Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[13-1] የጸረ ክርስቶስ መገለጥ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 13፡1-18 ››

የጸረ ክርስቶስ መገለጥ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 13፡1-18 ››
‹‹በባህርም አሸዋ ላይ ቆምሁ፡፡ አንድም አውሬ ከባህር ሲወጣ አየሁ፡፡ አስር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፡፡ በቀንዶቹም ላይ አስር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ፡፡ ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፡፡ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፣ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ፡፡ ዘንዶውም ሐይሉንና ዙፋኑን፣ ትልቅም ሥልጣን ሰጠው፡፡ ከራሶቹም ለሞት እንደታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፤ ለሞቱ የሆነውም ቁስል ተፈወሰ፡፡ ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፡፡ ለዘንዶውም ሰገዱለት፤ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፡- አውሬውን ማን ይመስለዋል? እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት፡፡ ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፡፡ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሰራ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ እግዚአብሄርንም ለመሳደብ፣ ስሙንና ማደሪያውንም፣ በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ፡፡ ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፡፡ በነገድና በወገንም፣ በቋንቋም፣ በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል፡፡ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ፡፡ ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገደል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል፡፡ የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው፡፡ ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፡፡ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት፡፡ እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር፡፡ በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል፡፡ ለሞቱ የሆነውም ቁስል ተፈወሰለት፡፡ ለፊተኛውም አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል፡፡ እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል፡፡ በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፡፡ የሰይፍም ቁስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል፡፡ የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱትን ሁሉ ሊያስገድላቸው ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው፡፡ ታናናሾችና ታላላቆችም፣ ባለጠጋዎችና ድሆችም፣ ጌታዎችና ባርያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፤ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቁጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል፡፡ ጥበብ በዚህ አለ፡፡ አእምሮ ያለው የአውሬውን ቁጥር ይቁጠረው፤ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፤ ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- በባህርም አሸዋ ላይ ቆምሁ፡፡ አንድም አውሬ ከባህር ሲወጣ አየሁ፡፡ አስር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፡፡ በቀንዶቹም ላይ አስር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ፡፡
ሐዋርያው ዮሐንስ አንድ አውሬ ከባህር ሲወጣ አየ፡፡ ዮሐንስ ባየው በዚህ አውሬ አማካይነት እግዚአብሄር ጸረ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ በሚገለጥበት ጊዜ የሚያደርገውን አሳይቶታል፡፡ እግዚአብሄር ለዮሐንስ ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶች ያሉትን ይህንን አውሬ ያሳየው በትክክል በዚህ ዓለም ላይ እንደሚገለጥ ሊነግረን ሳይሆን የዚህ አውሬ ሥልጣንና ሐይል ያለው አንድ ሰው ተገልጦ ቅዱሳኖች እንደሚያሳድድና ሰማዕታት እንደሚያደርጋቸው ሊነግረን ነው፡፡
ታዲያ ይህ ማለት በራዕይ ውስጥ የታየው እያንዳንዱ ነገር ተምሳሌታዊ ብቻ ነው ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም! እግዚአብሄር የጸረ ክርስቶስን መገለጥና ሥራዎች ለመግለጥ በእነዚህ ራዕዮች መናገር ፈለገ፡፡ ይህ እግዚአብሄር ብቻ ሊናገርበት የሚችልበት ጥበብና ሐይል ነው፡፡ እኛም በራዕይ 13 ቃል አማካይነት የዘመን መጨረሻውን ግልጽ ስዕል ማየት መቻል አለብን፡፡
በመጀመሪያ ዮሐንስ ያየው ከባህር የወጣ አውሬ ነበር፡፡ የአውሬው ሰባቱ ራሶችና አስሩ ቀንዶች እዚህ ላይ የሚያመለክቱት በዚህ ዓለም ላይ የሚገለጠውን የጸረ ክርስቶስ ሐይል ነው፡፡ ‹‹በቀንዶቹም ላይ አስር ዘውዶች በራሱቹም ላይ የስድብ ስም ነበር›› የሚለው ሐረግ ጸረ ክርስቶስ የዓለምን መንግሥታቶች በአንድ ላይ አስተባብሮ በእግዚአብሄር ላይ ይነሳል ማለት ነው፡፡ ይህም በዓለም ነገሥታቶች ሁሉ ላይ እንደሚነግስም ይነግረናል፡፡ አስሩ ዘውዶች ድላቸውን ያመለክታሉ፡፡ በአውሬው ራስ ላይ ያለው የስድብ ስም ኩራታቸውን ያመለክታል፡፡
ወደፊት ዓለም እንዲህ የተባበሩትን መንግሥታቶች የጋራ ፍላጎቶች በሚያሟላ አንድ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ በተመሰረተ የተባበረ የመንግሥታቶች አካል ትተዳደራለች፡፡ ይህ የተቀናጀ ልዕለ ሐያል ግዙፍ ልዕለ ብሄራዊ አካል ሉዓላዊነቱን በማስፋፋት በዓለም መንግሥታቶች ሁሉ ላይ ይገዛል፡፡ ውሎ አድሮም ጸረ ክርስቶስ በመጨረሻ በዚህ ምድር ላይ ሲመጣም የእርሱን ሥራዎች ይሰራለታል፡፡ እርሱ የሰይጣንን ሐይል ለብሶ የዲያብሎስ አገልጋይ በመሆን የሚሰራ የእግዚአብሄር ጠላት ነው፡፡
 
