Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-12] በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን ሕይወታችሁን ለመኖር ‹‹ ቲቶ 3፡1-8 ››

በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን ሕይወታችሁን ለመኖር
‹‹ ቲቶ 3፡1-8 ››
‹‹ለገዦችና ለባለሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ የተዘጋጁ፣ ማንንም የማይሳደቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው፡፡ እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፣ የምንስት፣ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፣ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፣ የምንጣላ፣ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን፡፡ ነገር ግን የመድሃኒታችን የእግዚአብሄር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም፡፡ ያን መንፈስም በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው፡፡ ቃሉ የታመነ ነው፡፡ እግዚአብሄርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፤ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ፡፡ ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፡፡
 
 
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
የእግዚአብሄርን ፈቃድ መረዳትና በዚያም መሰረት ወንጌልን መስበክ ይኖርብናል፡፡

በኢየሱስ የሚያምኑና ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸው በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር አለባቸው፡፡ እግዚአብሄር ከክርስቲያኖች የሚጠይቀውም በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን እንዲኖሩ ነው፡፡ እኛም የእርሱን ትዕዛዛቶች መከተል አለብን፡፡ ታዲያ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላን ሕይወት መኖር የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ የተናገረውን ማስተዋል አለብን፡፡ 
 


በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር የሚያስፈልገው ምንድነው?  
 

ጳውሎስ በቲቶ 3፡1 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹ለገዦችና ለባለሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ የተዘጋጁ፣ ማንንም የማይሳደቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው፡፡›› ከሁሉ በፊት ለገዥዎችና ለባለሥልጣናት እንድንገዛ፣ እንድንታዘዝና በጎ ሥራዎችንም እንድንሰራ ነግሮናል፡፡ እርሱ ለማለት የፈለገው የዓለምን ሕጎች የማንታዘዝ ከሆነ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር አንችልም ነው፡፡ የዓለም ገዦችና ሕጎች ከእውነት ጋር የሚቃረኑ ከሆኑ ልንታዘዛቸው አይገባንም፡፡ ነገር ግን ሕጎቹ ከእምነታችን ጋር የማይቃረኑ ከሆኑ ወንጌልን በሰላም ለማገልገል ልንታዘዛቸው ይገባናል፡፡
ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ የተቀበልነው እኛን ነን፡፡ ዓለማዊ ሕጎችን የምንቃወም ከሆንን እንዴት በመንፈስ ቅዱስ የተሞላን ሕይወት መኖር እንችላለን? ሰለዚህ በመንፈሰ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር የዓለምን ሕጎች መታዘዝ አለብን፡፡ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉ ሰዎች ማህበራዊ ስርዓቶችን መታዘዝ አለባቸው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር መጓዝ የምንችለው የዓለምን ሕጎች ስንታዘዝ ብቻ ነው፡፡
ወደ ቤተክርስቲያን እየሄድን ሳለን ከእኛ አንዳችን ወንጀል ፈጸምን እንበል፡፡ ጌታን በምቾት ማገልገል እንችል ነበር? ከሕግ ውጪ የሚኖር ከሆነ እንዴት በጌታ አስተምህሮቶች መሰረት ሊኖር ይችል ነበር? በመንፈስ እየተመላለስን ሳለን ማህበራዊ ስርዓቶችን መጣስ የለብንም፡፡ ሕግን ከመጣስ የሚመጣ በጎ ነገር የለም፡፡ ወንጌልን ስንሰብክ ትክክለኛ ሕይወትን ለመኖር መጣር አለብን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር ቅዱሳን በማህበረሰቡ ሕጎች መሰረት ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡
 
 

