Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[21-1] ከሰማይ የምትወርደው ቅድስት ከተማ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 21፡1-27 ››

ከሰማይ የምትወርደው ቅድስት ከተማ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 21፡1-27 ››
‹‹አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፡፡ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፡፡ ባሕርም ወደፊት የለም፡፡ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሄር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፡፡ ታላቅም ድምጽ ከሰማይ፡- እነሆ የእግዚአብሄር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእነርሱም ጋር ያድራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሄርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፡፡ ዕንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፡፡ ሞትም ከእንግዲህ አይሆንም፡፡ ሐዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፡፡ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ፡፡ በዙፋንም የተቀመጠው፡- እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ፡፡ ለእኔም፡- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ፡፡ አለኝም፡- ተፈጽሞአል፡፡ አልፋና ዖሜጋ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ፡፡ ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል፤ አምላክም እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፡፡ ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ፣ የርኩሳንም፣ የነፍስ ገዳዮችም፣ የሴሰኛዎችም፣ የአስማተኛዎችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩ፣ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው፡፡ ሰባቱንም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፡- ወደዚህ ና፤ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ፡፡ በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፡፡ የእግዚአብሄርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሄር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያስጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፡፡ ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፤ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፡፡ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር፡፡ በምሥራቅ ሦስት ደጆች፣ በሰሜንም ሦስት ደጆች፣ በደቡብም ሦስት ደጆች፣ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ፡፡ ለከተማይቱ ቅጥር አስራ ሁለት መሰረቶች ነበሩአት፤ በእነርሱም ውሰጥ የአስራ ሁሉ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር፡፡ የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው፡፡ ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፤ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ፡፡ ከተማይቱንም በዘንግ ለካት፤ አስራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፡፡ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው፡፡ ቅጥርዋንም ለካ፤ መቶ አርባ አራት ክንድ በሰው ልክ እርሱም በመልአክ ልክ፡፡ ቅጥርዋም ከኢያስጲድ የተሰራ ነበረ፡፡ ከተማይቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች፡፡ የከተማይቱም ቅጥር መሠረት በከበረ ድንጋይ ሁሉ ተጊጦ ነበር፤ ፊተኛው መሠረት ኢያስጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣ አምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ወራወሬ፣ አሥረኛው ክርስጵራስስ፣ አስራ አንደኛው ያክንት፣ አስራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ፡፡ አስራ ሁለቱም ደጆች አስራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እያንዳንዱ ደጅ ከአንድ ዕንቁ የተሰራ ነበረ፡፡ የከተማይቱም አደባባይ ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረ፡፡ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም፡፡ ለከተማይቱም የእግዚአብሄር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለሆነ፤ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጉትም ነበር፡፡ አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፡፡ በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፡፡ የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ፡፡ ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኩሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም፡፡›› 
 
 
ትንታኔ፡፡ 
 
ቁጥር 1፡- አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፡፡ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፡፡ ባሕርም ወደፊት የለም፡፡
ይህ ቃል ጌታ አምላካችን አዲሱን ሰማይና ምድሩን በመጀመሪያው ትንሳኤ ዕድል ላገኙት ቅዱሳኖች በስጦታ መልክ እንደሚያበረክትላቸው ይናገራል፡፡ ከዚህች ቅጽበት ጀምሮም ቅዱሳን በፊተኛው ሰማይና ምድር ሳይሆን በአዲሱ ሁለተኛ ሰማይና ምድር ይኖራሉ፡፡ ይህ በረከት እግዚአብሄር ለቅዱሳኑ የሚያበረክተው ስጦታ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ያለውን በረከት የሚሰጠው የመጀመሪያውን ትንሳኤ ላገኙ ቅዱሳን ነው፡፡
በሌላ አነጋገር በዚህ በረከት የሚደሰቱት ክርስቶስ በሰጠው ቅዱስ የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን የሐጢያት ስርየትን የተቀበሉ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ጌታችን የቅዱሳን ሙሽራ ነው፡፡ ከአሁን ጀምሮም ሙሽሪቶቹን የሚጠብቃቸው ነገር ቢኖር የሙሽራቸው የበጉ ሙሽሪቶች እንደመሆናቸው የሙሽራውን ጥበቃ፣ ባረኮቶችና ሥልጣን መልበስ ነው፡፡ በከበረው መንግሥቱ ውስጥም በክብር ይኖራሉ፡፡
 
