Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[4-1] በእግዚአብሄር ዙፋን ላይ የተቀመጠውን ኢየሱስን ተመልከቱ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 4፡1-11 ››

በእግዚአብሄር ዙፋን ላይ የተቀመጠውን ኢየሱስን ተመልከቱ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 4፡1-11 ››
‹‹ከዚህ በኋላም አየሁ፡፡ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፡፡ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት የፊተኛው ድምጽ ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ፡፡ ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፡፡ እነሆም ዙፋን በሰማይ ቆሞአል፡፡ በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፡፡ ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖንን ዕንቁ ይመስል ነበር፡፡ መልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበር፡፡ በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፡፡ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር፡፡ ከዙፋኑም መብረቅና ድምጽ ነጎድጓድም ይወጣል፡፡ በዙፋኑም ፊት ሰባት የእሳት መብራቶች ይበሩ ነበር፡፡ እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሄር መናፍስት ናቸው፡፡ በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባህር ነበረ፡፡ በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሉባቸው አራት እንሰሶች ነበሩ፡፡ ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፡፡ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፡፡ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፡፡ አራተኛውም እንሰሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል፡፡ አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፡፡ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፡፡ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረውና ያለው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም፡፡ እንስሶቹም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴ ምስጋናም በሰጡት ጊዜ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ፡- ጌታችንና አምላካችን ሆይ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር፣ ውዳሴ፣ ሐይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- ‹‹ከዚህ በኋላም አየሁ፡፡ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፡፡ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት የፊተኛው ድምጽ ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ፡፡››
የሰማይ ደጅ ከዚህ በፊት ተዘግቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በዮሐንስ በመጠመቅ፣ በመስቀል ላይ በመሞትና ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት ሐጢያተኞችን ከበደሎቻቸው ባዳናቸው ጊዜ ይህ በር ወለል ብሎ ተከፈተ፡፡ እግዚአብሄር በመላዕክቶቹ አማካይነት ዓለም በመጨረሻው ዘመን ምን እንደሚጠብቃት ለሐዋርያው ዮሐንስ ገለጠለት፡፡
 
ቁጥር 2፡- ‹‹ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፡፡ እነሆም ዙፋን በሰማይ ቆሞአል፡፡ በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፡፡››
ዮሐንስ በተከፈተው የሰማይ በር በኩል በሰማይ የቆመ ሌላ ዙፋን እንደነበረና በእርሱ ላይ የተቀመጠውም ኢየሱስ እንደሆነ ተመለከተ፡፡ በዙፋኑ ዙሪያም አራት እንስሶች፣ 24 ሽማሌዎችና ሰባቱ የእግዚአብሄር መናፍስቶች ነበሩ፡፡
ጌታ ሐጢያተኞችን ከዓለም ሐጢያቶች የማዳን ሥራውን ለማጠናቀቅ የእግዚአብሄርን ዙፋን ከአብ ተቀበለ፡፡ ጌታ በዚህ ምድር ላይ በነበረ ጊዜ ከአጥማቂው ዮሐንስ ጥምቀትን በመቀበል፣ በመስቀል ላይ በመሞትና ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት ሐጢያተኞችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው አዳናቸው፡፡ እግዚአብሄር አብ በሰማይ ያለውን ይህንን ዙፋን ለልጁ የፈቀደለት ለዚህ ነው፡፡
ኢየሱስን የእግዚአብሄር ልጅና አዳኝ አድርጎ ውስን በሆነ ደረጃ የመመልከትና ከዚያ የማይዘልቅ አድርጎ የማየት ዝንባሌ አለ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አሁን በሰማይ የነገሰ ሉዓላዊ ንጉሥ ሆኖ በእግዚአብሄር ዙፋን ላይ ተቀምጦዋል፡፡
ይህ ማለት ግን ኢየሱስ የአባቱን ዙፋን ተቀናቅኖዋል ማለት አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር አብ ዙፋን አሁንም እዚያው አለ፡፡ ልጁን የሰማይ ንጉሥ አድርጎ በማንገሥና እግዚአብሄርን የሚቃወሙትን እንዲፈርድ ፈራጅ አድርጎ በመሾም በሰማይ ሌላ ዙፋን አዘጋጅቶለታል፡፡ አብ ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ አድርጎ በሰማይና በምድር ከማንኛውም ሌላ ሰው ሁሉ በላይ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ አዳኛችንና አምላካችን የሆነውን ኢየሱስን ማመስገንና ማምለክ አለብን፡፡
 
ቁጥር 3፡- ‹‹ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖንን ዕንቁ ይመስል ነበር፡፡ መልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበር፡፡››
ይህ ቁጥር በአዲሱ ዙፋን ላይ የተቀመጠውን የእግዚአብሄር ክብር ያብራራል፡፡
 