ገርነትን በልባችን መጠበቅ አለብን 

 
ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ማንንም የማይሳደቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው፡፡›› በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር ማንንም የማንሳደብ፣ የማንከራከርና ለሰዎች የዋህነትን የምናሳይ ልንሆን ይገባናል፡፡
በእነዚያ ዳግም በተወለዱት ሰዎች ልብ ውስጥ ገርነት፣ ራስን መቆጣጠርና ደግነት አለ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን በመኖሩ ነው፡፡ ጳውሎስ እርስ በርሳችን በመጣላት ወንጌሉን ማሳነስ እንደሌለብን ተናግሮዋል፡፡ የዓለም ሕግ ወንጌላችንን የሚጻረር ከሆነ መዋጋት አለብን፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሰላማዊ ሆነን መኖር አለብን፡፡ ሰዎች ‹‹አንዳንድ ጊዜ አንበሳ ቢመስልም እንደ ርግብ የዋህ ነው፡፡ በክርስትና ላይ ያለው እምነቱ ምናልባትም ጭምትና አመዛዛኝ ሰው ሳያደርገው አልቀረም›› ብለው ስለ እኛ እንዲያስቡ ማድረግ አለብን፡፡
በሥጋ ምኞት ውስጥ ገርነት ወይም የዋህነት የለም፡፡ ነገር ግን በዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስና እኛን ከሐጢያቶቻችን ባዳነን ጌታ አማካይነት ለሌሎች ገሮች መሆን እንችላለን፡፡ ክፉኛ የበደለኝን ሰው ይቅር ማለት እውነተኛ ‹‹ይቅርታ›› ነው፤ እርሱን ከልቤ በትህትና ማስተናገድም እውነተኛ ‹‹ገርነት›› ነው፡፡ በተጨባጭ እየጠላሁት ደግ ልሆንለት ማስመሰል ትህትና አይደለም፡፡ ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች ውስጣዊ ሥነ ምግባር በትህትናና በይቅርታ የተሞላ ልብ መያዝ ነው፡፡
ሰዎች ሲበድሉን ደጎች መሆን አለብን፡፡ ለወንጌል እንቅፋት እስካልሆኑ ድረስ ለሰው ሁሉ ደጎች መሆን ይገባናል፡፡ እንደዚያ የማይሆኑ ከሆነ ግን የደግነትን ብርሃን በእውነት ብርሃን መተካት ይገባናል፡፡ ደግነት የሚገኘው በእግዚአብሄር እውነት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄርን ቃል የሚቃወሙ፣ የሚከላከሉ ወይም የሚሳደቡ በደግነት ሊስተናገዱ አይገባቸውም፡፡
እግዚአብሄር የሚቃወሙትን ይቅር አይላቸውም፤ ነገር ግን ዋጋ እንዲከፍሉ ያደርጋቸዋል፡፡ እግዚአብሄር አብርሃምን እንዲህ አለው፡- ‹‹የሚባርኩህንም እባርካለሁ፤ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፡፡›› (ዘፍጥረት 12፡3) የእውነትን ወንጌል የሚቃወሙ ሰዎች የሚድኑበት መንገድ የለም፡፡ ሕይወታቸውን ብቻ ሳይሆን የዘሮቻቸውን ሕይወት እስከ ሦስተኛ ትውልዶች ድረስ የሚያበላሸውን ጥፋት ማስወገድ አይችሉም፡፡
ታጋሾችና የዋሆች መሆን ያለብን ያለብን ለምንድነው? በቲቶ 3፡3 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፣ የምንስት፣ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፣ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፣ የምንጣላ፣ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን፡፡›› ዳግም ከመወለዳችን በፊት ልክ እንደ እነዚህ ሰዎች ነበርን፡፡ እኛም በአንድ ወቅት እንደ እነርሱ ስለነበርን ቻዮችና ይቅር ባዮች ልንሆን ይገባናል፡፡
ቲቶ 3፡4-8 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ነገር ግን የመድሃኒታችን የእግዚአብሄር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም፡፡ ያን መንፈስም በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው፡፡ ቃሉ የታመነ ነው፡፡ እግዚአብሄርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፤ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ፡፡ ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፡፡››
በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችን ያዳነን በጎ ሥራዎችን ስለሰራን አይደለም፡፡ ዳግም የመወለድን በረከት የሰጠን ስለወደደንና ስለራራልን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ አለም መጣ፤ ተጠመቀ፤ በመስቀል ላይ ሞተ፤ ተነሣ፤ ሐጢያቶቻችንንም ሁሉ አነጻ፡፡ ኢየሱስ ተነሣ፡፡ አሁን በእግዚአብሄር ቀኝ ተቀምጦዋል፡፡ እንደገና ከሙታን መካከል በመነሳቱ በዓለም ላይ ያሉት ያልተጠናቀቁ ነገሮች ሁሉ ፍጹም ሆኑ፡፡
እግዚአብሄር በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ ባረከን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ በዮሐንስ ተጠመቀና ሐጢያቶቻችን ሁሉ ይቅርታን ያገኙ ዘንድ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ እኛም ዳንንና ጻድቃን ሆንን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንደ ዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች መሆን አለብን፡፡›› ይህ ማለት እኛ የእግዚአብሄር ወራሾች እንደ መሆናችን የእርሱን ሐብትና ክብር የወረስነው እኛ ነን ማለት ነው፡፡ የዚህ አይነት የተባረከ ሕይወት ለመምራት በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት መኖር አለብን፡፡ እናንተ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን፣ ለሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ይቅርታን ማግኘትና ወንጌልን ለሌሎች መስበክ አለባችሁ፡፡
ስለዚህ ለሐጢያቶቻችን ይቅርታን በማግኘታችን ለሌሎችን ለመጥቀም መስራት አለብን፡፡ የዓለምን ሕጎች መጠበቅና እግዚአብሄርን ለሚሹትም ወንጌልን መስበክ አለብን፡፡ ውብ የሆነውን ወንጌል ለመስበክ እንቅፋት እንዳይሆኑብንም የበደሉንን ይቅር ማለትና በደግነትና በትህትና ማስተናገድ አለብን፡፡ ‹‹ይህ መልካምና ለሰዎችም የሚጠቅም ነው፡፡›› የመንፈስ ቅዱስን ሙላት የምትሹ ከሆናችሁ ጳውሎስ የነገረንን ማስታወስ አለባችሁ፡፡ ይህ የተለየ ነገር ላይመስል ይችላል፤ ነገር ግን እነዚህ አስፈላጊ ቃሎች ናቸው፡፡
የምንኖረው በዚህ ዓለም ላይ ስለሆነ የዚህን ዓለም ሕጎች እየጣስን ከሌሎች ጋር የምንጋጭ ከሆንን በመንፈስ ቅዱስ ልንሞላ አንችልም፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሄር ቃል ጋር የሚቃረን እስካልሆነ ድረስ ሕጉን መታዘዝ ይኖርብናል፡፡ የዓለምን ሕጎች መታዘዝ አለብን፡፡ እምነት ቢኖረንም በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር ሕግን መታዘዝ የተሻለ ምርጫ ነው፡፡ በጎ ሥራዎችን እንሰራ ዘንድ የዓለምን ሕጎች መታዘዝና ከባልንጀሮቻችን ጋር መስማማት አለብን፡፡
 


በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር ትፈልጋላችሁን?
 

