Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 3፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል

[3-9] የአብን ፈቃድ በእምነት እንፈጽም፡፡ ‹‹ ማቴዎስ 7፡21-23 ››

የአብን ፈቃድ በእምነት እንፈጽም፡፡
‹‹ ማቴዎስ 7፡21-23 ››
‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ  የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያን ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም፤ በስምህ አጋንንትን አላወጣንምን፤ በስምህ ብዙ ተዓምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመጸኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ፡፡››
 

ምናልባት እኔም አንዱ ነኝ…፡፡
 
‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ› የሚል ሁሉ መንግሥተ ሰማያት ይገባልን? 
አይገባም፤ የሚገቡት የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚያደርጉ ብቻ ናቸው፡፡ 
 
ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም›› ይላል፡፡ እነዚህ ቃሎች በበርካታ ክርስቲያኖች ልቦች ውስጥ ፍርሃትን በመጫር የእግዚአብሄርን ፈቃድ ያደርጉ ዘንድ እንዲጥሩ አድርገዋቸዋል፡፡
በርካታ ክርስቲያኖች መንግሥተ ሰማያት ለመግባት የሚያስፈልጋቸው ብቸኛው ነገር በኢየሱስ ማመን እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ› የሚል ሁሉ መንግሥተ ሰማያት እንደማይገባ ማቴዎስ 7፡21 ይነግረናል፡፡
ይህንን ጥቅስ ያነበቡ ብዙዎች ‹‹አንዱ እኔ ሳልሆን አልቀርም›› ይላሉ፡፡ ‹‹አይደለም፤ ኢየሱስ የተናገረው ስለማያምኑት ነው›› በማለት ራሳቸውን ይሸነግላሉ፡፡ አሳቡ ግን በአእምሮዋቸው ውስጥ ይቀርና ያውካቸዋል፡፡
ስለዚህ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ›› በሚለው የጥቅሱ ቀጣይ ክፍል ላይ ይንጠለጠላሉ፡፡ ‹‹የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ›› በሚሉት ቃሎች ላይ በመንጠልጠል አስራትን በታማኝነት በመክፈል፣ የንጋት ጸሎት በመጸለይ፣ በመስበክ፣ በጎ ምግባሮችን በማድረግና ሐጢያትን ባለመስራት ያንን ማድረግ እንደሚችሉ ያስባሉ፡፡…ጠንክረው ይሞክራሉ፡፡ እነርሱን ማየት ያሳዝነኛል፡፡
ብዙ ሰዎች ይህንን ጥቅስ ባለመረዳታቸው ስህተቶችን ይሰራሉ፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የእግዚአብሄርን ፈቃድ አውቀን በዚያ እንኖር ዘንድ ይህንን ጥቅስ በግልጽ ላብራራው እወዳለሁ፡፡
በመጀመሪያ የእግዚአብሄር ፈቃድ ልጁ የሰዎችን ሐጢያቶች በሙሉ መውሰዱንና በዚህም እኛን ከሐጢያት ነጻ ማድረጉ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡
በኤፌሶን 1፡5 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹በበጎ ፈቃዱ እንደወደደ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን፡፡››
በሌላ አነጋገር የእርሱ ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ያስወገድበትን እውነተኛ ወንጌል አውቀን ዳግም እንድንወለድ መፍቀድ ነው፡፡ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወደ ልጁ ኢየሱስ በማሻገር ከውሃና ከመንፈስ ዳግም እንድንወለድ ይፈልጋል፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡
 