ቁጥር 2፡- ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሄር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፡፡
እግዚአብሄር ለቅዱሳን ቅድስቲቱን ኢየሩሳሌምን አዘጋጅቷል፡፡ ይህች ከተማ የእግዚአብሄር ቅድስት ቤተ መንግሥት አዲሲቱ የኢየሩሳሌም ከተማ ነች፡፡ ይህ ቤተ መንግሥት ለእግዚአብሄር ቅዱሳን የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጌታ አምላካችን ዩኒቨርስን ከመፍጠሩ በፊት በኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን የታቀደ ነበር፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ጌታ አምላክን ለጸጋ ስጦታው ከማመስገንና በእምነታቸውም ክብርን ሁሉ ለእርሱ ከመስጠት በቀር ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር የለም፡፡
 
ቁጥር 3፡- ታላቅም ድምጽ ከሰማይ፡- እነሆ የእግዚአብሄር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእነርሱም ጋር ያድራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሄርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፡፡
ቅዱሳን ከአሁን ጀምሮ በእግዚአብሄር መቅደስ ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ፡፡ ይህ ሁሉ በጌታ አምላክ ጸጋ የሆነ ነው፡፡ ይህ ቅዱሳን በውሃና በመንፈስ የደህንነት ቃል ባላቸው እምነታቸው የተቀበሉት ስጦታ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ጌታ መቅደስ የመግባትንና ከእርሱ ጋር የመኖርን በረከት የለበሱ ሁሉ ለጌታ አምላክ ምስጋናንና ክብርን ያቀርባሉ፡፡
 
ቁጥር 4፡- ዕንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፡፡ ሞትም ከእንግዲህ አይሆንም፡፡ ሐዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፡፡ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ፡፡
አሁን እግዚአብሄር ከቅዱሳን ጋር ስለሚኖር ከእንግዲህ ወዲህ ተጨማሪ የሐዘን ዕንባዎች አይኖሩም፡፡ የሚወዱዋቸውን በማጣትም ማልቀስ በሐዘንም መጮህ አይኖርም፡፡
የመጀመሪያው ሰማይና ምድር ሐዘን በሙሉ ከቅዱሳን ሕይወት ውስጥ ይወገዳል፡፡ ቅዱሳን የሚጠብቃቸው ነገር ቢኖር በእርሱ አዲስ ሰማይና ምድር ከጌታ አምላካቸው ጋር የተባረከውንና የከበረውን ሕይወታቸውን መኖር ነው፡፡ጌታ አምላካችን የራሳቸው የቅዱሳን አምላክ ሆኖ ሲያበቃ ዳግመኛ የሐዘን ዕንባዎች፣ ጩኸት፣ ሞት፣ ዋይታ፣ ሕመም፣ በመጀመሪያው ምድር ያሰቃያቸው ማንኛውም ሌላ ነገር እንዳይኖር ሁሉንም ነገሮችና ሁሉንም አካባቢዎች አዲስ ያደርጋል፡፡
 
