Search

በክርስቲያን እምነት ላይ አዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎች፤

ርዕስ 1፡ ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ መወለድ፤

1-22. በደግነትህ የላክልኝን መጽሐፎች ሳነብ በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ያሉህ አንዳንድ እሳቤዎች አስደሳች ሆነው አግኝቼአቸዋለሁ፡፡ የእኛ ጥምቀት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ሞትና ትንሳኤ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ልትነግረኝ ትችላለህን? 

ከሁሉ በፊት በዕብራውያን 6፡2 ላይ እንደተጻፈው ‹‹የጥምቀቶችን ትምህርት›› ልናተኩርበት ይገባናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ሦስት የተለያዩ ጥምቀቶች አሉ፡፡ እነርሱም የዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት፣ ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀትና እኛ እንደ ስርዓት የምንወስደው የውሃ ጥምቀታችን ናቸው፡፡   
እኛ የምንወስደው ጥምቀት በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ያለንን እምነት የምንመሰክርበት ነው፡፡ ይህ ማለት እኛ የምንጠመቀው ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለመውሰድ እንደተጠመቀና እነርሱንም ደግሞ ለማስተሰረይ በመስቀል ላይ እንደሞተ እንደምናምን እምነታችንን ለመመስከር ነው፡፡ ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና›› የሚለውን ማቴዎስ 3፡15ን መረዳት ትችላለህ፡፡ እዚህ ላይ ‹‹እንዲህ›› ማለት ኢየሱስ ራሱ የሰው ዘር ወኪል በሆነው በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ተሸክሞዋል ማለት ነው፡፡      
ይህ እኛን ከማናመልጥበት የሐጢያት ወጥመድ ለማዳን እግዚአብሄር ያቀደው ጥልቅ ዕቅድ ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሄር ‹‹የሁላችንንም በደል በእርሱ ላይ አኖረ፡፡›› (ኢሳይያስ 53፡6) የእርሱንም ጽድቅ ሰጠን፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ጽድቅ›› ማለት በግሪክ ‹‹ዲካዮሱኔ›› ማለት ሲሆን የሚያመላክተውም ‹‹ትክክለኛነትንና ፍትህን›› ነው፡፡ ይህም ኢየሱስ በእጆች መጫን መልክ በመጠመቅ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ እጅግ ትክክለኛና ጻድቅ በሆነ መንገድ እንደተሸከመ ይነግረናል፡፡ 
የዳንነው በኢየሱስ ጥምቀት፣ በመስቀል ላይ ሞቱና በትንሳኤው ላይ ባለን ጠንካራ እምነት ነው፡፡ ሐጢያቶችን ሁሉ ከልባችን ውስጥ ቆርጦ የጣለው የጥምቀቱ መንፈሳዊ ግርዘት ሐይል (ሮሜ 2፡29) በልባችን ውስጥ ያሉትን ሐጢያቶች አንጽቷል፡፡ ስለዚህ በበዓለ ሃምሳ ቀን ሐዋርያው ጴጥሮስ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ንስሐ ግቡ፤ ሐጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድም እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፡፡ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡38)     
ሐጢያተኞች በሙሉ በኢየሱስ ስም በማመን በልቦቻቸው ውስጥ የሐጢያቶችን ይቅርታ መቀበል ይገባቸዋል፡፡ የስሙ ትርጉም ምንድነው? ‹‹እርሱ ሕዝቡን ከሐጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ፡፡›› (ማቴዎስ 1፡21) ኢየሱስ የሚለው ስም ሕዝቡን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የሚያድን ‹አዳኝ› ማለት ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነን እንዴት ነበር? ኢየሱስ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነን በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ሞቱ አማካይነት ነው፡፡   