‹‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ›› ለማለት ብቻ፡፡
 
በኢየሱስ ስናምን ምን ማወቅ አለብን?
የአብን ፈቃድ፡፡
 
‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡›› (ማቴዎስ 7፡21)
የአብን ፈቃድ በሁለት መንገድ መረዳት አለብን፡፡ በቅድሚያ ለሐጢያቶቻችን ይቅርታን ማግኘትና ከውሃውና ከመንፈስ ዳግም መወለዳችን የእርሱ ፈቃድ እንደሆነ ማወቅ ይገባናል፡፡ ሁለተኛ በዚያ እምነት መሰረት መስራት አለብን፡፡
በምድር ላይ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ሐጢያት መደምሰስ የእርሱ ፈቃድ ነው፡፡ ሰይጣን ቅድመ አያታችን አዳም በሐጢያት እንዲወድቅ አደረገ፡፡ ነገር ግን የአባታችን ፈቃድ የሰውን ሐጢያቶች በሙሉ ማጥፋት ነው፡፡ አሥራትን በታማኝነት መክፈልና የንጋት ጸሎት መጸለይ ለእኛ የአብ ፈቃድ ሳይሆን ሁላችንንም ከሐጢያት ማዳን ነው፡፡ ሁላችንንም በሐጢያት ባህር ውስጥ ከመስመጥ ማዳን የእርሱ ፈቃድ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ማንም ‹‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ›› የሚል ሁሉ መንግሥተ ሰማያት እንደማይገባ ይናገራል፡፡ ይህም ማለት በኢየሱስ ማመን ብቻ ሳይሆን አባታችን ከእኛ የሚሻውን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ አዳምና ሔዋን ያስቀመጡልን ቅርስ ቢኖር በሐጢያት ውስጥ መኖር መሆኑን ስለሚያውቅ ከሐጢያትና ከሲዖል ፍርድ ያድነን ዘንድ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡
 


የእግዚአብሄር ፈቃድ፡፡

 
የእግዚአብሄር ፈቃድ ምንድነው? 
ከሐጢያቶቻችን በማንጻት እኛን የእርሱ ልጆች ማድረግ፡፡
 
ማቴዎስ 3፡15 ‹‹እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና›› ይላል፡፡ ኢየሱስ ሁላችንንም ለማዳን ወደዚህ ዓለም የመጣው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈጸም ነበር፡፡ ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ የእግዚአብሄር ፈቃድ ተፈጸመ፡፡
እርሱ እኛን ለማዳንና የእርሱ ልጆች ለማድረግ ፈለገ፡፡ ያንን ለማድረግ የእርሱ ልጅ የእኛን ሐጢያቶች ሁሉ መውሰድ ነበረበት፡፡ ለዚህም በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ የወደቁትን ሰዎች ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ ልጁን ላከ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ የእርሱ ልጆች ይሆኑ ዘንድ የገዛ ልጁን ሕይወት ለእነርሱ ሲል ማቅረብ ነበረበት፡፡
ኢየሱስ በተጠመቀና በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የእግዚአብሄር ፈቃድ ተፈጸመ፡፡ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ሐጢያቶቻችን ወደ እርሱ እንደተሻገሩና በመስቀል ላይ ሞቱም የመተላለፎቻችንን ፍርዶች በሙሉ እንደወሰደ ማመን እግዚአብሄር ለእኛ ያለው ፈቃድ ነው፡፡
‹‹እግዚአብሄር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡›› (ዮሐንስ 3፡16) እግዚአብሄር ሕዝቡን ከሐጢያት አዳነ፡፡ ያንን ለማድረግ ኢየሱስ በይፋ አገልግሎቱ መጀመሪያ ያደረገው ነገር ቢኖር በአጥማቂው ዮሐንስ መጠመቅ ነው፡፡
‹‹ኢየሱስም መልሶ፡- አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው፡፡ ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡›› (ማቴዎስ 3፡15) ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም መምጣቱ፣ በጥምቀቱ አማካይነትም የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ መውሰዱ፣ በመስቀል ላይ መሞቱና መነሳቱም የእግዚአብሄር ፈቃድ ነበር፡፡
ይህንን በግልጽ ማወቅ አለብን፡፡ ብዙዎች ማቴዎስ 7፡21ን በማንበብ ቤተክርስቲያንን ለመገንባት ዓለማዊ ሐብቶቻችንን በሙሉ በመስጠት እስከ ሞት ድረስ ጌታን ማገልገል እግዚአብሄር ለእኛ ያለው ፈቃድ ይህ እንደሆነ ያስባሉ፡፡
ውድ ወዳጆች እኛ በኢየሱስ የምናምን መጀመሪያ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ ከዚያም መፈጸም አለብን፡፡ የእርሱን ፈቃድ ሳታውቁ ራሳችሁን ለቤተክርስቲያን ቀድሶ መስጠት ስህተት ነው፡፡
ሰዎች በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኖቻቸው አምኖ ከመኖር ውጪ ሌላ ምን አማራጭ አለ በማለት ራሳቸውን ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን እኔ ራሴ በፕሪስባይቴርያን ቤተክርስቲያን ውስጥ የካልቪንን ትምህርት ተምሬያለሁ፡፡ እንደ ማንኛውም መጋቢ ሃይማኖተኛ በነበረች አሳዳጊ እናት እጅም አድጌያለሁ፡፡  ‹‹ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን›› ተብሎ በሚጠራ ውስጥ ተማርሁ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ከብንያም ነገድ በመሆኑና በወቅቱ በነበረው በገማልያል እግር ስር ሕግን በመማሩ ትምክህት ነበረው፡፡ ጳውሎስ ዳግመኛ ከመወለዱ በፊት በኢየሱስ ያመኑትን ለማሰር እየተጓዘ ነበር፡፡ ነገር ግን በደማስቆ መንገድ ላይ በኢየሱስ አመነና ከውሃና ከመንፈስ ዳግም በመወለድ በረከት አማካይነት ጻድቅ ሆነ፡፡
 


የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከማድረጋችን በፊት ልናውቀው ይገባናል፡፡

 
በኢየሱስ ከማመናችን በፊት የሚያስፈልገው ምንድነው?
በመጀመሪያ ፈቃዱን ማወቅ አለብን፡፡
 
ቅድስናችን የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡ ‹‹ይህ የእግዚአብሄር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፡፡›› (1ኛ ተሰሎንቄ 4፡3) በውሃውና በመንፈሱ አማካይነት ሙሉ በሙሉ መቀደስና በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በእምነት መኖር የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡
በኢየሱስ የሚያምን ነገር ግን በልቡ አሁንም ድረስ ሐጢያት እንዳለበት የሚያስብ ከሆነ በእግዚአብሄር ፈቃድ መሰረት እየኖረ አይደለም፡፡ የእርሱን ፈቃድ መከተል በኢየሱስ በተገኘው ደህንነት አማካይነት መቀደስን ይጠይቃል፡፡ ይህንን ማወቅ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ ነው፡፡
‹‹በኢየሱስ ብታምኑም አሁንም ድረስ በልቦቻችሁ ውስጥ ሐጢያት አለን?›› ብዬ ስጠይቃችሁ መልሳችሁ አዎን ከሆነ በግልጽ የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንደማታውቁ መናገር ይቻላል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባለን እምነት መቀደሳችንና ከሐጢያት መንጻታችን የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡
በአንድ ወቅት ታዛዥ ልጆች ያሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ አንድ ቀንም ከሁሉም ታላቅየውን ጠርቶ ‹‹ልጄ ከሜዳው ባሻገር ወዳለው መንደር ሂድ…›› አለው፡፡
አባቱ ንግግሩን ሳይጨርስ ልጁ ‹‹እሺ አባቴ›› ብሎ ወደዚያ መንደር ጉዞ ጀመረ፡፡ እዚያ ሄዶ ምን መስራት እንዳለበት ሳይጠብቅ በቀጥታ ተጓዘ፡፡
አባትየውም ከኋላው ተከትሎት ‹‹ልጄ የምልህን መስማትህና ታዛዥ መሆንህ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን እኔ እንድታደርገው የምፈልገውን ነገር ማወቅ አለብህ›› አለው፡፡
ልጁ ግን አሁንም ‹‹አባቴ ችግር የለውም፡፡ ከእኔ በላይ የሚታዘዝህ ማን አለ?›› አለው፡፡
ነገር ግን ባዶ እጁን ተመለሰ፡፡ አባቱ ምን እንደፈለገ ሳያውቅ ሊያደርገው የሚችለው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ በእውር ድንብር ታዘዘ፡፡
እኛም ኢየሱስን የማናውቀው ከሆነ ልክ እንደ ልጁ እንሆናለን፡፡ ብዙዎች የነገረ መለኮት ትምህርቶችን በመከተል፣ አስራትን በታማኝነት በመክፈል፣ ሌሊቱን በመጸለይና በመጾም ራሳቸውን ቀድሰው ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ፈቃድ አያውቁም፡፡
በልቦቻቸው ውስጥ ሐጢያት እያለ ከሞቱ ከሰማይ በር ይመለሳሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ሥራ ለመስራት በጣም ጉጉቱ ያላቸው ቢሆኑም እግዚአብሄር ምን እንደፈለገ ግን በትክክል አያውቁም፡፡
 
ዓመጻን ማድረግ ማለት ምን ማለት ነው? 
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳያውቁ ሐጢያተኛ ሆኖ በኢየሱስ ማመን ነው፡፡
 
‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያን ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም፤ በስምህ አጋንንትን አላወጣንምን፤ በስምህ ብዙ ተዓምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመጸኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ፡፡›› (ማቴዎስ 7፡22-23)
እግዚአብሄር እኛ እንድንሰራቸው የሚፈልጋቸው ነገሮችና  ከእኛ የሚጠይቀው እምነት አለ፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በጥምቀቱ እንደወሰደልን እንድናምን ይፈልጋል፡፡ ብዙዎች የወሃውንና የመንፈሱን እውነት ሳያውቁ  ትንቢት ይናገራሉ፤ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በስሙ ድንቆችን ያደርጋሉ፡፡
ድንቆችን ማድረግ ማለት በርካታ ቤተክርስቲያናትን መገንባት፣ ንብረትን ሁሉ ለቤተክርስቲያን መለገስና የገዛ ራስን ሕይወት ለእግዚአብሄር መስጠት ማለት ነው፡፡
በስሙ ትንቢትን መናገር ማለት መሪ መሆን ማለት ነው፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች ኢየሱስን እየተቃወሙት በሕጉ እንደሚኖሩ የሚታበዩ ፈሪሳውያንን ይመስላሉ፡፡ ይህ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ነን የሚሉትንም ይመለከታል፡፡
አጋንንትን ማውጣት ማለት ሥልጣንን መጠቀም ማለት ነው፡፡ ሁሉም በእምነታቸው የጋሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ጌታ በመጨረሻው ቀን እንደማያውቃቸው ይነግራቸዋል፡፡ እርሱ ሳያውቃቸው እነርሱ እንዴት ሊያውቁት እንደቻሉም ይጠይቃቸዋል፡፡
‹‹የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመጸኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ፡፡›› ይላል፡፡ በዚህ ቀን ብዙ ሰዎች ‹‹ጌታ ሆይ እኔ አምንብሃለሁ፡፡ አዳኜ እንደሆንህ አምናለሁ›› እያሉ ይጮሃሉ፡፡ እንደሚወዱት ይናገራሉ፡፡ በልባቸው ውስጥ ግን ሐጢያት አለ፡፡ ኢየሱስ ዓመጻን የሚያደርጉ (ያልዳኑ ሐጢያተኞች) ብሎ ይጠራቸዋል፡፡ ከእርሱ እንዲርቁም ይጠይቃቸዋል፡፡
በዚያ ቀን ዳግም ሳይወለዱ የሞቱትም በኢየሱስ ፊት ያለቅሳሉ፡፡ ‹‹እኔ ትንቢትን ተናግሬያለሁ፡፡ ቤተክርስቲያናትንም ገንብቻለሁ፡፡ በስምህ 50 ሚሽነሪዎችን ልኬያለሁ፡፡››
ኢየሱስ ግን ለእነዚያ ሐጢያተኞች ‹‹ከቶ አላወቅኋቸውም፡፡ እናንተ ዓመጸኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባችኋለሁ›› ይላቸዋል፡፡
‹‹ምን ማለትህ ነው? በስምህ ትንቢት መናገሬን አታውቅምን? በቤተክርስቲያን ለብዙ ዓመት አገልግያለሁ፡፡…ሌሎችም በአንተ ያምኑ ዘንድ አስተምሬአቸዋለሁ፡፡ እንዴት እኔን አታውቀኝም?››
እርሱም ሲመልስ ‹‹ከቶም አላወቅሁህም፡፡ አንተ እኔን እንደምታውቅ ብትናገርም አሁንም በልብህ ውስጥ ሐጢያት ስላለ ከእኔ ራቅ›› ይለዋል፡፡
በልብ ውስጥ ሐጢያት እያለ ማመን ወይም በደህንነት ሕግ መሰረት አለማመን በእግዚአብሄር ፊት ዓመጸኝነት ነው፡፡ ፈቃዱን ሳያውቁ ፈቃዱን ለማድረግ መሞከር ወይም  ከውሃና ከመንፈስ ዳግም የመወለድን በረከት ሳያውቁ የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም መሞከርም ዓመጸኝነት ነው፡፡ ፈቃዱን ሳይታዘዙ እርሱን መከተልም ዓመጸኝነት ነው፡፡ ዓመጸኝነት  ሐጢያት ነው፡፡
 