ቁጥር 2፡- ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፡፡ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፣ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ፡፡ ዘንዶውም ሐይሉንና ዙፋኑን፣ ትልቅም ሥልጣን ሰጠው፡፡
ይህ ጸረ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በቅዱሳንና በዓለም ሕዝብ ላይ የሚያደርገውን ነገር ይነግረናል፡፡ የሚመጣው ጸረ ክርስቶስ በቅዱሳን ላይ እንዲህ ያሉ የጭካኔ ነገሮችን ለማድረግ ሥልጣንንና ሐይልን ከሰይጣን በመቀበሉ ነው፡፡ ይህም ጸረ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምን ያህል በቅዱሳኖች ላይ እንደሚጨክን በማሳየት ቅዱሳኖች በሰማዕትነታቸው ምን ያህል ጸረ ክርስቶስ የሚያመጣባቸውን መከራ እንደሚቋቋሙ ይጠቁማል፡፡
ይህ ቃል ጸረ ክርስቶስ ምን ያህል ጨካኝ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ‹‹እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች ነበሩ›› የሚለው ሐረግ ሥልጣኑ ምን ያህል አጥፊ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ዘንዶው›› በመጀመሪያ በእግዚአብሄር የተፈጠረ የእርሱን ዙፋን ለመንጠቅ ያሴረ መልአክ ነበር፡፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ የተገለጠው አውሬ ሥልጣንን ከዘንዶው የተቀበለውንና እግዚአብሄርንና ቅዱሳኖችን የመቃወም ሥራዎችን የሚሰራውን ሐይል ነው፡፡
ከሰማይ የተባረረው ሰይጣን ለእግዚአብሄር ተቃዋሚና እግዚአብሄርንና ቅዱሳኖችን በመዋጋት ወደ ሞት ለሚነዳው አካል ሐይሉንና ሥልጣኑን ይሰጠዋል፡፡ የሰይጣንን ሥልጣን የለበሰው ጸረ ክርስቶስ ወደፊት የእግዚአብሄርን ሕዝብና የሰውን ዘር በሙሉ ክፉኛ ያስጨንቃል፡፡
 
ቁጥር 3፡- ከራሶቹም ለሞት እንደታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፤ ለሞቱ የሆነውም ቁስል ተፈወሰ፡፡ ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፡፡ ለዘንዶውም ሰገዱለት፤
ይህ ቁጥር ጸረ ክርስቶስ ከሰባቱ ነገሥታቶች አንዱ ሆኖ እንደሚመጣ ይነግረናል፡፡ ጸረ ክርስቶስ አውሬ ተብሎ የተጠራው በቅዱሳኖች ላይ አውሬያዊ ነገሮችን ስለሚያደርግ ነው፡፡
እዚህ ላይ የእግዚአብሄርና የቅዱሳን ጠላት በመጨረሻው ዘመን የሞትን ችግር መፍታት የሚችል ሆኖ ይገለጣል፡፡ ስለዚህ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ምድርን የቀሰፉትን ችግሮች ሁሉ የመፍታት አቅም አለው ብለው ያምኑበታል፡፡ እርሱ ግን የእግዚአብሄር ጠላት ነው፡፡ የዓለም ሕዝብ ለእርሱ እንዲያጎበድዱ ቢያደርግም እግዚአብሄርንና የእርሱን ቅዱሳኖች በመቃወሙ በመጨረሻ ይጠፋል፡፡
 
