Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 10-2] እውነተኛ እምነት ከመስማት ይመጣል፡፡ ‹‹ሮሜ 10፡16-21››

‹‹ሮሜ 10፡16-21››
‹‹ነገር ግን ሁሉ ለምስራቹ ቃል አልታዘዙም፡፡ ኢሳይያስ፡- ጌታ ሆይ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአል፡፡ እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ ዳሩ ግን፡- ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ፡፡ በእውነት ድምጻቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ፡፡ ነገር ግን እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ፡፡ ሙሴ አስቀድሞ እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ፡፡ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ ብሎአል፡፡ ኢሳይያስም ደፍሮ፡- ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፤ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ አለ፡፡ ስለ እስራኤል ግን፡- ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል፡፡››
 
 
ቁጥር 17 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡›› አንድን ሰው ከሐጢያቶቹ የሚያድነው እምነት የሚመጣው ከየት ነው? እውነተኛ እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ቃል በመስማት ነው፡፡
 
እኔ በቃሉ አማካይነት የእግዚአብሄርን ጽድቅ ወንጌል በመመስከር መቀጠልን እወዳለሁ፡፡ ሮሜ 3፡10-20ን በመመልከት እንጀምር፡፡
 
‹‹እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ እግዚአብሄርንም የሚፈልግ የለም፡፡ ሁሉም ተሳስተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፡፡ ቸርነትን የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም፡፡ ጉሮሮአቸው እንደተከፈተ መቃብር ነው፡፡ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፡፡ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፡፡ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፡፡ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፡፡ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፡፡ የሰላምንም መንገድ አያውቁም፡፡ በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሄርን መፍራት የለም፡፡ አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሄር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፡፡ ይህም የሕግን ሥራ በመስራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፡፡ ሐጢያት በሕግ ይታወቃልና፡፡››
 
ደህንነትን ለመቀበል እነዚህን ምንባቦች መረዳትና ማመን የሚኖርብን እንዴት ነው? ገና ከመጀመሪያው ጻድቅ የሆኑም ሆኑ እግዚአብሄርን የሚሹ አልነበሩም፡፡ ሁሉም ሐጢያተኞች ነበሩ፡፡ ጉሮሮዋቸው እንደተከፈተ መቃብር ነበር፡፡ ምላሶቻቸውም እንደ እባብ መርዝ መርዛም ናቸው፡፡ በሽንገላ፣ በእርግማንና በምሬት የተሞላ ነው፡፡ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣን ነበሩ፡፡ የሰላምን መንገድ አላወቋትም፡፡ በዓይኖቻቸውም ፊት እግዚአብሄርን መፍራት የለም፡፡ በራሳቸው የጥፋትና የጉስቁልና መንገድ ብቻ ይጓዛሉ፡፡ ሰው ሁሉ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ከማወቁና ከማመኑ በፊት ሐጢያተኛ ነበር፡፡ እነርሱ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኞች መሆናቸውን ያወቁበት መንገድ ሕጉ ነው፡፡
 
እኛ ያለ ሕግ እንዴት ሐጢያቶቻችንን ማወቅ እንችላለን? እግዚአብሄርን ፈርተን እናውቃለንን? ሮሜ 3፡18 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሄርን መፍራት የለም፡፡›› የሥጋ ዓይኖቻችንስ አይተውት ያውቃሉን? ምናልባት በመጠኑም ቢሆን ስለ እግዚአብሄር መኖር እናውቅ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አይተነውም ሆነ ፈርተነው አናውቅም፡፡ ታዲያ ሐጢያተኞች መሆናችንን ያወቅነው እንዴት ነው? የእግዚአብሄርን መኖር ያወቅነው የተጻፈውን ቃሉን በመስማት ነው፡፡ መስማት ከእግዚአብሄር ቃል የሚመጣው ለዚህ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ዓለምን የፈጠረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሄር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ›› (ዘፍጥረት 1፡1) ተብሎ ሰስለተጻፈ ነው፡፡ የእርሱን መኖር ያወቅነውና ያመንነው ቃሉን በመስማት ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ባይሆን ኖሮ እርሱን የሚያውቅም ሆነ የሚፈራ ሰው ባልነበረም ነበር፡፡ ያለ እግዚአብሄር ቃል ሐጢያቶቻችንንም ማወቅ ባልቻልን ነበር፡፡
          
በሌላ አነጋገር እኛ ከንቱ ነገሮችን በማምለክና ሐጢያቶቻችንን ባለማወቅ እግዚአብሄርን የማናውቅ ሰዎች ነበርን፡፡ እግዚአብሄር ግን ሕጉን ሰጠን፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያቶቻችንን ያወቅነው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ጉድለቶቻችንንና ሐጢያቶቻችንን ያወቅነው የእርሱን የሕግ ቃል አስርቱን ትዕዛዛትና 613ቱን ዝርዝር የሕግ አንቀጾች በመስማት ነው፡፡
 