ቁጥር 5፡- በዙፋንም የተቀመጠው፡- እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ፡፡ ለእኔም፡- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ፡፡
አሁን ጌታ ሁሉን አዲስ ያደርጋል፡፡ አዲስ ሰማይና ምድርንም ይፈጥራል፡፡ የመጀመሪያውን ሰማይና ምድር ፍጥረቱን በማስወገድ አዲስ ሁለተኛ ሰማይና ምድር ይፈጥራል፡፡ ይህ ቁጥር እግዚአብሄር አሮጌውን ዳግመኛ እንደሚያድሰው ሳይሆን በምትኩ አዲስ ዩኒቨርስን እንደሚፈጥር ይነግረናል፡፡ በዚህም እግዚአብሄር አዲስ ሰማይና ምድርን ይፈጥርና ከቅዱሳን ጋር አብሮ ይኖራል፡፡ የመጀመሪያውን ትንሳኤ ያገኙ ቅዱሳን የዚህም በረከት ተከፋይ ይሆናሉ፡፡ ይህ የሰው ዘር ሰው ሰራሽ በሆኑት አስተሳሰቦቹ ሊያልመው የማይችለው አንዳች ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር ግን ለቅዱሳኖቹ ያዘጋጀው ይህንን ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳንና ሁሉም ነገሮች ለዚህ ታላቅ ሥራ ክብርን፣ ምስጋናን፣ ውዳሴንና አክብሮትን ለእግዚአብሄር ይሰጣሉ፡፡
 
ቁጥር 6፡- አለኝም፡- ተፈጽሞአል፡፡ አልፋና ዖሜጋ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ፡፡
ጌታ አምላካችን እነዚያን ነገሮች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ አቅዶ ፈጽሞዋቸዋል፡፡ ጌታ ያደረጋቸውን ነገሮች በሙሉ ያደረገው ለራሱና ለቅዱሳኖቹ ነው፡፡ አሁን ቅዱሳን ‹‹የክርሰቶስ›› ሆነው ተጠርተው የእግዚአብሄር ሕዝብ ሆነዋል፡፡ አሁን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የእግዚአብሄር ቅዱሳን የሆኑ ሰዎች ለዛለም እግዚአብሄርን ቢያመሰግኑና ቢያወድሱም ለጌታ አምላክ ፍቅርና ሥራዎች ገናም እንደሚገባ ሊያመሰግት እንዳልቻሉ ይገነዘባሉ፡፡
‹‹ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ፡፡›› ጌታችን በአዲስ ሰማይና ምድር ለቅዱሳን የሕይወትን ውሃ ምንጭ ሰጥቶዋቸዋል፡፡ ይህ እግዚአብሄር ለቅዱሳኖች የለገሳቸው እጅግ ታላቁ ስጦታ ነው፡፡ አሁን ቅዱሳን በአዲስ ሰማይና ምድር ለዘላለም ሊኖሩና ዳግመኛ ለዘላለም ሊኖሩና ዳግመኛ ለዘላለም እንዳይጠሙም ከሕይወት ውሃ ምንጭ ሊጠጡ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ቅዱሳን አሁን ልክ እንደ እግዚአብሄር አምላክ የዘላለም ሕይወት ያላቸው የእግዚአብሄር ልጆች ሆነው በእርሱ ክብር ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ይህንን ታላቅ በረከት ስለሰጠን ጌታ አምላካችንን ደግሜ አመሰግነዋለሁ፤ አከብረውማለሁ፡፡ ሐሌሉያ!
 
ቁጥር 7፡- ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል፤ አምላክም እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፡፡
እዚህ ላይ ‹‹ድል የሚነሣ›› የሚለው የሚመላክተው ጌታ የሰጣቸውን እምነት የጠበቁትን ነው፡፡ ይህ እምነት ቅዱሳን ሁሉ ዓለምንና የእግዚአብሄርን ጠላቶች እንዲያሸንፉ ይፈቅድላቸዋል፡፡ በጌታ አምላክና እርሱ በሰጠው እውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ፍቅር ላይ ያለን እምነታችን በዓለም ሐጢያቶች ሁሉ ላይ በእግዚአብሄር ፍርድ በጠላቶቻችን፣ በድካሞቻችንና በጸረ ክርስቶስ ስደት ላይ ድልን ያቀዳጀናል፡፡
በሁሉም ላይ ድልን ላቀዳጀን ጌታ አምላካችን ምስጋናንና ክብርን እሰጣለሁ፡፡ በጌታ አምላክ የሚያምኑ ቅዱሳን በእምነታቸው ጸረ ክርስቶስን በብቃት ያሸንፉታል፡፡ ጌታ አምላካችን ጠላቶቻቸውን ሁሉ ለማሸነፍ በሚያደርጉት ተጋድሎዋቸው ማሸነፍ ይችሉ ለቅዱሳን ሁሉን ይህንን ሰጥቶዋቸዋል፡፡
አሁን እንዲህ በእምነታቸው ዓለምንና ጸረ ክርስቶስን ያሸነፉ አዲሱን ሰማይና ምድር እንዲወርሱ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ጌታ አምላካችን ቅዱሳን የእርሱን መንግሥት መውረስ ይችሉ ዘንድ ድል የሚቀዳጁበትን እምነት ሰጥቶዋቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ጸረ ክርስቶስን የምናሸንፍበት እምነት ስለሰጠን እርሱ አሁን አምላካችን ሆኖዋል፡፡ ጌታ አምላካችን ጠላቶቻችንን ሁሉ ድል የምናደርግበትን ይህንን እምነት ስለሰጠን አመሰግነዋለሁ፤ አወድሰውማለሁ፡፡
 
