Search

የመገናኛው ድንኳን ጥናት፤

ቅድስተ ቅዱሳን

ተዛማጅ ስብከቶች

· እነዚያ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችሉት፡፡ ‹‹ዘጸዓት 26፡31-33››

እነዚያ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችሉት፡፡
‹‹ ዘጸዓት 26፡31-33 ››
‹‹መጋረጃውንም ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊም፣ ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም አድርግ፡፡ ብልህ ሰራተኛ እንደሚሰራ ኪሩቤል በእርሱ ላይ ይሁኑ፡፡ በወርቅ በተለበጡት ከግራር እንጨትም በተሰሩት በአራቱ ምሰሶች ላይ ስቀለው፡፡ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ አራቱም እግሮቻቸው ከብር የተሠሩ ይሁኑ፡፡ መጋረጃውንም ከመያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለሁ፡፡ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክርን ታቦት አግባው፡፡ መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁን፡፡››
 
 
የመገናኛው ድንኳን ቁሳቁሶች፡፡ 
 
የመገናኛው ድንኳን በአራት ዓይነት መደረቢያዎች የተሸነፈ ትንሽዬ ተጣጣፊ ቤት ነበር፡፡ የተሰራውም ከተለያዩ ቁሳ ቁሶች ነበር፡፡ ለምሳሌ ግድግዳዎቹ ከ48 የግራር እንጨት ሳንቃዎች የተሰሩ ነበሩ፡፡ የእያንዳንዱ ሳንቃ ቁመት 15 ጫማ (10 ኪዩቢት) ሲሆን ወርዱ 2.2 ጫማ (1.5 ኪዩቢት) ነበር፡፡ ሳንቃዎቹ በሙሉ በወርቅ የተለበጡ ነበሩ፡፡
 
የመገናኛው ድንኳን መደረቢያዎች ከሚከተሉት ቁሳ ቁሶች የተሰሩ ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው መደረቢያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ ከተፈተሉ መጋረጃዎች የተሰራ ነበር፡፡ ሁለተኛው መደረቢያ ከፍየሎች ጠጉር የተሰራ ነበር፡፡ ሦስተኛው መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት የተሰራ ነበር፡፡ አራተኛው መደረቢያ ከአቆስጣ ቁርበት የተሰራ ነበር፡፡
 
ቀደም ብለን እንደመረመርነው የመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በሮች በሙሉ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተፈተሉ ነበሩ፡፡ 
ለቅድስተ ቅዱሳኑ የመጋረጃ በር ጥቅም ላይ የዋሉት አራቱ ማጎች ሰዎችን ከሐጢያት ያዳኑትን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራዎች ይገለጣሉ፡፡ እነዚህ አራቱ ቀለማቶች ኢየሱስ ክርስቶስ የሐጢያት ስርየትን ስጦታ የሚሰጠን የመሆኑን የእውነት ብርሃን ስለሚገልጡ ምዕመናን ፈጽመው አመስጋኞችና አወዳሾች ሊሆኑበት የሚገባ አንዳች ነገር ናቸው፡፡
 
 
የቅድስቱና የቅድስተ ቅዱሳኑ በሮች የተሰሩባቸው ቁሳ ቁሶች፡፡ 
 
ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ፈትል ከጥሩ በፍታ የተሸመኑ ጨርቆች
የቅድስቱና የቅድስተ ቅዱሳኑ በሮች ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ ተጠልፈው የተሰሩ ነበሩ፡፡ የመገናኛው ድንኳን በሮች በሙሉ የተሰሩት ከእነዚህ ማጎች ነበር፡፡ አንድ ሰው ወደ ቅድስቱ የሚወስደውን የመገናኛውን ድንኳን በር ካለፈ በኋላ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ በር ይደርሳል፡፡ የቅድስተ ቅዱሳኑ በር ጌታ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጡት በአራቱ አገልግሎቶቹ ሐጢያቶቻችንን እንዳስወገደ ያሳየናል፡፡
 
ለቅድስቱና ለቅድስተ ቅዱሳኑ ጥቅም ላይ የዋሉት ሰማያዊው፣ ሐምራዊው፣ ቀዩ ማግና ጥሩው በፍታ መሲሁ ወደዚህ ምድር መጥቶ መጠመቁን፣ ደሙን ማፍሰሱንና በዚህም የደህንነትን ሥራዎች መፈጸሙን የሚገልጡ ጥላ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ሰማያዊው ማግ ኢየሱስ የተቀበለውን ጥምቀት የሚያሳይ ጥላ ነው፡፡ ቀዩ ማግም ለተሸከመው የዓለም ሐጢያቶች የሚያቀርበውን መስዋዕት የሚያሳይ ጥላ ነው፡፡ ጌታችን ሐጢያቶቻችንን ለማስወገድ ተጠምቆ የሐጢያትን ኩነኔ ተሸከመ፡፡ የቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ በር የሚያመላክተው ይህንን ነው፡፡
 