ኤፌሶን 5፡8-11 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፡፡ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእምነትም ሁሉ ነውና፡፡ በጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፡፡ ፍሬም ከሌለው የጨለማ ሥራ ጋር ጋር አትተባበሩ፤ ይልቁንም ግለጡት እንጂ፡፡›› ይህ ምንባብ እንደ ብርሃን ልጆች እንድንመላለስና የብርሃንን ፍሬዎች እንድናፈራ ይነግረናል፡፡
ኤፌሶን 5፡12-13 ደግሞ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳን ነውር ነውና፡፡ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፡፡ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና፡፡›› ጳውሎስ እዚህ ላይ ሁሉ ነገር በብርሃን ሲገለጥ እንደሚታይ ይነግረናል፡፡ ጻደቅ ሰው በቅድስና የማይኖር ከሆነ በእግዚአብሄር ወይም ደግሞ በራሱ ሊጋለጥ እንደሚችል ይነግረናል፡፡ አንድ ሰው የጨለማ ስራን ቢሰራና በብርሃን ቢገሰጽ ምን ያደርጋል? ስህተቶቹን ከተቀበለ በኋላ እግዚአብሄርን እንደገና በሚጋፈጥበት ጊዜ ልቡ ይበራል፡፡ ‹‹ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፡፡ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና፡፡›› ለብርሃን መጋለጥ ጥሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ መተላለፋችንን አምነን መቀበልና ወደ እግዚአብሄር መመለስ እንችላለን፡፡   
በእርግጥም እኛ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር የምንፈልግ ከሆነ በልባችን ውስጥ ደግነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ምንም እንኳን አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ሐጢያት ባይኖርበትም ይህ ሰው ደግ መሆን የለበትም ማለት አይደለም፡፡ በልባችን በደግነትና በመልካምነት ልንኖር ይገባናል፡፡ በጥበብ ልንሰብክ፤ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የማያውቁ ሰዎችም ከሐጢያቶቻቸው ይድኑ ዘንድ ይህንን ወንጌል እንዲያስተውሉና የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ እንዲያገኙ ልንጸልይላቸው ያስፈልገናል፡፡ ሌሎችንም በፍጹም ልንጎዳቸው አይገባንም፡፡ ልንበላ፣ ልንተኛና እንደዚሁም ለወንጌል መኖርና ሌሎችን ማገልገል ያስፈልገናል፡፡ 
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመምራት ስለ ጊዜ ጥቅም በደንብ ልናስብና ልክ እንደ ጠቢባን ሰዎች ውብ የሆነውን ወንጌል ማገልገል አለብን፡፡ አለምን ስንወድ ለጨለማ ማጭበርበሪያ እንሸነፍና የእግዚአብሄርን ስራ በመስራት ረገድ ግድ የለሽ ልንሆን እንችላለን፡፡ ስለዚህ አይኖቻችንን በጌታ ላይ መትከልና እርሱ የሚፈልገውን ማድረግ አለብን፡፡ እግዚአብሄር በሰጠን ደህንነት እያመንን ሁሌም ንቁዎች መሆን አለብን፡፡ የመንፈስ ጥበብ ያለው ሰው ዓለም በጨለማ ከመሞላትዋ በፊት ውብ የሆነውን ወንጌል በመላው ዓለም ለመስበክ ራሱን የቀደሰ መሆን ይኖርበታል፡፡ 
 
 
የጌታን ፈቃድ ማስተዋል
 
እግዚአብሄርን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ ለማወቅ መሞከር አለብን፡፡ እርሱ በቤተክርስቲያኑና በቃሎቹ አማካይነት ምን ማድረግ እንደሚፈልግብን መማር አለብን፡፡ እግዚአብሄርን ለማስደሰትና እርሱ ለእኛ ያለውን ፈቃድ ለማወቅ ምን ማድረግ እንደምንችል ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን ያገኙ ሰዎች ዳግም የተወለዱ ናቸው፤ ዳግም የተወለዱ ሰዎችም ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ አላቸው፡፡ በውስጣቸው መንፈስ ቅዱስ ያለባቸው ሰዎች  በእርግጥም ቅዱስ ሕዝብና የእግዚአብሄር ልጆች ናቸው፡፡ የቅዱሳን ሁሉ ተግባር ይህ ነው፡፡ የሌሎችን ፍላጎት ችላ ብለን ችሎታዎቻችንንና ጉልበቶቻችንን በራሳችን ላይ ማባከን የለብንም፡፡ ከጊዜው ፍሰት ጋር እየነጎድን የእግዚአብሄርን ሥራዎች ማደናቀፍ የለብንም፡፡
በእግዚአብሄር ፍቅር አማካይነት ተቀድሰንና አዲስ ልደትን አግኝተን ከሆነ የእርሱን ሥራ ለመቀጠልና ለመሥራት ጥሩ ሰው መሆን ይኖርብናል፡፡ በእርሱ በማመን የእግዚአብሄር ልጆች ከሆንን በጎነትን የሚያደርጉ ሰዎች የመሆን መብት አለን፡፡
የእግዚአብሄር ልጆች የለበሱት ሥጋ ከፍጽምና በጣም የራቀ ነው፡፡ ነገር ግን ስለ እግዚአብሄር ፈቃድ የምናስብና በጎ ነገሮችን የምናደርግ ከሆንን እግዚአብሄር ይደሰታል፡፡ ዳግም የተወለዱትም ቢሆኑ ለራሳቸው ብቻ የሚኖሩ ከሆኑ በሌሎች ላይ ክፋትን ለማድረግ ያዘነብላሉ፡፡ ‹‹መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ›› (ኤፌሶን 5፡18) ማለት በሥጋ ፍትወቶች መስከር የለብንም፤ ነገር ግን የቸርነትን ሥራዎች ማከናወን ይኖርብናል ማለት ነው፡፡
ጳውሎስ በኤፌሶን 5፡19-21 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፡፡ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ፡፡ ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ፡፡›› በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር የምንፈልግ ከሆነ በደህንነት ወንጌል ማመንና መስበክ፣ እንደዚሁም እግዚአብሄር ያደረገልንን መግለጥ አለብን፡፡
በምንጸልይበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሄር ይባርከናል፡፡ በአንድ ድምጽ እርሱን እንድናመሰግን እነዚህን ሁሉ በረከቶች በመዝሙር፣ በዝማሬዎችና በመንፈሳዊ ቅኔዎች ውስጥ መዝግቦልናል፡፡ እርሱን ማወደስ፣ ማመስገንና ማክበር ይገባናል፡፡ ገና ላልዳኑትና ለእርስ በርሳችን በምንጸልይበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የተባረከ ሕይወትን እንኖራለን፡፡ ከልባችን እግዚአብሄርን ማመስገንና ያዳነንን ኢየሱስ ክርስቶስን ማክበር አለብን፡፡ እነዚህን አሳቦች በልቦቻችን ውስጥ ይዘን  ስህተቶቻችንን ማመን ለሐጢያቶቻችን መንጻት ያለንን ከበሬታ መግለጥና እርሱንም መታዘዝ መቻል አለብን፡፡
 