ቁጥር 8፡- ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ፣ የርኩሳንም፣ የነፍስ ገዳዮችም፣ የሴሰኛዎችም፣ የአስማተኛዎችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩ፣ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው፡፡
ጌታ አምላካችን በማንነቱ የእውነትና የፍቅር አምላክ ነው፡፡ ታዲያ ከመሰረቱ በእግዚአብሄር ፊት ፈሪ የሆኑት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? እነዚህ በአዳም ሐጢያት የተወለዱና ጌታ በሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ቃል ከገዛ ራሳቸው ሐጢያቶች ሁሉ ያልነጹ ሰዎች ናቸው፡፡ በማንነታቸው ከእግዚአብሄር ይልቅ ለክፉዓን ስለሚሰግዱ በግልጽ የሰይጣን አገልጋዮች ሆነዋል፡፡ እነርሱ በጌታ አምላክ ፊት ፈሪዎች ከመሆን በቀር ሌላ ማድረግ የሚችሉት ነገር አይኖርም፡፡
እግዚአብሄር በማንነቱ ብርሃን ነው፡፡ ስለዚህ ራሳቸው ጨለማ የሆኑት እነዚህ ሰዎች እግዚአብሄርን መፍራታቸው የጸና እውነታ ነው፡፡ የሰይጣን ባሮች የሆኑ ሰዎች ጨለማን ስለሚወዱ ራሱ ብርሃን በሆነው በሆነው በእግዚአብሄር ፊት ፈሪዎች ናቸው፡፡ ክፋታቸውንና ድክመቶቻቸውን ለእግዚአብሄር ማቅረብና የሐጢያቶቻቸውንም ስርየት ከእርሱ መቀበል ያለባቸው ለዚህ ነው፡፡
ልባቸው በመሰረቱ በጌታ አምላካችን ፍቅርና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ‹‹የማያምን›› ሰዎች የእርሱ ጠላቶችና በእግዚአብሄርም ፊት እጅግ ታላቅ ሐጢያተኞች ናቸው፡፡ ነፍሳቸው የረከሰ ስለሆነ፣ እግዚአብሄርን ስለሚቃወሙ፣ ሐጢያትን አለ የተባለውን ሐጢያት ሁሉ ስለሚሰሩ፣ የሐሰት ምልክቶችን ስለሚከተሉ፣ ሁሉንም ዓይነት ጣዖት ስለሚያመልኩ፣ ሁሉንም ዓይነት ውሸቶችንም ስለሚዋሹ ስለዚህ በእግዚአብሄር የጽድቅ ፍርድ ሁሉም በእሳትና በዲን ወደሚቃጠል ባሕር ይጣላሉ፡፡ ይህ የሁለተኛው ሞት ቅጣታቸው ነው፡፡
እግዚአብሄር በፊቱ ፈሪዎች ለሆኑት፣ በውሃውና በመንፈሱ የወንጌል ቃል ለማያምኑት፣ የሰይጣን አገልጋዮች በመሆንም ለረከሱት ለእነዚህ ሰዎች አዲሱን ሰማይና ምድር አልፈቀደላቸውም፡፡ እግዚአብሄር ለእነርሱ የፈቀደላቸው ዘላለማዊ ቅጣቱን ሁሉንም (ነፍስ ገዳዮችን፣ ሴሰኞችን፣ አስማተኞችን፣ ጣዖት አምላኪዎችንና ውሸታሞችን ሁሉ ጨምሮ) ወደ እሳትና ዲን ባህር መጣልን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚሰጣቸው ሲዖል ሁለተኛው ሞታቸው ነው፡፡
 
