Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[12-1] ወደፊት በአያሌው የምትጎዳው የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 12፡1-17 ››

ወደፊት በአያሌው የምትጎዳው የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 12፡1-17 ››
‹‹ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፡፡ ጸሐይንም ተጎናጽፋ፣ ጨረቃም ከእግሮችዋ በታች ያላት፣ በራስዋም ላይ የአስራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ እርስዋም ጸንሳ ነበር፡፡ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች፡፡ ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፡፡ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶችም ነበሩት፡፡ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፡፡ ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው፡፡ ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕጻንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ፡፡ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ልጅዋም ወደ እግዚአብሄርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ፡፡ ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡዋት በእግዚአብሄር ተዘጋጅቶላት ወደነበረው ስፍራ ወደ በረሃ ሸሸች፡፡ በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላዕክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፡፡ ዘንዶውም ከመላዕክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፡፡ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም፡፡ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፡፡ ወደ ምድር ተጣለ፡፡ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡ ታላቅም ድምጽ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፡- አሁን የአምላካችን ማዳንና ሐይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፤ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና፡፡ እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፡፡ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም፡፡ ስለዚህ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ ደስ ይበላችሁ፡፡ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፤ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና፡፡ ዘንዶውም ወደ ምድር እንደተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት፡፡ ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፣ ዘመናትም፣ የዘመንም እኩሌታ ወደምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሃ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት፡፡ እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውሃ ከአፉ በስተኋላዋ አፈሰሰ፡፡ ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፡፡ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው፡፡ ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሄርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፡፡ በባህርም አሸዋ ላይ ቆመ፡፡››
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፡፡ ጸሐይንም ተጎናጽፋ፣ ጨረቃም ከእግሮችዋ በታች ያላት፣ በራስዋም ላይ የአስራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡
ይህ በሰማዕትነት አማካይነት ለእርሱ ክብርን ስለምትሰጠው የአምላክ ቤተክርስቲያን ይነግረናል፡፡ ‹‹ጸሐይን የተጎናጸፈችው ሴት›› በዚህ ምድር ላይ ያለችውን የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ታመለክታለች፡፡ ‹‹ጨረቃም ከእግሮችዋ በታች ያላት›› የሚለው ሐረግም ቤተክርስቲያን አሁንም ድረስ በዓለም አገዛዝ ሥር ነች ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹በራስዋም ላይ የአስራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት›› የሚለው ሐረግ የእርሱ ቤተክርስቲያን በሰማዕትነትዋ የሰይጣንን ስደትና ዛቻዎች ታሸንፋለች ማለት ነው፡፡
ይህ ቁጥር በታላቁ መከራ ውስጥ ያለችውን የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በመጨረሻው ዘመን ከሰይጣን ዘንድ ታላላቅ ጉዳቶች ይደርሱባታል፡፡ ሰማዕትም ትሆናለች፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ሰይጣንን በእምነቷ አሸንፋ በእግዚአብሄር ትከብራለች፡፡ በመከራው ዘመን ውስጥ እንኳን የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ቅዱሳኖች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ጸረ ክርስቶስን ድል ያደርጉታል፡፡ በሰማዕትነታቸውም ያሸንፉታል፡፡ 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግመኛ የተወለዱት የእግዚአብሄር ልጆች በመጨረሻው ዘመን በእርግጠኝነት ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ መከራው ከመምጣቱ በፊት አስቀድመው ያመኑ እግዚአብሄርን ያገለገሉና በወንጌል አምነው በመከራው ውስጥ እንደ ብዙ የጅብ ጥላ ተክሎች የሚነሱት ሰዎች ሁለቱም ጸረ ክርስቶስን መቋቋምና ማሸነፍ የሚያስችል ሰማዕት የመሆን እምነት ይኖራቸዋል፡፡
እርሱን በመክዳት ከሰማዕትነት የሚገለሉ ሰዎችም ከሰማይም እንደዚሁ ይገለላሉ፡፡ ከሰይጣን ጋርም ወደ ገሃነም ሲዖል ይወርዳሉ፡፡ ለእኛ የተዘጋጁልንን ዘላለማዊ በረከቶቻችንን እንዳናጣ ሰማዕትነታችንን ቆራጥ በሆነ እምነት ለመቀበል መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ሁሉ የሰይጣን ዛቻ እንደሚገጥማቸው ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ሰማዕትነት የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ይህ አጭር ጊዜ ሲያበቃም የሺህው ዓመት መንግሥትና ሰማይ የእኛ ይሆናሉ፡፡
ስለዚህ የመጨረሻው ዘመን ሲመጣ በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ሰማዕት እንደምንሆን በማወቅ ይህንን የአሁኑን ዘመን ልንኖረው ይገባናል፡፡ ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በዚህ የሰማዕትነት ዘመን የምንናገራቸውን ቃሎች በመስጠት ስደታችንን በድፍረት እንድናሸንፈውና እምነታችን ሳንከዳ በውዴታ ሰማዕትነትን እንድንቀበል ያስችለናል፡፡
በአስፈሪው መከራ ውስጥም ቢሆን የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ሰማዕት በመሆን ሰይጣንን ተዋግታ ታሸንፋለች፡፡ ቤተክርስቲያን በመጨረሻው የሰይጣን ዘመን ውስጥም እንኳን የጌታን ቃል በማመን ጸረ ክርስቶስን አሸንፋ ሽልማቶችዋን ከእግዚአብሄር ዘንድ እንደምትቀበል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
 
