በክርስቲያን እምነት ላይ አዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎች፤
ርዕስ 1፡ ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ መወለድ፤
1-24. የዮሐንስ ጥምቀት ምንድነው?
አጥማቂው ዮሐንስ ከኢየሱስ 6 ወራት በፊት ቀደም ብሎ የተወለደና በብሉይ ኪዳን ውስጥም በሚልክያስ የመጨረሻው ነቢይ እንደሆነ የተተነበየለት የእግዚአብሄር ባርያ ነበር፡፡
‹‹ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የባርያዬን የሙሴ ሕግ አስቡ፡፡ እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሄር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ፡፡ መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል፡፡›› (ሚልክያስ 4፡6-8)
ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ የእግዚአብሄርን ኪዳን ቃሎች ትተው ለእንግዳ አማልክቶች ይሰግዱ ነበር፡፡ እውርና ነውር ያለባቸውን እንስሶች መስዋዕቶች አድርገው ያቀርቡ ነበረ፡፡ የእግዚአብሄርንም መቅደስ የንግድ ስፍራ አድርገውት ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደዚሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት ተተንብዮለታል፡፡ ሕጉ ሰዎች ምን ያህል ሐጢያተኞች እንደሆኑ በማሳየት የሐጢያትን እውቀት ሰጥቶዋቸዋል፡፡ (ሮሜ 3፡20) በሕጉ መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው አንድ ትዕዛዝ አለመኖር ሐጢያት ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ከሕጉ አንቀጾች አንዳቸውን የተላለፈ ሐጢያተኛ በመገናኛው ድንኳን ፊት የሐጢያት መስዋዕት ያቀርብና ሐጢያቶቹን ወደ እርሱ ለማስተላለፍ በሐጢያት መስዋዕቱ ራስ ላይ እጆቹን ይጭናል፡፡ የሐጢያት ይቅርታን ለማግኘትና እንደገና ከእግዚአብሄር ጋር ለመስማማት የሐጢያት መስዋዕቱን ያርደዋል፡፡ ከዚያም ካህኑ ከደሙ የተወሰነውን ይወስድና በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ቀንዶች ላይ ይቀባዋል፡፡ የቀረውንም ደም ከመሰውያው በታች ያፈስሰዋል፡፡
ሆኖም የእስራኤል ሕዝብ በየቀኑ በርካታ መስዋዕቶችን ቢያቀርቡም ከሐጢያቶቻቸው መዳን አልቻሉም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር የዘላለም ስርዓት የሆነውን የስርየት ቀን አደረገላቸው፡፡ እግዚአብሄር በሰባተኛው ወር በአስረኛው ቀን ዓመታዊ ሐጢያቶቻቸውን ይቅር የሚለው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ በዚያ ቀን ሊቀ ካህኑ አሮን ሁለት ፍየሎችን ወስዶ ዕጣ ይጥልባቸዋል፡፡ አንዱ ለእግዚአብሄር ሌላው ደግሞ ለሚለቀቅ ፍየል ይሆናል፡፡ ከዚያም የእስራኤልን ሕዝብ ዓመታዊ ሐጢያቶች በሙሉ በእርሱ ላይ ለማኖር በፍየሉ ራስ ላይ እጆቹን ይጭናል፡፡ አሮንም ያርደውና ደሙን ወስዶ በስርየት መክደኛው ላይና ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፡፡
ቅድስቱን ስፍራ ማስተሰረይ ከፈጸመ በኋላም ሌላውን እንስሳ ያቀርባል፡፡ በሕያው ፍየሉ ላይ እጆቹን በመጫንም የእስራኤሎችን ዓመታዊ ሐጢያቶች ይናዘዝበታል፡፡ በዚህ ዘዴ ዓመታዊ ሐጢያቶቻቸው በሙሉ ወደ እርሱ ይተላለፋሉ፡፡ በተመረጠው ሰው እጅም ወደ ምድረ በዳ ይሰደዳል፡፡ እስራኤሎችም በዚህ መንገድ ከዓመታዊ ሐጢያቶቻቸው ይድኑ ነበር፡፡