 
የመገናኛው ድንኳን ወለል፡፡ 
 
የመገናኛው ድንኳን የተሰራው በአሸዋማ መሬት ላይ ነበር፡፡ እዚህ ላይ መሬቱ የሚያመለክተው የሰዎችን ልብ ነው፡፡ የመገናኛው ድንኳን ወለል ከአሸዋ ከአፈር መሰራቱ ኢየሱስ የልባችንን ሐጢያቶች ለመደምሰስ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር እንደመጣ ይነግረናል፡፡ ኢየሱስ በሰው ዘር ድካሞች ሁሉ ውስጥ ስላለፈ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ክቡር ደሙ ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ አስወግዶዋል፡፡ ጌታችን የእውነትን ብሩህ ብርሃን በዚህ ዓለም ላይ ለማብራትና የሰውን ዘር መሰረታዊ ችግር ለማስወገድ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ ኢየሱስ አጽናፈ ዓለማትንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረ አምላክ ነው፡፡ እርሱ የሰውን ዘር ከእርግማኖቻቸውና ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ለማዳን ወደዚህ ምድር የመጣ የደህንነት ብርሃን ነው፡፡
 
 
የቅድስተ ቅዱሳኑ ምሰሰዎች፡፡ 
 
የቅድስተ ቅዱሳኑ ምሰሶዎች የተሰሩት ከአራት የግራር እንጨት አምዶች ነበር፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 4 ቁጥር መከራን ያመለክታል፡፡ የቅድስተ ቅዱሳኑ ምሰሶዎች ሰዎች በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጠው የሚያበራ የደህንነት ብርሃን እስካላመኑ ድረስ መዳን እንደማይችሉ ያሳያል፡፡ በሌላ አነጋገር በራሱ በእግዚአብሄር በመከራው በተፈጸመው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ብሩህ የሆነውን የደህንነት ብርሃን መረዳት እንደምንችል ይገልጣሉ፡፡
 
ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባትና እግዚአብሄር ባዘጋጀው የደህንነት ወንጌል በሚያበራው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማመን አለባቸው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ባዘጋጀው ወንጌል ሳያምኑ ወደ እግዚአብሄር የሚቀርቡ የእርሱ ብርቱ ቁጣ ይገጥማቸዋል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት የሚቀርቡ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጠው ብሩህ እውነት የሚያምን እምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሁላችንም በሚያበራው የእውነት ብርሃን አማካይነት እግዚአብሄር ወደሚኖርበት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት አለብን፡፡
 
በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተገለጠው የሐጢያት ስርየት ወንጌል በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ ውስጥ የተገለጠ የደህንነት እውነት ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተገለጠው የሐጢያት ስርየት ወንጌል ኢየሱስ በተቀበለው ጥምቀት፣ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙና በትንሳኤው ተፈጽሞዋል፡፡ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የምንችለው በዚህ እጅግ ቅዱስ ወንጌል የሚያምን እምነት ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ 
 
 

በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጠው ደህንነታችን ማመን አለብን፡፡ 

 
ዕብራውያን 11፡6 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ወደ እግዚአብሄር የሚደርስ እግዚአብሄር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና፡፡›› እግዚአብሄር ለዘላለም ይኖራል፡፡ እርሱ የዘላለምን ሕይወት ይሰጠን ዘንድ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመጣው በተጠመቀው፣ በተሰቀለው፣ በሞተው፣ ዳግመኛም ከሙታን በተነሳውና በዚህም አዳኛችን በሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለን እምነታችን አማካይነት የሐጢያቶቻችንን ስርየት እንድንቀበል ባርኮናል፡፡ የአሮጌው ማንነታችንን ሐጢያቶች በሙሉ ለሐጢያቶቻችን በይፋ ፍርድ ተቀብሎ በማስወገድና ለነፍሳቶችም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምን እምነት በመስጠት ጌታ ምሉዕ በሆነ የፍጽምና ቅድስና አሸብርቆናል፡፡
 
ጌታችን እኛን አዲስ ሕይወት በማልበስ በእግዚአብሄር ፊት ቀርበን ወደ እርሱ እንድንጸልይ አስችሎናል፡፡ ከዚህም በላይ በእግዚአብሄር ሕልውና ፊት እንድንቆምና አባታችን ብለን እንድንጠራው የሚያስችለንን ጸጋም እንደዚሁ ሰጥቶናል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እርሱ በሰጠን የእግዚአብሄር ስጦታዎች የተገኙ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ደህንነት በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ እውነት አማካይነት ለእኛ በመስጠት እንድንድንና በእርሱ ፊት ለመቆም የሚያስችለን እምነት እንዲኖረን አድርጎናል፡፡
 
