Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[12-2] ሰማዕትነታችሁን ደፋር በሆነ እምነት ተቀበሉት፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 12፡1-17 ››

ሰማዕትነታችሁን ደፋር በሆነ እምነት ተቀበሉት፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 12፡1-17 ››
 
ምዕራፍ 12 የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የዘመን መጨረሻዎቹን መከራዎችዋን እንዴት እንደምትጋፈጥ ያሳየናል፡፡ ቁጥር 1 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፡፡ ጸሐይንም ተጎናጽፋ፣ ጨረቃም ከእግሮችዋ በታች ያላት፣ በራስዋም ላይ የአስራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡›› ‹‹ጸሐይን የተጎናጸፈችው ሴት›› በዚህ ምድር ላይ ያለችውን የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ታመለክታለች፡፡ ‹‹ጨረቃም ከእግሮችዋ በታች ያላት›› የሚለው ሐረግም ቤተክርስቲያን አሁንም ድረስ በዓለም አገዛዝ ስር ነች ማለት ነው፡፡ ይህም በዚህ ዓለም ላይ ያለችው የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያንና በእርስዋ ውስጥ ያሉት ቅዱሳን ሰማዕት በመሆን እግዚአብሄርን እንደሚያከብሩት ይነግረናል፡፡
 
‹‹በራስዋ ላይ የአስራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት›› የሚለው ሐረግ የእርሱ ቤተክርስቲያን በመጨረሻው ዘመን በሰማዕትነትዋ የሰይጣንን ስደትና ዛቻዎች እንደምታሸንፍ ያሰያል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል እንደሚነግረን ቤተክርሰቲያን በእርግጥም ታሸንፋለች፡፡ ሰይጣን እምነታችንን ለማጥፋት በሁሉም ዓይነት መንገዶች ቢዝትብን፣ ቢያሰቃየን፣ ቢጎዳንና ውሎ እድሮም ሕይወታችንን ቢጠይቅም አሁንም እምነታችንን ጠብቀን በጽድቅ ሰማዕት እንሆናለን፡፡ የእምነት ድል ይህ ነው፡፡
 
በጥንቷ ቤተክርስቲያን ዘመን ከእኛ የቀደሙ ብዙ ቅዱሳን ሰማዕት ሆነዋል፡፡ ይህ ሰማዕትነት የሚመጣው በእኛ ጉልበት ሳይሆን በልባችን ውስጥ በሚያድረው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
 
‹‹ጸሐይን የተጎናጸፈች ሴት›› በሚለው ሐረግ ውስጥ ‹‹ሴት›› የሚለው እዚህ ላይ የሚያመለክተው የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያን ሲሆን ‹‹ጸሐይን ተጎናጽፋ›› ማለት ደግሞ ቤተክርስቲያን ክፉኛ ትሰደዳለች ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን አስፈሪ በሆኑት መከራዎችና የዘመን መጨረሻ መቅሰፍቶች ውስጥ እንኳን በድፍረት እምነታቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ፈጽሞም ለሰይጣን አያጎበድዱም፡፡ ለምን? ምክንያቱም በልባቸው ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ ጸንተው በመቆም ሰይጣንን እንዲዋጉ ያደርጋቸዋል፡፡ ሕይወታቸውንም ቢሆን አደጋ ላይ እስኪጥሉ ድረስ ለማናቸውም ዛቻ ወይም ስደት ፈጽሞ እንዳይንበረከኩ የሚያደርጋቸውን እምነትም ይሰጣቸዋል፡፡
 
ተስፋቸውን በመንግሥተ ሰማይ ላይ ያደረጉ ሰዎች የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች በቅርቡ እንደሚያበቁና ምድርን ጠራርገው በሚያጠፉ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች እንደሚተኩ በሚነግራቸው የእግዚአብሄር ቃል ስለሚያምኑ ፈጽሞ በሰይጣን ፊት አይንበረከኩም፡፡
 