ቁጥር 4፡- ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፡- አውሬውን ማን ይመስለዋል? እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት፡፡
ይህም ዘንዶው ሐይሉን ሁሉ ባርያው ላደረገውና አውሬዊ ነገሮችን ሁሉ ለሚያደርገው ለእርሱ እንደሚሰጠው ይነግረናል፡፡ ከዚህ የተነሳ የዚህ ዓለም ሕዝብ በሙሉ ዘንዶውን እንደ አምላክ ያስበውና በፍርሃት ይንቀጠቀጣል፤ ይሰግድለትማል፡፡ በዚህ ጊዜ አውሬው የያዘውን ዓይነት ሥልጣን የያዘ ንጉሥ በዚህ ምድር ላይ ስለሌለ ማንም ራሱን እንደ አምላክ ከማወጅና ከመደንፋት ሊያስቆመው አይችልም፡፡
ዘንዶው ለአውሬው ታላቅ ሥልጣን ሲሰጠው ሰው ሁሉ ዘንዶውንና አውሬውን ያከብራቸዋል፡፡ አውሬውንም አምላክ አድርገው ይሰግዱለታል፡፡ እንዲህ ያለ ታላቅ ሥልጣን ያለው ጸረ ክርስቶስ ሲገለጥ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን አብዝተው የሚወዱ ሰዎች ይከተሉታል፡፡ አምላካቸው አድርገውም ይሰግዱለታል፤ ከፍም ያደርጉታል፡፡
 
ቁጥር 5፡- ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፡፡ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሰራ ሥልጣን ተሰጠው፡፡
አውሬው ለሦስት ዓመት ተኩል (42 ወር) የትዕቢት ቃሎችን ይናገር ዘንድ ከዘንዶው የትዕቢትን ልብና ሥልጣን ይቀበላል፡፡ በዚህም አውሬው በእነዚህ ሦስት ዓመታት ተኩል ውስጥ ቅዱሳኖችንና የዚህን ዓለም ሕዝብ ለመጉዳት ሥልጣንን ይቀበላል፡፡
ጸረ ክርስቶስ የሆነው አውሬው ለሦስት ዓመታት ተኩል እግዚአብሄርን የሚቃወሙና ቤተክርስቲያኑን የሚሳደቡ ቃሎችን ለመናገር ሥልጣን ይቀበላል፡፡ በዚህም ሐጢያተኞች በሙሉ ለዚህ አውሬ ያጎበድዳሉ፡፡ ወዲያውም ከአውሬው ጋር አብረው ይጠፋሉ፡፡
 
ቁጥር 6፡- እግዚአብሄርንም ለመሳደብ፣ ስሙንና ማደሪያውንም፣ በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ፡፡
አውሬው ሐይልን ከዘንዶው ከተቀበለ በኋላ ለሦስት ዓመታት ተኩል እግዚአብሄርን፣ የእርሱን መላእክቶችና ቅዱሳኖች በሙሉ በመሳደብ ይረግማቸዋል፤ ያወግዛቸውማል፡፡ እነዚህ ነገሮች በሙሉ የሚደረጉት ዘንዶው እንዲያድርግ በነገረው መሰረት ነው፡፡ እዚህ ላይ ይህ የሰይጣን ድርጊት ማለትም እግዚአብሄርን ለሦስት ዓመታት ተኩል ለመስደብ ለአውሬው ሥልጣንን መስጠት ተግባራዊ የሚሆነው በእግዚአብሄር ፈቃድ ብቻ ነው፡፡
በመሰረቱ ጸረ ክርስቶስ የሚኖረው እግዚአብሄርንና የእርሱን ሕዝብ ለመስደብ ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ ከዘንዶው ሥልጣንን ከተቀበለ በኋላ በታላቁ መከራ የመጀመሪያ ሦስት ዓመታት ተኩል ውስጥ የእግዚአብሄርን ስምና የእርሱን ሕዝብ ይሳደባል፡፡
 
ቁጥር 7፡- ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፡፡ በነገድና በወገንም፣ በቋንቋም፣ በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው፡፡
አውሬው ቅዱሳኖችን ለመግደልና ሰማዕታት ለማድረግ ከዘንዶው ሥልጣንን ይቀበላል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው በእርሱ አገዛዝ ሥር አድርጎ የሚገዛበት ሥልጣን ከተሰጠው በኋላ መላውን ዓለም ይገዛል፡፡
ጸረ ክርስቶስ ቅዱሳኖችን ይገድላል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚነግስበት ብቸኛው መንገድ ቅዱሳኖችን በመዋጋትና በማሸነፍ ነው፡፡ የጸረ ክርስቶስ አዛዥ ልክ እንደ እግዚአብሄር እንዲሰገድለት የሚሻው የወደቀው መልአክ ዲያብሎስ ነው፡፡ እርሱ ቅዱሳንን በመግደል ዳግመኛ ባልተወለዱት ሰዎች እንደ አምላክ ይሰገድለታል፡፡ በዚህ የመከራ ዘመን ቅዱሳን ሁሉ በጸረ ክርስቶስ ይሰደዳሉ፡፡ ሰማዕታትም ይሆናሉ፡፡
 