ያለ ሕጉ ቃል ማንም የራሱን ሐጢያቶች ማወቅ አይችልም፡፡ በግዞት ቤት ያለ እያንዳንዱ ፍርደኛ ወንጀሉ ምን እንደነበር ወይም ለምን እንደታሰረ እንደማያውቅ ይናገራል፡፡ ብዙዎቹ ንጹሐን ስለመሆናቸውና ወደ እስር ቤት የተላኩት በስህተትና ከፍትህ ውጪ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ሕግ ሳናውቅ ‹‹ሁልጊዜም እንደዚህ ሳደርግ ነበር፡፡ ይህ እንዴት ሐጢያት ሊሆን ይችላል?›› ስለምንል የራሳችንን ሐጢያቶች ማወቅ አንችልም፡፡
 
ሐጢያቶቻችንን ወደ ማወቅ የደረስነው የእግዚአብሄርን ሕግ በማየትና በመስማት ብቻ ነው፡፡ ሌሎች አማልክቶችን ማምለካችንን፣ የእግዚአብሄርን ስም በከንቱ መጥራታችንን፣ ሰንበትን መጠበቅ ያቃተን መሆናችንን፣ ነፍስ መግደላችንን፣ ማመንዘራችንን፣ መስረቃችንን፣ መዋሸታችንን፣ ምቀኞች መሆናችንን፣ በአጭሩ በእግዚአብሄር ቃል መኖር ያቃተን መሆናችንን የተረዳነውና የተገነዘብነው በሕጉ ቃል ነው፡፡ ይህ ሕግ ሳይመጣ በፊት ሐጢያቶቻችንን አናውቅም ነበር፡፡
 
ሐጢያተኞች መሆናችንን ከተረዳን በኋላ በእግዚአብሄር ፊት ምን ማድረግ ይገባናል? ሐጢያቶቻችን እንዴት ይቅርታን እንደሚያገኙ መጠየቅ ያስፈልገናል፡፡ ሐጢያቶቻችንን የምናውቀውና የመዳን ፍላጎታችንን የምንገነዘበው የእግዚአብሄርን ቃል በመስማት ነው፡፡ የተራበ ሰው ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ የእግዚአብሄርን ሕግ መጣሳቸውን የሚገነዘቡና የከፉ ሐጢያተኞች መሆናቸውን የሚያውቁ ሰዎች ደህንነት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቃሉ፡፡ እግዚአብሄርን የምንሻውና እርሱ በላከልን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በጽድቅ የማመናችንን ፍላጎት የምንገነዘበው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ‹‹እምነት ከመስማት ስለሚመጣ›› የእግዚአብሄርን ቃል በማመን ሐጢያቶቻችንን እናውቃለን፡፡
 
 

አሁን ሐጢያተኞች መሆናችንን እናውቃለን፤ ታዲያ ከሐጢያቶቻችን ለመዳን ምን ማድረግ ይገባናል?

 
የእግዚአብሄርን ቃል በመስማትና በመማር ሐጢያቶቻችንን እንዳወቅን ሁሉ ደህንነትም የሚመጣው በልባችን ማዕከል ላይ በቆመው ቃሉ በማመን ነው፡፡ ሮሜ 3፡21-22 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፡፡ እርሱም ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡››
 
እግዚአብሄር ሕጉን በመስጠት በቃሉ መኖር ስላቃተን በፊቱ ሐጢያተኞች እንደሆንን እንድናውቅ ፈቀደ፡፡ እኛ ሁለት የተለያዩ ፍላጎቶች አሉን፡፡ በሕጉ መኖር እንፈልጋለን፡፡ በዚያው ጊዜ ግን ከሐጢያት መዳናችንንም እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ‹‹…አሁን የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለ ሕግ ስለተገለጠ›› ከሐጢያቶቻቸው መዳን የሚፈልጉ ሰዎች በሕጉ ሳይሆን በዚህ የእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ ባላቸው እምነት ቤዛነታቸውን ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህ አርነት የሚመጣው እኛን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባዳነን የእግዚአብሄር ጽድቅ በእግዚአብሄር በተሰጠው ደህንነት በማመን እንጂ የእግዚአብሄርን ሕግ በመታዘዝ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡
 
ይህ የእግዚአብሄር ጽድቅና የእርሱ ደህንነት ታዲያ ምንድነው? ይህ በሁለቱም የብሉይና የአዲስ ኪዳናት ውስጥ የተነገረው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በብሉይ ኪዳን ውስጥ በመስዋዕቱ ሥርዓት በማመን የሚገኝ ደህንነት ሆኖ ተገልጦዋል፡፡ ሮሜ 3፡21-22 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፡፡ እርሱም ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡››
 