ቁጥር 2፡- እርስዋም ጸንሳ ነበር፡፡ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች፡፡
ይህ ቁጥር በመከራዎች ውስጥ ስላለችው የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ይነግረናል፡፡ መላው ቤተክርስቲያን ሰይጣን ባመጣቸው የዘመን መጨረሻ ስደቶችና መከራዎች ውስጥ ጸንታ እንደምታልፍ ይነግረናል፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ከጸረ ክርስቶስ ጋር በምትጋደልበት በታላቁ መከራ ውስጥ ታልፋለች፡፡ ያን ጊዜ ቅዱሳን በመከራ ውስጥ ሲያልፉ የሚጠሩት የእግዚአብሄርን ስም ብቻ ይሆናል፡፡ ‹‹አቤቱ ፈጥነን በእነዚህ መከራዎች ውስጥ እናልፍ ዘንድ ጸጋህን ስጠን፡፡ እነዚህን መከራዎች ሁሉ በመከልከል እርዳን፡፡ መከራዎቻችንን እንድናሸንፍ ፍቀድልን፡፡ ሰይጣንን እንድናሸነፍ አድርገን!›› እያሉ ይጸልያሉ፡፡
 
ቁጥር 3፡- ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፡፡ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶችም ነበሩት፡፡ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፡፡
ሰይጣን ወደፊት በዚህች ምድር ላይ ሲገለጥ አምላክ መስሎ ይንቀሳቀሳል፡፡ የዓለምን መንግሥታቶች በሙሉ በአንድ ላይ በማከማቸትም ዓላማዎቹን እንዲፈጽሙለት መሳርያዎቹ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ቅዱሳኖችን እንደሚገድልና ልክ እንደ አምላክና ንጉሥም በዓለም ላይ እንደሚነግስ በሚገባ የተረጋገጠ ነው፡፡
‹‹እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶችም ነበሩት፡፡ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ›› የሚለው ሐረግ ሰላም አደፍራሹ ሰይጣን ሰባት ነገሥታቶችንና አስር መንግሥታቶችን በእርሱ ትዕዛዝ ሥር አድርጎ እንደሚያንቀሳቅስ ያሳያል፡፡ ይህም ሰይጣን ከነማንነቱ እግዚአብሄርን አክርሮ እንደሚቃወም ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 4፡- ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው፡፡ ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕጻንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ፡፡
ይህ ቁጥር ሰይጣን ምን እንደሚያደርግ ይነግረናል፡፡ ዘንዶው በሰማይ በእግዚአብሄር ላይ በመነሳቱ ከዚያ ተጣለ፡፡ የሰማይን መላእክቶች ሲሶ ወደ ራሱ በረት ስቦ በማስገባት ከራሱ ጋር አብሮ ወደ ጥፋት ነዳቸው፡፡ ነገር ግን እዚህ ምድር ላይ ሆኖም በዚያ የሚያምኑትን በማሳደድ የእግዚአብሄርን ወንጌል ሥራ ለማቆም አሁንም ይሞክራል፡፡
 