እናንተና እኔ ነገ የምንሞት ብንሆን ሁላችንም ሰማይ እንደምንገባ እርግጠኞች አይደለንምን? እዚህ ላይ ለቅጽበት ስለ ወደፊት ዕጣ ፈንታችን እናስብ፡፡ ሰዎች ሲሞቱ ሁሉም በእግዚአብሄር የፍርድ ዙፋን ፊት ይቆማሉ፡፡ ይህ ማለት በዚህ ምድር ላይ የሰራናቸወን ሐጢያቶች ችግር በሙሉ መፍታት አለብን ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ጉዳይ የምንፈታው እንዴት ነው? ኢየሱስ አዳኛችን መሆኑን የምናምነው በዕውር ድንብር ብቻ ከሆነ ይህ ማለት የምናምነው ተራ በሆነ ሐይማኖት ነው ማለት አይደለምን?
 
በሕይወቴ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳላውቅ የሐጢያቶቼን ችግር በመስቀሉ ደም በዕውር ድንብር በማመን ብቻ ለመፍታት የሞከርሁበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ኢየሱስ የተሰቀለውና የሞተው እንደ እኔ ላሉት ሰዎች እንደሆነና የሐጢያት ችግሮችንም በሙሉ እንደፈታ በግትርነት አምን ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ እምነት በየቀኑ የምሰራቸውን ሐጢያቶች ችግር መፍታት አልቻልሁም፡፡ ከዚህ ይልቅ መንፈሴ ሙሉ በሙሉ ዳግመኛ የተወለደው በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀዩ ማግ በተገለጠው ደህንነት በማመኔ ነው፡፡
 
በዕውር ድንብር ኢየሱስን አዳኝ አድርገን ባመንን ጊዜ በእርግጥ ሐጢያቶቻችን በሙሉ ተደምስሰዋልን? ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ለመቅረብ የሚያስችለን እምነት እርሱን በዕውር ድንብር በማመን ውስጥ የሚገኝ ሳይሆን እውነቱን በማወቅና በማመን ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ምንም ያህል ኢየሱስን አዳኛችን አድርገን በትጋት ብናምንም ሐጢያተኞችን በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ ያዳነውን የወንጌል እውነት ካላወቅን ቅዱሱን አምላክ መገናኘት አንችልም፡፡ ታዲያ ድነን በእግዚአብሄር ፊት እንድንቀርብ የሚያስችለንን እውነት የሚያዋቅሩት የእምነት ቁሶች ምንድናቸው? የዚህ ዓይነት እምነት ይኖረን ዘንድ የሚያስችለን ወንጌል ምንድነው? ይህ ወንጌል የሚያበራው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ነው፡፡
 
ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ በዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች ወሰደ፤ ተሰቀለ፤ ደሙን አፈሰሰ፤ በሦስት ቀንም ከሙታን ተነሳ፡፡ በዚህም ለምናምነው ለእኛ ፍጹም የሆነውን ደህንነቱን ፈጸመ፡፡ ነፍሳችን ከሐጢያት መንጻት ከፈለገች ብሩህ ወደሆነው የእውነት ግዛት መግባት የምንችለው ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀትና (ማቴዎስ 3፡15) በመስቀሉ ደም (ዮሐንስ 19፡30) ብቻ ነው፡፡ አዳኛችን ሆኖ በሚያበራው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ እስካላመንን ድረስ እንደ በረዶ ነጭ የሆነ ልብ ፈጽሞ አይኖረንም፡፡
አንዳንድ ጊዜ የሥጋ ድካሞቻችንን እንመለከትና እናዝናለን፡፡ ነገር ግን እንደዚያም ቢሆን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የተነሳ አሁንም ለእግዚአብሄር ምስጋናን እናቀርባለን፡፡ ምክንያቱም ጌታ በጥምቀቱና በደሙ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ደምስሶዋልና፡፡ እናንተና እኔ በሌላ በማንኛውም መንገድ በጭራሽ ቅዱሳን መሆን አንችልም፡፡ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ቅዱሳን ሆነናል፡፡ ጌታችን ፈጽሞ ከሐጢያት አድኖናል፡፡ በሰማያዊውና በቀዩ ማግ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነንን ብሩህ የእውነት ብርሃን መረዳት እንችላለን፡፡ ጌታ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ጤናማና ቅዱሳን አድርጎናል፡፡
 