ለሰይጣን ቢያጎበድዱ የተሻለ ዓለም እንደማይጠብቃቸው የሚያምኑ ሰዎች ፈጽሞ ለሰይጣን ሊያጎበድዱ አይችሉም፡፡ በጸረ ክርስቶስና በተከታዮቹ ላይ የሚወርዱት የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ያለ ዕረፍትና ያለ ምህረት ይፈጁዋቸዋል፡፡ ስለ እነዚህ መቅሰፍቶች የሚያውቁ ቅዱሳን ሁሉም ከዛቻዎች የተነሳ ፈጽሞ እምነታቸውን አይጥሉም፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ሰይጣንን የምንቋቋምበትን፣ የምናሸንፍበትንና ሰማዕት የምንሆንበትን ጉልበት ይሰጠናል፡፡
 
የአራተኛው መለከት መቅሰፍት አልፎ የአምስተኛውና የስድስተኛው መለከት መቅሰፍቶች ሲመጡ ‹‹ሰማዕትነት›› ወደ እኛ ይመጣል፡፡ እምነታቸውን የሚጠብቁና ሰማዕት የሚሆኑት ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ሲወርዱ ጸረ ክርስቶስ በእግዚአብሄር ተፈቅዶለት በዓለም ላይ ለጊዜው ይሰለጥናል፡፡
 
የሰይጣን አገልጋይ የሆነው ጸረ ክርስቶስ ሥልጣኑ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሆነ ስለሚያውቅ በተቻለ መጠን ብዙ ሕዝቦችን ከእርሱ ጋር አብሮ ወደ ሲዖል ለመውሰድ ኢየሱስ ክርስቶስን ጌታቸው አድርገው የሚያገለግሉትን ያሳድዳል፡፡ ነገር ግን በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ወደ ኢየሱስ ያስተላለፉ ሰዎች ለጸረ ክርስቶስ ስደት አይንበረከኩም፡፡ ሆኖም በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠውን ወንጌል በቆራጥነት ተከላክለው ሰማዕት ይሆናሉ፡፡
ስለዚህ ሰማዕትነት የእምነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህ ማረጋገጫ ያላቸው ሰዎች ጌታ ያዘጋጀላቸውን የሺህ ዓመት መንግሥትና አዲስ ሰማይና ምድር ያገኛሉ፡፡ ይህም በመላው ዓለም ተበታትነው ያሉትንና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትን ይመለከታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳን ሁሉ በእነዚህ በመጨረሻዎቹ ዘመናቶች ወቅት ሰማዕት እንደሚሆኑ ይነግረናል፡፡
 
ነገር ግን ከሰማዕትነት ለማምለጥ ሲሉ በውሃውና በመንፈሱ ላይ ያላቸውን እምነት የሚተዉ ሰዎች ከጸረ ክርስቶስ ጎን ቆመው እርሱን እንደ አምላክ ስለሚያገለግሉትና ስለሚሰግዱለት በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶችና በራሱ በጸረ ክርስቶስ እጅ ይገደላሉ፡፡ ሞታቸው ተስፋ ቢስ የሆነ ከንቱ ሞት እንጂ ፈጽሞ ሰማዕትነትን የተላበሰ አይሆንም፡፡ ሰይጣንና ጸረ ክርስቶስ ወደ ሲዖል ሲጣሉ እነዚህ ሰዎችም አብረው ይጣላሉ፡፡
 
ሰማዕትነትን ለማምለጥና የመከራዎቹን ስቃዮች ለማሳነስ ተብሎ ኢየሱስ ክርስቶስን መካድ የሞኝ ድርጊት ነው፡፡ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ሲያበቁና እምነታቸውን የጠበቁትም ሰማዕት ሲሆኑ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ፈጥነው ይህችን ምድር ያወድሙዋታል፡፡ የሚተርፉትም ጥቂቶች ይሆናሉ፡፡ የሐጢያት ስርየትን የተቀበሉ ሰዎች ሰማዕት መሆናቸው በሚገባ የተረጋገጠ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እኛ በዚህ የሰማዕትነት ወቅት ጌታችንን እንዳንክድ ስለ መጨረሻው ዘመን ትክክለኛ እውቀትና ትክክለኛ የቃል መረዳት ይዘን በማመን አሁኑኑ እምነታችችንን ማዘጋጀት አለብን፡፡
 
