Search

ስብከቶች፤

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[3-5] ለሎዶቅያ ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕ 3፡14-22 ››

ለሎዶቅያ ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕ 3፡14-22 ››
‹‹በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ አሜን የሆነው፣ የታመነውና እውነተኛው ምስክርም፣ በእግዚአብሄርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፡- በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ፤ በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር፤ እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድ ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው፡፡ ሐብታም ነኝና ባለጠጋም ሆኜአለሁ፤ አንድም አያስፈልገኝም የምትል ስለሆንህ ጎስቋላና፣ ምስኪንም፣ ደሃም፣ ዕውርም፣ የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ ባለጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፣ ተጎናጽፈህም የራቁትነትህ ሐፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፣ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኩል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ፡፡ እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገስጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸውማለሁ፡፡ እንግዲህ ቅና፤ ንስሐም ግባ፡፡ እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፡፡ ማንም ድምጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል፡፡ እኔ ደግሞ ድል እንደነሳሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ ድል ለነሳው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ፡፡ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 14፡- ‹‹በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ አሜን የሆነው፣ የታመነውና እውነተኛው ምስክርም፣ በእግዚአብሄርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፡-››
ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈጸም እስከ ሞት ድረስ እግዚአብሄር አብን ታዘዘ፡፡ በሌላ አነጋገር የአብ ፈቃድ ከሆነ ማናቸውንም ትዕዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ ታዘዘ፡፡ ጌታችን የእግዚአብሄር አብ መንግሥት ታማኝ አገልጋይና የእግዚአብሄር ልጅና አዳኝ እንደሆነ ስለ ራሱ የመሰከረ እውነተኛ ምስክር ነው፡፡ ጌታችን የፍጥረት መጀመሪያም አምላክ ነው፡፡
 
ቁጥር 15፡- ‹‹በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ፤ በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር፤››
እግዚአብሄር የሎዶቅያ ቤተክርስቲያንን አገልጋይ ለብ ስላለው እምነቱ ነቀፈው፡፡ ይህ አገልጋይ የእግዚአብሄር ቁጣ ይገባው ነበር፡፡ የማንኛውም ሰው እምነት በእግዚአብሄር ፊት ለብ ያለ ከሆነ እምነቱን ወይ በራድ አለበለዚያም ትኩስ በማድረግ ማጥራት አለበት፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ የሚጠይቀው እምነት ወይ በራድ አለበለዚያም ትኩስ የሆነ ግልጽ እምነት ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለማመንም ይህ ግልጽ የሆነ እምነት አስፈላጊ ነው፡፡
እግዚአብሄርን ወደ ማመን ስንመጣ ሁለት ዓይነት ምዕመናኖች አሉ፡፡ በአንድ በኩል የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነተኛ ወንጌል ነው፤ ከዚህ ውጪ ሌላ ወንጌል የለም የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ውጭ ሌሎች ወንጌሎችም አሉ ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ የእነዚህ የኋለኞቹ እምነት ለብ ያለ እምነት ነው፡፡
እነርሱ በኢየሱስ ማመን በቂ ነው፤ በእውነተኛው ወንጌልና በሐሰተኛ ወንጌሎች መካከል መለየትም አያስፈልግም ብለው ያስባሉ፡፡ ከእነርሱ አንዳንዶቹም ብቸኛው አዳኝ ኢየሱስ አይደለም፤ ደህንነት በዚህ ዓለም ላይ ባሉ በሌሎች ሐይማኖቶች ውስጥም ሊገኝ ይችላል ብለው የሚያስቡም አሉ፡፡ የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን አገልጋይ እምነትም ልክ እንደ እነርሱ እምነት በእውነተኛው ወንጌልና በሐሰተኛው ወንጌል መካከል አንዳች ግልጽ የሆነ ልዩነት ማለትም ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል በቀር ሌላ ወንጌል አለ እንደሚሉት ለብ ያለ ነበር፡፡ ይህ አገልጋይ እግዚአብሄርን ያስጨነቀውና የእርሱን ቁጣ ያከማቸው ለዚህ ነው፡፡
 
ቁጥር 16፡- ‹‹እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድ ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው፡፡››
ጌታ አምላካችን ከአገልጋዩ ግልጽ የሆነ እምነት ጠየቀ፡፡ እግዚአብሄር ትኩስም ሆነ በራድ እምነትን እንደማይወድ መገንዘብ አለብን፡፡ ስለዚህ በጌታ ስናምን በእግዚአብሄር ቃል በመለካትና በዚያም አምነን ጸንተን በመቆም በግልጽና ያለ ምንም ማወላወል ልባችንን ማቅናት አለብን፡፡ እንዲህ ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ጎን በግልጽ በመቆም ከዚህ እውነተኛ ወንጌል ውጪ ሌሎች ወንጌሎችን የሚያሰራጩትን ያለ ምንም ማመቻመች ሊጋፈጡዋቸው ይገባል፡፡ እግዚአብሄር ጻድቃን ግልጽ በሆነው የእምነት ወገን ካልቆሙ እንደሚተፋቸው ይነግረናል፡፡ አሁን እምነታችሁ የቆመው የት ነው?
 