የእግዚአብሄር ፈቃድ በመጽሐፍ ቅዱስ፡፡

 
ጻድቃን እነማን ናቸው?
ምንም ሐጢያት የሌለባቸው ጻድቃን ናቸው፡፡
 
ከውሃና ከመንፈስ ዳግም በምንወለድበት ወንጌል እንድናምን የእርሱ ፈቃድ ነው፡፡ እውነተኛው ወንጌል ዳግም ውልደታችንን ያጠናክራል፡፡ የእርሱ ልጆች ሆነን ለወንጌሉ መኖራችንም የእርሱ ፈቃድ ነው፡፡ እኛም የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ አለብን፡፡ ነገር ግን እጅግ ብዙዎች ከውሃና ከመንፈስ ዳግም የምንወለድበትን ወንጌል አያውቁም፡፡
ሰዎችን ለምን በኢየሱስ እንደሚያምኑ ስጠይቃቸው ብዙዎች በኢየሱስ የሚያምኑት ከሐጢያቶቻቸው ለመዳን  ነው ይላሉ፡፡
‹‹ታዲያ በልባችሁ ውስጥ ሐጢያት አለ?›› ብዬ ስጠይቅ፤
መልሳቸው ‹‹አዎን አለብኝ›› ነው፡፡
‹‹ታዲያ ድናችኋል ወይስ አልዳናችሁም?››
‹‹በእርግጥ ድኛለሁ፡፡››
‹‹በልቡ ውስጥ ሐጢያት ያለበት ሐጢያተኛ ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊገባ ይችላልን?››
‹‹የለም አይችልም፡፡››
‹‹ታዲያ የምትገቡት መንግሥተ ሰማይ ነው ወይስ ወደ ሲዖል እሳቶች?››
እነርሱ መንግሥተ ሰማይ እንደሚገቡ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን መግባት ይችላሉን? ወደ ሲዖል ይወርዳሉ፡፡
አንዳንዶች በልባቸው ውስጥ ሐጢያት ያለ ቢሆንም እንኳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናቸው ብቻ መንግሥተ ሰማይ መግባት የሚችሉና እንዲህ ማድረግም የእግዚአብሄር ፈቃድ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን በመንግሥተ ሰማይ አይቀበልም፡፡
የእግዚአብሄር ፈቃድ ምንድነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የእግዚአብሄር ፈቃድ በልጁ እንድናምንና በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ በመቤዠት በረከት እንድናምን ነው፡፡
ከውሃና ከመንፈስ ዳግም በመወለድ በረከት የሚያምኑ ሰዎች የእርሱ ልጆች ይሆናሉ፡፡ የእርሱ ልጆች መሆን ክብራችን ነው፡፡ የእርሱ ልጆች ጻድቃን ናቸው፡፡
እግዚአብሄር እኛን ጻድቃን ብሎ ሲጠራን ሐጢያተኛ የሆነውን ክርስቲያን ጻድቅ አድርጎ ይቆጥረዋልን? እግዚአብሄር በጭራሽ አይዋሽም፡፡ ስለዚህ በእርሱ ፊት እናንተ ወይ ሐጢያተኛ አለበለዚያም ጻድቃን ናችሁ፡፡ ‹ያለ ሐጢያት ሆኖ መቆጠር› የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ለቅድስና የሚጠራቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትን ብቻ ነው፡፡
 
የእግዚአብሄር ልጆች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? 
የውሃውንና የደሙን ወንጌል በመቀበል ነው፡፡
 