ታዲያ የእግዚአብሄርን ጽድቅ መቀበል የምንችለው እንዴት ነው? በሕግና በነቢያት በተመሰከረለት የእግዚአብሄር ቃል አማካይነት ኢየሱስ አምላክና አዳኝ እንደሆነ በማወቅና በእርሱ ላይ ባለን እምነትም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ በመዳን የእግዚአብሄርን ጽድቅ መቀበል እንችላለን፡፡
በሌላ አነጋገር በብሉይ ኪዳን በሕግና በነቢያት በተመሰከረለት የእርሱ ቃል በማመን የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንቀበላለን፡፡ ሕግና ነቢያት የእግዚአብሄርን ቃል መመስከራቸው በዕብራውያንና በሮሜ የመጀመሪያ ምዕራፎች ውስጥ ታይቷል፡፡
 
ኢየሱስ እኛን ለማዳን የመጣው እግዚአብሄር ለእኛ በገባው የተስፋ ቃል መሰረት ነው፡፡ ይህ ከሕግ በታች የነበሩትንና ለጥፋት የታጩትን ሐጢያተኞች የማዳን ተስፋ ከሺህ ዓመታቶች በፊት በእግዚአብሄር የተሰጠ ነበር፡፡ እርሱ በተደጋጋሚ ይህንን ተስፋ በመናገር ከእኛ በፊት በመጡት በብዙዎቹ የእርሱ ባሮች በኩል እንዴት ሊፈጽመው እንዳቀደ ገልጦዋል፡፡
 
ለምሳሌ አንድ ምንባብ እንመልከት፡- ዘሌዋውያን 16፡21 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፡፡ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ፣ መተላለፋቸውንም ሁሉ፣ ሐጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፡፡ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፡፡ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል፡፡›› በሮሜ 3፡21-22 ላይ የእግዚአብሄር ጽድቅ በሕግና በነቢያት እንደተመሰከረለት የሚናገረው ምንባብ የኢየሱስ ምሉዕ ደህንነት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በሚቀርቡት የብሉይ ኪዳን መስዋዕቶችና እንደ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ኤርምያስና ዳንኤል ባሉት ነቢያቶች በኩል ተገልጦዋል ማለቱ ነው፡፡
 
በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር በብሉይ ኪዳን ቃል አማካይነት አስቀድሞ እንዴት የደህንነት ተስፋውን እንደሚፈጽም ይህንንም ኢየሱስ ክርስቶስን በመላክ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንዲወስድ አድርጎ በእኛ ፋንታ በመስቀል ላይ እንዲሞት በሰውነቱም የሐጢያቶቻችንን ዋጋ በሙሉ በመክፈል በእግዚአብሄር ጽድቅ አማካይነት ከሐጢያታችን እንዴት እንደሚያድነን ገልጦዋል፡፡ ስለዚህ ደህንነታችን በሕግ ሳይሆን በሕግና በነቢያት እንደተመሰከረው የእግዚአብሄር ጽድቅ በሆነው በራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለን እምነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችን የዳንነው በኢየሱስ ክርስቶስ በተፈጸመው የእግዚአብሄር ጽድቅ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ እምነታችን የመጣውም ይህንን የእግዚአብሄር ቃል፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመስማት ነው፡፡ ኢየሱስ አዳኛችን መሆኑን ማወቅና ማመን የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ አዳኛችን መሆኑን የምናውቀውና የምናምነው በዕቅዱ መሰረት እኛን ለማዳን እንደመጣ ለባሪያዎቹ የተናገረውን የእግዚአብሄር ቃል በመስማት ነው፡፡ በዳንኤል 9፡24 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹ዓመጻን ይጨርስ፣ ሐጢአትንም ይፈጽም፣ በደልንም ያስተሰርይ፣ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፣ ራዕይንና ትንቢትን ያትም፣ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባኤ ተቀጥሮአል፡፡››
     
 

እግዚአብሄር ለሕዝባችን ሰባ ሱባኤ ቀጥሮአል፡፡

 
ከዳንኤል መጽሐፍ ባየነው በዚሁ ምንባብ እንቀጥላለን፡፡ ምንባቡ የሚያብራራው በባቢሎን የሆነውን የእስራኤል ውድቀት ነው፡፡ እስራኤሎች በጣዖት አምልኮዋቸው የተነሳ ምርኮኞች ሆነው ወደ ባቢሎን እንዲወሰዱና ለሰባ ዓመታት ባሮች ሆነው እንዲኖሩ እግዚአብሄር ወሰነ፡፡ በእግዚአብሄር ውሳኔ መሰረትም እስራኤል በባቢሎን ተጠቃች፤ ተሸነፈችም፡፡ ውድመቱን መቋቋም ባለመቻልዋ ከእስራኤሎች ብዙዎቹን ምርኮኛ በማድረግ የእነርሱ ባሮች እንዲሆኑ ላደረጉዋቸው ወራሪዎች እጃቸውን ሰጡ፡፡ ከተወሰዱት ምርኮኞች መካከል የባቢሎን ንጉሥ አማካሪ የሆኑ እንደ ዳንኤል ያሉ ጠቢባን ነበሩ፡፡
 