በማቴዎስ 19፡24 ላይ ጌታችን እንዲህ አለ፡- ‹‹ዳግመኛም እላችኋለሁ፤ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል፡፡›› በመንፈስ ባለጠጋ የሆኑ ሊድኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያት ስርየትን መቀበል እንደሚችሉ አያምኑምና፡፡ ሰማይ የመግባት ፍላጎት ያላቸው የእግዚአብሄርን ዕርዳታ የሚለምኑ የራሳቸውን ጽድቅ ወደዚያ ጥለው በፈንታው መቶ በመቶ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ፣ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የዘላለምን ሕይወት ማግኘት የሚችሉ፣ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብቻ ናቸው፡፡ እኛ እጅግ ቅዱስ የሆነውን አምላክ እንገናኘው ዘንድ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ብሩህ የሆነውን የደህንነት ብርሃን አብርቶልናል፡፡ በራሳችን አቅም በጭራሽ ቅዱሳን መሆን አንችልም፡፡ ነገር ግን በጌታ በተሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ስናምን በእርግጥም ቅዱሳን መሆንና ብሩህ ወደሆነውም የእውነት ግዛት መግባት እንችላለን፡፡
 
 
ሐይማኖታዊና ዶክትሪናዊ እምነትን መተው አለብን፡፡ 
 
በዮሐንስ 3፡3 ላይ ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሄርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡፡›› ለዚህም በምላሹ ኒቆዲሞስ እንዲህ ሲል ጠየቀ፡- ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማህጸን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?›› (ዮሐንስ 3፡4)
ዳግመኛ ያልተወለዱ ሰዎች በእምነት ብቻ ዳግመኛ መወለድ የማይቻል ይመስላቸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንኳን የእርሱን ቃል አልተረዱትም፡፡ ቃሉንም ቢሆን ተጠራጥረውታል፡፡ ስለዚህ ጌታ በአንድ ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሄር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል፡፡›› (ማቴዎስ 19፡26) ሰዎች በሐይማኖታዊ እምነታቸው ወደ እግዚአብሄር መንግሥት መግባት እንደማይቻላቸው እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ወደ መንግሥቱ መግባት ይችላሉ፡፡ በራሳችን ቅዱሳን መሆን ባንችልም ጌታ ወደዚህ ምድር መጥቶ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያት በሰውነቱ እንደወሰደ፣ እንደተሰቀለ፣ ዳግመኛም ከሙታን እንደተነሳና በዚህም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለዘላለም የደመሰሰውን የደህንነት ብሩህ ብርሃን እንዳበራ የሚያምኑ እግዚአብሄር ወደ መንግሥቱ እንዲገቡ አስችሎዋቸዋል፡፡
 
የመገናኛው ድንኳን ቁሳቁሶች ሆነው ጥቅም ላይ የዋሉት በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የተገለጠው እውነት ኢየሱስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከፈጸመው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ከተገለጠው እውነት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰማያዊው፣ ሐምራዊውና ቀዩ ማግ የእርሱ ትክክለኛ ደህንነት ጥላ ናቸው፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ደግሞ የዚህ ጥላ እውነተኛው አካል ነው፡፡
 
ስለዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ብሩህ የሆነውን የደህንነት እውነት ተረድተን በእርሱ ላይ ማረፍ እንችላለን፡፡ ልክ ጡት የሚጠባ ልጅ በእናቱ ዕቅፍ ውስጥ ሆኖ እንደሚጫወት፣ እንደሚያርፍና እንደሚተኛ ሁሉ በሚያበራው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ውስጥም ሰላም አለ፡፡ እጅግ ቅዱስ የሆነውን አምላክ መገናኘት የቻልነው በወንጌል ውስጥ ያለውን እጅግ የተቀደሰ ብርሃን ስላገኘን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ደህንነት ማግኘት የምንችለው በሚያበራው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ነው፡፡ ዘላለማዊ ዕረፍትን ማግኘት የሚችሉት በእግዚአብሄር በተሰጠው በዚህ ደህንነት የሚያምኑ ብቻ ናቸው፡፡
 
በአጭሩ እጅግ ቅዱስ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማመን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንድንገባ የሚያስችለን ብቸኛው እምነት ነው፡፡ በአጭሩ እጅግ ቅዱስ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማመን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንድንገባ ያስችለናል፡፡ በዚህ ብሩህ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሚያምነው እምነት የሐጢያት ስርየትን የራሳችን አድርገን እንድንወስድ ያስችለናል፡፡ ጌታችን ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ በወንጌሉ እውነትም በጥምቀቱና በመስቀሉ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ደመሰሰልን፡፡ አሁን እርሱ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ከእኛ ጋር የገባውን ተስፋ ፈጸመ፡፡ የዘላለምን ሕይወት መቀበልና ሰማይ መግባት የሚችሉት ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ብቻ ናቸው፡፡
 
ይህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል ከ30 ዓመታት በፊት ጀምሮ ተሰብኮ ቢሆን ኖሮ በእርግጥም ዓለምን ያጥለቀልቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ እውነት በዘመኑ መጨረሻ ይሰራጭ ዘንድ የአግዚአብሄር ፈቃድ ሆነ፡፡ ጌታችን በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ በመጨረሻው ዘመን እጅግ ብዙ ሰዎች ከሐጢያቶቻቸው እንደሚድኑ ተናግሮዋል፡፡ ብዙ ሰማዕታት የሚሆኑ እንደሚኖሩና በመከራው ዘመንም በጌታ አምነውና ሰማዕትነታቸውን ተቀብለው እምነታቸውን የሚያሳዩ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩም ተናግሮዋል፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታችን የዘመኑ መጨረሻ ብዙ ነፍሳቶች የሚሰበሰቡበት የመከር ዘመን እንደሚሆን ትኩረት አድርጓል፡፡ የእግዚአብሄር ዕቅድ በዚህ የእውነት ወንጌል ከልባቸው የሚያምኑ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የሚድኑበትን የደህንነት ስጦታ እንዲቀበሉ ብቻ ነው፡፡
 
እናንተ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ መዳን የቻላችሁት አሁን በዚሀ ዘመን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመስማት ዕድለኞች በመሆናችሁ ነው፡፡ እኔ ይህንን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ስለሰጠን እግዚአብሄርን ከልቤ አመሰግነዋለሁ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ባንሰማ ኖሮ ሁላችንም ምን ይገጥመን ነበር? ነገር ግን አሁንም እንኳን ሁሉ ሰው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንዳልተቀበለ እውነት ነው፡፡ ይህ እውነት በማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ የሚገባ አንዳች ነገር አይደለም፡፡
 
በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ክርስቲያኖች ያሉ ቢሆኑም ብዙዎቹ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል አያውቁም አያምኑበትምም፡፡ ታዲያ እውነተኛውን ወንጌል የማያውቁት እነዚህ ሰዎች እንዴት ከሐጢያት ሊድኑ ይችላሉ? እግዚአብሄር በክርስቲያን ጽሁፍ አማካይነት እውነተኛውን ወንጌል እንድናሰራጭ የፈቀደልን ለዚህ ነው፡፡
 
በመላው ዓለም ብዙዎች እኛ እያሰራጨነው ያለውን የወንጌል ጽሁፍ ካነበቡ በኋላ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ወደ ማወቅ እንደመጡ መስክረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከማወቃቸው በፊት ያውቁ የነበሩት የመስቀሉን ደም ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ግልጽ ወደሆነ የውሃና የመንፈስ ወንጌል አስተውሎት ላይ መድረስ ስለቻሉና ይህንንም ስላመኑ ጌታን እያመሰገኑ ነው፡፡ እንደዚሁም ብዙዎች እንዲህ ያለ ትላቅ ቁም ነገር ኢየሱስ በዮሐንስ በመጠመቁ እውነታ ውስጥ መደበቁን እንዳላወቁም መስክረዋል፡፡ አሁን እነርሱ በዚህ ወንጌል ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ወንጌል ጌታን ለማመስገን ቃላቶች አጥረዋቸዋል፡፡
 
ልክ እንደ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል ሁሉ የመገናኛው ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በርም የተሰራው እንደዚሁ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ እንደሆነ ማየት እንችላለን፡፡ እነዚህ አራት ቀለማቶች ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መንገድም የሚያበራው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በቅድስቱ ስፍራ ባለው የመጋረጃ በርና በቅድስተ ቅዱሳን ባለው የመጋረጃ በር ውስጥም ተገልጦዋል፡፡ ከዚህም በላይ የመገናኛው ድንኳን የመጀመሪያው መሸፈኛ ከእነዚሁ አራት ቀለማቶች ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተፈተለ ነበር፡፡ ይህ እውነት የኢየሱስን ጥምቀትና ደም ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ ራሱን ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚወስድ መንገድ አድርጎ ያወጀው ለዚህ ነው፡፡ እርሱ ወደዚህ ምድር መጥቶ ሐጢያተኞችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማዳን የሚያምኑትን ሐጢያት አልባ አደረጋቸው፡፡
 
ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚወስደው መንገድ የሚገኘው በኢየሱስ ጥምቀትና ደም በሚያምነው እምነት ውስጥ ነው፡፡ ኢየሱስ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ፈጽሞ ከሐጢያት አድኖናል፡፡ ይህንን እውነት የምታገኙት የት ይመስላችኋል? ኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ የምታምኑ ከሆነ ያን ጊዜ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ድናችሁ ለአንዴና ለመጨረሻ የዘላለምን ሕይወት ትቀበላላችሁ፡፡
 
ታዲያ እንዲያው ለነገሩ በኢየሱስ በሚያምነው እምነትና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በትክክል በሚያምነው እምነት መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ጌታ ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ያዳናቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስለሆነ በዚህ ወንጌል ማመን በትክክል በጌታ ማመን ነው፡፡ ጌታ ሐጢያተኞችን ያዳነው በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በመሆኑ ይህንን ጌታ አዳኝ አድርጎ ማመን እርሱ በፈጸመው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ከሐጢያት ከመዳን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በስሙ ብቻ እንደ ነገሩ ማመን ማለት ሐጢያቶቻችን ተወግደው ሰማይ እንገባለን ማለት አይደለም፡፡
 