እኛ የሐጢያቶቻችንን ስርየት ተቀብለናል፡፡ ሰማዕት ስንሆንም ከዚህ ቀደም የማናውቀውን ደስታ እንለማመዳለን፡፡ እግዚአብሄር ያበረታናልና፡፡ እናንተና እኔ ዕጣ ፈንታችን ለእግዚአብሄር ሰማዕት ለመሆን እንደሆነ የተወሰነልንን እምነታችንን በልባችን ውስጥ በግልጽ ልናጸናው ይገባል፡፡ ይህ የሰማዕትነት ወቅት ሲያልፍ እግዚአብሄር ትንሳኤያችንንና ንጥቀታችንን በእርግጠኝነት በመስጠት በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ እንድንከብር ይፈቅድልናል፡፡ የራሱን ዘላለማዊ አዲስ ሰማይና ምድር በመስጠት እንድንነግስ ያደርገናል፡፡ ለዘላለምም በብልጥግና እንድንኖር ይፈቅድልናል፡፡ እኛ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ በጽናት ብናምን መከራችን ራሱ ወደ ደስታችን ይለወጣል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ስቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡›› (ሮሜ 8፡18) ጳውሎስ ወንጌልን ሲያገለግል ክፉኛ መከራን ተቀብሎዋል፡፡ በብዙ አጋጣሚዎችም ከአንድ ጊዜ በላይ እስከ ሞት ድረስ ተደብድቦዋል፡፡ ነገር ግን ይህ መከራ ለእግዚአብሄር ክብር እንደነበር በማመን የጳውሎስ ስቃይ ድንቅ የሆነ ደስታ ሆነለት፡፡ በታሪክ ዘገባዎችና አፈ ታሪኮች መሰረትም ጳውሎስን ጨምሮ አብዛኞቹ ሐዋርያቶች ሰማዕት ሆነዋል፡፡ ጴጥሮስ በቫቲካን ኮረብታ ላይ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎዋል ይባላል፡፡ ፖሊካርፕን ጨምሮ የጥንት ቤተክርስቲያን መሪዎችና ብዙ ሌሎች ቅዱሳኖች በእንጨት ላይ እስከ ሞት ድረስ ይቃጠሉ በነበረ ጊዜ ለእግዚአብሄር የምስጋና መዝሙሮችን ይዘምሩ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ቅዱሳኑን ባያበረታቸው ኖሮ እንደዚህ ያሉ ነገሮች የማይቻሉ ነበሩ፡፡
 
በዚህ ዘመን እንደ እነዚህ ያሉ ታማኝ ቅዱሳኖች የነበሩትን ያህል እምነታቸውን የካዱም ደግሞ ነበሩ፡፡ በዛሬዎቹ የሥነ መለኮት ሊቃውንቶች ትልቅ ክብር የሚሰጠው የሥነ መለኮት ሊቅ ኦሪጀን ወንጌልን በቀጥታ ከሐዋርያቶች የሰማ ሰው ነበር፡፡ ነገር ግን ሰማዕት የሚሆንበት ጊዜ ሲመጣ ሸሸ፡፡ ወገን ቅዱሳኖቹ ሰማዕት ሲሆኑ የእርሱ ሕይወት ግን ተረፈ፡፡ ኢየሱስ ለእርሱ ያደረገለትን ነገር ሁሉ ባይክድ ኖሮ ይህ የሚቻል አልነበረም፡፡ ስለዚህ ኦሪጀን የኢየሱስን መለኮታዊነት የካዱ ሰዎች ወኪል ነበረ፡፡ ነገር ግን ክህደቱ እንዳለ ሆኖ የዛሬዎቹ የሥነ መለኮት ሊቃውንቶች እጅግ ከተከበሩ የሥነ መለኮት ሊቃውንቶች መካከል ከፍተኛ ቦታ ሰጥተውታል፡፡
 