ስለዚህ እግዚአብሄር ስለ ሐጢያቶቻቸው እስራኤሎችን በዚህ መንገድ ቀጣቸው፡፡ ነገር ግን መሃሪ ስለሆነ ቁጣውን ለዘላለም አልያዘም፡፡ ሆኖም በ70 ሱባኤ ውስጥ ነጻ ሊያወጣቸው አቀደ፡፡
 
ዳንኤል ሕዝቡን ወክሎ በእግዚአብሄር ፊት ንስሐ በመግባት ምህረቱንና ማዳኑን ሲለምን እግዚአብሄር ከላይ ያለውን ምንባብ የተናገረውን መልአክ ላከ፡፡ ‹‹ዓመጻን ይጨርስ፣ ሐጢአትንም ይፈጽም፣ በደልንም ያስተሰርይ፣ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፣ ራዕይንና ትንቢትን ያትም፣ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባኤ ተቀጥሮአል፡፡›› ይህ ምንባብ እግዚአብሄር መተላለፎቻቸው ሲያበቃ በ70 ሱባኤ ውስጥ የሕዝቡን ሐጢያቶች በሙሉ ይቅር እንደሚል ለዳንኤል የተሰጠ ተስፋ ነው፡፡ እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ለእኛ ተስፋ የሰጠንን ማዳንም ይገልጣል፡፡
 
እስራኤሎች ብዙ ሐጢያቶችን ስለሰሩ እግዚአብሄር ቀጣቸው፡፡ 70 ሱባኤ ለከፈሉትም ዋጋ እግዚአብሄር ያለፉትን ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ይቅር አላቸው፡፡ መተላለፉ ከተዋጀና ሐጢያቶቹም ከተጨረሱ በኋላ የእስራኤሎች ሐጢያቶች በሙሉ እዚያው አልነበሩም፡፡ የበደል ዕርቅ ሲደረግም የዘላለም ጽድቅ ገባ፡፡ ራዕይና ትንቢትም ታተሙ፡፡ በኤርምያስ የተነገሩት የእግዚአብሄር ቃሎችም በሙሉ ተፈጸሙ፡፡ እነዚህ ሁሉ በ70 የባርነት ሱባኤ አማካይነት ተጠናቀቁ፡፡ በ70ኛው ሱባኤም እስራኤሎች ወደ አገራቸው መመለስ ነበረባቸው፡፡
 
እግዚአብሄር በመልአኩ በኩል ለዳንኤል የነገረው ይህንን ነው፡፡ ይህ ተስፋ ለእስራኤሎች የተሰጠ ተስፋ ነበር፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊ ትርጉምም አለው፡፡ እግዚአብሄር ለእስራኤል ሕዝብና ለቅድስቲቱ ከተማ 70 ሱባኤን እንደወሰነ ሁሉ በእርሱ ለምናምነው ሁሉም ቅድስቲቱን የሰማይ ከተማ የእግዚአብሄር መንግሥታችንን አዘጋጅቶልናል፡፡
 
በሮሜ ውስጥ እንዲህ ይላል፡- ‹‹አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፡፡ እርሱም ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡›› ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በተጠመቀና በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ መተላለፎቻችን ሁሉ ተወገዱ፡፡ ሐጢያቶቻችንም አበቁ፡፡ የዘላለም ጽድቅም ተገለጠ፡፡ ራዕይና ትንቢትም ታተመ፡፡ የዳንኤል ምንባብ የሚያበቃው ‹‹ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ›› በማለት ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?ቅዱሰ ቅዱሳን የሚያመለክተው ቅቡዕ ለመሆን ወደዚህ ምድር የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጂ ሌላ ማንንም አይደለም፡፡ 
 
መቀባት ማለት ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ሦስቱን የእግዚአብሄር መንግሥት ማለትም የንጉሥ፣ የሊቀ ካህንና የነቢይ ማዕረጎችን ይወስዳል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ንጉሣችን፣ ሊቀ ካህናችንና ነቢያችን በመሆን እኛን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለማዳን የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈጸም ነበረበት፡፡ ለዳንኤል የነገረው መልአክ እንደተነበየው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ በእኛ ፋንታ ተኮነነ፡፡
 