ቁጥር 8፡- ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል፡፡
ጸረ ክርስቶስ ይህችን ምድር ሲያሸንፍ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ ከተወለዱት በስተቀር ማለትም ዳግመኛ ያልተወለዱ ሁሉ አምላካቸው አድርገው ለእርሱ ይሰግዱለታል፡፡ ጸረ ክርስቶስ ግን የሚደሰገድለት ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ ባልተጻፉላቸው ሐጢያተኞች ብቻ ይሆናል፡፡
 
ቁጥር 9፡- ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ፡፡
ይህም የእግዚአብሄር የሆነ ሰው ሁሉ ሰማዕት ለመሆን እምነቱን ማዘጋጀት እንዳለበት ነግረናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ሁሉ በመጽሐፍ ውስጥ እንደተጻፈው በትክክል ይፈጸማሉና፡፡
 
ቁጥር 10፡- ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገደል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል፡፡ የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር በመጨረሻው ዘመን ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳኖችን በሚገድሉት ላይ ተመሳሳይ ሞትንና መከራዎችን እንደሚያመጣባቸው ይናገራል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ተኩል ሲያልፉ ቅዱሳን በጸረ ክርስቶስና በተከታዮቹ ይገደላሉ፡፡ ነገር ግን ቅዱሳኖችን እንዲህ የገደሉትን ሁሉ እግዚአብሄር በላቀ መከራዎችና ስቃዮች ይበቀላቸዋል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ሁሉ ልቦቻቸውን አስተባብረው በጌታ ቃል ላይ ባላቸው እምነት ይህንን አስቸጋሪ መከራ ማሸነፍና ሰማዕትነታቸውን በመቀበል ለእግዚአብሄር ከብርን መስጠት አለባቸው፡፡
 
ቁጥር 11፡- ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፡፡ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት፡፡ እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር፡፡
እዚህ ላይ የምናየው የመጀመሪያውን አውሬ ሳይሆን ሁለተኛውን አውሬ ነው፡፡ ሁለተኛውም አውሬ እንደዚሁ ልክ እንደ ዘንዶው ያስባል፤ ይናገራልም፡፡ እርሱ ዘንዶውን እንደሚመስል የሚያስብ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ድርጊቶቹን በዚህ እምነቱ ላይ በማድረግ ቅዱሳኖችን ይበልጥ በጭካኔ ያሳድዳል፡፡
 
ቁጥር 12፡- በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል፡፡ ለሞቱ የሆነውም ቁስል ተፈወሰለት፡፡ ለፊተኛውም አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል፡፡
በመጀመሪያው አውሬ ሥልጣን የተሰጠው ሁለተኛው አውሬ ለመጀመሪያው አውሬ ይሰግዳል፡፡ ገናም በዚህ ምድር ላይ የቀረው ሰው ሁሉም ለእርሱ እንዲሰግዱለት ያደርጋል፡፡ የእርሱ ሥራ የመጀመሪያውን አውሬ እንደ ጣዖት ማምለክና ሰው ሁሉ እርሱን እንደ አምላክ አድርጎ እንዲሰግድለት ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሥራ ምክንያት የመጀመሪያው አውሬና እርሱ ሰዎች ሁሉ ልክ እንደ እግዚአብሄር የሚሰግዱላቸው አካሎች ናቸው፡፡ የሰይጣን መሰረታዊ ባህርይና እውነተኛ ማንነት ይህ ነው፡፡
 
ቁጥር 13፡- እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል፡፡
ሰይጣን በዚህች ምድር ላይ በሰዎች ፊት ታላላቅ ተዓምራቶችን ሲፈጽም ብዙ ሰዎችን ማሳት ይችላል፡፡ እርሱ እሳትን ከሰማይ ወደ ምድር የማውረድ ሥልጣንም እንኳን ይኖረዋል፡፡
 
ቁጥር 14፡- በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፡፡ የሰይፍም ቁስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል፡፡
ነገር ግን ሰይጣን በቅርቡ እውነተኛ ማንነቶቹን ይገልጣል፡፡ እርሱ ማድረግ የሚፈልገው ከሰዎች ልቦች ውስጥ በእግዚአብሄር ላይ ያላቸውን እምነት መስረቅና በምትኩ ለእርሱ እንዲሰግዱለት ነው፡፡ ይህንን ለማሳካትም በሰዎች ፊት ብዙ ተዓምራቶችን ያደርጋል፡፡ የእግዚአብሄርንም ሕዝብ ይገድላል፡፡ የመጨረሻ ዓላማውን ለመፈጸምም ማለትም አምላክን ለመምሰል ወደ እግዚአብሄር ስፍራ ለመውጣት ይሞክራል፡፡ በዚህም ለመጀመሪያው አውሬ ምስልን በመስራት ሰዎች እርሱን አምላክ አድርገው እንዲሰግዱለት ያደርጋል፡፡
 
