄር ፊት ከመቅረቡ በፊት መስዋዕትን በማቅረብ የሐጢያቶቹን ስርየት እስካልተቀበለ ድረስ የእግዚአብሄርን ኩነኔ መሸሽ አይችልም፡፡
 
የቤተ መቅደሱ መጋረጃ የተቀደደው መቼ ነበር? የተቀደደው ኢየሱስ ደሙን አፍስሶ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ነበር፡፡ እርሱ ለመሞት በመስቀል ላይ ደሙን ማፍሰስ ያለበት ለምንድነው? ምክንያቱም የእግዚአብሄር ልጅ የሆነወ ኢየሱስ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመምጣት በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ተጠምቆ የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች ሙሉ ስለወሰደ ነው፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ አማካይነት በመውሰዱ የሐጢያትን ኩነኔ ወደ ፍጻሜ ማምጣት የሚችለው በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ ሲሞት ብቻ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን ከቅድስቱ የሚለየው መጋረጃ ከላይ እስከ ታች የተቀደደው ለዚህ ነው፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሄርን ከሰው ዘር የለየው የሐጢያት ግድግዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ፈርሶዋል ማለት ነው፡፡
 
በሌላ አነጋገር ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት ሐጢያቶችን በሙሉ አስወግዶዋል፡፡ እግዚአብሄር አብ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ደም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ አስወግዶዋል፡፡ እግዚአብሄር አብ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ደም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ አስወግዶ አሁን በእነዚህ የኢየሱስ ጥምቀትና የፈሰሰ ደም በማመን ማንኛውም ሰው ሰማይ መግባት ይችል ዘንድ የሰማይን መንገድ ከፈተ፡፡
 
ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ እርሱ ለሦስት ሰዓታት በቆየበት ስፍራ ጨለማ ሆነ፡፡ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ተሸክሞ ከተሰቀለ በኋላ ሞቱ ሲቃረብ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?›› በማለት ጮኸ፡፡ ትርጓሜውም ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸን?›› (ማቴዎስ 27፡46) ማለት ነው፡፡ ከዚያም ‹‹ተፈጸመ!›› በማለት የመጨረሻ ቃሉን ሰጥቶ ሞተ፡፡ በሦስት ቀናት ውስጥም ዳግመኛ ከሙታን ተነሳ፡፡ ለ40 ቀናትም መሰከረ፡፡ ከዚያም ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርቱና ተከታዮቹ እያዩት ወደ ሰማይ አረገ፡፡
 
 
በእርግጥ አብ ኢየሱስን ትቶት ነበርን? 
 
ኢየሱስ የገጠመው ስቃይ እጅግ ብርቱ ስለነበር አባቱ የተወው መስሎ ተሰማው፡፡ የሐጢያት ኩነኔው ስቃይ ያን ያህል ትልቅ ነበር፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች በመውሰዱ በመስቀል ላይ የሐጢያትን ኩነኔ በተሸከመ ጊዜ ለጊዜው አብ ትቶት የነበረ መሆኑ እውነት ነው፡፡ እግዚአብሄር አብ ሐጢያት ያለበትን ማንኛውንም ሰው መቅጣት ነበረበት፡፡ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ኢየሱስ በመሻገራቸው ኢየሱስ ለእነዚህ ሐጢያቶች ቅጣት ይሆን ዘንድ በመስቀል ላይ መቸንከርና ደሙን ማፍሰስ ነበረበት፡፡
በማንነቱ ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ በጥምቀቱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰዱ የዓለም ሐጢያቶች ወደ እርሱ ቅዱስ ሰውነት ተሻገሩ፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በመውሰዱ ለጊዜው በእግዚአብሄር አብ መተውና የሐጢያቶቻችንን ደመወዝ በሙሉ ለመክፈል በመስቀል ላይ ሞቶ የሰውን ዘር ከሐጢያቶቹ ሁሉ ማዳን ነበረበት፡፡ ኢየሱስ በሐጢያት ኩነኔ ምክንያት ክፉኛ የተሰቃየው ለዚህ ነበር፡፡ እግዚአብሄር አብም ለጊዜው ፊቱን የሰወረበት ለዚህ ነው፡፡
 
ይህ ማለት ግን አብ ኢየሱስን ለዘላለም ትቶታል ማለት አይደለም፡፡ በፈንታው ይህ ማለት በአጭሩ ኢየሱስ የሐጢያቶቻችንን ኩነኔ በይፋ መሸከም ነበረበት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አብ ለጊዜው ብቻ ተወው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?›› ብሎ በስቃይ የጮኸው እኛ ከሐጢያት ኩነኔ እንድን ዘንድ እንዲህ ባለ መጠን ያለፈ የሐጢያት ስቃይ ስለተሰቃየ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ስለ ሐጢያቶቻችን ሊተወን የሚገባው እኛን ነበር፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ወስዶ በመስቀል ላይ የሐጢያት ኩነኔን ስቃይ ተሰቃየ፡፡ ከዚህም በላይ ስለ እኛ ሲል አብ ለጊዜውም ቢሆን ተወው፡፡
 
ቀደም ብላችሁ እንደምታውቁት በሰለሞን የአገዛዝ ዘመን ቤተ መቅደሱ ከተገነባ በኋላ የመገናኛው ድንኳን ስርዓት መሰረታውያን ከግንባታው በፊት ጥቅም ላይ ውለው እንደነበሩት ለቤተ መቅደሱም በትክክል ጥቅም ላይ ውለው ነበር፡፡ ስለዚህ የመቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ከቅድስቱ የሚለይ መጋረጃም እንደዚሁ ነበር፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?›› ብሎ በጮኸበት ቅጽበት የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ላይ እስከ ታች ተቀደደ፡፡ በዚህ ሁነት የተነገረው እውነት ጌታ በተቀበለው ጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሐጢያቶቻችንን ስላስወገደ የሚያምኑ ሁሉ ይገቡበት ዘንድ አሁን የሰማይ በር ወለል ብሎ መከፈቱን መናገሩ ነው፡፡ አሁን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ሁላችንም በእምነት ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡
 
የብሉይ ኪዳን ሰዎች በመገናኛው ድንኳን ስርዓት መገለጥ አማካይነት ኢየሱስ መሲህ ሆኖ እንደሚመጣ በማመናቸው ሐጢያቶቻቸው በሙሉ ይቅርታን አግኝተው የእግዚአብሄር ልጆች ሆነዋል፡፡ በአዲስ ኪዳን የሐጢያት ስርየት የሆነው የእግዚአብሄር ጽድቅ በሙሉ ጌታችን በተጨባጭ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ለአንዴና ለመጨረሻ ተፈጽሞዋል፡፡ ጌታ የሰጠንን የሐጢያት ስርየት ወንጌል ሰምተን በማመን አመስጋኝ ልብ ሊኖረን የሚገባን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ስላለን ነው፡፡
 
በራሳችን ጥረት ከሐጢያት ነጻ መውጣት አንችልም፡፡ ነገር ግን በውሃና በመንፈስ አማካይነት በሰጠን የደህንነት እውነት በማመን ከሐጢያቶቻችን ነጻ መውጣት ችለናል፡፡ ኢየሱስ በሰጠን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመናችን ሐጢያቶቻችን ጠፍተዋል፡፡ አሁን እኛ በእምነት መንግሥተ ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡ ታዲያ እግዚአብሄርን እንዴት አናመሰግነውም? ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ጌታችን በሞተበት ቅጽበት የሰማይ በር ከላይ እስከ ታች እንደተተረተረ እናውቃለንና፡፡ ይህ ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ መውሰዱንና በመስቀሉ ደምም የሐጢያት ኩነኔን ተሸክሞ የሚያምኑትን ሁሉ ከሐጢያት እንዳዳናቸው የሚነግረን የምስራች ነውና፡፡
 
ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የመቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች የመቀደዱ እውነታ አሁን በዚህ ዘመን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ከሐጢያት የነጹ በሙሉ ሰማይ መግባት የሚችሉ የመሆኑ እውነት ያስተምረናል፡፡ ጌታ የፈቀደልን አሳማኙ የደህንነት እውነት ማስረጃ ይህ ነው፡፡ እኛ ሐጢያተኞች ስለነበርን በእግዚአብሄር ፊት ከመቅረብ የከለከለን የሐጢያት ግድግዳ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ በጥምቀቱና በደሙ ይህንን የሐጢያት ግድግዳ ለአንዴና ለመጨረሻ አፈረሰው፡፡ እግዚአብሄር የቤተ መቅደሱን መጋረጃ ከላይ እስከ ታች መቅደዱ የእግዚአብሄር ልጅ የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በሙሉ በወሰደበት ጥምቀትና በመስቀሉ ደም የሚያምን ማንኛውም ሰው አሁን ከሐጢያቶቹ ፈጽሞ ነጽቶ ያለ ምንም ክልከላ ሰማይ መግባት እንደሚችል ያመለክታል፡፡ እግዚአበሄር በዚህ መልክ ከሐጢያት አድኖናል፡፡
ኢየሱስ ለፈጸማቸው ለእነዚህ የደህንነት ሥራዎች ማስረጃ ይሆን ዘንድ የቤተ መቅደሱን መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ቀደደው፡፡ ስለዚህ ዕብራውያን 10፡19-22 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንግዲህ ወንድሞች በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን በእግዚአብሄርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውሃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፡፡››
 
ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ መጋረጃው ስለተቀደደ የቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ ወለል ብሎ ተከፈተ፡፡ እዚህ ላይ ይህ የተከፈተው የቅድስተ ቅዱሳን በር ወደ ሰማይ የሚያደርስ አዲስና ሕያው መንገድ የከፈተው የእግዚአብሄር የወንጌሉ ቃል ነው፡፡ እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የልባችንንና የሰውነታችንን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱና (ንጹህ ውሃ) በደሙ ስለተደመሰሱ በእርሱ ፍጹም ደህንነት ላይ ባለን ሙሉ መረዳት መንጻት እንደምንችል ዳግመኛ ይነግረናል፡፡
 
ለዚህም እግዚአብሄርን በሚገባ አመሰግነዋለሁ፡፡ እኛ ምንም ያህል ብንለፋም ሰማይ መግባት አንችልም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ እኛን በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ የጽድቅ ተግባራት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አድኖን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑት ብቻ ሰማይ መግባት ይችሉ ዘንድ የሰማይን በር ወለል አድርጎ ከፈተው፡፡ አሁን እኛ ከሐጢያቶቻችን ነጽተን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በሚያምነው እምነት ሰማይ መግባት የሚቻለን ይሆናል፡፡
 
ጌታ በጥምቀቱና በስቅለቱ የሰማይን በር ስለከፈተልን አሁን ከሐጢያቶቻችን ነጽተን በዚህ እውነት በማመን ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡ ታዲያ እግዚአብሄርን እንዴት አናመሰግነውም? መስዋዕትነትን ስለከፈለበት ፍቅሩ በበቂ ሁኔታ አላመሰገንነውም፡፡ የቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በወሰደበት ጥምቀቱና ለእነዚህ ሐጢያቶቻችን በይፋ እንዲኮነን መስዋዕት አድርጎ ባቀረበው ሥጋው ተቀደደ፡፡
 
 
ሰማይ ለመግባት ያለው አንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ 
 
እኛ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ ስለምናምን ሰማይ እንገባለን፡፡ በዚህ የእውነት ወንጌል በማመን ካልሆነ ሰማይ የሚገባበት ሌላ መንገድ የለም፡፡ ሰማይ መግባት የምንችለው ኢየሱስ ለእኛ ያደረገውን በማመን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር በኢየሱስ የውሃና የደም ወንጌል ለሚያምኑ እነዚህን ሥራዎች ፈጽሞላቸዋልና፡፡
 
ክርስቲያኖች በጥረቶቻቸው፣ በመሰጠታቸው ወይም በሌሎች የግብዝነት ሙከራዎች ሰማይ መግባት የማይችሉት ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰማይ መግባት የሚችሉት ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀትና ባፈሰሰው ደሙ በማመን ከሐጢያቶቻቸው የነጹት ብቻ ይሆኑ ዘንድ ወስኖዋል፡፡ በዚህ እውነት የሚያምኑ ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ፣ ራሱ አምላክና በጥምቀቱና ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት ከሐጢያት ያዳናቸው መሆኑን የሚያምኑ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር በእምነት መንግሥተ ሰማይ ይገቡ ዘንድ በእነዚህ እንዲያምኑ ያስቻላቸው ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀቱና በመስቀል ላይ በተሸከመው ስቃይ አማካይነት ብቻ ነው፡፡
 
ሰማይ ለመግባት ገንዘብ ያስፈልገናልን? ነገሩ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ገንዘብ በመክፈል ደህንነታችንን እናገኝ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በጌታ የሚሰጥ ነጻ ደህንነት አይሆንም ነበር፡፡ እኛ ሰማይ ለመግባት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከሚያምን እምነት ውጪ ሌላ አንዳች ነገር አያስፈልገንም፡፡ በሌላ አነጋገር ሰማይ ለመግባት የእኛ ክፍያ፣ ምግባር ወይም ጥረት ምንጊዜም አያስፈልግም፡፡ ሰማይ ለመግባት ከሰው የሆነ ባህርይ አያስፈልግም፡፡ እኛ ሰማይ ለመግባት ብቁ እንሆን ዘንድ እግዚአብሄር ከእኛ አንዳች ጥረት፣ ድርጊት፣ ፈቃድ፣ ካሳ ወይም ቸርነት አልጠየቀም፡፡
 
ሰማይ እንገባ ዘንድ በጣም አስፈላጊ የሆነው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ይህም ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተቀበለው ሐጢያትን የሚያስወግድ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ ለሐጢያቶቻችን ስርየት የከፈለውን መስዋዕትነት የሚያምን እምነት ነው፡፡ ሌላ መንገድ የለም፡፡ የሚያስፈልገን ብቸኛው ነገር በኢየሱስ ጥምቀትና ደም የሚያምን እምነት ነው፡፡ እኛ የሐጢያት ስርየትን እንድንቀበልና ሰማይ እንድንገባ ኢየሱስ በፈጸመው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማመን ያለብን ለዚህ ነው፡፡
 
የፍቅር ጌታ የሆነው ኢየሱስ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ፍጹም የሆነውን ደህንነታችንን ፈጽሞታል፡፡ ኢየሱስ የሐጢያት ስርየትን ደህንነት አስቀድሞ ስላጠናቀቀው ሐጢያተኞች በዚህ የወንጌል እውነት ከልባቸው ቢያምኑ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ መዳን ይችለሉ፡፡ ሐጢያቶቻችንን ብዙ ወይም ጥቂት ይሁኑ ጌታችን ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወስዶ ማንም ሰው በእምነት ሰማይ እንዲገባ አስችሎታል፡፡
 
ሐጢያተኞች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ይገቡበት ዘንድ የሰማይን በር መክፈቱ በእርግጥ ልዩ የሆነ የደህንነት ጸጋ ነው፡፡ ‹‹ጌታ ሐጢያቶቼን ሁሉ ለመሸከም ተጠመቀ፤ በእኔ ፋንታም በመስቀል ላይ ሞተ! ሐጢያቶቼን ሁሉ አስወግዶ የሰማይን በር ከፈተልኝ! እኔን አብዝቶ ስለወደደኝ ተጠመቀ፤ ደሙን አፈሰሰ፤ በዚህ መልኩም የሐጢያት ስርየቴን ፈጸመ!›› በዚህ መንገድ በደህንነት እውነት ስታምኑ በዚህ እምነት ሰማይ ትገባላችሁ፡፡
 
ሰዎች ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው ለማመን ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ነገር ግን ቀላል ነው፡፡ ማድረግ ያለባቸው ነገር ቢኖር ኢየሱስ ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ አስቀድሞ ያከናወናቸውን የተጠናቀቁ እውነታዎች ተቀብሎ በእነርሱ ማመን ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ደምስሶ በዮርዳኖስ ወንዝ ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙና በመንፈሱ አማካይነት ነጻ ስላወጣን ይህንን ኢየሱስን በልባችን ስናምነው ሁላችንም እንድናለን፡፡
 
‹‹እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል፡፡›› (ዮሐንስ 8፡32) ሐጢያታችን ትልቅ ይሁን ወይም ትንሽ ኢየሱስ በጥምቀቱና ባፈሰሰው ደሙ ሁሉንም አስወግዶዋቸዋል፡፡ የዘላለም ደህንነታችንን መቀበልና የዚህን እውነተኛ ደህንነት ነጻነት መለማመድ የምንችለው ከሐጢያት ነጻ በሚያወጣን በዚህ እውነት በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ነው፡፡
 
ጌታችን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመፈጸም የሰማይን በር ወለል አድርጎ ከፍቶልናል፡፡ ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ ተጠመቀ፤ በመስቀል ላይ ሞተ፤ በሦስት ቀናትም ዳግመኛ ከሙታን ተነሳ፡፡ ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነት ወደ እግዚአብሄር አስጠግቶናል፡፡ ወደፊትም ሰማይ የእኛ ይሆን ዘንድ አስችሎናል፡፡ ሰማይ ለመግባትና ከሐጢያት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሄር ልጆች ለመሆን የምትፈልጉ ከሆነ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም በማመን የሐጢያት ስርየታችሁን መቀበል አለባችሁ፡፡ የሐጢያት ስርየትን እንድትቀበሉ የሚያስችላችሁና ወደ ሰማይ ደጅ የሚመራችሁ ይህ እምነት ነው፡፡
 
ጌታችን ስለ እኛ እያንዳንዱን ነገር ያውቃል፡፡ መቼ እንደተወለድን ያውቃል፡፡ የሰራናቸውንና የምንሰራቸውን ሐጢያቶች በሙሉ ያውቃል፡፡ ምንም ያህል ጠንክረን ብንሞክርም በራሳችን ጥረት ሐጢያቶቻችንን ማስወገድ እንደማንችል ያውቃል፡፡ ጌታ በሚገባ ስለሚያውቀን እርሱ ራሱ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ደምስሶዋል፡፡
 
 
ኢየሱስ ለምን ወደዚህ ምድር መጣ?
 