የኢየሱስ ሐዋርያት ወንጌልን በሰበኩ ጊዜ የኢየሱስን ጥምቀትና መስቀል ግልጽ በሆነ መረዳት አረጋግጠው እውነተኛውን ወንጌል አስተማሩ፡፡ ከዚያም በዚህ የሚያምኑትን አጠመቁ፡፡ እኛ የምንጠመቀው በልቡናችን ጥልቅ ውስጥ በኢየሱስ ጥምቀትና ሞት እንደምናምን በይፋ ለመመስከር ነው፡፡ ስንጠመቅ ‹‹ጌታ ሆይ ተመስገን፡፡ አንተ በጥምቀትህ አማካይነት ሐጢያቶቼን በሙሉ ተሸከምህ፤ ስለ እኔም ሞትህ፤ እኔን ለማዳንም ዳግመኛ ተነሳህ፡፡ በወንጌልህ አምናለሁ›› ብለን እንመሰክራለን፡፡ እርሱ በአጥማቂው ዮሐንስ እንደተጠመቀ ሁሉ እኛም በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ ላለን እምነት ምልክት ይሆን ዘንድ በአገልጋዮቹ በውሃው ውስጥ እንጠመቃለን፡፡ ስለዚህ በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ቅዱሳን በወንጌል ላይ ያላቸውን እምነት ከመሰከሩና የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ማለትም ቤዛነት ከተቀበሉ በኋላ ለእምነታቸው ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ ተጠምቀዋል፡፡    
የጥምቀት ስርዓት ለመዳን አስፈላጊ የሆነ ሁኔታ አይደለም፡፡ እምነታችንን ግልጽ ማድረጉ አስፈላጊ ቢሆንም የውሃ ጥምቀቶቻችን ከደህንነታችን ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡ መዳን የምንችለው በውሃውና በደሙ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በእርሱ ጥምቀት ባመንን ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እንደተጠመቅን (ሮሜ 6፡3፤ ገላትያ 3፡27) ይናገራል፡፡ 
ታዲያ እንዴት ‹‹በእርሱ ልንጠመቅ›› ቻልን? ይህ የሚቻለው በእርሱ ጥምቀት ስናምን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥጋ ማለትም አሮጌው ማንነታችን ከኢየሱስ ጋር ሊሰቀል የሚችለው በእርሱ ጥምቀት ላይ ባለን እምነት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስለተሸከመ ሞቱ የበደላችን ፍርድ ነበር፡፡ በመሆኑም እኛም ደግሞ ከእርሱ ጋር በመስቀል ላይ ሞተናል፡፡ በሌላ አነጋገር እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ሐጢያቶችን የሚሰራው ሥጋችን ለሐጢያት ሞቶዋል፡፡ እኛም በጥምቀቱ አማካይነት ከኢየሱስ ጋር በመተባበራችን ከበደሎቻችን ሁሉ ድነናል፡፡  
በእርሱ ጥምቀትና ሞት ከኢየሱስ ጋር የተባበሩ ሰዎች ከትንሳኤውም ጋር ደግሞ መተባበር ይችላሉ፡፡ የእርሱ ትንሳኤ እኛ ከሐጢያት ሞት የተነሳንበት ትንሳኤ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ፊት ቅዱሳን፣ ንጹህና ሐጢያት የሌለብን የእግዚአብሄር ልጆች ሆነን ዳግም እንድንወለድም ፈቅዶልናል፡፡ 
የእርሱን ጥምቀት ተጠራጥረን ሐጢያቶቻችንን ወደ እርሱ ባናስተላልፍ ኖሮ ሞቱና ትንሳኤው ከእኛ ደህንነት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ትርጉም አልባ ይሆኑብን ነበር፡፡ በእምነት ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ በእርሱ ላይ ያኖሩ ጻድቃን ሆነው ዳግም እንዲወለዱ ከሚፈቅድላቸው ከእርሱ የመስቀል ሞት ጋር የተባበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን የእርሱን ጥምቀት ባለማመን ሐጢያቶቻቸውን በእርሱ ላይ ያላኖሩ ሰዎች ከእርሱ ሞትና ትንሳኤ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡    
አንድ ባልና ሚስት በጋብቻ ስርዓት አማካይነት ሕጋዊ ጥንዶች መሆናቸውን እንደምንቀበል ሁሉ የምዕመናን ጥምቀትም እንደዚሁ የታመነ ነው፡፡ የቅዱሳን እምነት እንዲህ ያለውን ውስጣዊ እምነት የሚገልጡበት ውጫዊ መግለጫ ነው፡፡ በእግዚአብሄር፣ በቅዱሳንና በዓለም ፊት በእርሱ ጥምቀትና መስቀል ላይ ያለንን እምነት ስናውጅ እምነታችን ይበልጥ የማይናወጥ ይሆናል፡፡   
ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀት እውነተኛ ትርጉም በተሳሳተ መንገድ ከተረዳን በኋላ በእርሱ ጥምቀትና በፋይዳው ባናምን መዳን እንደምንችል ልናምን አይገባንም፡፡ ይህ በአጭሩ የዲያብሎስ ብልጣ ብልጥ ማታለያ ነው፡፡ በራሳችን ጥምቀት በማመን ፋንታ በኢየሱስ ጥምቀት በትክክል በልባችን በማመን የሐጢያቶቻችንን ስርየት መቀበልና ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