ቁጥር 9፡- ሰባቱንም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፡- ወደዚህ ና፤ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ፡፡
የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች ካወረዱት መላእክቶች አንዱ ዮሐንስን ‹‹ወደዚህ ና የበጉን ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ›› አለው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹የበጉ ሚስት›› የምታመለክተው በልባቸው ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽሮች የሆኑትን ነው፡፡
 
ቁጥር 10-11፡- በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፡፡ የእግዚአብሄርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሄር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያስጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፡፡
‹‹ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም›› የምታመለክተው ቅዱሳኖች ከሙሽራው ጋር የሚኖሩባትን ቅድስት ከተማ ነው፡፡ ዮሐንስ ያያት ይህች ከተማ በእርግጥም ውብና ድንቅ ነበረች፡፡ በመጠንዋ ግርማ ሞገስን የተላበሰች በስተ ውጭ በከበሩ ድንጋዮች ያጌጠች ንጹህና የጠራች ነበረች፡፡ መልአኩ ለዮሐንስ ቅዱሳኖች ከሙሽራቸው ጋር የት እንደሚኖሩ አሳየው፡፡ ከሰማይ የምትወርደው ይህች ቅድስቲት ከተማ ኢየሩሳሌም ለበጉ ሚስት የሚሰጣት የእግዚአብሄር ስጦታ ነች፡፡
የኢየሩሳሌም ከተማ ብሩህ ሆና ታበራለች፡፡ ብርሃንዋም ልክ እንደ ኢያስጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበር፡፡ ስለዚህ በእርስዋ ውስጥ ለሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሄር ክብር ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አብሮዋቸው ይሆናል፡፡ የእግዚአብሄር መንግሥት የብርሃን መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ ወደዚህች ከተማ መግባት የሚችሉት ከጨለማቸው፣ ከድካሞቻቸውና ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የነጹ ብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም እኛም ወደዚህች ቅድስት ከተማ ለመግባት ጌታችን የሰጠንን እውነተኛውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ቃል መማር፣ ማወቅና ማመን አለብን፡፡
 
ቁጥር 12፡- ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፤ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፡፡ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር፡፡
የዚህች ከተማ ደጆች በአስራ ሁለት መላዕክቶች የተጠበቁ ነበሩ፡፡ በደጆቹም ላይ የአስራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር፡፡ ከተማይቱ ‹‹ታላቅና ረጅም ቅጥር›› የነበራት መሆኑ ወደዚህች ቅድስት ከተማ የሚገባበት መንገድ ያንን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር በሰው ጥረቶች ወይም እግዚአብሄር በፈጠራቸው ቁሳዊ ነገሮች በእግዚአብሄር ፊት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ መዳን አዳጋች ነው፡፡
ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ድነን ወደ እግዚአብሄር ቅድስት ከተማ ለመግባት አስራ ሁለቱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የነበራቸውን ዓይነት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እውነት የሚያምነው እምነት ፈጽሞ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምን ይህ እምነት የሌለው ሰው መቼም ቢሆን ወደዚህች ቅድስት ከተማ መግባት አይችልም፡፡ ጌታ አምላክ የሾማቸው አስራ ሁለት መላእክቶች ደጆችዋን የሚጠብቁት ለዚህ ነው፡፡
በሌላ በኩል ‹‹በእነርሱ ላይ የተጻፉት ስሞች›› የሚለው ሐረግ የዚህች ከተማ ባለቤቶች ቀድሞውኑም እንደተወሰኑ ይነግረናል፡፡ ባለቤቶቹ ሌላ ሳይሆኑ እግዚአብሄርና ቅዱሳን ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከተማይቱ አሁን የእርሱ ልጆች የሆኑት የእግዚአብሄር ሕዝብ ንብረት ናትና፡፡
 