 
በቀሪው ሕይወታችን ውብ የሆነውን ወንጌል ማገልገል አለብን
 
መልካም ነገሮችን ለማድረግ ማቀድና እነዚህንም ለማከናወን ውብ የሆነው ወንጌል ክብር ሊኖረን ይገባል፡፡ ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ጋር በመቀላቀል አብረን መጸለይና እግዚአብሄር እያንዳንዱን ሰው ያድን ዘንድ መለመን አለብን፡፡ እግዚአብሄርን ቢሹትም ውብ የሆነውን ወንጌል ባለማወቃቸው ምክንያት ዳግም መወለድ ያልቻሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ‹‹አቤቱ እባክህ አድናቸው›› በማለት ለእነዚህ ሰዎች መጸለይ ይኖርብናል፡፡ የጠፉትን ለማዳን ወንጌልን በማገልገል ረገድ ንብረቶቻችንን ማቅረብ እንጂ ራስ ወዳድ መሆን አይኖርብንም፡፡ ለሌሎችና ለእግዚአብሄር መንግሥት መስፋት መኖር በጎ ሥራን መስራት ነው፡፡ 
የዚህ አይነት ሥራ መስራት ማለት በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር ማለት ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር ማለት በልሳን መናገርና ተዓምራቶችን ማድረግ ማለት ሳይሆን እግዚአብሄርን ማስደሰት መማር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር በሰጠን ደህንነት መኖር፣ እግዚአብሄርን በቅኔና በዝማሬ ማመስገንና ማክበር ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ እርሱን በሙሉ ልባችን ማመስገን፣ ማወደስና ማክበር፣ ሥጋችንንም የጽድቅ መሳሪያዎች አድርገን በማቅረብ እርሱን ማገልገል ማለት ነው፡፡ የእርሱን ትዕዛዛቶች መከተል ማለት በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር ማለት ነው፡፡ 
በመንፈስ የተሞላ ሕይወትን መኖር ማለት አንዳችን ሌላችንን መታዘዝ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ምክር ከለገሰን የሚናገረውን ማድመጥ አለብን፡፡ በተመሳሳይ መንገድ እኔም ለእርሱ ምክር የምለግሰው ከሆነ ከእኔ ጋር ባይስማማም ማድመጥ ይኖርበታል፡፡ ልክ እንደዚሁ እርሱ በርሳችን በመታዘዝና የእግዚአብሄርን ሥራ በመስራት በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር አለብን፡፡  
 
 
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር ማለት ኢየሱስ ክርስቶስን ማክበር ማለት ነው
 
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት መኖር ማለት የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዛት ማክበር ማለት ነው፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ኤፌሶን 6፡10-13ን በማንበብ እንመልከት፡- ‹‹በቀረውስ በጌታና በሐይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ፡፡ የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡ መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፤ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዥዎች ጋር፤ በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፋት መንፈሳውያን ሰራዊት ጋር ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ በክፉ ቀን ለመቃወም ሁሉን ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሱ፡፡›› 
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት መኖር ማለት ምን ማለት ነው? በጌታ መበርታትና በሐይሉ ማመን ማለት ነው፡፡ በገዛ ፈቃዳችን ብቻ ሳይሆን በውስጣችን በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ሐይል መኖር ማለት ነው፡፡ ከዚህም በላይ የጸሎትን ሕይወት መኖር ማለት ነው፡፡ ስንጸልይ እግዚአብሄር የሚሰጠንን የተለያዩ ችሎታዎችና በረከቶች በመቀበል ብርቱ ሕይወትን መኖር እንችላለን፡፡ የዚህ አይነት ሕይወት መኖር ማለት የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ መልበስ ማለት ነው፡፡ በጣም ደካሞች ስለሆንን ከእርሱ ጋር አብረን ለመጓዝ፣ እግዚአብሄርን ለማገልገልና ለመታዘዝ ብንሞክርም ቃሎቹን አጥብቀን ካልያዝን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር አንችልም፡፡
መንፈሳዊ ሐይላችንን ለማጠናከር በእግዚአብሄር ቃሎች ማመን አስፈላጊ ነው፡፡ እምነት ቢኖረንም ‹‹በእግዚአብሄር ቃሎች ውስጥ በተጻፈው መሰረት እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ›› በማለት የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ መልበስ አለብን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን እንድንኖር የሚያስችለን እምነት ይህ ነው፡፡ 
የዚህ አይነት ሕይወት መኖር ያቃታችሁ አላችሁን? እንግዲያውስ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል አስታውሱ፡፡ የእግዚአብሄርንም ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡ እግዚአብሄር ዕቃ ጦሩን ሁሉ እንድንለብስ ነግሮናል፡፡ ቃሎቹን በልባችሁ ጥልቅ ውስጥ በማስገባት የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ መልበስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትማራላችሁ፡፡ አካባቢያችን ምንም ይሁን ሌሎች ሰዎችም ስለ እኛ ምንም ይበሉ የእግዚአብሄርን ቃሎች አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል፡፡ በዚህ መንገድ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን እንኖራለን፡፡
ይህንን እምነት ማግኘት የምንችለው ከየት ነው? ዮሐንስ ራዕይ 3፡22 እንዲህ ይላል፡- ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡›› መንፈስ ለቤተክርስቲያን የሚለውን መስማት አለብን፡፡ በሌላ አነጋገር በእግዚአብሄር ባሮች ካልሆነ በስተቀር የእግዚአብሄርን ቃሎች መስማትም ሆነ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር አይችልም፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረው በማን በኩል ነው? እግዚአብሄር በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ባሉት ባሮቹ አማካይነት ለቅዱሳንና ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ይናገራል፡፡  
ይህ ማለት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ትምህርቶች በእርግጥም በእግዚአብሄር ቃሎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው መሆናቸውን ማመን ይኖርባችኋል ማለት ነው፡፡ ይህንን እምነት በልቦናችሁ ይዛችሁ የቤተክርስቲያንን ትምህርቶች መቀበል ያስፈልጋችኋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሰባኪው ውስጥ ከሌለ የራሱን አስተሳሰቦች ማስተማር ይቀለዋል፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያለው ሰባኪ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ስር ሆኖ የእግዚአብሄርን ቃሎች ይሰብካል፡፡ ይህንን የማያደርግና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለውን ነገር የሚሰብክ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በልቡ ውስጥ ስላደረበት ያስቆመዋል፡፡
መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውስጡ ስላደረበት የእግዚአብሄር ባርያ ሥልጣን እጅግ የላቀ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፡- ‹‹የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፡፡›› (ማቴዎስ 16፡19) የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ይህ ወንጌል ወደ ሰማይ ለመግባት ቁልፍ ነው፡፡ እግዚአብሄር የአምላክን ቃል የመስበኩን ሥልጣን የሰጠው ለጴጥሮስ ብቻ ሳይሆን ዳግም እስከተወለዱና ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው እስካለ ድረስ ለእያንዳንዱ የእግዚአብሄር ባርያ ነው፡፡
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ መልበስ አለብን፡፡ እምነት ከሌለን በቤተክርስቲያን ሥልጣንና በእግዚአብሄር ባሮች ሁሌም እያመንን የቤተክርስቲያንን ትምህርቶች በአእምሮዋችን ውስጥ መያዝ አለብን፡፡ ዛሬ የምትሰሙት ስብከት ጥቅም የሌለውና ከሕይወታችሁ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ባይሆንም ልታደምጡትና በልባችሁ ውስጥ ልታስቀምጡት ይገባል፡፡ ለቀን ተቀን ሕይወታችሁ የሚያስፈልጉትን ቃሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈልጉ፡፡ አጥብቃችሁም ያዙዋቸው፡፡ በዚህ መንገድ የእምነት ሰው ትሆናላችሁ፡፡ በዚህ መንገድ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ትኖራላችሁ፡፡ ከእግዚአብሄርም ጋር ትጓዛላችሁ፡፡ በዚህ ዓለም የጨለማ ሥልጣናትና ሐይላት ላይም ድልን ትቀዳጃላችሁ፡፡
የዓለምን መሪዎች መታዘዝ ይገባችኋል ተብሎ ተነግሮዋችሁ አሁን ደግሞ የጨለማ ገዦችን መዋጋት እንደሚኖርባችሁ ሲነገራችሁ ግራ ተጋብታችሁ ይሆናል፡፡ በሮማውያን ዘመን የሮም ንጉሠ ነገሥት ራሱን አምላክ አድርጎ ይጠራ ነበር፡፡ ሕጉም ሰዎች ሁሉ እርሱን እንደ አምላክ እንዲቆጥሩት የሚጠይቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ክርስቲያኖች ሊያደርጉት የማይችሉት ነገር ነበር፡፡ ምክንያቱም ከእግዚአብሄር ቃል ጋር የሚቃረን ነበርና፡፡ ስለዚህ በዚያን ዘመን ክርስቲያኖች ራሱን አምላክ አድርጎ ሰዎች ሁሉ እንዲንበረከኩለት ያደረገውን የሮም ንጉሠ ነገሥት ከመዋጋት በቀር ምርጫ አልነበራቸውም፡፡ 
ከዲያብሎስ ጋር የሚደረገውን ውጊያ ለማሸነፍ በእግዚአብሄር ቃል ማመንና ቃሉንም አጥብቀን መያዝ አለብን፡፡ በእግዚአብሄር ቃል መሰረት የምንኖር ከሆንን የእርሱን በረከት እናገኝና ዲያብሎስንም ማሸነፍ እንችላለን፡፡ የዳንን ብንሆንም የእግዚአብሄርን ቃል አጥብቀን እስካልያዝን ድረስ ከሰይጣን ጋር በምናደርገው ጦርነት ተሸናፊዎች እንሆናለን፡፡ እግዚአብሄር አስጠንቅቆናል፡- ‹‹በመጠን ኑሩ ንቁም፤ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፡፡›› (1ኛ ጴጥሮስ 5፡8) በእግዚአብሄር ቃል የማያምን ሰው በቀላሉ በዲያብሎስ ሊጠቃ ይችላል፡፡ 
ኢየሱስም ቢሆን በእግዚአብሄር ቃል ባይሆን ኖሮ ሰይጣንን ማሸነፍ ባልቻለም ነበር፡፡ ‹‹ሰው ከእግዚአብሄር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎዋል፡፡›› (ማቴዎስ 4፡4) እርሱ በተጻፈው ቃል መሰረት በእምነት ዲያብሎስን አባረረ፡፡ እኛስ? እኛ ጥበብ ስለሚጎድለን ከኢየሱስ ጋር አንወዳደርም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄርን ቃል ማመንና አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል፡፡
‹‹ቃሎቹ እውነት እንደሆኑ አስባለሁ፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ላምንባቸው አልችልም›› ማለት አይኖርብንም፡፡ ቃሎቹን አጥብቀን መያዝ አለብን፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር በተጻፈው መሰረት እንደሚፈጸም አምናለሁ፡፡›› ትክክለኛው እምነት ይህ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ እንድንለብስም ይፈቅድልናል፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር ጌታችን በተናገረው መሰረት ይሆናል›› የሚሉ ሰዎች ይባረካሉ፡፡ አንድ ሰው የእግዚአብሄርን ቃል አጥብቆ ከያዘና ከተደገፈበት እንደ እምነቱ ነገሮች ሁሉ ይከናወኑለታል፡፡ ዲያብሎስ ሊፈትነን ቢሞክርም ‹‹በእግዚአብሄር ቃል አምናለሁ፤ ቃሉ ትክክለኛ መልሶች እንዳሉት አምናለሁ›› ስንል በእርግጥም ሸሽቶ ይሄዳል፡፡ ከዲያብሎስ ጋር የሚደረገውን ጦርነት የማሸነፊያው መንገድ ይህ ነው፡፡
 