ሆኖም በብሉይ ኪዳን ሕግ መሰረት የቀረበው መስዋዕት ያለ ማቋረጥ መስዋዕቶችን ያቀረቡትን ፍጹማን ሊያደርጋቸው አልቻለም፡፡ ይህ ሊመጡ ያሉ (የመሲሁ የጽድቅ ምግባሮች) በጎ ነገሮች ጥላ ብቻ ነበር፡፡ (ዕብራውያን 10፤1) የእስራኤል ሕዝብ አዳኙን ኢየሱስ ክርስቶስን አልጠበቁትም፡፡ በፋንታው በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያሉትን የነቢያቶች ቃሎች ትተው የሐጢያተኛውን ዓለም እንግዳ አማልክቶች አመለኩ፡፡
ስለዚህ እግዚአብሄር የእስራኤሎችን ልብ ለማደስ፣ ወደ እርሱ ለመመለስና ልባቸውም ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲቀበል ለማዘጋጀት አጥማቂውን ዮሐንስን እንደሚልክ ተነበየ፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ ኢየሱስን ከማጥመቁ በፊት በይሁዳ ምድረ በዳ ሕዝቡን በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ፡፡
እነርሱን በውሃ ያጠምቅ የነበረበት አላማው ኢየሱስን እንዲጠብቁና እንዲያምኑበት ለመምራት ነበር፡፡ እርሱ አዳኙ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ በእጆች መጫን መንገድ በእርሱ እንደሚጠመቅና እነርሱን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ለማዳን እንደሚሰቀል አስተማረ፡፡ እርሱ ኢየሱስ እንሚመጣና ያለፉትን ጎዶሎ መስዋዕቶች ወስዶ በሥጋው የዘላለም መስዋዕት እንደሚያቀርብ ተናግሮዋል፡፡ የእስራኤል ሕዝብ ነውር የሌለበትን የሐጢያት መስዋዕት በማቅረብ፣ እጆቻቸውን በእርሱ ላይ በመጫንና በብሉይ ኪዳን ውስጥ ባለው የመስዋዕት ስርዓት መሰረት በማረድ እንደዳኑ ሁሉ እርሱም በጥምቀት አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወስዶዋል፡፡
ብዙ እስራኤላውያን ሐጢያቶቻቸውን ተናዘውና ንስሐ ገብተው በእርሱ ተጠምቀዋል፡፡ ‹‹ንስሐ›› ማለት ‹‹አእምሮን ወደ እግዚአብሄር መመለስ›› ማለት ነው፡፡ እነርሱ የብሉይ ኪዳንን ሕግ በማስታወስ ወደ ዮሐንስ መጥተው እስከሚሞቱ ድረስ ሐጢያቶችን ከመስራት በቀር ምንም ማድረግ ያልቻሉ ተስፋ ቢስ ሐጢያተኞች እንደነበሩ ተናዘዙ፡፡ በሕጉ መሰረትም በመልካም ምግባሮቻቸው መንግሥተ ሰማይ መግባት እንደማይችሉም ተናዝዘው ሐጢያቶቻቸውን ለአንዴና ለመጨረሻ በመደምሰስ የመንግሥተ ሰማይን በር ወለል አደርጎ ወደሚከፍትላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ አእምሮዋቸውን መለሱ፡፡
አጥማቂው ዮሐንስ ለእስራኤል ሕዝብ የሰጠው ጥምቀት የሚከተለው ነበር፡፡ በሕይወታቸው ምን ያህል ሐጢያት እንደሚሰሩ እንዲናዘዙ፣ ንስሐ እንዲገቡና ልክ እነርሱን እንዳጠመቀውም የሰው ዘር ወኪልና ሊቀ ካህን በሆነው በእርሱ የተጠመቀውንና ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ሊያድናቸውም የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲመለከቱ ፈቀደላቸው፡፡ እውነተኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንስሐ ይህ ነው፡፡
ስለዚህ ዮሐንስ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፡- ‹‹እኔስ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፡፡ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፡፡›› (ማቴዎስ 3፡11)
አጥማቂው ዮሐንስ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደሚወስድና (ዮሐንስ 1፡29) ለእነርሱም በይፋ እንደሚሞት በመመስከር የሕዝቦቹን አእምሮ ወደ ኢየሱስ መለሰ፡፡ በዚህም ኢየሱስ ራሱ ዮሐንስን የጽድቅን መንገድ ሊያሳየን እንደመጣ መሰከረ፡፡ (ማቴዎስ 21፡32)