ቁጥር 17፡- ‹‹ሐብታም ነኝና ባለጠጋም ሆኜአለሁ፤ አንድም አያስፈልገኝም የምትል ስለሆንህ ጎስቋላና፣ ምስኪንም፣ ደሃም፣ ዕውርም፣ የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፡፡››
በጌታ ያላቸው እምነት ለብ ያለ የሆነ ሰዎች እምነታቸው ደህና ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ስለዚህ የእምነታቸውን ድህነት አያውቁም፡፡ የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን አገልጋይም በራሱ ለብ ያለ እምነት ረክቶ ስለነበረ በእርግጥ ምን ያህል ጎስቋላ እንደነበር መረዳት ተስኖት ነበር፡፡ ስለዚህ ግልጽና ትክክለኛ እምነት እንዲኖረው ለእውነት ሲል መከራዎችንና ስደትን መጋፈጥና ከዋሾዎችም ጋር ጦርነት መግጠም አስፈለገው፡፡ በእርግጥ እምነት አልባ፣ ደሃና የተራቆተ መሆኑን ማወቅ የቻለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡
 
ቁጥር 18፡- ‹‹ባለጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፣ ተጎናጽፈህም የራቁትነትህ ሐፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፣ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኩል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ፡፡››
እግዚአብሄር ለሎዶቅያ በተክርስቲያን አገልጋይ እምነቱን እንዲያጠራ ነገረው፡፡ የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን አገልጋይ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለውን የእምነቱን መሰረት ዳግመኛ መገንባትና ምሉዕ የሆነ የጽድቅ ልብስ መልበስ አለበት፡፡ መመለሱን ተመልክቶም እምነቱን በጽናት መጠበቅ አለበት፡፡ እምነቱንም በግልጽ ዳግመኛ ማብራራት አለበት፡፡ እምነቱንም በጽናት መጠበቅ አለበት፡፡ እምነቱን በማጥራትም ተስፋውን መፈጸም አለበት፡፡
እናንተም እንደዚሁ እግዚአብሄር ለሰው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የእውነት ወንጌል ከበድ ባለ መከራና ስደት ውስጥ ማለፍ አለባችሁ፡፡ ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነት ምን ያህል ክቡር እንደሆነ መገንዘብ የምትችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የተገኘውን የእግዚአብሄር ጽድቅ ለመጠበቅ የራሳቸውን የሰው ጽድቅ አፍርሳችሁ ታውቃላችሁን? የሰውን ጽድቅ ያፈረሱ ሰዎች የእግዚአብሄር ጽድቅ ምንኛ ክቡርና የተባረከ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ በእግዚአብሄር የሚታመን እምነት ከሌላችሁ እምነታችሁ አይረቤ እንደሚሆን መገንዘብ አለባችሁ፡፡ ስለዚህ ጌታ ከእኛ በፊት ለቀደሙት አገልጋዮቹ ከሰጠው እምነት መማርና የእምነት አልባነታችሁን ሐፍረት መሸፈን አለባችሁ፡፡
እውነተኛውን እምነት ለመማር መስዋዕትነት የሚያስከፍል የመሆኑን እውነት መርሳት የለብንም፡፡ እውነተኛውን እምነት የምንማረው መንፈሳዊ ፋና ወጊዎች የተራመዱትን የእምነት እርምጃ ደረጃ በደረጃ በመራመደ የመስዋዕትነትን ዋጋ መክፈል አለብን፡፡ ለጌታ መንግሥት ግንባታና ለእምነታችን መዳበርና ለጌታ ስንል የዓለምን ነገሮችና እያንዳንዱን ነገር ለመጣል ዝግጁ መሆን አለብን፡፡
 
ቁጥር 19፡- ‹‹እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገስጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸውማለሁ፡፡››
ጌታ እምነታቸው ሥራ አልባ ከሆነ የእርሱን ፍቅር የሚያውቁትንና የሚያምኑትን ሰዎች ይገስጻል፤ ይቀጣልም፡፡ ስለዚህ ጌታ የሚወዳቸው ሰዎች ለእርሱ ጠንክረው መስራትና እርሱንም በእውነተኛ እምነት መከተል አለባቸው፡፡
 
ቁጥር 20፡- ‹‹እንግዲህ ቅና፤ ንስሐም ግባ፡፡ እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፡፡ ማንም ድምጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል፡፡››
የእግዚአብሄር አገልጋዮች የሆኑ ሰዎች በደስታና በሐዘን ከእርሱ ጋር ሕይወታቸውን ይጋራሉ፡፡ ለእግዚአብሄር የሚሰሩ ሰዎች ሁልጊዜም በጌታ ቃል በማመን ይኖራሉ፡፡ ጌታችንም በእምነታቸው አማካይነት ሁልጊዜም ሥራዎቹን ይፈጽማል፡፡
 
ቁጥር 21፡- ‹‹እኔ ደግሞ ድል እንደነሳሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ ድል ለነሳው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ፡፡››
እውነተኛ እምነት ሰው ሰማዕትነትን ለመቀበል ዝግጁ በመሆን አለመሆን ላይ ተመርኩዞ ሊገኝ ወይም ሊጠፋ ይችላል፡፡ በእግዚአብሄር ቃል በማመን ከሰይጣን ጋር የሚታገሉ ሰዎች ድልን ተቀዳጅተው ከጌታ ጋር ይከብራሉ፡፡ የእግዚአብሄር ቅዱሳንና አገልጋዮች ሁልጊዜም ከሰይጣን ጋር በሚደረግ መንፈሳዊ ተጋድሎ ውስጥ ይጠመዳሉ፡፡ በዚህ ተጋድሎ ውስጥ በእግዚአብሄር ቃል በማመን ሁልጊዜም ማሸነፍ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሰይጣን ጋር የሚያደርጉትን ተጋድሎ ድል ያደረጉ ሰዎች ከጌታ ጋር ይከብራሉ፡፡
 
ቁጥር 22፡- ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡››
ቅዱሳን ሁልጊዜም የእግዚአብሄርን ድምጽ መስማትና የመንፈስ ቅዱስን ምሪት መከተል አለባቸው፡፡ እንደዚያ ሲያደርጉ እምነታቸው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አብሮ የሚራመድ እምነት ይሆናል፡፡ መንፈሳዊ ድልም ሁልጊዜ የእነርሱ ይሆናል፡፡