ኢየሱስ የሚለው ስም አዳኝ ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ የተወለደው ከሐጢያት የመዳናችን ጉዳይ ያለው በመለኮት ሐይል ላይ እንጂ በሰው ክንውን ላይ ስላልነበረ ነው፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ ውልደት ግልጽ የሆነ ዓላማ ይዞዋል፡፡ ኢየሱስ የሰውን ዘር ከሐጢያቶች ለማዳን በድንግል ሥጋ አማካይነት ወደዚህ ምድር የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ከአዳምና ከሔዋን መተላለፍ የተነሳ ሐጢያትን ለወረሱት ሐጢያተኞች ሲል በሴት አካል ውስጥ አልፎ ተወለደ፡፡ ጌታ የዚህን ዓለም ሐጢያተኞች በሙሉ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የሚያድን አዳኝ ይሆን ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በእግዚአብሄር ሐይል በድንግል ማህጸን ውስጥ ተጸነሰ፡፡
 
ጌታችን ራሱ እንከን የሌለበት መስዋዕት ይሆን ዘንድ ራሱ በፈጠረው አካል በኩል ወደዚህ ምድር ተወለደ፡፡ ጊዜው ሲደርስም ደህንነትን ለእኛ ለማምጣት ዕቅዱን ደረጃ በደረጃ አከናወነ፡፡ ጌታችን 30 ዓመት ሲሞላው በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ በዚህ ምድር ላይ የተወለደበትን ዓላማ ለመፈጸም ኢየሱስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች መቀበል ነበረበት፡፡ በዮሐንስ የተጠመቀውም ይህንን ተግባር ለመፈጸም ነበር፡፡ (ማቴዎስ 3፡13-17)
 
ኢየሱስ በጥምቀት አማካይነት በዚህ መንገድ የዓለምን ሐጢያቶች ከተቀበለ ከሦስት ዓመታት በኋላ ተሰቀለ፡፡ ጌታችን ለሐጢያቶቻችን በይፋ የተኮነነው ስለተጠመቀና የዓለምን ሐጢያቶች ስለወሰደ ነው፡፡ ጌታ ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሐጢያቶችን በሙሉ አስወገደ፡፡ በዚህም የሚያምኑትን ከሐጢያቶቻቸው እንዲድኑ አስቻላቸው፡፡
 
ሰዎች ራሳቸውን እንዴት ባለ ድንቁርና ውስጥ ቢያገኙትም፣ እንዴት ባሉ ድካሞች ውስጥ ቢጠመዱና ምንም ዓይነት ሐጢያተኞች ሊሆኑ ቢችሉም እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምናምነውን አማኞች የጌታ መንግሥት ወደሆነው ሰማይ እንድንገባ አስችሎናል፡፡ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀውና በመስቀል ላይ ደሙን ያፈሰሰው የሐጢያትን ዋጋ ለመክፈል ነበር፡፡ ኢየሱስ የሐጢያቶችን ዋጋ በመክፈልና ራሱን መስዋዕት በማድረግ ከፈጸመው ደህንነት የተነሳ የምናምን ሰዎች አሁን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባለን እምነታችን ብቻ ከሐጢያቶቻችን መንጻት እንችላለን፡፡ ይህ መሰረታዊ የክርስትና እውነትና የሐጢያት ስርየት ማዕከል ነው፡፡
 
ጌታ ወደዚህ ዓለም የመጣው የዚህ ዓለም ሐጢያተኞች ሁሉ አዳኝ ለመሆን ነው፡፡ በእርግጥም ጌታ ሁላችንንም ከሐጢያት አድኖናል፡፡ ጌታችን እነርሱ ማንም ይሁኑ ሐጢያተኞች በእርሱ ሥራዎች በማመን ሰማይ እንዲገቡ አስችሎዋቸዋል፡፡
 
ይህ የጌታ ፍቅር ነው፡፡ ጌታ እኛን ለማዳን የተጠመቀውና ደሙን ያፈሰሰው አብዝቶ ስለወደደን ነው፡፡ ልክ እንደ ራሱ ሥጋ አብዝቶ የወደደንን እኛን ከሐጢያት ለማዳን ጌታችን በጥምቀቱና ደሙን በማፍሰስ ደህንነትን ፈጸመ፡፡ እኛ እስከምንሞትበት ቀን ድረስ ሐጢያትን በመስራት የምንቀጥል ሐጢያተኞች ነበርን፡፡ በሐጢያቶቻችን እየተሰቃየን ከእግዚአብሄር መራቃችንን ቀጥለናል፡፡ እንደ እኛ ያሉትን ሰዎች ለማዳን ጌታ ከእርሱ ጋር እንድንቆራኝ የሚያስችሉንን የደህንነት ሥራዎች መፈጸም ነበረበት፡፡
 
ጌታችን ሐጢያተኞች የነበርነውን እኛን በእግዚአብሄር ፍቅር አዳነን፡፡ እኛን ሐጢያተኞቹን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን ጥምቀትን በመቀበልና ደሙን በማፍሰስ የእግዚአብሄርን ጽድቅና ፍቅር ፈጸመ፡፡ እኛ በዚህ ወንጌል የምናምን ጌታ ስላደረገልን ነገር በጣም አመስጋኞች ስለሆንን በእርሱ ፊት ስንበረከክ ከእምነት የፈለቀውን ምስጋናችንን ለመግለጥ ቃላቶች ያጥሩናል፡፡ ጌታችን የሰጠን የሐጢያት ስርየት እውነት የሥነ አመክንዮ ቃላቶች ጣፋጭ ቃላቶች ምንጊዜም ሊገልጡት የማይችሉት የከበረና ፍጹም የሆነ ፍቅር ነው፡፡
 
ከ2,000 ዓመታት በፊት ማናችንም አልተወለድንም፡፡ የምድራዊው መቅደስ መጋረጃና የእግዚአብሄር መንግሥት ሰማያዊው መቅደስ የተከፈቱት ከ2,000 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በእናታችን ማህጸን ውስጥ እንኳን አልተጸነስንም፡፡ ጌታችን ግን ቀድሞውኑም ስለ እኛ ያውቅ ነበር፡፡ እንደምትወለዱና ሕይወታችሁንም በራሳችሁ የተለየ መንገድ መሰረት እንደምትኖሩ ያውቅ ነበር፡፡ ጌታ ወደደኝ፡፡ እኔን ብቻ ሳይሆን እናንተንና ሌላውን ሁሉ ሰው በተመሳሳይ መንገድ ወዶዋል፡፡ ጌታ አብዝቶ ስለወደደን ኢየሱስ በፈጸመልን የውሃ፣ የደምና የመንፈስ ወንጌል በማመን ሐጢያተኞች በሙሉ ሰማይ እንዲገቡ አስችሎዋቸዋል፡፡ ኢየሱስ ከሐጢያት መዳናችንን በውሃና በመንፈስ (በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ) አማካይነት ፈጸመው፡፡
የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች መቀደዱ በእርግጥም አስገራሚ ሁነት ነበር፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞቱ ብቻ ይህ የቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ እንዴት ሊቀደድ ቻለ? ይህ መጋረጃ እንደ ዘመኑ ምንጫፎች ነው፡፡ በጣም ወፍራምና ጠንካራ ሆኖ የተፈተለ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን በፓለስቲን ልከ እንደ ምንጣፎች የተፈተሉ የዚህ ዓይነት ወፍራም መጋረጃዎች ማግኘት እንችላለን፡፡ ጥብቅ ሆነው የተፈተሉ ስለሆኑ እነርሱን ለመቅደድ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚስቡ አራት ፈረሶች ያስፈልጋሉ ይባላል፡፡ ፈረስ ምን ያህል ጠንካራ ነው? ነገር ግን በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ እርሱን ለመቅደድ አራት ፈረሶች ሊስቡት የሚገባው መጋረጃ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ከላይ እስከ ታች ተቀደደ፡፡
 
መጋረጃው ለምን ተቀደደ? የተቀደደው ኢየሱስ በሰው ዘር ልቦች ውስጥ የነበሩትን ሐጢያቶች በሙሉ ስላስወገደ ነበር፡፡ የተቀደደው በመጠመቅና ለሞት በመሰቀል የጽድቅ ሥራዎቹን ሁሉ ስለፈጸመ ነበር፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ በመኮነን የዓለምን ሐጢያቶች ተቀብሎ ሰማይ ለመግባት ለሚያምኑ መንገዱን ከፈተላቸው፡፡ አሁን እናንተ ማድረግ የሚኖርባችሁ ማመን ብቻ ነው፡፡ ጌታ የሰማይን በር የከፈተው ሁላችሁም በማመን ብቻ ትገቡበት ዘንድ ነው፡፡
 
 
የኢየሱስ ጥምቀትና ደሙ ለደህንነታችን አስፈላጊ ናቸው? 
 
