Search

በክርስቲያን እምነት ላይ አዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎች፤

ርዕስ 1፡ ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ መወለድ፤

1-23. በየቀኑ ሐጢያትን እየሰራሁ እንዴት ‹‹ጻድቅ ነኝ›› ማለት እችላለሁ?  

እኛ ሰዎች እንደመሆናችን ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ እስከምንሞትበት ጊዜ ድረስ ሐጢያቶችን እንሰራለን፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የዚህ ምክንያቱ መሰረታዊው ተፈጥሮዋችን ነው፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ ሐጢያት እንሰራለን፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፡፡›› (ሮሜ 3፡10) ሐዋርያው ጳውሎስ በእግዚአብሄር ፊት እንዲህ ያለው ለዚህ ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹ሐጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፡፡›› (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡15)   
‹‹አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፡፡ እርሱም ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ሐጢአትን ሰርተዋልና የእግዚአብሄርም ክብር ጎድሎአቸዋል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ፡፡›› (ሮሜ 3፡21-24)      
ይህ የእግዚአብሄር ‹‹ጽድቅ›› ማለት አጥማቂው ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ማጥመቁ ነው፡፡ እርሱ በተጠመቀ ጊዜ ዮሐንስን እንዲህ አለው፡- ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› (ማቴዎስ 3፡15) የሰው ዘር ሁሉ ወኪል የነበረው አጥማቂው ዮሐንስ ባጠመቀው ጊዜ የዓለምን ሐጢያቶች እጅግ ተገቢና ቀና በሆነ መንገድ ተሸከመ፡፡ በዚህም ዮሐንስ ባጠመቀው ማግስት እንዲህ አለ፡- ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢያት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ፡፡›› (ዮሐንስ 1፡29) 
ታዲያ እዚህ ላይ ‹‹የዓለም ሐጢአት›› ማለት ምን ማለት ነው? ይህ የሚያመላክተው በምድር ላይ የመጀመሪያዎቹ የሰው ፍጡራን ከሆኑት ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ በዚህ ዓለም ላይ እስከሚኖረው የመጨረሻው ሰው ድረስ ያሉትን የሰዎች ሁሉ ሐጢያቶች ነው፡፡ ያለፉትም ሰዎች የዓለም ክፍል ናቸው፡፡ አሁን ያሉት ሰዎችም የዓለም ክፍል ናቸው፡፡ ወደፊት የሚኖሩትም ሰዎች እንደዚሁ የዓለም ክፍል ናቸው፡፡ አልፋና ዓሜጋ የሆነው በዮርዳኖስ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ በመሸከም ለሁሉም ዘመን ሐጢያቶች አንድን መስዋዕት አቀረበ፡፡ በመስቀል ላይም ሞተ፡፡ ‹‹በዚህም›› ተቀድሰናል፡፡     
መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል፡፡›› (ዕብራውያን 10፡10) ይህ የተጻፈው ተፍጻሜትን በሚያመላክት የአሁን ጊዜ እንደሆነ ልብ በል፡፡ እኛ በእግዚአብሄር ካመንበት ቅጽበት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለሁሌም ፈጽመን ተቀድሰናል፡፡ ሐጢያት አልባም ሆነናል፡፡ ጌታ ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ የዓለምን ጅማሬና ፍጻሜ በወፍ በረር አይን ያያል፡፡ እርሱ ከ2,000 አመታት ያህል ቢሆነውም ሰዎች ከዓለም ጅማሬ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሚሰሩዋቸውን ሐጢያቶች በሙሉ ወስዶዋል፡፡ ስለዚህ በመስቀል ላይ ከመሞቱ በፊት ‹‹ተፈጸመ!›› አለ፡፡ (ዮሐንስ 19፡30) እርሱ ከ2,000 አመታት በፊት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወስዶ እነዚያን ሐጢያቶች ለማንጻት በመስቀል ላይ ሞተ፡፡  
ከዳንን በኋላም እንኳን ቢሆን ሐጢያትን እንሰራለን፡፡ ምክንያቱም ሥጋችን ደካማ ነውና፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶችን በሙሉ በሰውነቱ ላይ በመሸከም ካለፉት፣ አሁን ካሉትና ከወደፊት ሐጢያቶች በሙሉ ታድጎን ለእነዚህ ሐጢያቶች በመስቀል ላይ ተኮነነ፡፡ ይህ ምሉዕና ጻድቅ የሆነ የእግዚአብሄር ማዳን ነው፡፡  
ኢየሱስ ወደፊት የምንሰራቸውን ሐጢያቶች በራሱ ላይ ባይወስድ ኖሮ አንድም ሰው በየቀኑ ከሚሰራቸው ሐጢያት አይድንም ነበር፡፡ ‹‹የሐጢአት ደመወዝሞት ነው፡፡›› (ሮሜ 6፡23) ያዕቆብና ኤሳው ገናም በእናታቸው ማህጸን ውስጥ ሳሉ ምንም መልካም ወይም ክፉ ነገር ሳይሰሩ እግዚአብሄር ሁለት ሕዝብ አድርጎ ለያቸው፡፡ ያዕቆብን ወደደው፤ ኤሳውንም ጠላው፡፡ እንዲህም አለ፡- ‹‹ታላቁ ለታናሹ ይገዛል፡፡›› (ዘፍጥረት 25፡23) ይህ ምንባብ የእግዚአብሄር ደህንነት ከእኛ ምግባሮች ጋር ምንም እንደማይገናኝ ነገር ግን በእርሱ ጥምቀትና ስቅለት በኩል ፍጹም በሆነው የእግዚአብሄር ደህንነት ለሚያምኑ ሰዎች እንደተሰጠ ይጠቁማል፡፡    
እኛ ሰዎች ከተወለድንበት ቅጽበት ጀምሮ እስከ ምንሞትበት ቅጽበት ድረስ ሐጢያተኛ ፍጡራን ሆነን ለሲዖል የታቸን ነን፡፡ እግዚአብሄር ግን ሐጢያቶቻችንን በአንድ እይታ አስቀድሞ አይቶ ስለወደደን በኢየሱስ ጥምቀትና መስቀል ሒያቶቻችንን በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ አስወገደ፡፡ የምንኖረው በተባረከ ዘመን ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ፡፡ የተቀጠረችበት ወራት እንደተፈጸመ ሐጢአትዋም እንደተሰረየ ከእግዚአብሄርም እጅ ስለ ሐጢአትዋ ሁሉ ሁለት ዕጥፍ እንደተቀበለች ወደ እርስዋ ጩኹ፡፡›› (ኢሳይያስ 40፡2) ስለዚህ የሐጢያት ባርያ የነበርንት ዘመን በኢየሱስ ጥምቀትና መስቀል ወንጌል አማካይነት አብቅቷል፡፡ በወንጌል የሚያምን ማንኛውም ሰው ከሐጢያቶቹ መዳን ይችላል፡፡ ‹‹ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን የህ ነው ይላል ጌታ፡፡ በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ ብሎ ከተናገረ በኋላ ሐጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም ይላል፡፡ የእነዚህም ስርየት  ባለበት ዘንድ ከዚህ ወዲህ ስለ ሐጢአት ማቅረብ የለም፡፡›› (ዕብራውያን 10፡16-18)   
እግዚአብሄር ከእንግዲህ ወዲህ በየቀኑ ለምንሰራቸው ሐጢያቶች አይፈርድብንም፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ አንጽቶ በኢየሱስ አማካይነት ኮንኖዋቸዋልና፡፡ 
ከዚህ የተነሳ በሕይወታችን አሁንም ድረስ ሐጢያቶችን ብንሰራም እንኳን ሐጢያት የሌለብን ጻድቃን ሆነን የጌታን ምጽአት መጠበቅና ቃሉን መከተል እንችላለን፡፡