ቁጥር 15፡- የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱትን ሁሉ ሊያስገድላቸው ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው፡፡
እርሱን የማውገዙ እጅግ ታላቁ እንቅፋት የሚመጣው ከእግዚአብሄር ሕዝብ በመሆኑ ሰይጣን እነርሱን ለማጥፋት ያለ የሌለ ሐይሉን ይጠቀማል፡፡ በዚህም ለአውሬው ምስል የማይሰግዱትን ሁሉ ቁጥራቸው ምንም ያህል ብዙ ይሁን ይገድላል፡፡ ቅዱሳኖች ግን ለዚህ አውሬ አይንበረከኩም፡፡ ስለዚህ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ቅዱሳን በዚህ ጊዜ ስለ እምነታቸው ሲሉ በፈቃደኝነት ሰማዕትነታቸውን በመቀበል ከሞት በኋላ ያላቸውን ሕይወት ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጸረ ክርስቶስ በቅዱሳን ላይ ታላላቅ መከራዎችን ሲያመጣ እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶችና ለዘላለም በሚቃጠል ሲዖል ውስጥ የሚቀጣበትን ቅጣት ለእርሱ ያዘጋጅለታል፡፡
 
ቁጥር 16-17፡- ታናናሾችና ታላላቆችም፣ ባለጠጋዎችና ድሆችም፣ ጌታዎችና ባርያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፤ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቁጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል፡፡
መከራው ከፍታው ላይ ሲደርስ ጸረ ክርስቶስ ሰው ሁሉ በእርሱ ቁጥጥር ሥር መሆኑን ለማረጋገጥ በቀኝ እጁ ወይም በግምባሩ ላይ ምልክትን እንዲቀበል ይጠይቃል፡፡ ይህ ምልክት የአውሬው ምልክት ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ ሰውን ሁሉ ባርያ ለማድረግ ሰዎች ምልክቱን እንዲቀበሉ ያስገድዳል፡፡
ጸረ ክርስቶስ የሰዎችን ሕይወት እንደ መያዣ በመያዝ የፖለቲካ ዓላማዎቹን ያካሂዳል፡፡ በዚህም ለእርሱ ያደረ ለመሆኑ ማስረጃ የሆነው የአውሬው ምልክት የሌለው ማንኛውም ሰው በማንኛውም መንገድ አንዳች ነገር እንዳይገዛ ወይም እንዳይሸጥ ያደርገዋል፡፡ ይህ ምልክት የአውሬው ስም ወይም የስሙ ቁጥር ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ወደ እሳትና ዲን ባህር እንደሚጣሉ እግዚአብሄር የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለራሳችን ማስታወስ አለብን፡፡
 
ቁጥር 18፡- ጥበብ በዚህ አለ፡፡ አእምሮ ያለው የአውሬውን ቁጥር ይቁጠረው፤ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፤ ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው፡፡
የአውሬው ቁጥር 666 ነው፡፡ ይህ ማለት በአጭሩ አውሬው ከእግዚአብሄር ጋር እኩል መሆኑን ያተኩርበታል ማለት ነው፡፡ ‹‹ሰው አምላክ›› መሆኑን የሚጠቁም ቁጥር አለ? እንዲህ ያለ ትርጉም ያለው ቁጥር የጸረ ክርስቶስ ቁጥር ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ይህንን ምልክት ሊቀበሉ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ለእነርሱ እውነተኛው አምላክ ስላሴ አምላክ ብቻ ነውና፡፡ ቅዱሳን በጌታ ባላቸው እምነት ሰይጣንን ማሸነፍና ለእግዚአብሄርም ክብርን መስጠት አለባቸው፡፡ ቅዱሳን ለጌታ ክብርን ሁሉ መስጠት የሚችሉበት ምርጥ እምነትና ስግደት ይህ ነው፡፡
 
 
ቁልፍ የሆኑ ቃሎችን ማብራራት፡፡ 
 
የምዕራፍ 13 ርዕሰ ጉዳይ የጸረ ክርስቶስና የሰይጣን መገለጥ ነው፡፡ እነርሱ በሚገለጡበት ጊዜ ቅዱሳን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ውስጥ ይሳተፋሉ፡፡ እነርሱም በጸረ ክርስቶስ ሰማዕት ከመሆን በቀር ምርጫ አይኖራቸውም፡፡ ጸረ ክርስቶስ ቅዱሳንን የሚያሳድድና ሰማዕት የሚያደርጋቸው የሰይጣን ባርያ ነው፡፡
 