‹‹እምነት ከመስማት ነው፡፡›› ታዲያ ይህንን የጽድቅ ወንጌል መስማትና ማመን የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ ማመን የምንችለው እንዴት ነው? በብሉይና በአዲስ ኪዳናት ውስጥ የተነገረውን የእግዚአብሄር ቃል የእግዚአብሄር ነቢያቶችና ባሮች የተናገሩዋቸዋን ቃሎች በመስማትና በማመን ነው፡፡ ጳውሎስ እምነት ከመስማት እንደሚመጣ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ ይህ እምነት የሚመጣው የክርስቶስን ቃል በመስማት ነው፡፡
 
እንደ ዳንኤልና ኢሳይያስ ያሉ የብሉይ ኪዳን ነቢያቶች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ተንብየዋል፡፡ በተለይ ኢሳይያስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸክሞዋል፡፡›› ‹‹ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡›› (ኢሳይያስ 53፡4,7)
 
በኢሳይያስ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ተራ ከሆኑ ሰዎች ሁሉ ተራ ሆኖ ከድንግል ማርያም በመወለድ ወደዚህ ምድር እንደሚመጣ፣ ለ33 ዓመት እንደሚኖር፣ እንደሚጠመቅ፣ እንደሚሰቀልና በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደሚነሳ ማን ያምን ነበር? ኢሳይያስ ግን ኢየሱስ ከመምጣቱ ከ700 ዓመታት በፊት እነዚህ ነገሮች እንደሚፈጸሙ አየ፤ ተነበየም፡፡ ክርስቶስ ደዌያችንንና ሕመማችንን የሚሸከም የመሆኑን እውነታ መሰከረ፡፡
 
ጳውሎስ የእግዚአብሄር ባሮች ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በመውሰድ በእግዚአብሄር ጽድቅ እንደሚያድነን ስለመመስከራቸው ለማብራራት በሮሜ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ የብሉይ ኪዳንን ቃል የተጠቀመው ለዚህ ነው፡፡
                      
 

ሁሉ ሐጢአትን ሰርተዋልና፡፡  

 
ሮሜ 3፡23-24 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሁሉ ሐጢአትን ሰርተዋልና የእግዚአብሄርም ክብር ጎድሎአቸዋል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ፡፡›› በሐጢያት ስለተወለድንና ሁላችንም በእግዚአብሄር ላይ ሐጢያት ስለሰራን ክብሩና መንግሥቱ ጎድለውናል፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በኩል በእግዚአብሄር ጸጋ እንዲያው ጸድቀናል፡፡ ጽድቃችን ያለ ዋጋ በነጻ የተሰጠ ነበር፡፡ ኢየሱስ እርሱን የምንሰማውንና በእርሱ የምናምነውን እኛን ለማዳን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስለወሰደና ዋጋውንም በመስቀል ላይ በሕይወቱ ስለከፈለ የሐጢያቶቻችንን ዋጋ መክፈል አይኖርብንም፡፡
 
ከሐጢያቶች ሁሉ በእምነት መዳን ማለት ምን ማለት ነው? በአጭሩ በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን ማለታችን ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን የሚገናኘው ከልባችን ጋር እንጂ ከምግባሮች ጋር አይደለም፡፡ የጌታችንን ቃል በመስማት ይህንንም በልባችን በማመን ጸድቀናል፡፡ ጌታችን እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን ወደዚህ ምድር መጥቶ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅና በመስቀል ላይ በመሞት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ የተሸከመ የእግዚአብሄር በግ ሆነ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙንታ ተነሳ፡፡ አሁን በእግዚአብሄር ቀን ተቀምጦዋል፡፡
 
ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ በራሱ ሕይወትም የሐጢያቶቻችንን ቅጣት ዋጋ ከፈለ፡፡ ከሙታንም ተነሳ፡፡ ይህንን ሁሉ ያደረገው እኛን ከተረጋገጠው ሞታችን ለማዳን ነው፡፡ በዚህ በማመን ድነናል፡፡ ደህንነታችን የመጣው በእምነት ነው፡፡ እምነታችን የመጣውም የተጻፈውን የእግዚአብሄር ቃል በማመን ነው፡፡ መስማታችንም የመጣው በክርስቶስ ቃል ነው፡፡
 
‹‹እምነት ከመስማት ነው፡፡›› እኛ በልባችን እናምናለን፡፡ አእምሮዋችን ለእውቀት ሲሆን ሰውነታችን ግን ለሥራ ነው፡፡ የምናምነውም በልባችን ነው፡፡ ታዲያ በልባችን የምናምነው ምንድነው እንዴትስ ነው? የእግዚአብሄርን ቃል በመስማት የእርሱን ወንጌል መስማት እንችላለን፡፡ የእርሱን ወንጌል መስማት እንችላለን፡፡ የእርሱን ወንጌል በመስማትም እምነት ይኖረናል፡፡ እምነት ሲኖረንም እድናለን፡፡ ስናምን የምናምነው የእግዚአብሄርን ቃል ነው፡፡ ማለትም ክርስቶስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን እንደወሰደ፣ እንደተሸከመ፣ በመስቀል ላይ እንደሞተና ዳግመኛም ከሙታን እንደተነሳ የሚያውጀውን የተጻፈ ቃል እናምናለን፡፡
 