እጆች በኢየሱስ ራስ ላይ የተጫኑት ከብሉይ ኪዳን ዘመን በፊት በታቀደው የደህንነት ዘዴ መሰረት ነው፡፡ ይህም ለመስዋዕትነት ለሚቀርቡት ቁርባኖች ብቻ ተለይቶ የተጠበቀ ስርዓት ነበር፡፡ ለመስዋዕት የቀረበው ቁርባን በእጆች መጫን ሐጢያቶችን ሁሉ ተቀብሎ መሞቱ በእግዚአብሄር የተወሰነ የደህንነት ሕግ በመሆኑ ኢየሱስ እኛን ለዘላለም ለማዳን የመስዋዕት ቁርባናችን ሆኖ በመምጣት፣ የእጆች መጫን ገጽታ የሆነውን ጥምቀቱን በመቀበል ብቻ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ መደምሰስ ችሎዋል፡፡ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ለመግባት ሊቀ ካህኑም ቢሆን በእጆች መጫን ሐጢያቶችን የወሰደውን የመስዋዕት ቁርባን ደም ይዞ ለመግባቱ እርግጠኛ መሆን ያለበት ለዚህ ነው፡፡
 
ታዲያ ሊቀ ካህኑ ደም ይዞ ወደዚህ ስፍራ የሚገባው ለምንድነው? ምክንያቱም የሥጋ ሕይወት ያለው በደም ውስጥ በመሆኑ እግዚአብሄር በፊቱ ከመቅረቡ በፊት ለነፍሱ ስርየትን ያደርግ ዘንድ ደሙን ለሊቀ ካህኑ ሰጥቶታል፡፡ (ዘሌዋውያን 17፡11) ሰዎች ሁሉ ለሐጢያቶቻቸው መሞት ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅና (ሐጢያቶች ሁሉ በጥምቀቱ ወደ ኢየሱስ መሻገር ነበረባቸው፡፡) ሁሉንም በመሸከም ተሰቀለ፡፡ በዚህም ባፈሰሰው ደሙ በራሱ ሕይወት አዳነን፡፡ ይህም ሐጢያተኞች በእግዚአብሄር ፊት ሲቀርቡ በውሃውና በደሙ የሚያምነውን እምነት ለመያዛቸው እርግጠኞች መሆን እንደሚገባቸው ይነግረናል፡፡ ለሐጢያቶቻችን ከመኮነን ማምለጥ የምንችለው ከሙሉ ልባችን በኢየሱስ የጥምቀት ውሃና ባፈሰሰው ደም ስናምን ብቻ ነው፡፡
 
አሁን ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስላስወገደ ማንም የሐጢያት ስርየትን ለማግኘት የንስሐ ጸሎት ማድረግ ወይም መጾም ወይም መስዋዕት ማቅረብ አይኖርበትም፡፡ የንስሐ ጸሎቶችን አናቀርብም፡፡ ለሐጢያቶቻችንም አንቀጣም፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ አስቀድሞ የሐጢያት ስርየትንና የኩነኔን ቁርባን አቅርቦዋልና፡፡ እኛ ማድረግ የሚኖርብን በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የተገለጠውን ደህንነት በልባችን ማመን ብቻ ነው፡፡
 
ማንም ሰው ማድረግ የሚኖርበት በብሉይ ኪዳን የመገናኛውን ድንኳን ጥቅም ላይ በዋለው ሰማያዊ ማግ እንደተመለከተው ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀትና በቀዩ ማግ እንደተመለከተውም በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን ነው፡፡ ኢየሱስ መሰረታዊ በሆነው ማንነቱ ንጉሥ የመሆኑ እውነት ለመገናኛው ድንኳን በር ጥቅም ላይ በዋለው ሐምራዊ ማግ ተገልጦዋል፡፡ ስለዚህ እኛ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጠው የሐጢያት ስርየት በማመን ከሐጢያቶቻችን ከነጻን አሁን ማናችንም መንግሥተ ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡ ይህ ወንጌል ዋናው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ነው፡፡
 
 
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት መጋረጃው ለምን ተቀደደ? ይህንን እንደገና እናጢነው፡፡ 
 
መስቀል
በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተገለጠው ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ ለሚያምኑት የሐጢያት ስርየትንና መንግሥተ ሰማይ የመግባትን በረከቶች የሚያመጣ ወንጌል ነው፡፡ ኢየሱስ ተጠምቆ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ መጋረጃው የተቀደደው ለዚህ ነው፡፡ በኢየሱስ ለሚያምኑት በራሱ በእግዚአብሄር የተሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል እውነት ይህ ነው፡፡ ‹‹አሃ ኢየሱስ ደሙን አፍስሶ በመስቀል ላይ በመሞት የሞትንና የሐጢያትን ዋጋ የከፈለው በእኔ ፋንታ በዮሐንስ ስለተጠመቀ ነበር፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ እየሞተ ሳለ ‹ተፈጸመ› አለ፡፡ መንግሥተ ሰማይ የምንገባበትን መንገድ የከፈተልን በዚህች ቅጽበት ነበር፡፡››
 
ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣው ከመገንባት በስተቀር ሊያስወግዱት በማይችሉት የሐጢያቶች ግድግዳ ከእግዚአብሄር የተነጠሉትን ለማዳን ነበር፡፡ ይህ የራሱ የኢየሱስ ውዴታ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም የእግዚአብሄር አብ ትዕዛዝና እርሱ ለእኛ ያለው ፍቅርም ነበር፡፡ ኢየሱስ የአብን ፈቃድ በመታዘዘ የዓለምን ሐጢያቶች ወደ ሥጋው ያሻገረውን ጥምቀት ተቀበለ፡፡ ኢየሱስ ወደ መስቀል የሄደው የተሰቀለው ደሙን አፍስሶ የሞተውና በሦስት ቀናት ከሙታን በመነሳት የደህንነት ሥራዎቹን የፈጸመው በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በመውሰዱ ነው፡፡ በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ በተገለጡት አገልግሎቶች እነዚህ ናቸው፡፡ ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ያዳነውና የመስዋዕቱን ስርዓት ያጠናቀቀው የሐጢያት ስርየትም ይህ ነው፡፡
 
እስካሁን ድረስ ማንም ሊገባበት ያልቻለው የሰማይ በር አሁን የተከፈተው ኢየሱስ በአገልግሎቶቹ ደህንነትን ስለፈጸመ ነው፡፡ ይህም በር ከእንግዲህ በብሉይ ኪዳን ለመስዋዕት በሚቀርበው እንስሳ ላይ እጆችን በመጫንና በደሙ የደህንነት በር እንደማይከፈት ያሳያል፡፡ ነገር ግን አሁን ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በሚያምነው እምነት በማመን ተከፍቷል፡፡ የመጋረጃው መቀደድ የደህንነትን መጠናቀቅ ያሳያል፡፡ አሁን እግዚአብሄር በጌታ የተፈጸመውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል አውቆ ከልቡ የሚያምነውን ማንኛውንም ሰው ሰማይ እንዲገባ አስችሎታል፡፡ የመቅደሱ መጋረጃ መቀደድ የነበረበት ለዚህ ነው፡፡
 
በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ በሚያምነው እምነት መንግሥተ ሰማይ መግባት አለባችሁ፡፡ ምንም ሐጢያት የሌለበት ኢየሱስ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመምጣት ሐጢያቶችን ሁሉ ለመሸከም በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ (ማቴዎስ 3፡15) ከዚህም በላይ ጌታችን ለሐጢያቶቻችን ዋጋ ክፍያ ይሆን ዘንድ ሥጋውን አሳልፎ በመስጠት በእግዚአብሄር ፊት ስንቀርብ አብረን ልንወሰደው የሚገባን የዘላለም የስርየት መስዋዕት ሆነ፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ኢየሱስ ደህንነታችን ይሆን ዘንድ ከተጠመቀ በኋላ ባፈሰሰው በዚህ ደሙ ማመን አለብን፡፡ ኢየሱስ የሰውን ዘር ከሐጢያት ለማዳንና የራሱ የእግዚአብሄር ሕዥብ ለማድረግ የራሱን ሥጋ በመቅደድ የሰማይን በር ከፈተ፡፡
 
በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ በሚያምነው እምነት መንግሥተ ሰማይ መግባት አለባችሁ፡፡ ምንም ሐጢያት የሌለበት ኢየሱስ የሰው ሥጋ ወደዚህ ምድር በመምጣት ሐጢያቶችን ሁሉ ለመሸከም በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ (ማቴዎስ 3፡15) ከዚህም በላይ ጌታችን ለሐጢያቶቻችን ዋጋ ክፍያ ይሆን ዘንድ ሥጋውን አሳልፎ በመስጠት በእግዚአብሄር ፊት ስንቀርብ አብረን ልንወስደው የሚገባን የዘላለም የስርየት መስዋዕት ሆነ፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ኢየሱስ የሰውን ዘር ከሐጢያት ለማዳንና የራሱ የእግዚአብሄር ሕዝብ ለማድረግ የራሱን ሥጋ በመቅደድ የሰማይን በር ከፈተ፡፡
 
