Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[2-6] ለጴርጋሞን ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡12-17 ››

ለጴርጋሞን ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡12-17 ››
‹‹በጴርጋሞንም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፡- በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል፡፡ የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፡፡ ስሜንም ትጠብቃለህ፤ ሰይጣንም በሚኖርበት በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም፡፡ ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ የምነቅፍበህ ጥቂት ነገር አለኝ፡፡ እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ፡፡ እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፡፡ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ፡፡ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ ድል ለነሳው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፡፡ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፡፡ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎዋል፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡

 
ቁጥር 12፡- ‹‹በጴርጋሞንም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፡- በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል፡፡››
ጴርጋሞን ነዋሪዎችዋ ብዙ አረማዊ አማልክቶችን የሚያመልኩባት በትንሽዋ እስያ የምትገኝ የአስተዳደር መናገሻ ከተማ ነበረች፡፡ በተለይ ደግሞ ለንጉሠ ነገሥት የሚሰገድባት ማዕከል ነበረች፡፡ ‹‹በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው›› ሲል ጌታ የእግዚአብሄርን ጠላቶች ይዋጋቸዋል ማለት ነው፡፡
 
ቁጥር 13፡- ‹‹የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፡፡ ስሜንም ትጠብቃለህ፤ ሰይጣንም በሚኖርበት በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም፡፡››
ጴርጋሞን ለንጉሠ ነገሥት የሚሰገድባት ምሽግ የነበረች ብትሆንም በጌታ ያለውን እምነቱን ለመጠበቅ ንጉሣዊ ጣዖት አምልኮን አሻፈረኝ ያለው የእግዚአብሄር አገልጋይ አንቲጳስ ሰማዕት የሆነባት ሥፍራም ነበረች፡፡ ሰዎች ጸረ ክርስቶስን እንዲያመልኩ የሚገደዱበት ጊዜ እንደገና ይመጣል፡፡ ነገር ግን ቅዱሳንና የእግዚአብሄር አገልጋዮች አንቲጳስ የራሱን ሕይወት መስዋዕት በማድረግ እምነቱን እንደጠበቀው ሁሉ እምነታቸውን እስከ መጨረሻው ድረስ ይጠብቃሉ፡፡ እንዲህ ያለ ደፋር እምነት እንዲኖረን በትናንሽ እርምጃዎች ብንጀምርም አሁኑኑ እምነታችንን ወደ ተግባር መለወጥ አለብን፡፡ የስደቱ ዘመን ሲመጣ ቅዱሳንና የእግዚአብሄር አገልጋዮች በተለይ በመንፈስ ቅዱስ ላይ መታመን ይገባቸዋል፡፡ ለእግዚአብሄር ክብርን መስጠትና ከእርሱ የሚመጣውን አዲስ ሰማይና ምድር መቀበል እንዲችሉ በእግዚአብሄር መታመንና በፈቃዳቸው ሰማዕትነታቸውን በተስፋ መቀበል አለባቸው፡፡
 
ቁጥር 14፡- ‹‹ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ የምነቅፍበህ ጥቂት ነገር አለኝ፡፡››
እግዚአብሄር ከአባላቶችዋ አንዳንዶቹ የበለዓምን ትምህርት በመያዛቸው የጴርጋሞንን ቤተክርስቲያን ወቀሰ፡፡ በለዓም እስራኤሎችን ከእግዚአብሄር ያራቀና ጣዖታትን ከሚያመልኩ የአሕዛብ ሴት ካህናት ጋር ግንኙነቶችን እንዲያደርጉ በመፈተን ጣዖትን እንዲያመልኩ ያደረገ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር፡፡ ጌታ እምነታቸው እግዚአብሄርን የተወውን ሰዎች ወቀሳቸው፡፡ የሕዝቡ ልብ እርሱን ትቶ ሐሳዊ ጣዖቶችን ያመልክ ነበር፡፡ የጣዖት አምልኮ ሐጢያትም በእግዚአብሄር ፊት እጅግ የከፋ ሐጢያት ነው፡፡
 