 
የእግዚአብሄርን ቃል አጥብቀን መያዝ አለብን 
 
‹‹ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም ሁሉን ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ፡፡ እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምታችሁ ቁሙ፡፡ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፡፡ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡›› (ኤፌሶን 6፡13-17)     
በዚህ ምንባብ ላይ ‹‹ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ›› የሚለው የእግዚአብሄር ቃል በወገብ ላይ ከሚደረግ ቀበቶ ጋር መነጻጸሩን ያሳያል፡፡ ይህ ማለት አእምሮዋችንን በእግዚአብሄር ቃል ማስታጠቅ አለብን ማለት ነው፡፡   ከእግዚአብሄር ጋር በአእምሮ አንድ መሆን እንችል ዘንድ የእውነት ቃሎች እንድንከተል እየነገረን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ቀበቶ በሰውነት ዙሪያ ልክክ ሲል እኛም እንደዚሁ ራሳችንን ጥብቅ አድርገን ከእግዚአብሄር ቃል ጋር ማቆራኘት አለብን፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር በአሳብ አንድ በምንሆንበት ጊዜ   ‹‹ሁሉም ነገር በጎ እንደሚሆን አምናለሁ፤ ሁሉም ነገር እግዚአብሄር እንደተናገረው ይከናወናል›› ብለን ለማመንና ለመናገር እንችላለን፡፡    
በመቀጠል የጽድቅን ጥሩር መልበስ ይኖረብናል፡፡ እግዚአብሄር እንዳዳነን የሚናገረውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ጥሩር መልበስ አለብን፡፡ የጽድቅን ጥሩር በመልበስ ወገባችንን በእውነት መታጠቅ አለብን፡፡ የከበሩ ዕንቁዎች ያሉበትን ጥሩር መልበስ አለብን፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ይቅር እንዳለን በማመን ልንለብሳቸው ይገባናል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ከሙሉ ልባችን ልናምነው ይገባናል፡፡ ሰላምን የሚሰጠውን የደህንነት ወንጌልም መስበክ አለብን፡፡      
ከላይ የተጠቀሱትን ቃሎች በሙሉ ከያዝን በኋላ እግሮቻችንን በሰላም ወንጌል መዘጋጀት በመጫማት የእግዚአብሄር ሰላም ለሰዎች ሁሉ የሚሰጠውን የደህንነት ወንጌል መስበክ አለብን፡፡ ከሐጢያቶቻችን ድነን ከሆነ እምነታችንን በአንደበታችን መናገር አለብን፡፡ ሐጢያታችንና ክፉ ሥራችን በሚገለጥበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሄር አስቀድሞ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ይቅር ማለቱን በሚናገረው እውነት ላይ በመደገፍ ልናስወግዳቸው ይገባናል፡፡ ይህንን ያደረገው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ነው፡፡ እግዚአብሄርን በማመስገን የክብር ሕይወትን መኖር አለብን፡፡ ከሐጢያቶቹ ላልዳነው ሁሉ ሰላምን የሚሰጠውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል መስበክ ነው፡፡   
ከሁሉም በላይ ክፉውን በእምነት ጋሻ ልንዋጋው ይገባናል፡፡ ሰይጣን በሚያጠቃበት ጊዜ በአንድ እጃችን በያዝነው የእምነት ጋሻና በሌላው እጃችን በያዝነው የእውነት ቃል ልናባርረው ይገባናል፡፡
ከዚያም የመዳንን ራስ ቁር መልበስ አለብን፡፡ ‹‹በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ከሐጢያቶቼ ሁሉ ድኛለሁ፡፡ እግዚአብሄር በዚህ መንገድ ሐጢያቶቼን ይቅር ብሎዋል›› በማለት የደህንነትን ቃሎች መቀበል አለብን፡፡ እውነቱን በአእምሮዋችን መረዳት አለብን፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል፣ የመዳንን ራስ ቁርና የመንፈስን ሰይፍ ዲያብሎስን የምንቃወምባቸው የጦር መሳሪያዎች ማድረግ ይኖርብናል፡፡
ሰይጣን የሚያጠቃን ከሆነ ሰይፋችንን መዝዘን ልናጠቃው ይገባናል፡፡ ‹‹እግዚአብሄር እንዲህ አለ! እንዲህ መሆኑን አምናለሁ!›› በእግዚአብሄር ቃሎች ላይ ባለን እምነት ሰይጣንን እናባርረዋለን፡፡ በእግዚአብሄር ቃል አምናችሁ መንፈሳዊ ሰይፋችሁን ስትመዙ ሰይጣን ‹‹ኦውች! እንዴት ይጎዳል›› ብሎ በመጮህ ይሸሻል፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ብናምን ማንኛውንም አይነት የሰይጣን ጥቃት መመከት እንችላለን፡፡ 