ኢየሱስ እኛን ወደ ማዳኑ ጉዳይ ስንመጣ እርሱ በመስቀል ላይ ደሙን ብቻ እንዳለፈሰሰ ማወቅ አለብን፡፡ በመስቀል ላይ ከመሞቱ ከሦስት ዓመታት በፊት በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን ወስዶዋል፡፡ ሰለዚህ ኢየሱስ በዮሐንስ የተጠመቀው ለመላው የሰው ዘር ነበር፡፡ ከዚያም በሮማውያን ወታደሮች ተሰቀለ፡፡ እናንተና እኔ ወደዚህ ዓለም ከመወለዳችነ በፊት እንኳን ኢየሱስ አስቀድሞ በጥምቀቱና ደሙን በማፍሰሱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ አንጽቷል፡፡
 
ኢየሱስ በዮሐንስ መጠመቁ ሐጢያቶቻችንን አስቀድሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ለመውሰድ በእርግጠኝነት የሚፈጽመው የደህንነት ዘዴ ነበር፡፡ ያፈሰሰው ደሙም ለእነዚያ ሐጢያቶች በሙሉ የተከፈለ ክፍያ ነበር፡፡ ኢየሱስ ራሱ አምላክ ስለሆነ የተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ መዳናችንን በእርግጠኝነት የሚያዋቅር ነበር፡፡ ጌታችን መላውን የሰው ዘር ለማዳን የከፈለው ፍጹም መስዋዕትነት ይህ ነበር፡፡ የውሃውና የመንፈሱ የወንጌል ቃል ከሐጢያቶቻችንንና ከኩነኔ ነጻ እንዳወጣን ታምናላችሁን?
 
 
በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ አሁን የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ተወግደዋል፡፡ 
 
ኢየሱስ በዮሐንስ የተጠመቀው የሰውን ዘር ሐጢያቶች ለማስወገድ ነበር፡፡ ይህንን የኢየሱስን ጥምቀት ከሕይወቱ አስወግደን የኢየሱስን የደህንነት አገልግሎቶች ብንመለከት ከዓለም ፍጥረት በፊት በኢየሱስ ክርስቶስ የታቀደው የሰው ዘር ደህንነት በሙሉ ወደ ውሸትነት ይለወጥ ነበር፡፡ ኢየሱስ ከዓለም ፍጥረት በፊትም ቢሆን የሰውን ዘር ሐጢያቶች ለመውሰድና ደሙን ለማፍሰስ ይጠመቅ ዘንድ ቀድሞውኑም ሲዘጋጅ ነበር፡፡
 
ኢየሱስ የሰው ዘር ሁሉ ወኪል በሆነው በአጥማቂው ዮሐንስ የተጠመቀውና ሐጢያቶችን ሁሉ የወሰደው ለዚህ ነው፡፡ (ማቴዎስ 11፡11-12፤ማቴዎስ 3፡15) በመጠመቅ የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች መውሰድ የደህንነት ዘዴ ነበር፡፡ ኢየሱስ የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በመቀበል አነጻቸው፡፡ እኛም ለሐጢያቶቻችን ከመሞት ፋንታ እርሱ በእኛ ፋንታ በይፋ ሞተ፡፡ እንዲህ በማድረጉም በዚህ የሚያምኑትን ከሐጢያቶቻቸውና ከኩነኔ ሁሉ አዳናቸው፡፡ በዚህ ዘዴ አማካይነት (በመጠመቅ ዘዴ) ኢየሱስ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በመቀበልና በመስቀል ላይም ደሙን በማፍሰስ የሐጢያትን ኩነኔ ሁሉ መሸከም ቻለ፡፡ ‹‹እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› (ማቴዎስ 3፡15) ኢየሱስ በዮርዳኖስ ተጠመቀ ማለት የእኛን የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በሙሉ ተቀበለ ማለት ነው፡፡
 
ወንድሞችና እህቶች ኢየሱስ ከ2,000 ዓመታት በፊት ወደዚህ ምድር እንደመጣ፣ 30 ዓመት ሲሆነው እንደተጠመቀና ለእናንተ ደሙን እንዳፈሰሰ በዓይኖቻችሁ ስላላያችሁ ብቻ ማመን አቅትቶዋችኋልን? ነገር ግን እግዚአብሄር አለመብቃቶቻችንን ሁሉ ስላወቀ ከዓለም ፍጥረት በፊት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሊያድነን አቀደ፡፡ በዚህ ዕቅድ መሰረትም ኢየሱስ ክርስቶስንና አጥማቂውን ዮሐንስን ወደዚህ ምድር በመላክ የሁላችንንም ደህንነት ፈጸመ፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ሁሉ እውነት እንድንገነዘብና እንድናውቅ ያስችለን ዘንድም የእርሱ ባሮች ቃሉን እንዲጽፉ አደረገ፡፡ እግዚአብሄር በተጻፈው ቃሉ አማካይነት ስለ ደህንነት ዕቅዱና አፈጻጸሙ ለመላው የሰው ዘር እያንዳንዱን ነገር ገለጠ፡፡ እርሱ አሁን በተጻፈው የእግዚአብሄር ቃል ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለመውሰድ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ የመጠመቁን እውነት ማንኛውም ሰው እንዲገነዘብ አስችሎታል፡፡
 
አሁን ሁላችንም ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀትና ለደህንነታችን በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን አለብን፡፡ በሥጋ ዓይናችን ባናየውም በልባችን ልናምነው ይገባናል፡፡ እውነተኛ እምነት ወደ እኛ የሚመጣው እምነታችን በቃሉ ላይ ሲመሰረት ነው፡፡ ጌታ ቶማስን እንዲህ አለው፡- ‹‹ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው፡፡›› (ዮሐንስ 20፡29) ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀትና ባፈሰሰው ደሙ እናንተንና እኔን አድኖናል፡፡ እግዚአብሄር በዚህ የሚያምነውን ማንኛውንም ሰው ሰማይ እንዲገባ አስችሎታል፡፡
 
ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ እግዚአብሄር የቤተ መቅደሱን መጋረጃ የቀደደው ለዚህ ነው፡፡ ኢየሱስ እኛን የሰው ዘሮች ከእግዚአብሄር የለየንን የሐጢያት ግድግዳ አፈረሰው፡፡ ማንኛውም ሰው በልቡ በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ያለ ምንም እንቅፋት ሰማይ እንዲገባ አስችሎታል፡፡ በልባችን በማመን ብቻ ሁላችንም በእርግጠኝነት ሰማይ እንገባ ዘንድ ይህንን እውነት ስለሰጠን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡
 
ኢየሱስ ሐጢያተኞችን ለማዳን ተራ ፍጥረት በሆነ ሥጋ ውስጥ ወደዚህ ዓለም የተወለደበት ይህ ሁነት ምንኛ ታላቅ ነው? በዓለም ላይ ካለው ፍጥረቱ ጋር ሲነጻጸር በእርግጥም አስደናቂ ሁነት ነው፡፡ ሁሉን የፈጠረው ፈጣሪ ጌታ ፍጥረቶችን መፍጠሩ የቁስ አካል ጉዳይ ብቻ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን ፈጣሪ ልክ እንደ ፍጥረት ሆኖ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ መውሰዱና መሰቀሉ ታላቅ የደህንነት ሁነት እንጂ ሌላ አንዳች ነገር ሊሆን አይችልም፡፡
 
ራሱ ፈጣሪ እንዴት ከፍጥረቶቹ አንዱ ሊሆን ቻለ? ነገር ግን ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ ይህን ያህል ራሱን ዝቅ በማድረግ የሰው ዘር ወኪል በሆነው በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ይህ ምንኛ አስገራሚ ሁነት ነው? ነገር ግን የነገሩ መጨረሻ ይህ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ለሞቱ እንኳን በመታዘዝ በመስቀል ላይ በርካታ አሰቃቂ መከራዎችን ለመቀበል፣ ደሙን ለማፍሰስና ለመሞት ራሱን ዝቅ አድርጓልና፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የእግዚአብሄር ፍቅር፣ የእርሱ ምህረትና የእርሱ ታላቅ ጸጋ እንጂ አንዳች ሌላ ነገር ሊሆኑ አይችሉም፡፡
 
የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በጌታ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ ለአንዴና ለመጨረሻ ፈጽመው ነጽተዋል፡፡ ኢየሱስ የመቅደሱን መጋረጃ በመቅደድ በሦስት ቀናት ውስጥ ከሙታን ተነስቷል፡፡ አሁን እርሱ በዚህ እውነት የሚያምኑትን ሁሉ በእውነቱ ሊገናኛቸው ይሻል፡፡ ሐጢያተኞችን ያዳኑት የጌታ ሥራዎች ይህንን አጸናፈ ዓለምና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ከፈጠረው የፍጥረት ሥራዎቹ እንኳን የሚበልጥና የሚልቅ ሁነት ነው፡፡ የኢየሱስ ውልደት፣ ጥምቀቱ፣ የመስቀል ላይ ሞቱ ትንሳኤው፣ ዕርገቱ፣ ዳግመኛ መመለሱና እኛን የራሱ ልጆች ማድረጉ የእግዚአብሄር ፍቅር ሥራዎች ናቸው፡፡
ጌታችን እናንተንና እኔን ከሐጢያቶቻችን አደኖናል፡፡ ጌታችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት እናንተንና እኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ከዓለም ሐጢያቶች ሁሉ አድኖናል፡፡ ስለዚህ በእምነት ጻድቃን ልንሆንና እግዚአብሄርን ልናመሰግን እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር የደህንነት በረከቱን በሙላት ለግሶናል፡፡ ታምናላችሁን?
 