እግዚአብሄር የሰው ልጆችን ሐጢያት በሙሉ ወደ ልጁ እንዲተላለፍ ስላደረገ ልጁ ራሱ በመስቀል ላይ ፍርድን መቀበል ነበረበት፡፡ እግዚአብሄር በጭራሽ ውሸት ሊናገር አይችልም፡፡ እርሱ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነው፡፡›› (ሮሜ 6፡23) ልጁ በሞተ ጊዜ በምድር ላይ ለ3 ሰዓታት ያህል ጨለማ ወረደ፡፡
‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ ይህም አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውኸኝ? ማለት ነው፡፡›› (ማቴዎስ 27፡46)
ኢየሱስ የሰው ልጆችን በሙሉ ከሐጢያት ለማዳን በጥምቀቱ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ወደ ራሱ ወሰደ፡፡ እንደሚሰቀልና አባቱ እግዚአብሄር እንደሚረሳው እያወቀ የሰውን ዘር ሐጢያቶች ወሰደ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በዮርዳኖስ በወሰዳቸው ሐጢያቶች የተነሳ በልጁ ላይ ፈረደና ለሦስት ሰዓታትም ፊቱን ከልጁ መለሰ፡፡
‹‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሄር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው፡፡›› (ዮሐንስ 1፡12)
እናንተ የእግዚአብሄር ልጆች ናችሁን? እኛ ከውሃውና ከመንፈሱ ዳግም የምንወለድበትን ወንጌል ስለተቀበልን ጻድቃን ነን፡፡ ከውሃና ከመንፈስ ዳግም የመወለድን ወንጌል ስለተቀበልን ዳግም የተወለድን ነን፡፡ከውሃና ከመንፈስ ዳግም የተወለዱ ጻድቃን ናቸው፡፡ አሁን እኛ ሁላችንም ጻድቃን ሆነናል፡፡
‹‹እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?›› (ሮሜ 8፡31) አንድ ጻድቅ ሰው በእግዚአብሄርና በሰዎች ፊት ራሱን ጻድቅ ብሎ በሚጠራበት ጊዜ ቤዛነትን ያላገኙ ሰዎች እርሱን ሊኮንኑት ይዳዳሉ፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እግዚአብሄር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል?›› (ሮሜ 8፡33) እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በኢየሱስ አማካይነት ጠራርጎ አስወገደና ቅዱሳን፣ ጻድቃንና ልጆቹ ብሎ ጠራን፡፡ የእግዚአብሄር ክቡር ልጆች እንድንሆን መብትን ሰጠን፡፡
እነዚያ ከውሃና ከመንፈስ ዳግም የተወለዱ የእርሱ ልጆች ናቸው፡፡ ከእርሱ ጋር ለዘላለም ይኖራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ እነርሱ በምድር ላይ የሚኖሩ ፍጡራን ብቻ ሳይሆኑ የሰማይ ዜጋ የሆኑ የእግዚአብሄር ልጆች ናቸው፡፡
እነርሱ የእግዚአብሄር ልጆች ከመሆናቸው የተነሳ የሚከሳቸው፣ የሚፈርድባቸው ወይም ከእግዚአብሄር የሚለያቸው ማንም የለም፡፡
በኢየሱስ በትክክል ለማመን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማወቅ አለብን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስንም በደንብ ማወቅ አለብን፡፡ እንደ እርሱ ፈቃድ ልንተገብረው እንችል ዘንድ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅና ማመን አስፈላጊ ነው፡፡
 


ሐጢያተኞች ከውሃና ከመንፈስ ዳግም ይወለዱ ዘንድ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡

 
እግዚአብሄር ልጁን በሐጢያተኛ ሰው ሥጋ የላከው ለምንድነው?
ሐጢያቶች ሁሉ ወደ እርሱ እንዲተላለፉ ነው፡፡
 
ቤዛነትን ማግኘታችንና ከውሃና ከመንፈስ ዳግም መወለዳችን የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡ ‹‹ይህ የእግዚአብሄር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፡፡›› (1ኛ ተሰሎንቄ 4፡3)
ሐጢያቶቻችን በሙሉ ወደ እርሱ መተላለፋቸውና እኛ መዳን እንችል ዘንድ ልጁን መላኩ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡ ይህ ከውሃና ከመንፈስ ለመወለድ የሚያስችለን የመንፈስ ቅዱስ ሕግ ነው፡፡ ይህም ከሐጢያቶቻችን በሙሉ ነጻ አወጣን፡፡
እኛ ቤዛነትን አግኝተናል፡፡ አሁንስ ሁላችሁም የእግዚአብሄርን ፈቃድ መገንዘብ ትችላላችሁን? ሁላችንንም ማዳን የእርሱ ፈቃድ ነው፡፡ እርሱ የሚፈልገው እኛ ከዓለም ጋር እንድንደራደር ሳይሆን በእርሱ ቃሎች እንድናምን ነው፡፡
ሌሎች ነፍሳቶችን ወደ እግዚአብሄር መልሰው በማምጣት ሥራ ውስጥ ተጠምደው ወንጌሉን እንዲሰብኩና በቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲኖሩ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡
ሐጢያትን የምንሰራው መስራት ፈልገን ሳይሆን ደካሞች ስለሆነን ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ እነዚያን ሐጢያቶች በሙሉ አነጻ፡፡ እግዚአብሄር የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በአጥማቂው ዮሐንስ አማካይነት ወደ ኢየሱስ አስተላለፈ፡፡ ልጁን ለዚያ ዓላማ ላከውና በዮሐንስ እንዲጠመቅ አደረገው፡፡ እኛም በዚህ በማመናችን ዳንን፡፡ ይህም የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡
 

