Search

በክርስቲያን እምነት ላይ አዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎች፤

ርዕስ 1፡ ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ መወለድ፤

1-27. ‹‹ሐዋርያት በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ትልቅ ትኩረት ለማድረጋቸው›› መረጃን የሚሰጡት ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?  

በአብዛኛው የእኛን ጥምቀት ትርጉም ከኢየሱስ ጥምቀት ትርጉም መለየት ይገባናል፡፡ የውሃ ጥምቀትን በመቀበል ብቻ ዳግም ልንወለድ አንችልም፡፡ ዳግም መወለድ የምንችለው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡ እንደ ጥምቀት ወይም ግርዘት ያሉ ስርዓቶች ለእግዚአብሄር ደህንነት አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎች አይደሉም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የምዕመናኖችን የውሃ ጥምቀት ለደህንነታቸው ግዴታ አድርጎ አይገልጠውም፡፡ በፋንታው ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት ላይ ትልቅ ትኩረት ያደርጋል፡፡    
የኢየሱስ ጥምቀት ለደህንነታችን ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች ይደግፋሉ፡፡ በመጀመሪያ የእርሱ ጥምቀት በአራቱም ወንጌሎች በእያንዳንዳቸው ውስጥ ምሉዕ ለሆነው የጽድቅ ሥራው እንደ መግቢያ ሆኖ ታውጆዋል፡፡ ለምሳሌ የማርቆስ ወንጌል የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የሚጀምረው በቀጥታ ከኢየሱስ ጥምቀት ነው፡፡ ዮሐንስ ወንጌልን የጻፈው ኢየሱስ ከተጠመቀበት ቀን ጀምሮ ‹‹በነገውም›› (1፡29) እና ‹‹በሦስተኛውም ቀን›› (2፡1) የሚሉ ቃላቶችን በመጠቀም ነው፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ›› (ዮሐንስ 1፡29) በማለት ኢየሱስ በተጠመቀ ማግስት የእግዚአብሄርን ቃል ተናገረ፡፡ ከዚያም ‹‹ተፈጸመ›› (ዮሐንስ 19፡30) በማለት ለሐጢያቶቻችን ስርየት በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ዳግመኛ ከሙታን ተነሳ፡፡   
ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ሐጢያታችን ሞተ፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡3) እዚህ ላይ መጽሐፍ የሚያመላክተው ብሉይ ኪዳንን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን አንድ ሐጢያተኛ ይቅርታን ለማግኘት መስዋዕትን ማቅረብ የሚችለው እንዴት ነበር? መስዋዕቱን ከማረዱ በፊት በሐጢያት መስዋዕቱ ራስ ላይ እጆቹን ይጭናል፡፡ ‹‹በሐጢያት መስዋዕቱ ራስ ላይ እጆችን የመጫን›› ሒደት ባያደርግ ሕገ ወጥ የሆነ መስዋዕት በማቅረቡ ይቅርታን ማግኘት አይችልም ነበር፡፡  
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?›› (ሮሜ 6፡3) ታዲያ እኛ በኢየሱስ መጠመቃችን የሚቻለው እንዴት ነው? በክርስቶስ ኢየሱስ መጠመቅ ማለት በእኛ የውሃ ጥምቀት ሳይሆን በዮርዳኖስ በሆነው የእርሱ ