Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-13] የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎችና ስጦታዎች ‹‹ ዮሐንስ 16፡5-11 ››

የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎችና ስጦታዎች
‹‹ ዮሐንስ 16፡5-11 ››
‹‹አሁን ግን ወደላከኝ እሄዳለሁ፤ ከእናንተም፡- ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም፡፡ ነገር ግን ይህን ስለተናገርኋችሁ ሐዘን በልባችሁ ሞልቷል፡፡ እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል፡፡ እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ፡፡ እርሱም መጥቶ ስለ ሐጢአት፣ ስለ ጽድቅም፣ ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፡፡ ስለ ሐጢአት በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፡፡ ስለ ፍርድም የዚህ ዓለም ገዥ ስለተፈረደበት ነው፡፡››   
 
 
የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎችምንድናቸው?
እርሱ ዓለምን ስለ ሐጢያት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ይወቅሳል፡፡
 
ዘፍጥረት 1፡2 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ምድርም ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም፡፡ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበር፤ የእግዚአብሄርም መንፈስ በውሃ ላይ ሰፍፎ ነበር፡፡›› መንፈስ ቅዱስ የሚያድረወ ውብ በሆነው ወንጌል በሚያምኑ ሰዎች ልብ ውስጥ ብቻ እንጂ በውዥንብርና በሐጢያት በተሞላ ልብ ውስጥ እንዳልሆነ ከዚህ ምንባብ ማየት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ግራ በመጋባታቸውና በባዶነት በመሞላታቸው በልባቸው ውስጥ ሐጢያት እያለባቸው ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል እንደሚፈልጉ በመናገር በጥራዝ ነጠቅ እምነት ተጽዕኖ ስር ይወድቃሉ፡፡  
በጥራዝ ነጠቅ ከልክ ያለፈ ስሜት ሁኔታ ውስጥ በመሆን ቅቡልነት ያገኘ መንፈስ ውብ መንፈስ አይደለም፡፡ የሰይጣን ሥራ ጥራዝ ነጠቅነት ውስጥ ባሉ አመጸኛ ምዕመናን ላይ ያርፋል፡፡ ጥራዝ ነጠቅ ሰዎችም በቀላሉ በሰይጣን ማታለያዎችና ሐይል ተጽዕኖ ስር ይወድቃሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን አእምሮ፣ ስሜትና ግልጽ የሆነ ፈቃድ ያለው ሰብዕ አምላክ ነው፡፡ ይህንን ዓለም በመፍጠር ከእግዚአብሄር አብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሰራ፡፡ አሁንመንፈስ ቅዱስ በዚህ ዓለም ላይ ምን አይነት ሥራ እንደሰራ እንማራለን፡፡
 
 

መንፈስ ቅዱስ ዓለምን ስለ ሐጢያት ይወቅሳል 

 
መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ የሰራው ሥራ ምንድነው? ዓለምን ስለ ሐጢያት ወቀሰ፡፡ በእርሱ የተወቀሱት ሰዎችም በዮሐንስ በኩል የሆነውን የኢየሱስን ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን ውብ ወንጌል ያልተቀበሉት ናቸው፡፡ እርሱ ሐጢያተኞችንና ውብ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የማያምኑትን ሰዎች ሐጢያቶች ይወቅሳል፡፡
 
 

ዓለምን ስለ እግዚአብሄር ጽድቅ ይወቅሳል

 
መንፈስ ቅዱስ ያደረገው ሁለተኛው ነገር ምንድነው? ስለ እግዚአብሄር ጽድቅና ኢየሱስ ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን ስለፈጸመው ሥራ መሰከረ፡፡ ዮሐንስ 16፡10 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህ በኋላም ስለማታዩኝ ነው፡፡›› በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሄር ጽድቅ ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ይህ ማለት ኢየሱስ በዮሐንስ በኩል በሆነው ጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወሰደ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በእግዚአብሄር ጽድቅ አማካይነት ጻድቅ መሆን ይችላል የሚል እውነት ነው፡፡ ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠመቀና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ተቀበለ፡፡ ደሙንም በመስቀል ላይ አፈሰሰ፡፡ ከሙታንም ተነሣ፡፡ የሐጢያተኞችም አዳኝ ሆነ፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን ውብ ወንጌል ይህ ነው፡፡ ኢየሱስ በእግዚአብሄር ፈቃድ መሰረት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በውሃውና በደሙ አማካይነት ወሰደና የሕይወታችንም ጌታ ሆነ፡፡
መንፈስ ቅዱስ በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ እንዲያምኑ ያግዛቸዋል፤ በዚህም ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ በሥላሴ ውስጥ የሚሰራው የእግዚአብሄር ሥራ አጋዥ ሥራ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ውብ ለሆነው ወንጌል በመስራት ሰዎች በእግዚአብሄር ፍቅር እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል፡፡ እውነተኛው ውብ የውሃና የመንፈስ ወንጌልም እውነት እንደሆነ ዋስትና ይሰጣል፡፡
 
 

ዓለምን ስለ ፍርድ ይወቅሳል 

 
ሦስተኛው የመንፈስ ቅዱስ ተግባር ምንድነው? እርሱ የሰይጣንን ሥራዎች ያፈርሳል፡፡ ሰይጣን ‹‹በኢየሱስ ማመን ትችላለህ፤ ነገር ግን ክርስትናን በምድር ላይ ካሉት ብዙ ሐይማኖቶች እንደ አንዱ አድርገህ አስበው›› በማለት በሰዎች አእምሮ ውስጥ ያንሾካሹካል፡፡ ሰይጣን ሰዎች በኢየሱስ ቢያምኑም ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን እንዳያገኙ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ባፈሰሰው ደሙ እንዳያምኑ ዕንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡ ሰይጣን ክርስትናን ‹‹ተራ›› ወደሆነ ሐይማኖት ስላዘቀጠው ብዙ ሰዎች ኢየሱስን የማመኑ ምክንያት ጥሩ ሰዎች ለመሆን ነው የሚለው የሰይጣን ማታለያ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስን የማመኑ እውነተኛ አላማ ጻድቅ ሰዎች ሆኖ ዳግም ለመወለድ ነው፡፡
ሐሰተኛ እምነት ሊኖራችሁ አይገባም፡፡ ምንም ያህል በኢየሱስ ብታምኑም ሐሰተኛ እምነት ሊቀድሳችሁ አይችልም፡፡ ሐሰተኛ እምነት ከያዛችሁ ከሰይጣን ውሸቶች የተነሳ ኢየሱስን ማወቅ ወይም ጥርት አድርጋችሁ ማየት ያዳግታችኋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ውብ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ለዳኑት የደህንነት ዋስትና ሆነ፡፡ በልባቸው ውስጥ ሐጢያት ያለባቸው ሰዎች የሚያምኑት እምነት በሙሉ ዋጋ የለውም፡፡
መንፈስ ቅዱስ ውብ ስለሆነው ወንጌል እውነት ይመሰክራል፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ ተጠመቀና የሐጢያትን ዋጋ ለመክፈል ተሰቀለ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእውነተኛው ወንጌል በማመን ለሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይቅርታን ያገኙ ዘንድ በዓለም ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ይመክራል፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የሚወቅሰውና የሚኮንነው ውብ የሆነውን ወንጌል በልባቸው ያልተቀበሉትን ሰዎች እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል፡፡
 
 
ሁሉም ሰው የተባረከ እምነት ሊኖረው ይገባል
 
የተባረከ እምነት ምንድነው? በሐጢያት ይቅርታ አማካይነት ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ እንድንቀበል የሚያስችለን እምነት ነው፡፡ ሆኖም በኢየሱስ ላይ ያላቸውን አመኔታ ለረጅም ጊዜ ይዘውት ቢቆዩም አሁንም ድረስ በልቦቻቸው ውስጥ ሐጢያት ያለባቸውን ብዙ ክርስቲያኖች በዓለም ላይ ማየት ይቻላል፡፡ ለረጅም ጊዜ በኢየሱስ   ቢያምኑም ይበልጥ ሐጢያተኞች ይሆናሉ፡፡ ከሐጢያቶቻቸው ነጻ ይወጡ ዘንድ ያደናቀፋቸው እጅግ ትልቁ ችግር በልሳን መናገርና ራዕዮችን ማየት መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ማስረጃ እንደሆነ ማሰባቸው ነው፡፡ እግዚአብሄር ስለ ሐጢያቶቻቸው እንደሚፈርድባቸው አያውቁም፡፡ 
በዚህ ዓለም ላይ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ከሰይጣን ሥራ መለየት አልቻሉም፡፡ የሰይጣን ሥራ የተሳሳቱ እምነቶችን በመስጠትና ወደ ጥፋት በመምራት ሰዎችን ወደ ውዥንብር ይመራል፡፡ ሰይጣን እግዚአብሄርን በመቃወም ለማሳካት የሚሞክረው ይህንን ነው፡፡ ሰይጣን ሰዎችን በባዕድ አምልኮ አመኔታዎች ተጽዕኖ ስር እንዲወድቁ ያደርግና የእርሱ ባሮች አድርጎ ይማርካቸዋል፡፡ ሰይጣን መለኮታዊ ተአምራቶችንና ድንቆችን የመለማመድን ፍላጎት በውስጣቸው በማስቀመጥ እነዚህ ልምምዶች ውብ በሆነው ወንጌል አማካይነት መንፈስ ቅዱስን ከመቀበል ይልቅ የበለጠ ዋጋ እንዳላቸው እንዲያስቡ ያደርጋል፡፡
መንፈስ ቅዱስ ግን ሰዎች የእግዚአብሄርን ዓለም በቃሉ አማካይነት እንዲያዩ ይፈቅድላቸዋል፡፡ እነርሱ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነትም እግዚአብሄር ሰዎችን እንደፈጠረ፣ እንደሚወዳቸውና ሊያድናቸውም እንደሚፈልግ ወደ ማወቁና ወደ ማመኑ ይመጣሉ፡፡ እርሱ ለሐጢያተኞች ያለው ዕቅድ ኢየሱስ ክርስቶስ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ከሐጢያቶቻቸው እንዲያድናቸውና በእምነትም በፍቅሩ እንዲኖሩ መጋበዝ ነው፡፡ 
1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡›› 1ኛ ጴጥሮስ 1፡23 ደግሞ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለምና፤ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሄር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡››
የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ሰው ስለ ሐጢያት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ያለውን እውነት አብርሆት እንዲያገኝና በእነዚህ  እውነቶች እንዲያምን ማድረግ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ስለ እግዚአብሄር ፍርድ እንዲያውቁና ውብ በሆነው የኢየሱስ ጥምቀት ወንጌልና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ እንዲድኑ ይፈቅድላቸዋል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሲያምኑ መንፈስ ቅዱስ ከእነርሱ ጋር በውስጣቸው ያለ የመሆኑን እውቀት ይሰጣቸዋል፡፡
እስከ አሁን ድረስ መንፈስ ቅዱስ የሚሰራቸውን ሥራዎች ሁሉ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስና የእግዚአብሄርን ፍቅር ማግኘት የሚችሉት ውብ በሆነው የኢየሱስ የውሃና የመንፈስ ወንጌል አምነው የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ሲቀበሉ ብቻ ነው፡፡
 
 
የመንፈስ ቅዱስ ማንነት
 
መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡ የማንነትን መሰረታዊ ባህርያት ማለትም እውቀትን ስሜትንና ፈቃድን ይዞዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ እውቀት ስላለው የእግዚአብሄርን ጥልቅ ነገሮችና (1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10) የሰዎችን ልቦች እንኳን ሳይቀር ይመረምራል፡፡   
መንፈስ ቅዱስ ስሜት ስላለው የእግዚአብሄርን ቃል በሚያምኑት ሲደሰት በማያምኑት ግን በጣሙን ያዝናል፡፡ ጻድቃንም እንደዚሁ የእግዚአብሄር ፍቅር ስሜቱ የሚሰማቸው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስ ‹‹አጽናኝ›› ተብሎም ተጠርቷል፡፡ ይህ ማለት መንፈስ ቅዱስ ጻድቃንን በችግሮቻቸው ይረዳቸውና ጠላቶቻቸውንም ይዋጋላቸዋል ማለት ነው፡፡ እርሱ ልክ እንደ እኛ እንደ ሰዎች እውቀት፣ ስሜትና ፈቃድ አለው፡፡ ውብ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በሚያምኑት ውስጥም ያድራል፡፡
 
 
የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደሚከተለው ነው
 
መንፈስ ቅዱስ ሰዎች የሐጢያት ይቅርታን እውነት እንዲረዱ ይፈቅድላቸውና በምዕመናን ልቦች ውስጥም ያድራል፡፡ የእርሱ ሥራ ኢየሱስ በጥምቀቱና በደሙ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ የመውሰዱን እውነት መመስከር ነው፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 5፡6-8) በማናቸውም ችግር ውስጥ ያሉትን ባሮቹንና ቅዱሳኑን በማጽናናት ዳግመኛ እንዲቆሙ ያበረታቸዋል፡፡ ምን እንደሚጸልዩ በማያውቁበት ጊዜም ይማልድላቸዋል፡፡ (ሮሜ 8፡26) በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ላሉት ጻድቃንም ዕረፍትን በመስጠት ወደ ቃሎቹ ሙላት ይመራቸዋል፡፡ (መዝሙረ ዳዊት 23)
 
 
የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተዛመደ ነው
 
መንፈስ ቅዱስ ጻድቃን እውነቱን በልባቸው አውቀውና አምነው ለሌሎች እንዲሰብኩ ይመራቸዋል፡፡ ‹‹የእግዚአብሄር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን የእግዚአብሄር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል፡፡›› (2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16)
‹‹በእግዚአብሄር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም አፌ አዝዞአልና፡፡ መንፈሱም ሰብስቦአቸዋልና፤ ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፤ ባልንጀራውንም የሚያጣ የለም፡፡›› (ኢሳይያስ 34፡16)
‹‹ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፡፡ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ዳሩ ግን በእግዚአብሄር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ፡፡›› (2ኛ ጴጥሮስ 1፡20-21)
መንፈስ ቅዱስ እናነበው ዘንድ የእግዚአብሄርን ቃል ይጽፉ ዘንድ የአምላክን ባሮች በመንፈስ ሞላቸው፡፡ ሰዎችንም ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ጋር አስተዋወቀና ለዓለም እንዲሰብኩ መራቸው፡፡ ስለዚህ ጻድቃን በሕይወታቸው ብዙ መከራዎች ቢገጥሙዋቸውም ለመንፈስ ቅዱስ ሐይል ምስጋና ይግባውና ሁሉንም ማሸነፍ ይችላሉ፡፡
 
 
የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችና ፍሬ
 
የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ማለት ውብ የሆነውን የእግዚአብሄር ወንጌል ለሌሎች ያሰራጩ ዘንድ ለቅዱሳኖች የሰጣቸው ችሎታዎች ማለት ናቸው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን እርሱ በሰጣቸው ስጦታዎች የእግዚአብሄርን ሥራ ለመስራት ራሳቸውን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለጌታ ክብርን እንዲሰጡ ይረዳቸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 12፡7)
የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አላማ ቅዱሳንን በእምነት ማስታጠቅና ከፊታቸው ያለውን ሩጫ እንዲሮጡ መርዳት ነው፡፡ (ኤፌሶን 4፡11-12) መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ያሰራጩ ዘንድ ለእግዚአብሄር ባሮችና ለቅዱሳን ችሎታዎችን ሰጥቶዋቸዋል፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደሱ ቅዱሳን ማህበረሰብ ነች፡፡ (1ኛ ቆሮንቶስ 1፡2)
ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ ስለሆነ መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ እያንዳንዱ ክርስቲያን በተሰጠው ሥልጣንና ተግባራት መሰረት መስራት ይኖርበታል፡፡ ቅዱሳን ለእግዚአብሄር መንግሥት ይሰሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ አስተውሎትንና ችሎታን ይሰጣቸዋል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን የወንጌል ክብር ለመግለጥ እያንዳንዱን ነገር ያደርጋል፡፡ እርሱ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሄር ክብር አድርጉት፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 10፡31)
 
 
የተለያዩ አይነት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች
 
12 አይነት የተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ስጦታዎች ለተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መልኮች እንደተገለጡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማየት እንችላለን፡፡ የስጦታዎቹ ረዘም ያለ ዝርዝር በሮሜ 12፡6-8፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡8-10 እና በኤፌሶን 4፡11 ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡ ቀጣዮቹ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12 ውስጥ የተነገሩት ዘጠኙ መንፈሳዊ ስጦታዎች ናቸው፡፡
1) የእውቀት ቃል፡- ይህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንድንረዳ መንፈሳዊ ምሪትን ይሰጠንና ይህንን ውብ የሖነ ወንጌልም እንድንሰብክ ይፈቅድልናል፡፡
2) የጥበብ ቃል፡- ይህ በጻድቃን ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን በርካታ ችግሮች በተጻፉት የእግዚአብሄር ቃሎች አማካይነት የማቃለል ችሎታ ነው፡፡
3) እምነት፡- መንፈስ ቅዱስ ቅዱሳን ነፍሳቶችን ከሐጢያቶቻቸውና ከሰይጣን የማዳን ተዓምራትን ይፈጽሙ ዘንድ ጠንካራ እምነትና መተማመን ይሰጣቸዋል፡፡ ጻድቃን የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ያገኛሉ፤ በእምነት ሐይል አማካይነትም መንፈሳዊ መዛባቶቻቸውን ይፈውሳሉ፡፡
4) ፈውሶች፡- መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሄር ቃል ላይ ባላቸው እምነት አማካይነት ጻድቃን ሰዎችን የመፈወስ ስጦታን ይሰጣቸዋል፡፡
5) ተዓምራትን ማድረግ፡- ይህ ቅዱሳን በእግዚአብሄር ቃል በማመን የእግዚአብሄርን ሥራ እንዲሰሩ የሚፈቅድላቸው አስገራሚ ስጦታ ነው፡፡ ተዓምር ከሰው የተፈጥሮ ሕግ እውቀት ልቆ በእምነት በኩል ከልዕለ ተፈጥሮ በላይ የሚሆን ነገር ነው፡፡
6) ትንቢት፡- በዚህ ዘመን በተጻፈው መሰረት ትንቢት መናገር የሚችሉት በእግዚአብሄር ቃል የሚያምኑና ያንንም የሚታዘዙት ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፈው ላይ ያልተመሰረቱ አመኔታዎች የሌለው ሰው ቃሎች   እውነተኛ ትንቢት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸው የእግዚአብሄር ባሮች የእግዚአብሄርን ቃል ይሰብኩና በዚያውም የእግዚአብሄር አካል በሆነችው ቤተክርስቲያን አማካይነት ሥራውን እንዲሰሩ ያንጹዋቸዋል፤ ያደፋፍሩዋቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ይህንን ችሎታ ለእግዚአብሄር ባሮችና ለቅዱሳን ሰጠ፡፡
7) መናፍስትን መለየት፡- ይህ አንድ ሰው ሐጢያቶቹ ይቅር ተብለውለት እንደሆነና እንዳልሆነ የመወሰን ችሎታ ነው፡፡ ይህ ስጦታ ከሌለን በሰይጣን ልንታለል እንችላለን፡፡ አለም በሰይጣን ቁጥጥር ስር ስለሆነ ይህንን ስጦታ ማግኘት የምንችለው እግዚአብሄር በሰጠን ውብ የሆነ ወንጌል በማመንና በዚህ ዓለም ላይ ያሉትን መከራዎች ሸክሞችና ክፋቶች በማሸነፍ ነው፡፡ ጻድቅ ሰው ይህንን ስጦታ የሚቀበለው በእውነተኛው ወንጌል በማመን ነው፡፡ በዚህም አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ሐጢያት እንዳለና እንደሌለ መናገር ይችላል፡፡
8) በልሳን መናገር፡- መጽሐፍ ቅዱስ በልሳን ስለ መናገር ይነግረናል፡፡ ‹‹ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማህበር ዕልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 14፡19) ቅዱስ ሰው ራሱ ሊያስተውለው የማይችለውን ልሳን ከመናገር ይልቅ የእግዚአብሄርን የእውነተ ቃል መረዳት የበለጠ ጠቀሜታ እንዳለው ማወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ በልሳን ከመናገር መታቀብ አለበት፡፡
9) የልሳን ቋንቋን መተርጎም፡- ይህ ስጦታ ለደቀ መዛሙርት የተሰጠው በጥንቷ ቤተክርስቲያን ዘመን ወንጌልን እንዲሰብኩ ለማድረግ ነበር፡፡ ዛሬ መንፈስ ቅዱስ በትርጉም አገልግሎትና መልዕክቶችን ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎም ወንጌልን እያሰራጨ ነው፡፡ ወንጌልን የሚሰብከው ግለሰብ ሌሎች ቋንቋዎችን ሁሉ መናገር የሚችል ከሆነ አስተርጓሚ አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን የቋንቋ ችግሮች በሚገጥሙን ጊዜ እግዚአብሄር ሥራውን ለመፈጸም ሁልጊዜም በሥርዓተ አልበኝነት ወይም ከልክ ባለፈ ስሜት ውስጥ አይሰራም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ውብ በሆነው ወንጌል በኩል በመስራት ቅዱሳን ወንጌልን ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች እንዲተረጉሙ ይመራቸዋል፡፡
 
 
የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ምንድናቸው?  
 
የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይነግረናል፡፡ ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው፡፡ እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም፡፡›› (ገላትያ 5፡22-23)
1) ፍቅር፡- ለጻድቃን እውነተኛ ፍቅር ማለት ሐጢያተኞችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን ውብ የሆነውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል መስበክ ማለት ነው፡፡ ጻድቃን እውነተኛው የኢየሱስ ፍቅር የሚገልጠው ውብ ወንጌል ስላላቸው የእውነተኛውን ወንጌል ፍቅር ይሰብካሉ፡፡ ለሌሎች ነፍሳቶችም እውነተኛ ፍቅር አላቸው፡፡
2) ደስታ፡- ይህ ዳግም በምንወለድበት ጊዜ ከልባችን ጥልቅ ውስጥ ፈልቆ የሚወጣ ሊገለጥ የማይችል የከበረ ሐሴት ነው፡፡ ጻድቅ ሰው ለሐጢያቶቹ ሁሉ ይቅርታን ስላገኘ በልቡ ውስጥ ደስታ አለው፡፡ (ፊልጵስዩስ 4፡4) በጻድቅ ልብ ውስጥ ደስታ ስላለ ደስታውን ከሌሎች ሰዎች ጋር የመጋራት ችሎታ አለው፡፡
3) ሰላም፡- በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመኑ የሐጢያቶቹን ይቅርታ ላገኘ ሰው የተሰጠ የሰላም ልብ ይህ ነው፡፡ ጻድቁ ውብ የሆነውን የሰላም ወንጌል እንዲሰብክ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህንን ውብ የሆነ የሰላም ወንጌል የሰሙ ሰዎች ሌሎችም የዓለም ሐጢያቶችን አሸንፈው በደህንነት ስጦታ ብርቱ እምነትና መተማመን እንዲኖራቸው መምራት ይችላሉ፡፡ በእግዚአብሄርና በሰው ዘር መካከል ሰላምን የሚፈጥሩ ጻድቃን የእግዚአብሄር ልጆች ተብለው የተጠሩ ናቸው፡፡ (ማቴዎስ 5፡9) ሌሎችም የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ እንዲያገኙ ይመሩዋቸዋል፡፡ (ምሳሌ 12፡20) መንፈስ ቅዱስ የጽድቅ ሕይወትን እንዲኖሩና ያማረውን ወንጌል በማሰራጨትም ሌሎችን በሰላም እንዲባርኩ ጻድቃንን ይመራቸዋል፡፡
4) ታጋሽነት፡- እውነተኛውን ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው በዳኑት ጻድቃን ልብ ውስጥ የትዕግስት ፍሬዎች አሉ፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ሕብረት በማድረግ ይህንን ፍሬ መያዝ እንችላለን፡፡ ጻድቁ የትዕግስትና የቻይነት ልብ አለው፡፡
5) በጎነት፡- እግዚአብሄር በሐጢያት በተሞላን ጊዜ ምህረትን ሰጠን፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነን፡፡ ኢየሱስ ስለማረንና ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ስለደመሰሰ በእርሱ ስላመንንና ጸጋውንም ስለተቀበልን እኛም ሌሎችን ልንወድና ምህረትን ልናደርግላቸው እንችላለን፡፡
6) ቸርነት፡- እዚህ ላይ ቸርነት ማለት ‹‹ጥሩ ትሩፋት›› ማለት ነው፡፡ ጻድቃን በልባቸው ጥልቅ ውስጥ ቸርነትና እምነት አላቸው፡፡
7) እምነት፡- ይህ በእግዚአብሄር እምነት የተሞላ ልብ ማለት ነው፡፡ በቅዱሳን ውስጥ ያለው ታማኝነት የሚመጣው ለኢየሱስ ታማኝ ከመሆን ነው፡፡
8) የውሃት፡- ይህ ማለት ሌሎችን በሚገባ የመረዳትና እነርሱንም በልባችን ውስጥ ከልባችንና በደግነት አጥብቀን የመያዝ ችሎታ ማለት ነው፡፡ ጻድቃን ጠላቶቻቸውን የሚወዱበትና ለደህንነታቸውም የሚጸልዩበት ልቦች አሉዋቸው፡፡
9) ራስን መግዛት፡- ራስን መግዛት ራስን የመምራት፣ የባከነ ሕይወትን የማስወገድና በፈንታው ራስን የመቆጣጠርና የመግዛት ችሎታ ነው፡፡
 
 
በመንፈስ ቅዱስ መሞላት
 
በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ውጤት ምንድነው? ይህንን በረከት መቀuል ቅዱሳን ራሳቸውን ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ጋር ቀላቅለው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነው እንዲኖሩ ይፈቅድላቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ጻድቃን የጽድቅ መሳሪያዎች እንዲሆኑና የክርስቶስን ፈቃድ ለመፈጸምም ራሳቸውን ቀድሰው እንዲሰጡ ያስችላቸዋል፡፡ የጻድቃን ፈቃድ በጌታ ፈቃድ ቁጥጥር ስር ነው፡፡ እነርሱም በፈቃዳቸው ያላቸውንና መክሊቶቻቸውን በሙሉ ለእርሱ ቀድሰው ይሰጣሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ጻድቃን የዓለምን ሐጢያቶች በድል አድራጊነት ስሜት የማሸነፍ የደስታና የመተማመን ኑሮን እንዲኖሩ እንጂ በመንፈሳዊ ድህነት፣ ሽንፈት ወይም ፍርሃት ውስጥ እንዲኖሩ አያደርግም፡፡ (ሮሜ ምዕራፍ 7)
‹‹ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ሐይልን ትቀበላላችሁ፡፡ በኢየሩሳሌም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 1፡8) የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ጻድቃን ወንጌልን እንዲሰብኩ ይመራቸዋል፡፡
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ባደረባቸው ውስጥ ብርቱ የሆነ እምነትን ሰጣቸው፡፡ ውብ በሆነው የኢየሱስ ወንጌል ላይ ባላቸው እምነት ሐጢያቶቻቸው ይቅር ለተባሉ ሰዎች  የእግዚአብሄርን ልጅነት መብት ሰጣቸው፡፡ (ዮሐንስ 1፡12) በእምነት አማካይነት የእግዚአብሄር ልጆች የሆኑ ጻድቃን በዚህ ዓለም ላይ ውብ የሆነውን ወንጌል መስበክ ይችላሉ፡፡
ጻድቃን ለሐጢያቶች ይቅርታ በተሰጠው ወንጌል አማካይነት ሰይጣንን የማሸነፍ ችሎታ አላቸው፡፡ መንፈሳዊ ደዌዎችንም የመፈወስ ሐይል አላቸው፡፡ (ማርቆስ 16፡18) የሰይጣንን ሥልጣን የመርገጥና (ሉቃስ 10፡19) መንግሥተ ሰማያት የመግባት ሥልጣን አላቸው፡፡ (ዮሐንስ ራዕ 22፡14) ጻድቃን በእግዚአብሄር የተስፋ ቃሎች በማመን እንደ ነገሥታት ሆነው በዚያው ሥልጣን ይኖራሉ፡፡ (2ኛ ቆሮንቶስ 6፡17-18)
መንፈስ ቅዱስ ጻድቃን ዓለማዊ ፍትወታቸውን ሁሉ እንዲያራግፉ ያደርጋቸዋል፡፡ እውነተኛውን ወንጌል እንድንሰብክም ይመራናል፡፡ (ገላትያ 5፡6)
መንፈስ ቅዱስ ጻድቃን ውብ የሆነውን ወንጌል አንብበው እንዲያምኑና ለሌሎች እንዲያስተምሩ ያደርጋል፡፡ (1ኛ ጢሞቴዎስ 4፡13)
መንፈስ ቅዱስ ጻድቃንን በየቀኑ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ይሰበስባቸዋል፡፡ (ዕብራውያን 10፡25)
መንፈስ ቅዱስ ጻድቃን ልባቸውን በእውነት ብርሃን መግለጥ ይችሉ ዘንድ ሐጢያቶቻቸውን እንዲናዘዙ ያደርጋል፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 1፡9፤ ኤፌሶን 5፡13)
መንፈስ ቅዱስ ጻድቃንን በሕይወታቸው በቀና መንገድ ይመራቸዋል፡፡ (መዝሙረ ዳዊት 23)
መንፈስ ቅዱስ ጻድቃንን የእርሱን ስጦታዎች እንዳያጠፉ ይነግራቸዋል፡፡ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፡19)
መንፈስ ቅዱስ ድንቅ በሆነው ወንጌል በኩል ታላላቅ ሥራዎችን ይሰራል፡፡ (ማርቆስ 16፡17-18)
መንፈስ ቅዱስ ጻድቃን ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ጋር በመቀላቀል የጌታ ደቀ መዛሙርት ሆነው እንዲኖሩ ይመራቸዋል፡፡ ጻድቃን ውብ የሆነውን ወንጌል በመስበክና በመንፈስ ቅዱስ በመሞላት መንፈሳዊ ሕይወትን እንዲኖሩ ይመራቸዋል፡፡ ይህ ድንቅ በሆነው ወንጌል አማካይነት የሚከናወን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው፡፡ (1ኛ ጴጥሮስ 2፡9)
እርሱ በዚህች ቅጽበት በቅዱሳን ልቦች ውስጥ እየሰራ ነው፡፡ ሐሌሉያ!