ወንድሞችና እህቶች እናንተና እኔ ወደ ሲዖል የምንጣል ሰዎች ነበርን፡፡ በሐጢያቶቻችን የምንሞትና ሕይወታችንን በሐዘን የምንኖር ሰዎች ነበርን፡፡ ነገር ግን ጌታ ከዓለም ፍጥረት በፊት ባቀደው ደህንነቱ ከሐጢያት አዳነን፡፡ እኛ በሐጢያቶቻችን መካከል ቁጭ ብለን እየቆዘምን፣ እየተበሳጨንና ዕድላችንን እያማረርን ከመኖር በስተቀር ምርጫ ያልነበረን ሰዎች ነበርን፡፡ ነገር ግን ጌታ እንደ እኛ ያሉ ሰዎች መንግሥተ ሰማይ እንዲገቡ ለማስቻል ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነን፡፡ በዚህም ጌታችን የደህንነታችን ጌታ ሆነ፡፡
 
ኢየሱስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሰጥቶናል፡፡ የሐጢያት ስርየት ዋስትናም ሰጥቶናል፡፡ ኢየሱስ ራሱን የደህንነታችን ጌታ ሆነ፡፡ ኢየሱስ በእኛ ፋንታ የዓለምን ሐጢያቶች ወሰደ፡፡ በምትካችንም ሞተ፡፡ በዚህም ፍጹም የሆነ አዳኛችን ሆነ፡፡
 
 
ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀትና ባፈሰሰው ደሙ ታምናላችሁን?
 
ከሐጢያት መዳናችን ፍጻሜውን ያገኘው ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ በማመን ነው፡፡ ሐጢያተኞች ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው በማመን ለመዳን ከፈለጉ የእርሱን ጥምቀትና መስቀል በቅደም ተከተላቸው መረዳታቸውን እርግጠኞች መሆን አለባቸው፡፡ ፍጹም የሆነው ደህንነት የሚተገበረው በእነዚህ በሁለቱ አንድነት መሆኑን ማመን አለባቸው፡፡
 
ኢየሱስ እንደተጠመቀና በመስቀል ላይ እንደሞተ እያመናችሁ አይደለምን? ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀት ችላ እያላችሁና በእርሱ ለማመንም እምቢተኞች እየሆናችሁ አይደለምን? የእግዚአብሄር ጽድቅ የተፈጸመው ኢየሱስ የተቀበለው ጥምቀት የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በሙሉ የወሰደበት ሒደት በመሆኑና ክቡር ደሙን በማፍሰስ የሞተው ሞትም የሐጢያቶቻችን ኩነኔ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ እናንተና እኔ በኢየሱስ እናምናለን ስንል የእርሱን ጥምቀትና የመስቀል ላይ ደሙን እንደ አንድ ደህንነት ማመን አለብን፡፡
 
እግዚአብሄር የኢየሱስን ጥምቀትና ያፈሰሰውን ደሙን አስፈላጊነት በቃሉ ውስጥ ጽፎታል፡፡ ነገር ግን ይህ ሆኖ ሳለ ብዙ ሰዎች አሁንም ለመዳን የሚያስፈልጋቸው በመስቀሉ ደም ማመን ብቻ እንደሆነ ክርር ይላሉ፡፡ እናንተ ከእነርሱ አንዱ ከሆናችሁ እምነታችሁን የምር እንደገና ልታጤኑት፣ ልትመለሱና በእነዚህ በሁለቱ መሰረታዊ ነገሮች ልታምኑ ይገባችኋል፡፡ እንደዚህ ካላደረጋችሁና በመስቀሉ ደም ብቻ የምታምኑ ከሆናችሁ የተቀደሱትን የጌታን የሕይወት አገልግሎቶች በሙሉ ከንቱ ታደርጉዋችዋላችሁ፡፡ እምነታችሁ እንደዚህ ከሆነ ከዚህ የተሳሳተ እምነት ተመልሳችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገረውን እውነተኛ እምነት መያዝ አለባችሁ፡፡ ያለ እርሱ ጥምቀት ለእኛ በመስቀል ላይ መሞቱ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ ባይጠመቅ ኖሮ ሞቱ ከሐጢያቶቻችን ጋር አንዳች የሚያገናኘው ነገር አይኖረውም ነበር፡፡
 
ወንድሞችና እህቶች ስማችሁን ከዕዳ መዝገብ ላይ መሰረዝ ብትፈልጉ ገንዘብ አምጥታችሁ ለአበዳሪዎቻችሁ አትከፍሉምን? ባለ ዕዳዎች ከዕዳቸው መጠን ጋር የሚስማማ ገንዘብ መክፈል አለባቸው፡፡ ከዕዳው መዝገብ ስሞቻቸውን መሰረዝ የሚችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ ኢየሱስ የሐጢያቶቻችንን ዋጋ ለመክፈል በጥምቀቱ እነዚህን ሐጢያቶችና በደሎቻችንን ተቀብሎ ደሙን በማፈሰስ ደመሰሳቸው፡፡
 
ጌታ በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት በተጨባጭ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወሰደ፡፡ ደሙን በማፍሰስ ለሐጢያቶቻችን ሁሉ የተኮነነው ለዚህ ነው፡፡ አንድ ሰው ዕዳውን ለመክፈል ከዕዳው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ መክፈል እንዳለበት አእምሮው ይነግረዋል፡፡ ባለዕዳዎች ገንዘብ ሳያመጡ በአፍ ብቻ ዕዳዎቻቸውን እንደከፈሉ በመናገር ስሞቻቸው ከዕዳው መዝገብ ላይ እንዲፋቁ ቢጠየቁ በእርግጥ ስሞቻቸው ይፋቃሉን? ስሞቻቸው እንደተፋቁ ምንም ያህል አጥብቀው ቢያመኑም እውነቱ ግን ስሞቻቸው አሁንም በዕዳው መዝገብ ላይ ያሉ መሆናቸው ነው፡፡
 
ባለዕዳዎች ከዕዳዎቻቸው ነጻ መውጣት የሚችሉት ዕዳዎቹ በትክክል ሲከፍሉ ብቻ እንደሆነ ሁሉ እኛም ሐጢያተኞች የሐጢያት ስርየትን ለማግኘት በልባችን ውስጥ ሐጢያቶቻችንን በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት ወደ ኢየሱስ መሻገራቸውን የሚያምነው እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሐጢያቶቻችንን በኢየሱስ ራስ ላይ ያሻገረውን ጥምቀት የሰጠነው እኛ ራሳችን አይደለንም፡፡
 
ነገር ግን አጥማቂው ዮሐንስ በተባለው ሸምጋይነት ሐጢያቶቻችንን ወደ ኢየሱስ ማሻገር ችለናል፡፡ በአጥማቂው ዮሐንስ የተጠመቀው ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች ተሸክሞ ወደ መስቀል ሄደ፡፡ ደሙንም አፍስሶ ሞተ፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ወስዶ እኛን ባዳነበት የደህንነት ምሳሌና ቅቡልነት በሆነው ጥምቀቱ በማመን የደህንነታችንን ማረጋገጫ መቀበል እንችላለን፡፡ ጌታችን በልባችን ውስጥ ያደረገውን በማመን አሁን የሐጢያት ስርየትን መቀበል እንችላለን፡፡ ለምን? ጌታችን በጥምቀቱና በደሙ አዲስ ሕይወት ሰጥቶናልና፡፡
 
ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ ለሁለት ተቀደደ፡፡ ምድርም ተናወጠች፡፡ ዓለቶችም ተፈረካከሱ፡፡ መቃብሮችም ተከፈቱ፡፡ አንቀላፍተው የነበሩ የቅዱሳን ሥጋዎች ብዙዎች ተነሱ፡፡ በእነዚህ ሁነቶች አማካይነት እግዚአብሄር ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ እንደሚደመስስና በቃሉ የሚያምኑትን እንደሚያስነሳ አሳይቷል፡፡ ኢየሱስ በእርግጥም ከሙታን እንደተነሳና በኢየሱስ ያመኑትም በእርግጥ ትንሳኤን እንደሚያገኙም አሳይቷል፡፡ ኢየሱስ ከሐጢያት ያዳነን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ሙታን ለነበርነውም አዲስ ሕይወትን ሰጥቶናል፡፡ ኢየሱስ የተጠመቀው፣ በመስቀል ላይ የሞተውና ዳግመኛም ሕያው የሆነው አዲስ ሕይወትን ሊሰጠን ነው፡፡ እግዚአብሄር ወደተቀደሰችው ከተማው ገብተን እዚያም ለዘላለም እንድንኖር አስችሎናል፡፡ እኔ በእምነቴ ልባዊ ምስጋናዬን ለእርሱ አቀርባለሁ፡፡
 