ቁጥር 13፡- በምሥራቅ ሦስት ደጆች፣ በሰሜንም ሦስት ደጆች፣ በደቡብም ሦስት ደጆች፣ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ፡፡
በከተማይቱ ምስራቅ ሦስት በሮች እንዳሉ ሁሉ በሰሜን፣ በደቡብና በምዕራብም በእያንዳንዳቸው ሦሰት ሦስት በሮች ነበሩ፡፡ ይህም ወደ ከተማይቱ መግባት የሚችሉት በልባቸው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን የሐጢያት ስርየትን የተቀበሉት ብቻ እንደሆኑ ያሳየናል፡፡
 
ቁጥር 14፡- ለከተማይቱ ቅጥር አስራ ሁለት መሰረቶች ነበሩአት፤ በእነርሱም ውሰጥ የአስራ ሁሉ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር፡፡
የሕንጻዎች ወይም የግንባታዎች መሰረቶች ሆነው የሚያገለግሉት ግዙፍ ዓለቶች ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‹‹ዓለት›› የሚለው ቃል የሚያመለክተው በጌታ አምላካችን ማመንን ነው፡፡ ይህ ቁጥር ወደ ጌታ አምላክ ቅድስት ከተማ ለመግባት እርሱ ለሰው ዘር የሰጠው ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ፈጽሞ እንዳዳነን የሚያምነው እምነት ሊኖረን እንደሚገባ ይነግረናል፡፡ የቅዱሳን እምነት ከቅድስቲቱ ከተማ ዕንቁዎች እንኳን ይበልጥ የከበረ ነው፡፡ ይህ ቁጥር እዚህ ላይ የከተማይቱ ቅጥር በአስራ ሁለት መሰረቶች ላይ እንደተገነባና በእነርሱም ላይ አስራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያቶች ስሞች እንደተጻፉ ይነግረናል፡፡ ይህም የእግዚአብሄር ከተማ የተፈቀደችው አስራ ሁለቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቶች የነበራቸው ዓይነት ተመሳሳይ እምነት ላላቸው ብቻ እንደሆነ ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 15፡- የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው፡፡
ሰው እግዚአብሄር ወደሰራት ከተማ ይገባ ዘንድ እግዚአብሄር የደገፈው የሐጢያት ስርየትን የሚያመጣ እምነት ሊኖረው እንደሚገባ ይህ ቃል ይናገራል፡፡ እዚህ ላይ ዮሐንስን ያነጋገረው መልአክ ከተማይቱን የሚለካበት የወርቅ ዘንግ እንደነበረው ተነግሮዋል፡፡ ይህ ማለት ጌታችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ እነዚህን ሁሉ በረከቶች እንደሰጠን ማመን አለብን ማለት ነው፡፡ ‹‹እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ›› (ዕብራውያን 11፡1) ስለሆነ እግዚአብሄር በእርግጥም እኛ ተስፋ ከምናደርጋቸው ነገሮች በላይም እንኳን ቅድስቲቱን ከተማና አዲስ ሰማይና ምድርን ሰጥቶናል፡፡
 
ቁጥር 16፡- ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፤ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ፡፡ ከተማይቱንም በዘንግ ለካት፤ አስራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፡፡ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው፡፡
ከተማይቱ አራት ማዕዘን ነበረች፡፡ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋና ቁመቷ ተመሳሳይ ነበረ፡፡ ይህም ሁላችንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የእግዚአብሄር ሕዝብ ሆነን ዳግመኛ የምንወለድበት እምነት ሊኖረን እንደሚገባ ይነግረናል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ጌታችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምን ይህ ትክክለኛ እምነት የሌለው ማንኛውም ሰው ወደ እግዚአብሄር መንግሥት እንዲገባ አይፈቅድም፡፡
አሁንም ድረስ ሐጢያት ቢኖርባቸውም ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ እንደሚገቡ በደብዛዛው የሚያስቡ ብዙዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ጌታችን ከሐጢያት መዳንንና መንፈስ ቅዱስን በመስጠት የራሱ ሕዝብ ያደረጋቸው በዚህ ምድር ላይ በተጠመቀው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ይቅር ያላቸው የመሆኑን እውነት ያመኑትን ብቻ ነው፡፡ ጌታችን ከእኛ የሚጠይቀው እምነት ይህንን ነው፡፡
 