እርሱ በላከው በኢየሱስ ማመናችንም የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡
 
ኢየሱስ በሐጢያተኛ ሰው ምሳሌ የመጣው ለምንድነው? 
የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ለማስወገድ ነው፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈጸም ማለት እርሱ በላከው ማመን ነው ይለናል፡፡ ‹‹እንግዲህ የእግዚአብሄርን ሥራ እንድንሰራ ምን እናደርግ? አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ፡- ይህ የእግዚአብሄር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው፡፡ እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሰራለህ? ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ አሉት፡፡›› (ዮሐንስ 6፡28-31)
ሕዝቡ ሙሴ ወደ ከንዓን እየተጓዘ ሳለ መናን ከሰማይ ለእስራኤሎች በመስጠት ምልክት እንደሰጠውና በዚያ የተነሳም በእግዚአብሄር እንዳመኑ ለኢየሱስ ነገሩት፡፡ (ዮሐንስ 6፡32-39) ሰዎችም ኢየሱስን ‹‹እንግዲህ የእግዚአብሄርን ሥራ እንድንሰራ ምን እናድርግ?›› ብለው ጠየቁት፡፡
ኢየሱስም የእግዚአብሄርን ሥራ ይሰሩ ዘንድ በእርሱ ማመን እንዳለባቸው መለሰላቸው፡፡ እኛም የእግዚአብሄርን ሥራ መስራት ካለብን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ማመን አለብን፡፡ ማመንና ወንጌሉን መስበክ ብቻ ሳይሆን ወንጌሉን መኖርም እግዚአብሄር ለእኛ ያለው ፈቃዱ ነው፡፡
እግዚአብሄር እንዲህ አዞናል፡- ‹‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋቸውንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡ እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡›› (ማቴዎስ 28፡19-20)
ኢየሱስ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ እንዳለብን በግልጽ ነግሮናል፡፡ ለአባቱና ለመንፈስ ቅዱስ ያደረጋቸው ነገሮችም በሙሉ በጥምቀቱ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ይህንን ስንረዳ በእግዚአብሄር ልናምንና ኢየሱስ በዚህ ዓለም ያደረገውንና መንፈሱም ስለዚያ የመሰከረውን ማመን እንችላለን፡፡
ኢየሱስ በእግዚአብሄር የተላከው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንዲመሰክር ነው፡፡ ልንድን የምንችለውም በእግዚአብሄር እውነተኛ ቃልና በአገልጋዩ ስናምን ብቻ ነው፡፡
 


የእግዚአብሄርን ሥራ ለመስራት፡፡

 
የሕይወታችን ዓላማ ምንድነው?
ወንጌሉን በመላው ዓለም በማሰራጨት የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈጸም፡፡
 
የእግዚአብሄርን ሥራ የምንሰራ ከሆነ በመጀመሪያ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ ማመን አለብን፡፡ እግዚአብሄር በላከው እንድናምንም የእርሱ ፈቃድ ነው፡፡ በኢየሱስ ለማመንም በመጀመሪያ በውሃውና በመንፈሱ እንዳዳነን ማመን አለብን፡፡
የእግዚአብሄር ፈቃድ የሚፈጸመው እኛ በኢየሱስ ስናምንና ወንጌልንም ስንሰብክ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የእግዚአብሄርን ሥራ እንሰራለን፡፡ እርሱ እንደነገረንም ከውሃውና ከመንፈሱ ዳግም በምንወለድበት ወንጌል የሚያምኑ ብቻ መንግሥተ ሰማይ እንደሚገቡ ነግሮናል፡፡
ቀጣዮቹን መሰረታዊ እውነቶች በመገንዘብ በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ የተቀመጠልንን ስፍራችንን እንውሰድ፡፡ ሐጢያቶቻችን በሙሉ በጥምቀቱ ወደ ኢየሱስ መሻገራቸውን በማወቅና በማመን እውነተኛውን የእግዚአብሄር ፈቃድ እንገነዘባለን፡፡ ለመንግሥቱ መስፋፋት ኑሩ፡፡ በመጨረሻም እስከ ዕለተ ሞታችሁ ድረስ ወንጌልን ስበኩ፡፡
አጋር ክርስቲያኖች እነዚያ የእግዚአብሄርን ሥራ የሚሰሩ ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ዳግም የተወለዱ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር በላከው ማመን ማለት የእግዚአብሄርን ሥራ መስራት ማለት ነው፡፡ ሐጢያቶቻችን በሙሉ እግዚአብሄር ወደላከው ወደ ኢየሱስ መተላለፋቸውን ማመንና ይህንንም መስበክ የእግዚአብሄርን ሥራ መስራት ነው፡፡
ሰውን ከሐጢያት የመታደጉ ሥራ ኢየሱስ በዮርዳኖስ በተጠመቀና ለሁላችንም በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ተጠናቆዋል፡፡ የእግዚአብሄር ሥራ ሁለተኛው ክፍል እርሱ በላከው ማመን የአለምን ሐጢያቶች በሙሉ በወሰደው አዳኝ ማመንና ወንጌልን በመላው ዓለም መስበክ ነው፡፡
አሁን እኛ ዳግም የተወለድን ወንጌልን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በመስበክ መኖር ይገባናል፡፡
 
የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሳያውቁ በኢየሱስ የሚያምኑ የሚሄዱት ወዴት ነው? 
የሚሄዱት ወደ ሲዖል ነው፡፡
 
‹‹በዚያን ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም፤ በስምህ አጋንንትን አላወጣንምን፤ በስምህ ብዙ ተዓምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመጸኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ፡፡›› (ማቴዎስ 7፡22-23)
ይህ ምንባብ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኞቹ እነማን እንደሆኑና ዓመጻን የሚያደርጉትም እነማን እንደሆኑ በግልጽ ያሳየናል፡፡
‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ› በሚሉት መካከል ዳግም ያልተወለዱ በርካቶች ናቸው፡፡ በልቦቻቸው ውስጥ ሐጢያት ስላለ እየተሰቃዩ ነው፡፡ ስለዚህ ከፊል ማጉረምረም በሚመስል መንገድ እውነተኛ የአምልኮ ጸሎት በማይመስል ሁኔታ ‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ› እያሉ በመጣራት ወደ እግዚአብሄር ይጮሃሉ፡፡
በጸሎት ቢጮሁ ሕሊናዎቻቸው እንደሚነጹላቸው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ሐጢያት በልቦቻቸው ውስጥ ስለሚቀሩ ይህ የሚቻል አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሩቅ ያለ ይመስልም በስቃይ እየጮሁ በተራሮች ላይ ይጸልያሉ፡፡ ምሉዕ እምነት ከሌለን በተደጋጋሚ ‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ› ብለን ወደ መጣራቱ እናዘነብላለን፡፡
ጉባኤው ዳግም ባልተወለደባቸው አንዳንድ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ በከፍተኛ የስሜት ግለት ስለሚጸልዩ ምስባኩ ይሰበራል፡፡
ነገር ግን ‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ› የሚል ሁሉ መንግሥተ ሰማይ እንደማይገባ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማየት እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄርን ሥራ የሚሰሩ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ብቻ ናቸው፡፡
እግዚአብሄር አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ሐጢያት እያለበት የእግዚአብሄርን ስም ቢጠራ ይህ ዓመጸኝነት መሆኑን ይናገራል፡፡ በተራራ ላይ በሚደረጉ የጸሎት ስብሰባዎች ላይ ተገኝታችሁ ታውቃላችሁን? አንዳንድ ዕድሜ ጠገብ ሴት ዲያቆናት የእርሱን ስም በመጥራት ደጋግመው ያለቅሳሉ፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስን በእውነት አልተገናኙትም፡፡ መንፈሱንም በልቦቻቸው ውስጥ አልተቀበሉትም፡፡ ከውሃና ከመንፈስም አልተወለዱም፡፡ ስሙን በጥድፊያ የሚጠሩት  ወደ ሲዖል እንወርዳለን በሚል ስጋት ውስጥ ስለሚኖሩ ነው፡፡
መጋቢ ወይም ሚሽነሪ ሆኖ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሕይወቱን የሰጠ ሰው በእግዚአብሄር ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት አጣ ብላችሁ ገምቱ፡፡ ወላጅ ወይም ሚስት ቢተዉዋችሁ ልባችሁ ይሰበራል፡፡ የነገሥታት ንጉሥና የነፍሳቶች ሁሉ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሄር ቢተዋችሁ የት ትደርሳላችሁ?
ይህ በእናንተ ላይ እንደማይደርስ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል አድምጡና እመኑበት፡፡ ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ዳግም መወለዳችንና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ መኖራችን የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡
እኛ ክርስቲያኖች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመንና  ጥንካሬንም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማግኘት አለብን፡፡ ከእግዚአብሄር ፍርድ ልንድን የምንችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