በእግዚአብሄር ቃል ማመን ማለት በእርሱ ጽድቅ ማመን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄርን ቃል ሳይሰሙ ማመን ከንቱና አይረቤ ነው፡፡ እግዚአብሄር በእከሌ ሕልሞች በኩል ተገለጠ ገለመሌ የሚሉት አባባሎች በሙሉ ውሸቶች ናቸው፡፡
 
የዳንነው በእምነትና በእምነት ብቻ ነው፡፡ እንደገና አንድ ጊዜ ሮሜ 3፡24-26ን እናንብብ፡- ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ፡፡ እርሱንም እግዚአብሄር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተሰርያ አድርጎ አቆመው፡፡ ይህም በፊት የተደረገውን ሐጢአት ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡›› አሜን፡፡ ጌታችን የሐጢያት ማስተሰርያ ተደረገ፡፡ በሐጢያቶቻችን ምክንያት የእግዚአብሄር ጠላቶች ተደረግን፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ በጥምቀቱ፣ በሞቱና በትንሳኤው ለሐጢያቶቻችን ማስተሰርያ በመሆን ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት እንደገና አደሰው፡፡
 
በሮሜ 3፡25 መካከል ላይ እንዲህ የሚል ምንባብ አለ፡- ይህም በፊት የተደረገውን ሐጢአት ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡›› ይህ ምንባብ እግዚአብሄር በጣም ለረጅም ጊዜ በትዕግስት እንደጠበቀና እስከ ፍርድ ቀን ድረስም እንደሚጠብቅ ይነግረናል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ፣ በውሃውና በደሙ ስለሆነው ደህንነት የሚያምኑ፣ ለእግዚአብሄር አብ ማስተሰርያ በሆነው በወልድ ማዳን የሚያምኑ ሰዎች ሐጢያቶቻቸው በሙሉ ወደ እግዚአብሄር ተላልፈውላቸዋል፡፡ ‹‹ሐጢያትን መተው›› ማለት እግዚአብሄር የአምላክን ቃል ሰምተው የሚያምኑትን፤ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ የሚያምኑትን ሰዎች ሐጢያቶች ትቶላቸዋል ማለት ነው፡፡
በሕይወታችን በየጊዜው እንደናቀፍ ይሆናል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ግን የሥጋችንና የአእምሮዋችን ድክመት ነው፡፡ የኢየሱስን ደህንነት እስካልካድን ድረስ እግዚአብሄር እነዚህን ሐጢያቶች በሙሉ እንደ ሐጢያቶች አያያቸውም፡፡ በሌላ አነጋገር በልባቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ውሃና ደም በማመን የዳኑትን ሰዎች ሐጢያቶች ይተዋቸዋል እንጂ አይመለከታቸውም፡፡
 
ታዲያ አግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን የተወው ለምንድነው? እርሱ ቅዱስና ጻድቅ አምላክ ሆኖ ሳለ እነዚህን ሐጢያቶች እንዴት ችላ ሊላቸው ይችላል? ለዚህ ምክንያቱ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ መሞቱ ነው፡፡ እግዚአብሄር ቀድሞ የተሰሩትን ሐጢያቶቻችንን የተወው ኢየሱስ በጥምቀቱና በስቅለቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ስለደደመሰሰ ነው፡፡ ቀድሞ  የተሰሩት ሐጢያቶች የሚያመላክቱት የአዳምን ሐጢያት ብቻ ነውን? አይደለም፡፡ ምክንያቱም የአዳም ሐጢያት መስለው ቢታዩም ለዘላለማዊው እግዚአብሄር አብ ሁሉም ነገር ያለፈ ነው፡፡
 
ከዘላለም ዕይታ አንጻር ጊዜ በዚህ ዓለም ላይ ሁልጊዜም ያለፈ መስሎ ይታያል፡፡ ይህ ዓለም የራሱ መጀመሪያና መጨረሻ አለው፡፡ እግዚአብሄር ግን ዘላለማዊ ነው፡፡ የእርሱን ዘመን ከዓለማዊ ዘመናችን ጋር ስናነጻጽረው የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ በእርሱ ፊት ባለፈ ጊዜ የተሰሩ ሆነው ይታያሉ፡፡ ‹‹ይህም በፊት የተደረገውን ሐጢአት ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፡፡›› እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን የማያየው ለዚህ ነው፡፡ ሐጢያቶቻችንን የሚያዩበት ዓይኖች ስለሌሉት ሳይሆን ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐጢያቶችንን ዋጋ በመክፈሉ አያያቸውም፡፡ የክርስቶስ ጥምቀትና ስቅለት ሐጢያቶቻችንን በማንጻታቸው በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት አልባ ሰዎች ሆነን እንቀርባለን፡፡
 