ቁጥር 17፡- ቅጥርዋንም ለካ፤ መቶ አርባ አራት ክንድ በሰው ልክ እርሱም በመልአክ ልክ፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አራት ቁጥር ፍቺው መከራ ነው፡፡ ጌታ ከእኛ የሚጠይቀው እምነት ማንም ሰው ሊኖረው የሚችለውን ዓይነት እምነት አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ እምነት ሊኖራቸው የሚችሉት ምንም እንኳን በራሳቸው አስተሳሰቦች ሙሉ በሙሉ ባይረዱትም የእግዚአብሄርን ቃል የተቀበሉት ናቸው፡፡ ክርስቲያን ሆኖ በኢየሱስ መስቀል፤ ጌታ አምላክና አዳኝ መሆኑን በማመን ብቻ ወደ እግዚአብሄር ቅድስት ከተማ መግባት አይቻልም፡፡ ጌታ በዮሐንስ 3፡5 ላይ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ታውቃላችሁን? ጌታችን ወደዚህ ምድር የመጣበትን፣ በዮሐንስ የተጠመቀበትን፣ የዓለምን ሐጢያት በመስቀል ላይ የተሸከመበትንና በመስቀል ላይም ደሙን ያፈሰሰበትን ትርጉም ታውቃላችሁን? ይህንን ጥያቄ መመለስ የምትችሉ ከሆናችሁ እዚህ ላይ የምናገረውን ትረዳላችሁ፡፡
 
ቁጥር 18፡- ቅጥርዋም ከኢያስጲድ የተሰራ ነበረ፡፡ ከተማይቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች፡፡
ይህ ቁጥር ወደ እግዚአብሄር ቅድስት ከተማ እንድንገባ የሚፈቅድልን እምነት ንጹህና ከዓለም ጋር ፈጽሞ ያልተቀላቀለ መሆኑን ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 19-20፡- የከተማይቱም ቅጥር መሠረት በከበረ ድንጋይ ሁሉ ተጊጦ ነበር፤ ፊተኛው መሠረት ኢያስጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣ አምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ወራወሬ፣ አሥረኛው ክርስጵራስስ፣ አስራ አንደኛው ያክንት፣ አስራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ፡፡
የከተማይቱ ቅጥር መሰረቶች በሁሉም ዓይነት የከበሩ ድንጋዮች አጊጠው ነበር፡፡ ይህ ቃል ከጌታችን ቃል በተለያዩ የእምነት ገጽታዎች ልንመገብ እንደምንችል ይነግረናል፡፡ እነዚህ የከበሩ ድንጋዮችም ጌታችን ለቅዱሳን የሚሰጣቸውን የበረከት ዓይነቶች ያሳዩናል፡፡
 
ቁጥር 21፡- አስራ ሁለቱም ደጆች አስራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እያንዳንዱ ደጅ ከአንድ ዕንቁ የተሰራ ነበረ፡፡ የከተማይቱም አደባባይ ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረ፡፡
ዕንቁ የሚያመለክተው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለን ‹‹እውነት›› ነው፡፡ (ማቴዎስ 13፡46) ከልቡ እውነትን የሚፈልግ ሰው የዘላለምን ሕይወት የሚሰጠውን እውነት ለማግኘት ያለውን ሁሉ በደስታ ይተዋል፡፡ ይህ ቁጥር ወደ ቅድስት ከተማ የሚገቡ ቅዱሳን በዚህ ምድር ላይ ሳሉ የእምነታቸውን ማዕከል በእውነት ላይ በጽናት ተክለው በመቆም ብዙ መታገስ እንደሚያስፈልጋቸው ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታ አምላክ በተናገረው የእውነት ቃል የሚያምኑ እምነታቸውን ለመጠበቅ ታላቅ ጽናት ያስፈልጋቸዋል፡፡
 