ስርየትን የተቀበሉ ሰዎች የሚኖሩበት ስፍራ ሰማይ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ የሐጢያት ስርየትን ያገኙ ሰማይ ገብተው በዚያ እንደሚኖሩ እመኑ፡፡ ሰማይ የሐጢያት ስርየትን የተቀበሉ ሰዎች የሚኖሩበት ስፍራ ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመንና ዳግመኛ መወለድ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ሳይሆኑ ሁለቱም ተመሳሳይ ናቸው፡፡
 
በውሃውና በመንፈሱ የወንጌል ቃል የሚያምን ማንኛውም ሰው ባመነበት በዚያች ቅጽበት ዳግመኛ ይወለዳል፡፡ ሐጢያተኞች የሐጢያት ስርየትን ሲቀበሉ የእግዚአብሄር ልጆች ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሄርም ለልጆቹ ሰማይን ስጦታ አድርጎ ሰጥቶዋቸዋል፡፡ በሥጋችን የራሳችን የሆነ ሥራ ባይኖረንም አንድ ነገርን እርሱም በአዳኝ የሚያምነውን እምነታችን በመመልከት ብቻ ጌታችን የሐጢያት ይቅርታንና ሰማይን ስጦታዎቹ አድርጎ ሰጥቶናል፡፡
 
ጌታችን ወደዚህ ምድር መምጣቱ፣ መጠመቁና ደሙን ማፍሰሱ በሙሉ እውነት ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ አስቀድሞ የዓለምን ሐጢያቶች በጥምቀቱ አማካይነት ወስዶዋል፡፡ ኢየሱስ አስቀድሞ በዮሐንስ ተጠምቆ ከመሰቀሉ በፊት የዓለምን ሐጢያቶች ተሸክሞ ነበር፡፡ ኢየሱስ የሐጢያት ደመወዝ ሞት መሆኑን የሚያውጀውን የሕግ ቅጣት የተሸከመው በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰዱ ነበር፡፡ ኢየሱስ የሰውን ዘር ከሐጢያት ለማዳን በጥምቀቱ የወሰዳቸውን የዓለም ሒያቶች በመሸከም በመስቀል ላይ መሞት ነበረበት፡፡
 
ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ እርሱን የቸነከሩት ሰዎች አይሁዶች አልነበሩም፡፡ የሮማውያን ወታደሮች ነበሩ፡፡ ኢየሱስ የተሰቀለው በአሕዛብ ወታደሮች ነበር፡፡ ኢየሱስ ለሐጢያቶቻችን ሲል ደሙን ሁሉ ካፈሰሰ በኋላ ‹‹ተፈጸመ!›› ብሎ በመጮህ መንፈሱን ሰጠ፡፡ በዚያች ቅጽበት የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ድረስ ለሁለት ተቀደደ፡፡ ከዚህም በላይ ምድር እንደተናወጠች፣ ዓለቶች እንደተሰነጠቁ፣ መቃብሮች እንደተከፈቱና አንቀላፍተው ከነበሩ የቅዱሳን ሥጋዎች ብዙዎቹ እንደተነሱ ይነግረናል፡፡ (ማቴዎስ 27፡51-52) ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የመቶ አለቃውና የሮማውያን ወታደሮች የሆነውን ካዩ በኋላ ‹‹በእውነት ይህ የእግዚአብሄር ልጅ ነበር›› (ማቴዎስ 27፡54) በማለት መሰከሩ፡፡ እግዚአብሄር የእነዚህ አሕዛብ ወታደሮች አንደበት ‹‹ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሄር ልጅ›› እንደነበር ይመሰክር ዘንድ አደረገ፡፡
 
እውነተኛውን ወንጌል በመላው ዓለም የምንመሰክረው እኛ እንጂ ሌሎች አይደሉም፡፡ ይህንን የሚያደርጉት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ አማኞች ናቸው፡፡ ሰው ሁሉ የሚለወጠው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ነው፡፡ ሰዎች የሐጢያት ስርየትን ከኢየሱስ ሲቀበሉ ያለ አንዳች መፍጨርጨር በመንፈሳዊ ሁኔታ ይለወጣሉ፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ ለማደር ይመጣልና፡፡ ዳግመኛ የተወለዱ ጻድቃን ልብም በየቀኑ ይታደሳል፡፡ ምክንያቱም እነርሱ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ በተደጋጋሚ የውሃውንና የመንፈሱን ቃለ ወንጌል ያዳምጣሉና፡፡ ቃሉን ለማድመጥና ኢየሱስን ለማመስገን ይመጣሉ፡፡ ሲያመሰግኑ ሳሉም የዜማዎቹ ቃላቶች በልባቸው ውስጥ ስለሚታተም ልባቸው በየቀኑ ይታደሳል፡፡ ጻድቃን ልባቸው በየጊዜው ይለወጣል፡፡ በውስጣቸውም እንዲህ ያሉ ተጨባጭ ለውጦች ይታወቁዋቸዋል፡፡
 
ጻድቃን የሆንነውን የእኛን የተለወጠ ማንነት በመመልከት አላማኒዎች ‹‹በእርግጥ ድነዋል፤ እነርሱ እውነተኛ ከርስቲያኖች ናቸው›› ብለው ይመሰክራሉ፡፡ የሐጢያት ስርየታችንም በእኛ ብቻ የተረጋገጠ የደህንነት ዓይነት አይደለም፡፡ የሮም መቶ አለቃና ወታደሮቹም እንደዚሁ ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ በተሰቀለ ጊዜ ሐጢያተኞችን ከዓለም ሐጢያቶች እንዳዳነ ይህንን እውነት መስክረዋል፡፡ እግዚአብሄርም ራሱ ኢየሱስ በውሃና በደም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነን የመሆኑን እውነት ለሚያምኑ መስክሮዋል፡፡
 
 
ዲያብሎስን እንኳን እንዲማረክ ያደረገው የውሃና የመንፈስ ወንጌል፡፡
 
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ዲያብሎስን እንኳን እንዲማረከ ያደረገ ደህንነት ነው፡፡ ኢየሱስ ሲሞት ‹‹ተፈጸመ!›› ባለ ጊዜ ዲያብሎስ ‹‹አሃ! ይህ አሳፋሪ ነው፡፡ ነገር ግን ስለዚህ ጉዳይ ላደርገው የምችለው አንዳች ነገር የለም! ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ዓለም ላይ ሐጢያት የለም፡፡ አሁን ሁለም ሰው ያለ አንዳች መድልዎ ፈጽሞ ሐጢያት አልባ ነው! ይህ ልቤን እየበላው ነው፡፡ ነገር ግን ስለዚህ ጉዳይ ላደርገው የምችለው አንዳች ነገር የለም!›› ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡
 
በሌላ አነጋገር ዲያብሎስ ራሱ ኢየሱስ የፈጸመውን ይህንን ደህንነት ከመቀበል ውጪ ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡ ነገር ግን አሁንም የእምነት ሕይወታቸውን በመኖር የሐጢያት ስርየትን የተቀበሉትን ሊያደናቅፍ ይሞክራል፡፡ በኢየሱስ በተፈጸመው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሚያምኑ የእግዚአብሄር ልጆች ስለሆኑ ለእርሱ ለመኖር ይጥራሉ፡፡ ለዲያብሎስ ግን ይህ ማለት በሐጢያት የታሰሩ የእርሱ አገልጋዮች ጥቂት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄር ባሮች ይህንን እውነት በመላው ዓለም እንዳያሰራጩ ለመከላከል ይሞክራል፡፡
 
የሐጢያት ስርየትን የተቀበሉ ሰዎች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማሰራጨታቸውን ከቀጠሉ ከሐጢያት ነጻ የሚወጡ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ሰይጣን ጥርሱን በሰዎች ድካሞች ላይ በመትከል አንድም ሰው ቢሆን እንኳን ኢየሱስን ከመከተል እንዲታገድ እንቅፋት በመሆን የተከለውን ጥርሱን የማይነቅለው ለዚህ ነው፡፡
 
ዲያብሎስ ‹‹ኢየሱስን ግደሉት!›› ብሎ በመንገር የሰዎችን ልብ ካነሳሳ በኋላ ለሞት እንዲሰቅሉት አደረጋቸው፡፡ ነገር ግን ዲያብሎስ በዚህ ሁኔታ ሁሉም ነገር እንደተጠናቀቀ ባሰበ ጊዜ የተሰቀለውና እየሞተ የነበረው ኢየሱስ በታላቅ ድምጽ ‹‹ተፈጸመ!›› ብሎ ጮኸ፡፡ በዚህም ሰይጣን ተደናገጠ፡፡ ኢየሱስ ከመከልከል ርቆ በዮርዳኖስ ወንዝ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ወስዶ በመስቀል ላይ በመሞት የሰውን ዘር ከሐጢያትና ከኩነኔ ያዳነውን ደህንነት በጽድቅ ፈጸመ፡፡ ዲያብሎስ ይህንን የእግዚአብሄር ጥበብ አላወቀም፡፡ ኢየሱስን በመስቀል ላይ ቢገድለው ሁሉም ነገር እንደሚያበቃ አሰበ፡፡ ነገሩ ግን እንደዚያ አልነበረም፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች ከወሰደ በኋላ ሥጋውን በመስቀል ላይ በመስጠትና በመሞት የሐጢያተኞችን የሐጢያት ስርየት ፈጸመ፡፡
 