የእግዚአብሄርን ጽድቅ የፈጸመው ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ በማዳን አስቀድሞ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስለወሰደ እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን እንዴት ሊያያቸው ይችላል? እግዚአብሄር አስቀድሞ የተሰሩትን ሐጢያቶች፤ አስቀድሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ዋጋ የተከፈለባቸውን ሐጢያቶች በመተው አሁን ጽድቁን ያሳየው በዚህ መንገድ ነው፡፡
                       
በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን የሚመጣው በክርስቶስ ቃል ነው፡፡ ምክንያቱም የራሱ የክርስቶስ ቃል የእግዚአብሄርን ቃል ይዞዋልና፡፡ እግዚአብሄር ጽድቁን በመግለጥ የራሱን ጽድቅ ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑትን ሰዎችም ጽድቅ አሳይቷል፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በሙሉ አስወግዶዋል፡፡ እኛም ኢየሱስ ሒያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደ በልባችን እናምናለን፡፡ ያንኑ የክርስቶስ ጽድቅ በመልበስ ሐጢያት አልባ የሆንነውና የጸደቅነው ለዚህ ነው፡፡ (ገላትያ 3፡27) እግዚአብሄርና እኛ ጻድቃን ስለሆነን አብረን ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን፡፡ እናንተና እኔም የእርሱ ልጆች ነን፡፡ በዚህ ያማረ የምስራች ታምናላችሁን?
 
ይህ ማለት እኛ በራሳችን የምንመካበት አንዳች ነገር አለን ማለት ነውን? በእርግጥ አይደለም! ደህንነትን ያገኘነው የክርስቶስን ቃል በመስማትና በማመን ብቻ ሆኖ ሳለ ከራሳችን የሆነና የምንመካበት ነገር እንዴት ሊኖር ይችላል? የዳንነው በምግባሮቻችን ነውን? ምን የምንመካበት ነገር አለን? ምንም! የዳናችሁት አንድም ጊዜ በእሁድ አገልግሎት ላይ ቀርታችሁ ስለማታውቁ ነበርን? የዳናችሁት ስጦታዎቻችሁን በታማኝነት በመስጠታችሁ ነውን?
 
እነዚህ ሁሉ ምግባሮች ናቸው፡፡ በምግባሮች ላይ የተመሰረተ እምነትና/ወይም በምግባሮች የተደገፈ እምነት የተሳሳተ እምነት ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን የዳንነው በልባችን በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመናችን ብቻ ነው፡፡ እምነት ከመስማት ነው፡፡ ደህንነት የሚመጣውም በክርስቶስ ቃል በማመን ነው፡፡
 
በኢየሱስ አምኖ ደህንነትን በንስሐ ጸሎት በኩል ለማግኘት መሞከርም እንደዚሁ የሐሰት እምነት ነው፡፡ እውነተኛ እምነት የሚመጣው በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ብቻ እንጂ በሕግ ሥራዎች አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል እንዲህ ይላል፡- ‹‹ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል፡፡ በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፡፡ በእምነት ሕግ ነው እንጂ፡፡ ሰው ሁሉ ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና፡፡ ወይስ እግዚአብሄር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን?...የአሕዛብ አምላክ ደግሞ ነው፡፡››
   
ደህንነት ለእስራኤሎችም ለአሕዛቦችም የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ በውሃውና በደሙ እንዳዳናቸው በመስማትና በልባቸው በማመን ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመናችን ከሐጢያቶቻችን ድነናል፡፡ እግዚአብሄር አባታችን ሆነ፡፡ እኛም ልጆቹ ሆንን፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን፣ የክርስቶስን ቃል በመስማትና በማመን የሚገኘው ደህንነት ይህ ነው፡፡ እምነታችን የመጣው በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ነው፡፡
 
ደህንነታችን የተገኘው በክርስቶስ ቃል ላይ ባለን እምነት ነው፡፡ ታዲያ ክርስቶስ አዳኛችሁ ሆኖ ወደዚህ ምድር እንደመጣ፣ በጥምቀቱም ለእግዚአብሄር ማስተሰርያ ይሆን ዘንድ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደወሰደና በመስቀል ላይ እንደሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተነስቶ በእግዚአብሄር አብ ቀኝ እንደተቀመጠ ታምናላችሁን?
 