ቁጥር 22-23፡- ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም፡፡ ለከተማይቱም የእግዚአብሄር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለሆነ፤ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጉትም፡፡
ይህ ምንባብ ቅዱሳን ሁሉ የነገሥታት ንጉሥ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ እቅፍ ውስጥ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌምም የመጀመሪያዎቹ ፀሐይና ጨረቃ አያስፈልጉዋትም፡፡ ምክንያቱም የዓለም ብርሃን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያበራላታልና፡፡
 
ቁጥር 24፡- አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፡፡
ይህ ምንባብ በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ ሲኖሩ የነበሩት ሕዝቦች አሁን ወደ አዲሱ ሰማይና ምድር እንደሚገቡ ይነግረናል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹የምድር ነገሥታት›› ውሰጥ ሲኖሩ የነበሩትን ቅዱሳን ነው፡፡ ቁጥሩ ሲቀጥል የምድር ነገሥታት ‹‹ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፡፡›› ይህም ቀድሞውኑም በከበሩ አካሎቻቸው ሲኖሩ የነበሩት ቅዱሳን አሁን ከሺህው ዓመት መንግሥት እግዚአብሄር አዲስ አድርጎ ወደፈጠረው የአዲስ ሰማይና ምድር መንግሥት እንደሚዛወሩ ይነግረናል፡፡
ስለዚህ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም መግባት የሚችሉት በዚህ ምድር ላይ ሳሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ የተወለዱና ለሺህ ዓመት በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ለመኖር የተነጠቁት ብቻ ናቸው፡፡
 
ቁጥር 25፡- በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፡፡
ቅድስቲቱ ከተማ ያለችበት አዲስ ሰማይና ምድር ቀድሞውኑም በቅዱስ ብርሃን ስለተሞላች በውስጥዋ ሌሊትም ሆነ ክፉ ሰዎች ሊኖሩ አይችሉም፡፡
 
ቁጥር 26፡- የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ፡፡
ይህም በጌታ አምላክ አስገራሚ ሐይል ለሺህ ዓመት በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ሲኖሩ የነበሩት አሁን ቅድስቲቱ ከተማ ወዳለችበት የአዲስ ሰማይና ምድር መንግሥት ለመዛወር ብዙ ስለ መሆናቸው ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 27፡- ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኩሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም፡፡
በዚህ ዓለም ላይ በሚኖሩ ክርስቲያኖችና ክርስቲያን ባልሆኑት መካከል ውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እውነት የማውቁ ሁሉ ጸያፎች፣ ርኩሳኖችና ውሸታሞች ናቸው፡፡ ስለዚህ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ አይገቡም፡፡
እዚህ ላይ የእግዚአብሄር ቃል ጌታ በዚህ ምድር ላይ የሰጠን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ሐይል ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ እናረጋግጥ ዘንድ ፈቅዶልናል፡፡ ምንም እንኳን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በዚህ ምድር ላይ ለብዙ ሰዎች እየተሰበከ ቢሆንም ይህ ወንጌል ክርስቲያኖች ተብለው በሚጠሩትም እንኳን ቸል የተባለበትና የተናቀበት ዘመን ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ሰማይ የሚያስገባው ቁልፍ ጌታ በሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማመን ብቻ ነው፡፡
አሁንም ድረስ ብዙ ሰዎች ይህንን እውነት ሳያውቁት ቀርተዋል፡፡ እናንተ ግን ጌታ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሰጠውን የሰማይ ቁልፎችና የሐጢያት ስርየት የሚያውቅና የሚያምን ማንኛውም ሰው ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይጻፋል፡፡
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እውነት ብትቀበሉና ብታምኑበት ቅድስቲቱ ከተማ የመግባትን ባርኮት ትለብሳላችሁ፡፡