ቁጥር 15፡- ‹‹እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ፡፡››
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‹‹ኒቆላውያን›› እና ‹‹በለዓም›› የሚሉት ቃሎች በመሰረቱ ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆኑ ትርጓሜያቸውም ‹‹እነዚያ በሰዎች ላይ የሰለጠኑ›› ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ‹‹የኒቆላውያንን ትምህርት የሚጠብቁ›› ብሎ ሲናገር የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ‹‹የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁትን›› መቃወም አለባት ማለቱ ነበር፡፡ እነዚህን የኒቆላውያንንና የበለዓምን ትምህርቶች የተከተሉ ሰዎች ቁሳዊ ትርፎቹንና ጣዖት አምልኮን የተከተሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች በእርግጥም ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን መባረር አለባቸው፡፡
 
ቁጥር 16፡- ‹‹እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፡፡ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ፡፡››
ስለዚህ እግዚአብሄር ለጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ሐሰተኛ አማልክቶችን ከማምለክና ዓለማዊ ትርፎችን ከመከተል ርቀው ወደ ትክክለኛው እምነት እንዲመለሱ ነገራቸው፡፡ ንስሐ ካልገቡም በአፉ ሰይፍ እንደሚዋጋቸው አስጠነቀቃቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ይህ እግዚአብሄር አማኞች ቢሆኑም እንኳን የበለዓምን ትምህርት ከመከተል ንስሐ የማይገቡትን እንደሚቀጣ ያስጠነቀቀበት ኮስታራ ገደብ ነው፡፡ ይህንን የእግዚአብሄር ማስጠንቀቂያ የሰሙና ወደ እርሱ የተመለሱ ሰዎች በሥጋም በመንፈስም በሕይወት ይኖሩ ነበር፡፡ ያንን ያላደረጉ ግን ራሳቸውን ለሥጋና ለመንፈስ ጥፋት ራሳቸውን ማዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ ቅዱሳንና የእግዚአብሄር አገልጋዮች በዚህ ምድርና በመጪው ዓለም መባረክ ከፈለጉ የእግዚአብሄርን ቃል መስማትና በእምነታቸውም ጌታን መከተል አለባቸው፡፡
 
ቁጥር 17፡- ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ ድል ለነሳው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፡፡ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፡፡ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎዋል፡፡››
እውነተኛ ቅዱሳኖች የራሳቸውን ሰማዕትነት እንኳን ይቀበላሉ፡፡ እግዚአብሄር በስሙ ሰማዕት ለሚሆኑት የሰማይን መና እንደሚሰጣቸውና ስሞቻቸውንም በመንግሥቱ ውስጥ እንደሚጽፍ ነግሮናል፡፡ እኛ በአካልም በመንፈስም በሕይወት እንኖር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ለእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የተናገረውን ማድመጥ አለብን፡፡ ድል ለነሱት ማለትም ከሰይጣን ተከታዮች ጋር ተጋድለው ድልን ለተቀዳጁት እግዚአብሄር ከሐጢያት የሚያድናቸውን የእምነት ጽድቅ ይሰጣቸዋል፡፡ ስለ እምነታቸውም ስሞቻቸውን በሕይወት መጽሐፍ ላይ ይጽፋል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ የተለያዩ ምንባቦች ውስጥ በተደጋጋሚ እስከ መጨረሻው ድረስ የሚጸኑ ሰዎች እንደሚድኑ ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር ቅዱሳን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያላቸውን እምነት መጠበቅ እንዲችሉ በመጨረሻው ዘመን ትዕግስተኞች መሆን አለባቸው፡፡ ዳግመኛ የተወለዱት ሰዎች ስሞች በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎዋል፡፡ ስለዚህ ምዕመናን በመጨረሻ በእግዚአብሄር ፊት እስከሚቆሙበት ቀን ድረስ ቁሳዊና ዓለማዊ ትርፎችን በመሻት ሳይሆን በእምነት ድል በመንሳት ወደ እግዚአብሄር መንግሥት መግባት አለባቸው፡፡