Search

የመገናኛው ድንኳን ጥናት፤

የምስክሩ ታቦት

የኪዳኑ ታቦት
 
የኪዳኑ ታቦት ይዞታዎች
 
የምስክሩ ታቦት ርዝመቱ 113 ሳንቲ ሜትር (3.7 ጫማ)፣ ወርዱ 68 ሳንቲ ሜትር (2.2 ጫማ) እና ቁመቱ 68 ሳንቲ ሜትር (2.2 ጫማ) ሆኖ ከግራር እንጨት የተሰራና በንጹህ ወርቅ የተለበጠ ነበር፡፡ በዚህ ታቦት ውስጥ አስርቱ ትዕዛዛት የተቀረጹባቸው ሁለት የድንጋይ ጽላቶችና መናውን የያዘ የወርቅ ማሰሮ በኋላ ደግሞ ያበበችው የአሮን በትር ነበሩበት፡፡ 
በታቦቱ ላይ የተቀመጠው የስርየት መክደኛ የተሰራው ከንጹህ ወርቅ ነበር፡፡ በሁለቱም ጫፎቹ ክንፎቻቸውን ከበላዩ የዘረጉና የታቦቱን መክደኛ ማለትም የስርየት መክደኛውን የሸፈኑ ኪሩቤሎች ነበሩ፡፡ ኪሩቤሎቹ ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ፡፡ የስርየት መክደኛው እግዚአብሄር በእምነት ወደ እርሱ በቀረቡት ላይ ጸጋውን የሚለግስበት ስፍራ ነው፡፡ 
በታቦቱ በእያንዳንዱ ማዕዘን ላይ አራት ቀለበቶች ተደርገዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ወገን ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ተደርገዋል፡፡ ታቦቱ ለሸክም እንዲመች በቀለበቶቹ ውስጥ መሎጊያዎች ገብተዋል፡፡ እነዚህ መሎጊያዎች ከግራር እንጨት ተሰርተው በወርቅ የተለበጡ ነበሩ፡፡ በአንዱ ወገን ባሉት ሁለት ቀለበቶች ውስጥ መሎጊያዎችን በማስገባት እግዚአብሄር ሁለት ሰዎች አንስተው ሊሸከሙት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡ ጌታችን እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹በስርየት መክደኛው ላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ፡፡››          
እግዚአብሄር በታቦቱ ውስጥ መሎጊያዎችን በማኖር የምስክሩን ታቦት ከስርየት መክደኛው ጋር አብረው እንዲሸከሙት እስራኤሎችን አዘዛቸው፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሄር ወንጌል በመላው ዓለም እንድናሰራጭ ይፈልግብናል ማለት ነው፡፡ ለዕጣኑ መሰውያውም ይኸው ነገር እውነት ነው፡፡ ማለትም በሁለቱም ወገን ቀለበቶች ተደርገውለት ነበር፡፡ በእነዚህ ቀለበቶች ውስጥ መሎጊያዎች ይገቡና ሁለት ሰዎች መሰውያውን ይሸከሙታል፡፡ 
ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ የመስዋዕቱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባል፡፡ ከዚያም ይህንን የመስዋዕቱን ደም በትክክል ሰባት ጊዜ ያህል ይረጨዋል፡፡ እግዚአብሄር በዚህ ጊዜ እስራኤሎችን በዚህ የስርየት መክደኛው ላይ እንደሚገናኛቸው ተናግሮዋል፡፡ እግዚአብሄር ሊቀ ካህኑ ያለውን ዓይነት እምነት ማለትም በመስዋዕታዊው ስርዓት ውስጥ የተገለጠው የሐጢያት ስርየቱ እምነት ያለውን ማንኛውንም ሰው ይገናኘዋል፡፡ 
በስርየት መክደኛው ላይ የሚረጨው የመስዋዕቱ ደም እግዚአብሄር በሐጢያት ላይ ያለውን ቅን ፍርድና ለሰው ዘር የሚሰጠውን ምህረት ያሳያል፡፡ በሰባተኛው ወር በአስረኛው ቀን ላይ የሚውለው የስርየት ቀን ሊቀ ካህኑ አሮን የእስራኤልን ሕዝብ ዓመታዊ ሐጢያቶች በሙሉ ለማሻገር እጆቹን በመስዋዕቱ ቁርባን ላይ  ይረጫል፡፡ ከዚያም ያርደውና ደሙን ይወስዳል፡፡ ከዚያም ይህንን ደም ወደ መጋረጃው ውስጥ በማስገባት በስርየት መክደኛው ላይ ይረጨዋል፡፡ (ዘሌዋውያን 16፡11-16) 
እንዲህ በተረጨው ደም አማካይነት እግዚአብሄር እስራኤሎችን ተገናኝቶ የሐጢያት ይቅርታን በረከት ሰጥቶዋቸዋል፡፡ እግዚአብሄር የመስዋዕቱን ስርዓት ያቋቋመው በእስራኤሎች ላይ ካለው ጸጋ የተነሳ ነበር፡፡ እግዚአብሄር በመስዋዕት እንስሳውና በደሙ ላይ በሚከናወነው እጆችን መጫን አማካይነት ሐጢያቶቻቸውን በጽድቅ ደምስሶ በጸጋው ምህረቱን ማለትም የሐጢያታቸውን ስርየት ሰጣቸው፡፡