በዚህ ዘመን የሚኖሩ የዓለም ክርስቲያኖችና ክርስቲያን ያልሆኑ ሁሉ የራዕይን ቃል ማወቅ አለባቸው፡፡ ራዕይ ምዕራፍ 13 ሰይጣን ጸረ ክርስቶስን ልክ እንደ አምላክ የሚያሞግስበት ዘመን እንደሚመጣ ይተነብያል፡፡ ሰይጣን ሐያል የፖለቲካ መሪዎች ከሆኑት ለአንዱ ሥልጣን ይሰጠውና እግዚብሄርንና ቅዱሳኖችን እንዲቃወም ያደርገዋል፡፡ በተለይ ጸረ ክርስቶስ ራሱን እንደ አምላክ በማሞገስ እግዚአብሄርን ይጋፈጠዋል፡፡ 
 
የእግዚአብሄርን ሕዝብ ጨምሮ ሰው ሁሉ በአውሬው ጸረ ክርስቶስ በሚመጡት መከራዎችና ስደቶች በአያሌው ይሰቃያል፡፡ ዋናዎቹ ምንባቦች የጸረ ክርስቶስ ምስል የሰይጣንን የሕይወት እስትንፋስ ከተቀበለ በኋላ በሕይወት ያለና ሰዎችን የመጉዳት ሥልጣን ያለው መስሎ እንደሚናገር ያሳየናል፡፡ ዳግመኛ ያልተወለዱ ሰዎች ለእርሱ ያጎበድዳሉ፡፡ የእርሱም ባሮች ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል ለተሞገሰው የሰይጣን ምስል የማይሰግዱ ሁሉ ቁጥራቸው ምንም ያህል ብዙ ቢሆንም ይገደላሉ፡፡ ሰይጣንም ደግሞ ሁሉም ምልክቱን በእጁ ወይም በግምባሩ እንዲቀበል ያደርጋል፡፡
 
ሁላችንም አስቀድመን በራዕይ 13 ውስጥ የተገለጠውን የዚህን ቃል ትርጉም በመረዳትና እምነታችንን በቅድሚያ አዘጋጅተን ሰይጣንን መዋጋትና ማሸነፍ አለብን፡፡ የዘመኑ የእግዚአብሄር ሕዝቦች ከዚህ የራዕይ ቃል በመማርና ይህንንም በማመን ጸረ ክርስቶስን በጽናት በመቋቋምና በድል አድራጊነት በማሸነፍ ለጌታ ክብርን መስጠት አለባቸው፡፡
 
 
የሲዖል ጅማሬ፡፡ 
 
በመጀመሪያ ሲዖል ለምን መኖር እንዳለበትና ለምን እንደተፈጠረ ማወቅ አለብን፡፡ ሲዖል ለሰይጣን የተያዘ ስፍራ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እርሱ ከመጀመሪያም ሰይጣን እንዳልነበር ነገር ግን እግዚአብሄር ከፈጠራቸው ብዙ መላእክቶች አንዱ እንደነበር ይነግረናል፡፡ ነገር ግን በትዕቢቱ እግዚአብሄርን በመገዳደሩ ይህ መልአክ በሐጢያቱ ምክንያት ሰይጣን ሆነ ሲዖልም እግዚአብሄር እርሱን ለማሰር የፈጠረው ስፍራ ነው፡፡ እግዚአብሄር እርሱን ለሚቃወሙት ያዘጋጀውን ቅጣት ለሰይጣንና ለተከታዮቹ ለመስጠት ሲዖልን ፈጠረ፡፡
 
ኢሳይያስ 14፡12,15 ይህ መልአክ እንዴት ሰይጣን እንደሆነ ያብራራል፡- ‹‹አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቆረጥህ! አንተም በልብህ፡- ወደ ሰማይ አርጋለሁ፤ ዙፋኔንም ከእግዚአብሄር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፡፡ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፡፡ ከዳመናዎች ከፍታ በላይ አርጋለሁ፤ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ፡፡ ነገር ግን ወደ ሲዖል ወደ ጉድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ፡፡››
 
በሰማይ በእግዚአብሄር ላይ የተነሳው ይህ መልአክ የእግዚአብሄርን ዙፋን ተመኘ፡፡ ከእርሱ በላይ ያለው እግዚአብሄር ብቻ እንደሆነ አይቶ ሲያበቃ እርሱን አባሮ በዙፋኑ ላይ ሊቀመጥ ፈለገ፡፡ በዚህ በተቀለበሰው ዓመጽ የተነሳም እርሱ ራሱ በእግዚአብሄር ከሰማይ ተባሮ ሰይጣን ሆኖ ቀረ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዓመጽ ሰይጣንን የተከተሉትን መላእክቶች አጋንንቶች ብሎ ይጠቁማቸዋል፡፡
 