ሌሎች ቅዱሳን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ኦሪጀን ለምን ሸሸ? ይህ የሆነው የሌሎቹ ሰማዕት ቅዱሳን የፈቃድ ሐይል ጠንካራ ሆኖ የኦሪጀን የፈቃድ ሐይል ደካማ ስለነበረ አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን እያመሰገኑ ሰማዕት የሆኑት ቅዱሳን ይህንን ያደረጉት ጳውሎስ የተናገረውን ማለትም ‹‹ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ስቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ›› የሚለውን ስላመኑ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር እንደሚያስነሳቸውና እንደሚነጥቃቸው የሺህ ዓመቱንም መንግሥት እንደሚሰጣቸው የሚናገረውን የእግዚአብሄርን የተስፋ ቃል በማመናቸው የአሁኑን ዘመን ስቃያቸውን መሸከም ቻሉ፡፡
ሰማዕትነት እንደሚገጥመን በግልጽ መገንዘብ አለብን፡፡ ይህንን እውነት በግልጽ አውቀው የእምነት ሕይወታቸውን የሚኖሩ ሰዎች ከቀሩት የተለዩ ናቸው፡፡ በጥንት ቤተክርስቲያን ዘመን ሰማዕት በሆኑ ቅዱሳን ስዕል የሚያምኑ ሰዎች የራሳቸው ስዕል፣ የራሳቸው የእምነት ሕይወት ብርቱ፣ የከበረና ደፋር ሊሆንላቸው ይችላል፡፡ ያን ጊዜም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሁሉ የራሳቸው ታሪክ ይሆናል፡፡ እነርሱ ሁልጊዜም የሚኖሩት ሰማዕትነትን መቀበል በሚችል እምነት ነው፡፡ ማለትም ሁልጊዜም ከሰማዕትነታቸወ በኋላ እግዚአብሄር አስቀድሞ ለእነርሱ ያቀደላቸውን ትንሳኤያቸውንና ንጥቀታቸውን፣ አዲስ ሰማይና ምድርንም እንደሚሰጣቸው በማመን ይኖራሉ፡፡
 
በዚህ የሚያምኑ ሁልጊዜም ደፋር የእምነት ሕይወትን መኖር ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄርን እያመሰገኑ መሞት ይችሉ ዘንድ እምነታቸው ለፍጻሜያቸው ያዘጋጃቸዋልና፡፡ ይህ የተጨባጭ እምነት ጉዳይ እንጂ ቀላል የሆነ የእምነት ትምህርት ጉዳይ ስላልሆነ በዚህ ቃልና ወንጌል ሙሉ በሙሉ የማያምኑ ሰዎች እኛን ለጸረ ክርስቶስ ለመሸጥ የመጀመሪያዎቹ ይሆናሉ፡፡ አንድ ጊዜ እናንተና እኔ ሰማዕት እንደምንሆን ስናውቅ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ እምነት ያላቸውና ለዘላለምም አብረውን የሚሆኑ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለእኛ ጠቃሚዎች የሚሆኑት ለዚህ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ባሮች፣ የእርሱ ሕዝብና የእርሱ ቤተክርስቲያን እነዚህ ሁሉ ለእኛ ክቡር ናቸው፡፡
 
የጥንት ቤተክርስቲያን ዘመን ቅዱሳኖች አሁን በመጨረሻው ዘመን ከምንኖረው ከእኛ እምነት ይልቅ በጣም ታማኝና የማያወላውል እምነት ነበራቸው፡፡ እነርሱ ሰማዕትነታቸውን ተከትሎ በሚመጣው ትንሳኤያቸው፣ ንጥቀታቸው፣ በሺህ ዓመት መንግሥትና አዲስ ሰማይና ምድር አምነዋል፡፡ የእምነት ሕይወታቸውን በተጨባጭ በታላቁ መከራ ዘመን ውስጥ እየኖሩ እንዳለ፣ የጌታ ምጽዓትም እየቀረበ እንዳለ አድርገው ይኖሩ የነበሩት ለዚህ ነው፡፡ በቅርቡ በሚመጣው የታላቁ መከራ ዘመን ጊዜ ውስጥ የምንኖር ሰዎች ስለ እነርሱ ስናነብ ታሪኮቻቸው ተጨባጭና ግልጽ ሆነው ይማርኩናል፡፡ ምክንያቱም እነርሱም እንደዚሁ ስለ መከራው የሚናገረውን የእግዚአብሄርን ቃል ሁሉ ሰማዕትነታቸውን፣ ትንሳኤያቸውንና ንጥቀታቸውን አውቀው አምነዋልና፡፡
 