ቁጥር 5፡- አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ልጅዋም ወደ እግዚአብሄርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ፡፡
ይህም የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንዋ ሰማዕት ስለሆነች ከክርስቶስ ጋር ተነስታ ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደምትነጠቅ ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 6፡- ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡዋት በእግዚአብሄር ተዘጋጅቶላት ወደነበረው ስፍራ ወደ በረሃ ሸሸች፡፡
ይህ ቁጥር እግዚአብሄር በዚህ ዓለም ላይ የራሱን ሕዝብ ለሦስት ዓመት ተኩል እንደሚመግብ ይነግረናል፡፡ መከራው እንዳለ ከመምጣቱ በፊት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ለ1,260 ቀናት በእግዚአብሄር ትመገባለች፤ ትጠበቅማለች፡፡ ጊዜው ሲደርስም ከጸረ ክርስቶስ ጋር ተዋግታ ሰማዕት ትሆናለች፡፡
 
ቁጥር 7-8፡- በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላዕክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፡፡ ዘንዶውም ከመላዕክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፡፡ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም፡፡
ይህ ሰይጣን ሙሉ በሙሉ ከሰማይ መባረሩን ይጠቁማል፡፡
ሰይጣን ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ሙሉ በሙሉ ከሰማይ ይጣላል፡፡ ሰይጣን ከእንግዲህ ወዲህ በሰማይ መቆየት አይችልም፡፡ በአየር ላይ ሥልጣን ያለው ሰይጣን በአየርና በምድር ላይ ተቀምጦ አሁን በእነርሱ ላይ ይሰለጥናል፡፡ ሙሉ በሙሉ ከሰማይ ሲወረወርና እግዚአብሄር ባዘጋጀው ጥልቅ ጉድጓድና ሲዖል ውሰጥ ፈጽሞ ይታሰራል፡፡
 
ቁጥር 9፡- ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፡፡ ወደ ምድር ተጣለ፡፡ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡
ሰይጣን በመጨረሻው ዘመን ከሰማይ ተጥሎ ወደዚህ ምድር ሲወረወር ለመጨረሻ ጊዜ ቅዱሳኖችን እያሳደደ ይገድላል፡፡ ያን ጊዜ ብዙ ቅዱሳን በእርሱ እጅ ሰማዕት ይሆናሉ፡፡
 
ቁጥር 10፡- ታላቅም ድምጽ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፡- አሁን የአምላካችን ማዳንና ሐይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፤ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና፡፡
ሰይጣን ከእንግዲህ ወዲህ በመንግሥተ ሰማይ አይገኝም፡፡ የዘመኑ መጨረሻ ሲያልፍ ከእንግዲህ ወዲህ በሰማይ አይቆይም፡፡ ዮሐንስ ራዕይ 21፡27 ክፉ አድራጊዎችም ሆኑ ውሸታሞች በሰማይ እንደማይገኙ የሚነግረን ለዚህ ነው፡፡
 
ቁጥር 11፡- እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፡፡ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም፡፡
የዘመኑ መጨረሻ ሲመጣ ቅዱሳን እምነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ በመጨረሻው ዘመን ቅዱስ የሆነ ማንኛውም ሰው የእምነትን ድል የሚያገኘው በእምነት ሰማዕት በመሆን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በጌታ የሚያምኑ ሰማዕታት ከራሳቸው ጋር ተዋግተው ያሸንፋሉ፡፡
 