እግዚአብሄር በሕልም እንዲገለጥላቸው የሚጠይቁና አንድ ጊዜ በዓይኖቻቸው ብቻ ቢያዩት በእርሱ እንደሚያምኑ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች ኢየሱስን በሕልማቸው እንዳዩ፣ እርሱም ይህንንና ያንን እንዲያደርጉ፣ ቤተክርስቲያን እዚህ፣ እዚያ ደግሞ የጸሎት ማዕከል ወ.ዘ.ተ እንዲሰሩ እንደነገራቸው የሚያወሩ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ገንዘብን በሚጠይቅ ነገርና እንዲህ ባሉ የሐሰት አባባሎች በመታለል ብዙዎች ተሳስተዋል፤ ተታልለዋልም፡፡ በክርስቲያኑ ዓለም ውስጥ በጣም ብዙ አሳዛኝ ገጠመኞች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የራሱ የዲያብሎስ እንጂ የጌታችን ሥራ እንዳልሆኑ መረዳት አለባችሁ፡፡
 
በአጋጣሚ ኢየሱስን በሕልማችሁ አይታችሁት ቢሆን በጣም አክብዳችሁ አትውሰዱት፡፡ ሕልሞች ሕልሞች ብቻ ናቸው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ ባለ ሁኔታ በፊታችሁ የሚገለጥ ሰው አይደለም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ ባለስፈለገም ነበር፡፡ ኢየሱስ አንድ ጊዜ እንኳን በፊታችን ቢገለጥ ያን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳችንን መክደን አለብን፡፡ ምከንያቱም ከእንግዲህ ወዲያ አያስፈልግምና፡፡ ይህ ግን በክርስቶስ የደህንነት ሥራ ላይ የጥፋት ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡
 
ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አምነነው ቢሆን ኖሮ እርሱ ለሰው ሁሉ ይገለጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጌታችን አስቀድሞ የደህንነትን መጠይቆች ሁሉ ፈጽሞዋልና፡፡ እምነት ከመስማትና የክርስቶስን ቃል ከማመን የሚመጣው ለዚህ ነው፡፡ ታዲያ ሰዎች ሁሉ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰምተዋልን? ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን ስም ሰምተውት ይሆናል፤ ነገር ግን ሁሉም እውነተኛውን ወንጌል አልሰሙም፡፡ ጳውሎስ ‹‹ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?›› ብሎ የጠየቀው ለዚህ ነው፡፡
 
ስለዚህ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የያዘውን ይህንን ወንጌል መስበክ አለብን፡፡ ግን በምንና እንዴት? ወንጌሉ በምን ዘዴና እንዴት ይሰበክ የሚለው አስፈላጊ አይደለም፡፡ የምስራቹን የማሰራጫ ዘዴዎች ሁሉ በሚነገሩ ቃሎች ወይም በሕትመት መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋል ይገባቸዋል፡፡ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም የክርስቶስን ቃል ከመስማት ይመጣል፡፡ ወንጌልን የሚሰብኩ የሕትመት ውጤቶችም እንዲሁ አንባቢዎችን ወደ እውነተኛው እምነት ሊመሩዋቸው ይችላሉ፡፡ ዘዴው ምንም ይሁን እምነት ሊመጣ የሚችለው ከመስማት ብቻ እንደሆነና መስማትም የሚመጣው የምስራቹን ከመስበክ ብቻ እንደሆነ ማስታወስ ይገባችኋል፡፡
በልባችሁ ውስጥ በእግዚአብሄር ቃል የሚያምን እምነት በእርግጥ ካላችሁ ያን ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያን እንደሆናችሁ ታውቃላችሁ፡፡ ይህንን ታውቁ ዘንድ፣ ከሐጢያቶቻችሁም እንደዳናችሁ ታውቁ ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እጸልይማለሁ፡፡ እንግዲህ ሮሜ 10፡17ን በአንድ ላይ በማንበብ ውይይታችንን እንደምድም፡፡
 
‹‹እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡›› አሜን፡፡ ይህንን የእግዚአብሄርን ቃል በመስማት በልባቸው የሚያምኑ ሰዎች እውነተኛ እምነት አላቸው፡፡ ይህ እውነተኛው እምነት አላችሁን? ጌታችን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አድኖናል፡፡
 
ጌታ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በመውሰዱ ምንኛ አመስጋኝና ደስተኞች ነን! ያለ ወንጌል ሰዎች ሁልጊዜም ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ መውሰዱን በመስማት ብቻ ልባችን በደስታ ይሞላል፡፡ እምነታችንም ማደግ ይጀምራል፡፡
 
ስላዳነን ጌታን እናመሰግናለን፡፡