እኛ ሕይወታችንን በተጨባጭ የምንኖረው የዘመኑ መጨረሻ በዓይኖቻችን ፊት እየተቃረበ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን በመሆኑ ሰማዕትነትን የምንቀበልበትን እምነታችንን በልባችን ውስጥ አጥብቀን ማዘጋጀት አለብን፡፡ ሰይጣን በክርስቶስ ውሃና ደም የሚያምነውን ሰው ሁሉ በመቃወም እምነቱን ለማፍረስ ይሞክራል፡፡ ለዚህ የሰይጣን ተቃውሞ ላለመንበርከክ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በልባችን ላይ በማሰር በአዲሱ ሰማይና ምድር ላይ ባለን ተስፋ አንድ ጊዜ ደግመን ጥንካሬውን በመመርመርና ይህ እምነታችን ሰማዕት እስከምንሆንበት ቅጽበት ድረስ እንደማይላላ ማረጋገጥ አለብን፡፡
 
የጥንት ቤተክርስቲያን ዘመን ቅዱሳኖች እምነታቸውን ባለ በሌለ ሐይላቸው የጠበቁት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መከራው፣ ስለ ሰማዕትነታቸው፣ ትንሳኤያቸውና ንጥቀታቸው የተናገረውን ሁሉ በማወቃቸውና በማመናቸው ነው፡፡ እናንተና እኔም እንደዚሁ ሰማዕት እንሆናለን፡፡ እኔ እሞታለሁ፤ እናንተም ደግሞ ትሞታላችሁ፡፡ ሁላችንም እምነታችን ለመጠበቅ እንሞታለን፡፡ ምናልባት ተጎትቼ ለመገደል የመጀመሪያው እኔ ልሆን እችላለሁ፡፡ ይህ በራሱ አስፈሪ ትዕይንት መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ በመጨረሻ ግን የሚያስፈራ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ሰማዕትነትን የመሸሹ ተጠየቃዊ ድምዳሜ እምነታችንን መካድ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ፈጽሞ ልናደርገው የማንችለው ነገር ነው፡፡
 
የሆኖ ሆኖ እግዚአብሄር በእኛ ሰማዕትነት ሊከበር ነው፡፡ እርሱ ይህንን የእኛ ዕጣ ፈንታ አድርጎ ወስኖታል፡፡ ስለዚህ ይህ ቢያንስ አንድ ጊዜ ልናልፍበት የሚገባን ነገር ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የማለፉን ነገር ልናስወግደውም ሆነ ልንሸሸው ስለማንችል በሙሉ ጉልበት ወደ እርሱ ሮጠን በድፍረት እንግባበት፡፡ እኛ ማንም ሌላ ሰው የሌለው የንጉሡ ሥልጣን አለን፡፡ የዘላለማዊ በረከቶች ተስፋም እንደዚሁ አለን፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር እንዲያበረታን ሁልጊዜም ወደ እርሱ መጸለይ እንችላለን፡፡ አብዝተንም ክብርን እንሰጠዋለን፡፡ ሰማዕትነታችንን ሳንፈራ በማመን የበለጠ ደስታን እንቀበላለን፡፡ ይህ ለእግዚአብሄር ታላቅ ክብር ለእኛም ታላቅ በረከት ነው፡፡
 
እግዚአብሄር የራዕይን መጽሐፍ የጻፈው ስለ ቅዱሳን ሰማዕትነት፣ ትንሳኤ፣ ንጥቀት፣ የሺህ ዓመት መንግሥትና አዲስ ሰማይና ምድር ሊነግረን ነው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ የራዕይ ዕውቀት ካላችሁ በዚህ እያሽቆለቆለ ባለው ዓለም ውስጥ እምነታችሁን መኖር ትችላላችሁ፡፡ በራዕይ ውስጥ ወዳለው አዲስ ሰማይና ምድር የሚወስደውን ጎዳና ያለ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል መጓዝ አይቻልም፡፡ ይህ እምነትም በሰማዕትነት ውስጥ ሳይታለፍ አይረጋገጥም፡፡ ስለዚህ ጊዜው ሲደርስ ሰማዕት እንደምትሆኑ እንጂ ወንጌልን እንደማትክዱ በማመንና በእምነታችሁም ወደፊት በማየት እምነታችሁን ከልባችሁ ጋር አጥብቃችሁ እንድታስሩ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እጸልያለሁም፡፡ ያን ጊዜ የእምነት ሕይወታችሁ ከዚህች ቅጽበት ጀምሮ በሚገባ ይለወጣል፡፡
 