‹‹ሥጋዬ ፍጹም አይደለም፤ ነገር ግን እኔ ቤዛነትን የተቀበልሁ የእግዚአብሄር ሰው ነኝ፡፡ እግዚአብሄር የነገረኝን ቃሎች አጥብቄ የያዝሁ የእግዚአብሄር ሰው ነኝ›› በማለት የዚህ አይነት ሐይማኖታዊ ሕይወት መኖር ይገባናል፡፡ የዚህ አይነት እምነት ካለን የታመነ ሕይወታችንን ለማተራመስና ለማኮላሸት በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ሰይጣንን በእውነት ሰይፍ ማባረር እንችላለን፡፡ ተራ በሆኑ ምድራዊ ቃሎች የአጸፋ ጥቃት ብንሰነዝር ሰይጣን ንቅንቅ እንኳን  አይልም፡፡ ስለዚህ ‹‹እግዚአብሄር የተናገረው ይህንን ነው›› በማለት ልንዋጋው ይገባናል፡፡ ያን ጊዜ ሰይጣን በእግዚአብሄር ቃል ሥልጣን ፊት ይማረካል፡፡  
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር የምንፈልግ ከሆነ ቤተክርስቲያን፣ ቅዱሳን ሁሉና የእግዚአብሄር ባሮች ወንጌልን ለመስበክ ራሳቸውን ይሰጡ ዘንድ ወደ እግዚአብሄር መጸለይ ይኖርብናል፡፡ ‹‹የወንጌልን ምስጢራት በድፍረት ልግለጥ›› ብለን በመጸለይ ወንጌልን በማገልገል ላይ ያነጣጠረ ሕይወት እንኖራለን፡፡ ይህ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር ለቅዱሳን ሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡ እኛ እውነተኛ ቅዱሳን ከሆንን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር አለብን፡፡ የሐጢያት ስርየትን መቀበል ለእያንዳንዱ ነፍስ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ የዚህ አይነት ሕይወትም እንደዚሁ ለቅዱሳን ሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ትዕዛዝ ነው፡፡      
ከሐጢያቶቻቸው ድነው እንዴት የታመነ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ የማያውቁ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት እንዳለ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እግዚአብሄር የሚሻው ይህንን ነው፡፡  ቅዱሳን የጌታ ፈቃድ የሆነውን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር አለባቸው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት በጎ ሥራዎችን በመስራት ወንጌልን እንዲሰብኩ ቅዱሳንን ያነሳሳቸዋል፡፡ እነርሱ ወንጌልን መስበክ ይወዳሉ፡፡ ወደ እግዚአብሄር ይጸልያሉ፡፡ በእግዚአብሄር ቃሎችም ያምናሉ፡፡ አጥብቀውም ይይዙዋቸዋል፡፡ የመዳንን ራስ ቁርና የጽድቅን ጥሩር መልበስና ‹‹እኔ ሁሌም ጻድቅ ነኝ›› በማለት ሰይጣንን ማባረር አለብን፡፡
ቅዱሳን ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ስላላቸው በመንፈስ ይመላለሳሉ፡፡ የመንፈስ ቅዱስንም ሐይል መቀበል ይችላሉ፡፡ በእምነት ጸሎት በተገኙት የእግዚአብሄር በረከቶች የእርሱን ሥራ ይሰራሉ፡፡ ሰይጣንን አሸንፈው በእግዚአብሄር ፊት እስከሚቆሙ ድረስ በመንፈስ መመላለስ ይኖርባቸዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ የሚለብሱ የእግዚአብሄር ሕዝቦች በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር የሚችሉ ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡
‹‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፤ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህን ከጨለማ ዓለም ገዥዎች ጋር፤ በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፋት መንፈሳውያን ሰራዊት ጋር ነው እንጂ፡፡›› (ኤፌሶን 6፡12) ዳግም የተወለዱ ሰዎች የሚዋጉት ውጊያ የሥጋና የደም ውጊያ አይደለም፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸው ሰዎች የሚዋጉት ውጊያ ከክፋት መንፈሳውያን ሰራዊቶችና የታመነ ሕይወታችንን ከሚቃወሙት፣ ወንጌልን ከማያገለግሉና ከሚረብሹን ጋር የሚደረግ ውጊያ ነው፡፡
ለጌታ ወንጌል መንፈሳዊ ጦርነትን ለመዋጋት ስንወጣ የመንፈስን ራስ ቁርና ዕቃ ጦር መልበስ አለብን፡፡ በዚህ ጦርነት ውስጥ ተራ ልብሶችን ብቻ ከለበስን እንቆስላለን፡፡ ስለዚህ ዕቃ ጦሩን መልበስ አለብን፡፡ ሰይፍ፣ ጋሻና ራስ ቁር ያስፈልጉናል፡፡ ጦርነቱን ለማሸነፍ ከጦርነቱ በፊት በሚገባ መዘጋጀት አለብን፡፡ ጥሩር መልበስ፣ ወገባችንን መታጠቅና  በእግሮቻችንም ጫማን መጫማት አለብን፡፡ ያን ጊዜ በሁለቱም እጆቻችን በያዝናቸው ሰይፍና ጋሻ ጠላቶቻችንን ማሰነፍ አለብን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት ይህ ነው፡፡
 