እግዚአብሄር በእርሱ ላይ ለተነሱት ፍጥረቶች ቅን የሆነ ቅጣቱን ይሰጥ ዘንድ ‹‹ሲዖል›› ተብሎ የሚጠራውን ይህንን ስፈራ ሰራ፡፡ ሰይጣን ያለ ማቋረጥ እግዚአብሄርን የሚገዳደርና ሥራዎቹን የሚሳደብ ቢመስልም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ለሁሉም በሚሰበክበት ጊዜ ውሎ አድሮ ሺህ ዓመት በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ይታሰራል፡፡
 
ሰይጣን በመሰረቱ በእግዚአብሄር ላይ ካመጸበት ሐጢያቱ ንስሐ ስለማይገባ ራሱን ከእግዚአብሄር በላይ ከፍ የማድረግ ሙከራውን ይቀጥልና መጨረሻው ለዘላለም አስፈሪውን የሲዖል ቅጣት መቀበል ይሆናል፡፡ ሰይጣን ሰዎች እርሱን ጣዖት እንዲያደርጉት በማድረግ እስከ መጨረሻ እስትንፋሱ ድረስ እግዚአብሄርንና ጻድቃንን መቃወሙን ይቀጥላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሄርንና የእርሱን ቅዱሳን የሚሰድበውን ይህንን የወደቀ መልአክ ሰይጣን ወይም ዲያብሎስና ዘንዶው ወይም የቀደመው እባብ ብሎ ይጠራዋል፡፡ (ዮሐንስ ራዕይ 12፡9)
 
 

666 የአውሬው ቁጥር፡፡ 

 
በመጨረሻ እግዚአብሄር ሰይጣንን በራሱ ግዞት ቤት ያስረዋል፡፡ ነገር ግን ሰይጣን በሲዖል ከመታሰሩ በፊት ሰዎች በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው የ666 ምልክትን፣ ስሙንና ቁጥሩን እንዲቀበሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ምልክት የሌለበት ሰው ምንም ነገር እንዳይገዛ ወይም እንዳይሸጥ ይከለከላል፡፡
 
7 ቁጥር እግዚአብሄርን የሚመለክት የተፍጻሜት ቁጥር ነው፡፡ በሌላ በኩል 6 ቁጥር ሰውን ያመለክታል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር በራሱ አምሳልና መልክ ሰውን የፈጠረው በስድስተኛው ቀን ነውና፡፡ እዚህ ላይ 666 የሚለው የአውሬው ቁጥር እንደ ስላሴ አምላክ ለመሆን የሚሞክረውን የሰውን ትዕቢት ይገልጣል፡፡ ብዙ በማይርቀው ወደፊት ሰዎች ይህንን 666 ምልክት የሚቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፡፡
 
ዮሐንስ 13፡1 ከአስሩ መንግሥታት ሰባት ነገሥታት እንደሚወጡ ይነግረናል፡፡ ከእነርሱ ውስጥ ከሰይጣን ታላቅ ሐይልና ሥልጣን የሚቀበለው ንጉሥ ይህንን ዓለም በአገዛዙ ሥር ያደርገዋል፡፡ ለሞቱ የሆነውን ቁስል እንደ መወሰንና ከሰማይ እሳትን እንደ ማውረድ ያሉ ታላላቅ ምልክቶችን በማድረግ የዓለም ሕዝብ በሙሉ እርሱን እንዲከተለው ያደርጋል፡፡
 
በሌላ አነጋገር ሰይጣን ሰዎች እግዚአብሄርን ከመከተል ይልቅ እርሱን እንዲከተሉ ሲያደርግ ብዙ ሰዎች እርሱን እንደ አምላክ በመቀበል ይሰግዱለታል፡፡ ጀግኖች በአስቸጋሪ ወቅቶች ስለሚነሱ ጸረ ክርስቶስም ከሰይጣን ትልቅ ሥልጣንን ከተቀበለ በኋላ ዓለም በወቅቱ እየገጠማት ያሉትን አስቸጋሪ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች በመፍታት ሰው ሁሉ አምላክ እንደሆነ አድርጎ እንዲከተለው ይሻል፡፡ ውሎ አድሮም ሰይጣን በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሄርን በቀጥታ በመገዳደር እውነተኛ ማንነቱን ይገልጣል፡፡
 
ከዳንኤል መጽሐፍ ማየት እንደምንችለው ታላቁ መከራ በመጀመሪያው አጋማሽ ፍጻሜው ላይ ሲደርስ እጅግ አሰቃቂ ይሆናል፡፡ ለሦስት ዓመት ተኩል የሚቆየው ይህ የመጀመሪያው አጋማሽ አስፈሪ መቅሰፍቶች የሚወርዱበትና ሰይጣን በሐይል የሚነግስበት ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ተኩል ሲያበቁ ቀጥሎ የሚመጣው እጅግ የከፋ የመከራዎች አውሎ ነፋስ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰይጣን እርሱን የማይሰማውን ሁሉ በመግደል እሳትን ከሰማይ በሚያወርዱት ተዓምሮቹም በማሳት ራሱን እንደ ጣዖት በማወደስና እግዚአብሄርን የመሳደብ ሥራዎችን እንዲሰሩ በማድረግ በዓለም ሕዝብ መካከል ሥራዎቹን ያደርግ ዘንድ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡
 