ኢየሱስ በሥጋው ሞት አስቀድሞ የሐጢያትን ዋጋ ከፍሎዋል፡፡ ስለዚህ ሐጢያት ከእንግዲህ በሰዎች ውስጥ አይገኝም፡፡ ለምን? ምክንያቱም የሐጢያት ደመወዝ ሞት መሆኑን በሚናገረው ሕግ መሰረት ኢየሱስ በሐጢያተኞች ፋንታ አስቀድሞ ሞቷል፡፡ ኢየሱስ በሐጢያተኞች ፋንታ በይፋ መሞት የቻለው የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በሙሉ በዮርዳኖስ ወንዝ ስለወሰደ ነው፡፡
 
‹‹ተፈጸመ!›› ኢየሱስ የመጨረሻውን እስትንፋሱን በሰጠ ጊዜ በመስቀል ላይ የጮኸው ይህንን ነበር፡፡ ኢየሱስ ስለሞተ ዲያብሎስ ከእንግዲህ ‹‹ሐጢያት አለባችሁ፡፡ የለባችሁምን?›› ሊለን አይችልም፡፡ ከኢየሱስ ወልደት፣ ከጥምቀቱ፣ በመስቀል ላይ ከሆነው ደሙና ከትንሳኤው የተነሳ ዲያብሎስ በኢየሱስ ፊት ክፉኛ ተሸንፏል፡፡ ዲያብሎስ ሁልጊዜ ሐጢያት እንድንሰራ በማድረግ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት ቢበጥስም በመጨረሻ ግን የእግዚአብሄር ልጅ በሆነው የኢየሱስ ጥበብ ሐጢያታችንንና ኩነኔን በማስወገዱ ምክንያት ሰይጣን ፈጸሞ ከመሸነፍ በስተቀር ማምለጥ አልቻለም፡፡
 
በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ ስታምኑ አሁንም ሐጢያት አለባችሁን? የለባችሁም! ሐጢያት የለብንም ብሎ መናገር በሥጋ እሳቤ ሊነገር የሚችል አንዳች ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ጥምቀትና ደም በማመን አሁን በድፍረት ሐጢያት አልባ መሆናችንን መናገር እንችላለን፡፡ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን የመውሰዱን፣ በእኛ ፋንታ በመስቀል ላይ የመሞቱንና በዚህም ያዳነን የመሆኑን እውነት ታምናላችሁን? በዚህ እውነት በማመናችን አሁን ሐጢያት የለብንም ማለት እንችላለን፡፡ በእርግጥም በልባችን ውስጥ ፈጽሞ ሐጢያት የለም፡፡ የሳንቲምን ያህል ያነሰ ሐጢያት እንኳን የለብንም፡፡ በውስጣችን በእግዚአብሄር ፊት አመስጋኝ ልብ የሚበቅለውና በእምነት ምስጋናችንን የምናቀርበው ለዚህ ነው፡፡
 
‹‹አቤቱ እምነቴ ትልቅ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ኢምንት በሆነው እምነት እንኳን አሁንም ለአንተ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ እኔ የአንተን ትልቅ ፍቅር እንኳን መሸከም ያልቻልሁ ሰው ነበርሁ፡፡ ነገር ግን አሁንም አንተ ወደ ልቤ ገብተሃል፡፡ ስለዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በሚያምነው እምነቴ አሁን ፍቅርህን በልቤ ይዣለሁ፡፡ ልቤ በየቀኑ አንተን ያመሰግናል፡፡ ምክንያቱም ጌታ በልቤ ውስጥ ይኖራል፡፡ ከእኔም ጋር ነው፡፡ ይህንን ልብ ስሰጥ ምስጋናዬን ሁሉ ለአንተ አቀርባለሁ፡፡›› ከዚህ የተነሳ ጌታችን አመስጋኝ ልብ ሰጠቶናል፡፡ ጌታችን በየቀኑ ይባርከናል፡፡
 
ስለዚህ እኔ ብቻ ሳልሆን የእርሱን ፍጹም የደህንነት እውነት ሰምቶ ያመነ እያንዳንዱ ሰው ሁሉ በልቡ ውስጥ በጭራሽ ሐጢያት የለበትም፡፡ እኛ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እውነት ስለምናምን የደህንነትንና የእግዚአብሄር ልጆች የመሆንን በረከት ተቀብለናል፡፡ እግዚአብሄርም ከልቡ ሁሉም በኢየሱስ ውልደት፣ በጥምቀቱና በደሙ አምኖ ወደ እርሱ በመመለስ በዚህ እውነት ሳያምን ከሐጢያቶቹ ሁሉ የሚድንበት መንገድ እንደሌለ እንዲገነዘብ ይፈልጋል፡፡
 
የሐዋርያት ሥራ 4፡12 እንዲህ ይላል፡- ‹‹መዳንም በሌላ በማንም የለምና፤ እንድንበት ዘንድ ለሰዎች የተሰጠን ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለምና፡፡›› እኛ ኢየሱስ አዳኛችን መሆኑን እናምናለን፡፡ በዚህ የሚያምኑ ሰዎች አመስጋኝ ልብ ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ እኛ ጌታን የሚያመሰግን ልብ አለን፡፡ ጌታችን ደህንነትን ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሄር እነዚህን የተትረፈረፉ በረከቶች ሁሉ ስለሰጠን እርሱን ከማክበር በቀር ሌላ የምናደርገው ነገር የለም፡፡
 
እምነታችን እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ትንሽ ብትሆንም ኢየሱስ በልባችን ውስጥ ለእኛ ባደረገው ነገር የምናምን ከሆነ ሁላችንም መዳን እንችላለን፡፡ እኛ ከማመን፣ እግዚአብሄር በነጻ የሰጠንን ይህንን ደህንነት ከማወቅና በእርሱም ከማመን በቀር ለደህንነታችን ልናደርገው የምንችለው አንዳች ሌላ ነገር እንደሌለ ሁላችሁም ታውቁ ዘንድ እማጸናችኋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ብቻውን በግሉ ሐጢያቶቻችንን የደመሰሰውና ለምናምነውም ደህንነቱን የሰጠን የሐጢያት ስርየት በግል ጥረቶቻችን ሊደረስበት ስለማይችል ነው፡፡ አሁን እኛ እናደርገው ዘንድ የቀረልን ነገር ቢኖር ይህንን የሐጢያት ስርየት በእምነት መቀበል ብቻ ነው፡፡
 
በኮርያ ‹‹ነጻ ስጦታዎችን አብዝተህ የምትሻ ከሆነ ራሰ በራ ትሆናለህ›› የሚል አባባል አለ፡፡ ይህ በእንግሊዝኛ አባባል ‹‹ነጻ ምሳ የሚባል ነገር የለም›› ከሚለው ጋር ይስማማል፡፡ ይህ በእርግጥም እውነት ነው፡፡ በሕይወት ውስጥ በነጻ የሚሰጠን አንዳች ነገር የለም፡፡ በምላሹ አንዳች ነገር ሳይሰጡ ስጦታዎችን ለመቀበል የሚጓጉ ሰዎችን ለመውቀስ ፈጣኖች ነን፡፡ ነገር ግን ድኖ ወደ ሰማይ መሄድ የሚገኘው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን ነው፡፡ ይህም ነጻ ስጦታ ነው፡፡ በጣም ብዙ ነጻ ስጦታዎችን ከመቀበል የተነሳ ራሰ በራ መሆን በሥጋ የሚያሳፍር ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ስጦታ በመቀበል መንፈሳዊ ራሰ በራ መሆን በእግዚአብሄር ፊት በረከት ነው፡፡ ሁላችሁም እግዚአብሄር ሐጢያት አልባ ልባችንን ሲመለከት እንደሚደሰትና ይህንንም አይቶ በክንዶቹ እንደሚያቅፈን ትረዱ ዘንድ እጸልያለሁ፡፡
 
እኛ የእግዚአብሄርን ነጻ ጸጋ እንወደዋለን፡፡ ለዚህም ጌታን እናመሰግነዋለን፡፡ ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ በውሃ ተጠመቀ፡፡ በመስቀል ላይም ደሙን አፈሰሰ፡፡ በዚህም የሰማይን በር ከፈተ፡፡ የቅድስተ ቅዱሳኑን መጋረጃም ከላይ ወደ ታች በመቅደድ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ የተወለደ ማንኛውም ሰው መንግሥተ ሰማይ እንዲገባ አስችሎታል፡፡ እናንተም ደግሞ በልባችሁ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ሰማይ መግባት አለባችሁ፡፡
ጌታ ስለተጠመቀ፣ ደሙን ስላፈሰሰ ከሙታን ስለተነሳና በዚህም የሐጢያት ስርየትን በር በጸጋው ስለከፈተልን አመሰግነዋለሁ፡፡