በሰይጣን ወጥመዶች ውስጥ ተይዘን በከንቱ አንሞትም፡፡ በልባችን ውስጥ የሚሰራውን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ተከትሎ እምነታችንን ለመጠበቅ እንሞታለን፡፡ ሰማዕት የምንሆንበት ቀን በእርግጥም ይመጣል፡፡ ይህ ዋናው ሰማዕትነት ነው፡፡ እኛ ግን አንፈራውም፡፡ ምክንያቱም ሥጋችን በሰይጣን ቢገደልም እግዚአብሄር እንደገና በአዲሱ ክቡር አካሎቻችን በሕይወት እንድንኖር ያደርገናል፡፡ ሰማዕትነታችን ተከትሎም ወዲያውኑ ትንሳኤያችንና ንጥቀታችን እንደሚመጣ እናውቃለን፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚጠብቀን ነገር ቢኖር በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ የመንገስ በረከትና በሰማይም ዘላለማዊ ንግሥናችን ነው፡፡
 
ጥንት የሮም ንጉሠ ነገሥት ኔሮ ከተማይቱን እንደገና ለመገንባት ሲል በእሳት አቃጥሎዋት ነበር፡፡ የሮም ዜጎች በዚህ ክፉኛ በተቆጡ ጊዜ ሰደድ እሳቱን የለኮሱት ክርስቲያኖች ናቸው ብሎ በእነርሱ ላይ በማላከክ ማንንም ሳይለይ ፈጃቸው፡፡ ልክ እንደዚሁ በታላቁ መከራ ወቅት የተፈጥሮ ጥፋቶች ዓለምን ሲመቷት ጸረ ክርስቶስ መቅሰፍቶቹን ሁሉ በእኛ በቅዱሳን ላይ በማላከክ በሐሰት ይከሰንና ይገድለናል፡፡
 
ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ መሞት የምንችልበትን እምነት፤ ሰማዕት የምንሆንበትን እምነት ይሰጠን ዘንድ ወደ እግዚአብሄር መጸለይ አለብን፡፡ እምነታችንን ካልተውንና ሰማዕት ከሆንን የእግዚአብሄር ክብር ይገለጣል፡፡ ነገር ግን እምነታችንን ትተን ለጸረ ክርስቶስ በመንበርከክ እርሱን አምላክ አድርገን የምንቀበል ከሆንን ወደ ዘላለም እሳት እንወረወራለን፡፡ በሌላ አነጋገር ጸረ ክርስቶስን ማሸነፍ የምንችልበትን እምነት ይሰጠን ዘንድ ወደ እግዚአብሄር ብንጸልይ ጌታችን ጉልበትንና ሐይልን ይሰጠናል፡፡ ነገር ግን ልባችንን ካላጸናንና እምነታችንን ከካድን እርሱ የሚሰጠን ሲዖልን ብቻ ይሆናል፡፡
 
ከኮርያ ጦርነት የተገኘ አንድ አጭር ታሪክ ልንገራችሁ፡፡ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች በሰሜናዊው የገጠር ከተማ ወደምትገኝ አንዲት ቤተክርስቲያን መጡ፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ መሪ ቹዳል ቤ የሚባል ዲያቆን ነበር፡፡ የቤተክርስቲያኑ ግቢ ቆሽሾ ስለነበር ወራሪው ወታደር ለዲያቆኑ ግቢውን እንዲያጸዳ ነገረው፡፡ ይህ ዲያቆን ግን የጌታን ቀን ቀድሶ መጠበቅ እንዳለበት በመናገር ያንን ለማድረግ አሻፈረኝ አለ፡፡ ወታደሮቹ ስለተበሳጩ ግቢውን ካላጸዳ በጉባኤው ፊት እንደሚገድሉት ዛቱበት፡፡ ዲያቆኑ ግን እምነቱን መጠበቅ እንደነበረበት በመናገር በእምቢተኛነቱ ቀጠለ፡፡ ውሎ አድሮም ተገደለ፡፡ በኋላም አንዳንድ ክርስቲያኖች የእርሱን ሞት ሰማዕትነት ብለው ጠሩት፡፡ ለምን? ሰማዕትነት ለጽድቅ ሥራ መሞት ማለትም የእግዚአብሄርን ክብር መግለጥ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ስም በመጠቀም በግትርነት መሞት ከሰማዕትነት የራቀ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር የሰጠንን የደህንነት ፍቅር መወርወር እንችላለንን? በእንከኖቻችንና በሐጢያቶቻችን ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በጥምቀቱ ወስዶ ለሞት ተሰቀለ፡፡ እኛ ለዚህ ለጌታችን ፍቅር ሙሉ ታማኝነትን እስከ ሞት ድረስ መስጠት የማንችል ከሆንን በሞታችን ለሚጠፋው ሥጋ ስንል አዲስ ሰማይና ምድርን የሰጠንን ወንጌል ከመወርወር አንመለስም፡፡ እኛ ወደዚህ የተወለድንበት ዕጣ ፋንታ እግዚአብሄር ለእኛ ለሰጠን ክብር ስንል የሰይጣንን የእምነት ተግዳሮት ለማሸነፍ በእምነት መኖርና ሰማዕት መሆን እንደሆነ አትርሱ፡፡
 