በዚያው ጊዜም ጸረ ክርስቶስ ሥልጣንን ሁሉ ከሰይጣን ከተቀበለ በኋላ ቅዱሳኖችን ይሳደባል፡፡ ለእርሱ የማይታዘዙትን ቅዱሳን ሁሉም ይገድላል፡፡ ቁጥር 7-8 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፡፡ በነገድና በወገንም፣ በቋንቋም፣ በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል፡፡›› ሆኖም በዚህ ጊዜ ለአውሬው መስገድን አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህም ስሞቻቸው በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉላቸው የእግዚአብሄር ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ናቸው፡፡
 
 
የሰማዕትነት ሁነት፡፡ 
 
ሰማዕትነት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳን የሰይጣንን ምልክት ባለመቀበል በጌታ ያላቸውን እምነት የሚጠብቁበት ሁነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ታላቁ መከራ የመጀመሪያው የሦስት ዓመት ተኩል አጋማሽ ሲቃረብ ወደ ሐይለኛ ደረጃ ይሸጋገራል፡፡ በዚህ ጊዜ የጻድቃን እምነት ለሰማዕትነታቸው መዘጋጀት አለበት፡፡
 
ሆኖም ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው ያመኑ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሳያምኑ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያላገኙና በልባቸው ውስጥ ገናም ሐጢያት ያለባቸው ሰዎች መጨረሻቸው ከሰይጣን ጋር ማበርና ውሎ አድሮም ለእርሱ ማጎብደድ ይሆናል፡፡ በኢየሱስ የሚያምኑ ነገር ግን ዳግመኛ ያልተወለዱ ክርስቲያኖች በልባቸው ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ስለሌለ ግፊቱ ሲበረታ ለሰይጣን ይንበረከካሉ፡፡ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክቱን ይቀበላሉ፡፡ በመጨረሻም እርሱን እንደ አምላክ ያመልኩታል፡፡
 
በዚህ ጊዜ ለሰይጣን የማይሰግዱት ሰዎች የሐጢያቶቻቸውን ስርየት የተቀበሉት ብቻ መሆናቸውን በግልጽ ማወቅ አለብን፡፡ እግዚአብሄር ለአውሬው የሚንበረከኩትን ከሰይጣን ጋር አብሮ ወደ እሳትና ዲን ባህር እንደሚወረውራቸው በግልጽ እንደነገረንም መገንዘብ አለብን፡፡
 
ቁጥር 9-10 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ፡፡ ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገደል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል፡፡ የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው፡፡›› በዚህ ጊዜ ጸረ ክርስቶስና ተከታዮቹ በጻድቃን ላይ ትልቅ ስደትን ያመጣሉ፡፡ ይሸጡዋቸዋል፤ በሰይፍም ይገድሉዋቸዋል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ በግልጽ መገንዘብ የሚገባን ነገር ቢኖር እግዚአብሄር ጻድቃንን ያሳደዱትንና የገደሉትን ጠላቶቻችንን በእርግጠኝነት የሚበቀላቸው መሆኑን ነው፡፡
 
ስለዚህ ቅዱሳን በእግዚአብሄር ተስፋዎች በማመን በስደታቸውና በሞታቸው ውስጥ ማለፍ አለባቸው፡፡ እግዚአብሄር ጠላቶቻችንን ባይበቀል ተስፋ አስቆራጭ በሆነው የፍትህ ስሜታችን እንዴት ዓይኖቻችንን መክደን ይቻለናል? ነገር ግን እግዚአብሄር በእኛ ላይ ጉዳት ያደረሱትን ጠላቶቻችንን እንደሚበቀላቸው ተስፋ ስለሰጠን ሞታችን በከንቱ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ጻድቃንን ያሰቃዩትንና የጨቆኑትን በእርግጠኝነት ይበቀላቸዋል፡፡ ጻድቃኖችንም ወደ ትንሳኤያቸው፣ ንጥቀታቸውና የበጉ ሰርግ እራት በመምራት ከጌታ ጋር ለሺህ ዓመት እንዲነግሱና ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንዲኖሩ ይመራቸዋል፡፡ ሁላችንም በዚህ እናምናለን፡፡ ተስፋም እናደርገዋለን፡፡ ስለዚህ ጌታችን ተስፋዎቻችንን ሁሉ የሚፈጽምልን ምርጥ አምላክ ነው፡፡