የሐጢያት ስርየታችንን መቀበልና የራሱ የእግዚአብሄር ሕዝብ መሆን የምንችለው ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል በዮሐንስ መጠመቁን፣ በመስቀል ላይ ደሙን ማፍሰሱን፣ የሐጢያቶችን ሁሉ ኩነኔ መሸከሙንና ከሙታን መነሳቱን በትክክል በማመን ነው፡፡ እግዚአብሄር መንግሥተ ሰማይ እንዲገቡ የሚፈቅድላቸው እጅግ ቅዱስ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሚያምኑትን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑ መንግሥተ ሰማይ አይገቡም፡፡ ምክንያቱም ዳግመኛ አልተወለዱምና፡፡
 
በመገናኛው ድንኳን በተገለጠውና ብሩህ ብርሃን በሆነው የውሃውና የመንፈሱ ወንገል በማመን በዚህ ምድር ላይ እየኖርን እጅግ ቅዱስ የሆነውን እምነት መቀበል እንችላለን፡፡ ምግባሮቻችን ብቁ ባይሆኑም እንደዚህ ዓይነት እምነት ካለን ጻድቃን አይደላችሁም የሚል ማነው? በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ቅዱሳን ሆነን ሳለን እንዴት አሁንም ሐጢያት ሊኖርብን ይችላል? አንዳንድ ሰዎች ገናም ሐጢያት በመስራት የሚቀጥል ሥጋ ለብሰን ሳለን ሐጢያት የለብንም ብለን በመናገራችን ግራ ይጋባሉ፡፡
 
ይህ ግን የራሳቸው የሥጋ አስተሳሰብ ብቻ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል አውቀው የሚያምኑበት ሰብዓዊ ፍጡራን ፍጹም ያልሆነ አካል ስላላቸው እስኪሞቱ ድረስ ሐጢያት ከመስራት በቀር የሚያደርጉት ነገር እንደሌለ ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን ፍጹም በሆነው የኢየሱስ ጥምቀት ደህንነትና በመስቀሉ ውስጥ ለዘላለም ወደፊት የሚሰሩትን ሐጢያቶቻቸውን ጨምሮ ከሐጢያቶቻቸው በሙሉ ለዘላለም እንደዳኑም ደግሞ ያምናሉ፡፡
 
እናንተና እኔ በዚህ ምድር ላይ እየኖርን እንዲህ ያለውን የመንፈሳዊ እምነት ቃል መካፈል የቻልነውና እጅግ የተቀደሰ እምነት ሊኖረን የቻለው ጌታ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠውን መዳናችንን ስለሰጠን ነው፡፡ ይህ የሆነው ጌታ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እውነት እንድናምን ያስቻለንን እምነት ስጦታ አድርጎ ስለሰጠን ነው፡፡ በጌታ ባለን እምነታችን ጌታን እያገለገልንና እርስ በእርስ እየተዋደድን እርስ በርሳችን ሕብረት ሊኖረንና ኑሮዋችንን ልንኖር እንችላለን፡፡ እውነተኛው ሐሴታችን ያረፈው እዚህ ላይ ነው፡፡
 
ለዚህ ወንጌል እግዚአብሄርን ከማመስገን በቀር የምናደርገው ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማወቅ መቻሌና በእርሱ ማመኔ እንዴት ድንቅ ነው! በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ቅንጣት ያህል ዕውቀት የሌለኝ ሆኜ ሳለሁ እግዚአብሄር ለልቤ በውሃውና በመንፈሱ የሚያምነውን እምነት ሰጠኝ፡፡ እኛ ሁላችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሰማይን በረከቶች ተቀብለናል፡፡
 
 
በልቤ ውስጥ ያለውን እውነተኛ ወንጌል በእውነተኛ ምስጋና እሰብከዋለሁ፡፡ 
 
መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ በአእምሮዬ ውስጥ ጥያቄ መፈጠር ጀመረ፡፡ ኢየሱስ ለምን ተጠመቀ? ይህ ጥያቄ በመፈጠሩ ምክንያት መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማግኘት ፈለግሁ፡፡ ነገር ግን ሊያስተምረኝ የሚችል ማንም አልነበረም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ወደ ማወቅ እስከምደርስ ድረስ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እጅጉን የተመሰጥሁት ለዚህ ነበር፡፡
 