ቁጥር 4፡- ‹‹በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፡፡ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር፡፡››
በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን ዙሪያ የእርሱ አገልጋዮች ተቀምጠዋል፡፡ እዚህ ላይ የእግዚአብሄር ዙፋን በ24 ተጨማሪ ዙፋኖች እንደተከበበና በእነዚህ ዙፋኖች ላይ በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊሎችን የደፉ 24 ሽማግሌዎች እንደተቀመጡ ነግሮዋል፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች በ24 ዙፋኖች ላይ መቀመጣቸው ትልቅ የእግዚአብሄር በረከት ነበር፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች በዚህ ምድር ላይ ይኖሩ በነበሩበት ጊዜ ለጌታ መንግሥት የለፉና ሰማዕት የሆኑ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህ ቃል መንግሥተ ሰማይ አሁን የጌታ አምላካችን መንግሥት ሆና በእርሱ አገዛዝ ሥር ለዘላለም እንደምትኖር ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 5፡- ‹‹ከዙፋኑም መብረቅና ድምጽ ነጎድጓድም ይወጣል፡፡ በዙፋኑም ፊት ሰባት የእሳት መብራቶች ይበሩ ነበር፡፡ እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሄር መናፍስት ናቸው፡፡››
መናፍስቶች ሁሉ የፈጠረውና የሚገዛው እግዚአብሄር ነው፡፡
 
ቁጥር 6፡- ‹‹በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባህር ነበረ፡፡ በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሉባቸው አራት እንሰሶች ነበሩ፡፡››
አራቱ እንስሶች ከ24ቱ ሽማግሌዎች ጋር አብረው የእግዚአብሄር መንግሥት አገልጋዮች ናቸው፡፡ እነርሱ ሁልጊዜም የእግዚአብሄርን ፈቃድ ይሻሉ፡፡ ቅድስናውንና ክብሩንም ያመሰግናሉ፡፡ በመታዘዝ የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚተገብሩትም እነርሱ ናቸው፡፡
 
ቁጥር 7፡- ‹‹ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፡፡ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፡፡ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፡፡ አራተኛውም እንሰሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል፡፡››
አራቱ እንሰሶች ለእያንዳንዳቸው በተሰጡ የተለያዩ ተግባራቶች ላይ በመሳተፍ የእርሱን አሳቦች በሙሉ በታማኝነት የሚያገለግሉ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ናቸው፡፡
 
ቁጥር 8፡- ‹‹አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፡፡ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፡፡ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረውና ያለው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም፡፡›› 
እግዚአብሄር እንደማያንቀላፋ ሁሉ እንሰሶቹም በአጠገቡ ሁልጊዜም ነቅተው ስለ ክብሩና ቅድስናው ያለ ማቋረጥ ያመሰግኑታል፡፡ በግ የሆነውን የእግዚአብሄር ቅድስናና ሁሉን ቻይ ስልጣኑን ያመሰግናሉ፡፡ እግዚአብሄርን የነበረ፣ ያለና የሚመጣ አምላክ አድርገው ያመሰግኑታል፡፡ እንዲህ በእነርሱ የተመሰገነው አምላክ እግዚአብሄር አብና አምላክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
 
ቁጥር 9፡- ‹‹እንስሶቹም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴ ምስጋናም በሰጡት ጊዜ፡፡››
የእግዚአብሄር አገልጋዮች ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእርሱ ክብር ወዳሴና ምስጋናን ያቀርባሉ፡፡
 
ቁጥር 10፡- ‹‹ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ፡-››
አራቱ እንስሶች እግዚአብሄርን ሲያመሰግኑ በ24 ዙፋኖች ላይ የተቀመጡት ሽማግሌዎች አክሊሎቻቸውን በእግዚአብሄር ፊት በማኖር ‹‹ጌታችን ሆይ ክብር፣ ውዳሴ፣ ሐይልም ልትቀበል ይገባሃል›› በማለት ያመሰግኑታል፡፡
 
ቁጥር 11፡- ‹‹ጌታችንና አምላካችን ሆይ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር፣ ውዳሴ፣ ሐይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ፡፡››
24ቱ ሽማግሌዎች ለእግዚአብሄር የሰጡት ምስጋና የፈለቀው እግዚአብሄር ሁሉን ስለፈጠረና ሁሉም በእርሱ ስለተፈጠሩ ክብርን፣ ውዳሴንና ሐይልን ሁሉ ሊቀበል የተገባው ስለመሆኑ ካላቸው እምነት ነው፡፡