 
ውብ የሆነውን ወንጌል መጠበቅ አለብን
 
ጳውሎስ እንዲህ ነገረን፡- ‹‹መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ፡፡›› (2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡14) ጥሩ ተቀማጭ ምንድነው? ከሐጢያቶቻችን ያዳነን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ ቲቶ 3፡5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንደ ምህረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆን መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን፡፡›› ጌታችን በዚህ ዓለም ላይ የሰራናቸውን ሐጢያቶች በሙሉ አንጽቶ በመስቀል ላይ ሞተ፤ ከዚያም ተነሳ፡፡ ይህንን ውብ ወንጌል መጠበቅ አለብን፡፡ የመዳንን ራስ ቁርና የጽድቅን ጥሩር መልበስ አለብን፡፡ ወገባችንንም በእውነት መታጠቅ አለብን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን አለብን፡፡
ራሳችንን በዚህ መንገድ ካስታጠቅን በኋላ በሰይጣን ላይ የከፈትውን ጦርነት ማሸነፍ አለብን፡፡ ድልን የምንቀዳጀውና ይህንንም ከሌሎች ጋር የምንጋራው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣንን በመቃወም ብዙ መንፈሳዊ ውጊያዎችን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ወደ ጌታ መንግስት እስከምንገባበት ቀን ድረስም ብዙ ድሎችን ከእርሱ መንጠቅ አለብን፡፡ ባላጋራችንን በመቃወም ብዙ ጦርነቶችን ባሸነፍን ቁጥር ቀጣዩ ጦርነት እየቀለለ ይሄዳል፡፡ የእርሱ መንግሥት እንዲሰፋና እንዲያድግ ሁላችንም መጸለይ ይገባናል፡፡ ያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት እናገኛለን፡፡
ለሐጢያቶቻችን ይቅርታን በማግኘታችን መርካት አይኖርብንም፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር አለብን፡፡ ለወንጌልና ለበጎ ሥራዎቻችን ስንል በእግዚአብሄር ቃል ማመን አለብን፡፡ ከሰይጣን ጋር የምናደርገውን ውጊያ ተሸንፈን እንዳንጠፋ በመንፈስ ቅዱስ መመራትና የእግዚአብሄርን ቃል መጠበቅ እንደዚሁም ማመን አለብን፡፡
አስተውላችሁኛልን? በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን የምንኖረው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንደምታገለግሉ፣ በእግዚአብሄር ቃል ላይ እንደምትደገፉና እንደምትከተሉት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሁላችንም ሰዎችን ከሰይጣን የማዳን ሥራ እንስራ፡፡ ጌታ ዳግመኛ እስኪመጣ ድረስ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሕይወቶችን መምራት እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን ሁለተኛው ትዕዛዝ የመንፈስ ቅዱስን ሙላት መቀበል ነው፡፡ አመስግኑት፤ በልባችን ውስጥ የሐጢያት ስርየት ስላለ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ሊኖረን ይችላል፡፡ በዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ባይሆን ኖሮ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መጀመር አንችልም ነበር፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሕይወቶችን እንድንመራ ስለፈቀደልን ጌታን አመሰግናለሁ፡፡
ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ሊኖራችሁ እንደሚችል ታምናላችሁን? የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ ያገኘን ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ይኖረናል፡፡ ነገር ግን ሐጢያቶቻቸው ያልተፋቁላቸው ሰዎች ገና ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የላቸውም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የማያውቁ ወይም የማያምኑ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የላቸውም፡፡ በአለም ላይ ሰዎች ሁሉ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ከሌላቸው ወደ ሲዖል ይጣላሉ፡፡ 
እኛ በልባችን ውስጥ ሐጢያቶች ስለሌሉብን ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ አለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ በልቦቻችን ውስጥ ስለሚያድር በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት መኖር እንችላለን፡፡ እኛ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያለን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት የመንፈስን መሻት መታዘዝ አለብን፡፡ የመንፈስን መሻት አብዝተን በታዘዝን ቁጥር ሙሉ የጦር ዕቃ እንደለበሰ አርበኛ እምነታችን ይበልጥ ብርቱ ይሆናል፡፡ ነገር ግን መንፈስን መታዘዝ ከተሳነን የጦር ዕቃችንን ያወለቅን ያህል ለእኛ ተመሳሳይ ነው፡፡   
በመንፈስ ቅዱስ ቃሎች አማካይነት እያደግን የእምነት ሰው እንሁን፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ቃሎች ስንሰማ እምነታችን ይዳብራል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡›› (ሮሜ 10፡17) ስለዚህ ሰይጣን ቢያጠቃንም በእነዚህ ቃሎች በእምነት እንጠበቃለን፡፡ ሰይጣን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የእምነትን ጋሻ የታጠቁትን ማጥቃት አይችልም፡፡ ታማኝ የሆኑ ሰዎች የሰይጣንን ጥቃቶች በእምነታቸው መከላከል ይችላሉ፡፡
በእምነት አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን እንኑር፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በታማኝነት በዓለም ሁሉ የሚሰብክ ሕይወትን ያመለክታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት የዚህ አይነት ነው፡፡