እኔ ብዙውን ጊዜ ከማቴዎስ 3፡13-17 በተለይም ኢየሱስ ከመጠመቁ በፊት ለዮሐንስ የተናገረውን ምንባብ አነብ ነበር፡፡ ‹‹አሁንስ ፈቀድልኝ እንዲህ ጽድቅንሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› ነገር ግን ምስጢሩን ፈጽሞ መረዳት አልቻልሁም፡፡ ስለዚህ ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ ለምን እንደተጠመቀ ሌሎችን ብጠይቅም በፍጹም የሚያረካ መልስ አላገኘሁም፡፡ ሆኖም እግዚአብሄር ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀት ዓላማ እንድገነዘብ አስቻለኝ፡፡ ይህም ዕውር ሰው የዓይን ብርሃኑን እንዳገኘ ሁሉ ለእኔ መንፈሳዊ ለውጥ ነበር፡፡ ስለዚህ ከሐጢያቶቼ ያዳነኝንና በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የተገለጠውን እውነት ወደ ማወቅ የመጣሁት የማቴዎስ 3፡13-17ን ትርጉም ከተረዳሁ በኋላ ነበር፡፡
 
ይህንን እውነት ከመረዳቴ በፊት ደህንነቴ አድርጌ ሳምን የነበረው በመስቀሉ ደም ብቻ ነበር፡፡ እውነታው ግን አሁንም ሐጢያት ስለነበረብኝ ሐጢያተኛ መሆኔ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በኢየሱስ ደም ከአዳም ሐጢያት ብቻ ነጻ እንደምወጣ ሳምን ስለነበር በየቀኑ የምሰራቸው ሐጢያቶች አሁንም በልቤ ውስጥ ነበሩ፡፡ ሰውን ፈጽሞ ሐጢያት አልባ ስለሚያደርገው እምነት የማውቀው ነገር አልነበረኝም፤ ማለትም ኢየሱስ ከዮሐንስ ስለተቀበለው ጥምቀት ፈጽሞ ደንቆሮ ነበርሁ፡፡ ነገር ግን ብርሃን በጨለማ ክፍል ውስጥ እንደሚበራ እግዚአብሄር ልቤን በሐጢያት ስርየት ብሩህ ብርሃን አበራው፡፡ ‹‹አሃ ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀት በብሉይ ኪዳን ውስጥ በመስዋዕት ስርዓቱ ላይ ከሚደረገው የእጆች መጫን ጋር በሚገባ የተቆራኘ ነው! ስለዚህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ምንነት ይህ ነው!››
 
ነገር ግን ከዚያ በኋላስ? በመረዳቴ ስደነቅ ይህንን እውነት ከተገነዘብሁ በኋላ በልቤ ወስጥ ታላቅ ነውጥ መነሳት ጀመረ፡፡ ብቸኛው እውነተኛ ወንጌል ሌላ ወንጌል ሳይሆን ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ከሆነ ይህ ዓለም ምን ይገጥመዋል? የወንጌላውያን እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ትክክለኛ ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡ አሁን ግን ውሎ አድሮ ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ውጪ ሌሎች ወንጌሎች በሙሉ ከሰይጣን የመጡ ሐሰተኛ ወንጌሎች መሆናቸውን ወደ መረዳቱ ደርሻለሁ፡፡
 
ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያደረግሁት ነገር ቢኖር ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ውጪ ሌላ እውነተኛ ወንጌል አለመኖሩን ማመንና መስበክ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ አንዳንድ ሰዎች ወቅሰውኛል፡፡ እግዚአብሄርም እንደዚሁ ብዙ ሕጸጾች ያለብኝ ለሆንሁት ለእኔ በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀዩ ማግ የተገለጠውን እውነት ገልጦልኛል፡፡ ይህ እውነት ትክክለኛ ወንጌል መሆኑን እንዳምንና እንድሰብክም አስችሎኛል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ተመሳሳይ ወንጌሎች አሉ፡፡ ነገር ግን ያለው አንድ እውነተኛ ወንጌል ብቻ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመላው ዓለም ለመስበክ የወሰንሁት ለዚህ ነው፡፡
የሐጢያት ስርየትን እውነት እንዴት መስበክ እንደጀመርሁና እጅግ ቅዱስ የሆነውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንዴት ወደ ማወቅ፣ ወደ ማመንና ወደ ማሰራጨት እንደመጣሁ ሳስብ ምን ያህል በብዙ በእግዚአብሄር እንደተባረክሁ ወደ መረዳቱ እመጣለሁ፡፡ ያደረግሁት ነገር ቢኖር ኢየሱስ በዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች እንደወሰደና በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰ ሐጢያቶቼም በሙሉ እንደተወገዱ ማመን ብቻ ነው! የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ትክክለኛ እውነት ነው፡፡ ይህንን ወንጌል ስለሰጠኝ ጌታን አመሰግነዋለሁ፡፡ እኔ እግዚአብሄር በአያሌው የባረከኝ ሰው ነኝ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምታምኑትም እንደዚሁ የተባረካችሁ ሰዎች ናችሁ፡፡
 