እኛ በጣም ብዙ ጉድለቶች ያሉብንና በእንከኖች የተሞላን ስለሆንን በምንም ነገር ለእግዚአብሄር ክብርን መስጠት አንችልም፡፡ እንደ እኛ ዓይነት ላሉ ሰዎች እግዚአብሄር ለጌታ ታላቅ ክብርን የምንሰጥበት ዕድል ሰጥቶናል፡፡ ይህ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን ሰማዕትነት ነው፡፡ ከዚህ አትሽሹ፡፡ ብንለምነው የመከራውን ጊዜ በሚያሳንስልን በእግዚአብሄር እንመን፡፡ አዲስ ሰማይና ምድር የምንወርስበትን ተስፋ የሙጥኝ ብለን በመያዝ ፈጥኖ የሚያበቃውን አላፊውን መከራችንን እናሸንፍ፡፡ በታማኝነት ለእርሱ በኖሩት ላይ በጣም የከበደ መከራን እንደማይፈቅድ፤ እምነታቸውን እንዲክዱ የሚያደርጋቸውንም አንዳች ነገር እንደማይሰጥ በማመን እንኑር፡፡ ነገር ግን ይጠብቃቸዋል፡፡ ተጨማሪ የትተረፈፈ ጸጋም ይለግሳቸዋል፡፡
 
ሰማዕት እንደምንሆን በመገንዘብ መከራን የመጋፈጥ፣ በመከራ ውስጥ የመጽናትና ለጌታ የመስራት ተሞክሮ ያስፈልገናል፡፡ በእነዚህ ነገሮች አማካይነት ከጌታ ጋር በሚኖረን የጉዞ ተሞክሮ በእምነታችን እናድጋለን፡፡ የዘመኑ መጨረሻ ሲደርስ ጌታ በሰጠን ጉልበት ሰማዕትነታችንን መጋፈጥ እንችላለን፡፡ ለእግዚአብሄር መከራን የመቀበል፣ ለእርሱ ታማኝ የመሆን ወይም ለእርሱ የመስራትና መስዋዕት የመሆን አንዳች ተሞክሮ ሳይኖረን ከቀረን ሰማዕት የምንሆንበት ታላቁ የመከራ ጊዜ ሲመጣ አንዳች ፍርሃት ይወረናል፡፡ መከራቸውን ደግመው ማሸነፍ የሚችሉት ከዚህ ቀደም መከራን የተቀበሉና ስቃይን ያሸነፉ ብቻ ናቸው፡፡
 
የእምነት ሕይወታችሁ ለጌታ መከራን የመቀበልና በእርሱም ላይ ድል የምትቀዳጁበት እንዲሆንና ሰማዕት የመሆኛው ዘመን ሲመጣም እነዚህ ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሄር በረከትና ጸጋ አማካይነት ለክብራቸው የተፈቀዱላቸው እንደሆኑ በልባቸው ከሚያስታውሱና በአንደበታቸው ከሚመሰክሩ ታማኞች መካከል እንድትገኙ ወደ እግዚአብሄር እጸልያለሁ፡፡
 
መንግሥተ ሰማይን በእምነታችሁ ለማግኘት አብዝታቸሁ የምትሹ ከሆነ አዲስ ሰማይና ምድር በእርግጥም የእናንተ ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሄር ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲመጡ ይሻል፡፡ 91ኛ ጢሞቴዎስ 2፡4)