ቁጥር 12፡- ስለዚህ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ ደስ ይበላችሁ፡፡ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፤ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና፡፡
ሰይጣን ከሰማይ ሲወረወር በዓለም ላይ ጊዜያዊ ሥልጣን ስለሚኖረው ወደዚህ ምድር ሲወርድ ቅዱሳኖችን ክፉኛ ያሰቃያል፤ ያሳድዳቸውማል፡፡ ነገር ግን ሰማዕት የሚሆኑና በአየር ላይ የሚነጠቁ ቅዱሳን የሚጠብቃቸው ደስታ ብቻ ነው፡፡ ከንጥቀት በኋላ እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በምድር ሁሉና በባህር ላይ ያወርዳል፡፡
 
ቁጥር 13፡- ዘንዶውም ወደ ምድር እንደተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት፡፡
ይህ በታላቁ መከራ ጊዜ የሚመጣውን የቅዱሳን ስደት ያመለክታል፡፡ ቅዱሳንና የእግዚአብሄር ባሮች በዚህ ጊዜ ሰማዕት ሆነው ይሞታሉ፡፡ ነገር ግን ይህ በተጨባጭ የእምነት ድላቸው ስኬት ይሆናል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ በእነርሱ ላይ የሚሆን አንዳች ሞት፣ መከራ ወይም እርግማን አይኖርም፡፡ ለእነርሱ የሚቀርላቸው ነገር ቢኖር በሰማይ እግዚአብሄርን ማመስገንና ለዘላለም መክበር ነው፡፡
 
ቁጥር 14፡- ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፣ ዘመናትም፣ የዘመንም እኩሌታ ወደምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሃ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ንጥቀቱ የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ሦስት ዓመት ተኩል ካለፈ በኋላ እንደሚሆን ይነግረናል፡፡ ይህ ቃል እግዚአብሄር በታላቁ መከራ የተፈጥሮ መቅሰፍቶች ውስጥ ለቅዱሳኖቹ ልዩ ጥበቃውንና እንክብካቤውን እንደሚያደርግላቸው ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር ሰይጣንን በዚህ እምነት ተዋግተን እናሸንፈው ዘንድ እምነታችንን የጠበቅነውን ይመግበናል፡፡
አሁን ለውሃውና ለመንፈሱ ወንጌል መኖራችን መንፈሳዊ ምግባችን እንደሆነ ሁሉ ይህንን ወንጌል መስበካችንም እንደዚሁ መንፈሳዊ ምግባችን ነው፡፡ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች በዚህች ምድር ላይ እስከሚወርዱ ድረስ እንኳን ወንጌልን በመስበክ ሕይወታችንን መኖር እንቀጥላለን፡፡ ለምን? ምክንያቱም እስከ መጨረሻዋ የሰማዕትነታችን ቅጽበት ድረስ ይህንን ወንጌል ካልሰበክን በጣም ብዙ ነፍሳቶች በሲዖል ይጠፋሉ፡፡ ከአሁን የተሻለ ሌላ ጊዜ የለም፡፡
 
ቁጥር 15-17፡- እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውሃ ከአፉ በስተኋላዋ አፈሰሰ፡፡ ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፡፡ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው፡፡ ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሄርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፡፡
ሰይጣን ከዚህ ቀደም ቅዱሳኖችን በማሳደድና ከወንጌል እንዲርቁ በማድረግ ገድሎዋቸዋል፡፡ ዛሬ ግን ወንጌል በተለያዩ መንገዶች በስፋት ስለተሰራጨ ሐጢያትን በማፍሰስና በፍሰቱም እንዲሰምጡ በማድረግ ቅዱሳኖችን ለመግደል ይሞክራል፡፡ በዚህም ሰይጣን የሐጢያትን ወንዝ በማፍሰስና ከውሃው እንዲጠጡ በማድረግ ብዙ ቅዱሳኖችን ለመግደል ይሞክራል፡፡ ነገር ግን ዳግመኛ ያልተወለዱ ሰዎች የዚህን የሐጢያትን ወንዝ ውሃ በሙሉ ጠጥተዋል፡፡ በዚህ ጥረት ቅዱሳን ስለተረፉና ስላልተገደሉ ሰይጣን እነርሱን ሙሉ በመሉ ለመግደል በምዕራፍ 13 ላይ እንደታየው ሌላ ዘዴ ይዞ ይመጣል፡፡