እነዚህ ነገሮች ሁሉ እግዚአብሄር የለገሰኝ በረከቶች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ መስክሮዋል፡- ‹‹ዳሩ ግን በእግዚአብሄር ጸጋ የሆንሁትን ሆኛለሁ፡፡ በእኔ ዘንድ ያለው ጸጋውም ከንቱ አልሆነም፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡10) ስለተሰጠኝ ጸጋ እርሱን አመሰግናለሁ፡፡ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ባይሆን ኖሮ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ውስጥ የተገለጠውን የወንጌል እውነት ከየት ትሰሙት ነበር? የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውን፣ የቀዩን ማግና የጥሩውን በፍታ እውነት ሰምቶ የሚያምን ማንኛውም ሰው ልቡ ይነጻል፡፡ ታዲያ በዚህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የማያምኑ ስለዚህ ወንጌል ምን ያስባሉ? ለእነርሱ የውሃውና የመንፈሱ እውነት አሰልቺ ነው፡፡
 
ለቅድስተ ቅዱሳኑ የመጋረጃ በር ጥቅም ላይ በዋለው ሰማያዊና ቀይ ማግ የሚያምን እምነት አላችሁን? ይህንን ቃል ስትሰሙ ቀድሞውኑም እንደምታውቁት አታስቡ፡፡ ነገር ግን እውነቱ በልባችሁ ውስጥ ይገኝ እንደሆነ ለማየት ራሳችሁን መርምሩ፡፡ በሌላ አነጋገር በእግዚአብሄር ቃል መሰረት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምታምኑት እናንተ መሆን አለባችሁ፡፡ ወደ እግዚአብሄር ቤተክርሰቲያን ብትመጡ፣ ቃሉን ብትሰሙና ሰማይ የመግባት መብት ብታገኙ ዕድለኞችና ብሩካን ትሆናላችሁ፡፡
 
ነገር ግን አሰልቺና አድካሚ ሰው ሰራሽ ታሪኮችን በመስማት ብቻ ነገሩ ይህ ባይሆን፣ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማወቅ ባትችሉና መንግሥተ ሰማይ ባትገቡ ምን ጥቅም ታገኛላችሁ? የምታምኑት ወንጌል ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል የተለየ ከሆነ ነፍሳችሁ በእግዚአብሄር ፊት እንዴት ፋይዳ ሊኖረው ይችላል? የሐዋርያው ጳውሎስ እምነትና የእኛ እምነት ተመሳሳይ እንደሆነ ሁሉ የእግዚአብሄር ቃልና እምነታችሁም በትክክል ተመሳሳይ መሆን አለባቸው፡፡ ጴጥሮስ ያመነበት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እኛ ከምናምነው ወንጌል ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21)
 
በዚህ በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሄር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንድናምን ስለፈቀደልን በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡ በመጽሐፎቻችን ውስጥ ያሉትን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እውነት ይዛችሁ ለሌሎች ስታካፍሉ እነርሱም ደግሞ የሐጢያት ስርየትን ይቀበሉና በደስታ እግዚአብሄርን ያመሰግኑታል፡፡ የመገናኛው ድንኳን ምሳሌዎችና ዕቃዎች በሙሉ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ የደመሰሰውን የደህንነት ጌታ ስዕላዊ በሆነ መንገድ በዝርዝር የሚገልጡ መሆናቸውንም መገንዘብ አለብን፡፡ ለዚህ እውነትም እግዚአብሄርን ማመስገን አለብን፡፡
 
በቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ በር ላይ በተገለጠው እውነት ስናምን ለመዳን እንባረካለን፡፡ ከዚህም በላይ እግዚአብሄር ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተሰራውን የሐጢያት ስርየት እውነት በመላው ዓለም እንድናሰራጭ አስችሎናል፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ሥራ በአደራ ሰጥቶናል፡፡ ባለንባቸው የሐላፊነት ቦታዎች ለእያንዳንዳችን በተመደቡልን ሥራዎች ታማኞች ነን፡፡ እግዚአብሄርም ለዚህ ታማኝነት እየባረከን ነው፡፡
እኔ ለእግዚአብሄር ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር ጥቅም ላይ በዋሉት በሰማያዊው፣ በበሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በቅድስተ ቅዱሳኑ የመጋረጃ በር ላይ ከተገለጡት አራት ቀለማቶች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን በማመን በእምነቴ እርሱን አከብረዋለሁ፡፡ ሁላችሁም በእምነት ከሐጢያቶቻችሁ ድናችሁ እግዚአብሄር ለዘላለም በሚያድርበት ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ መግባት እንድትችሉ ከልቤ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የእናንተም እምነት በዚህ ላይ ጸንቷልን?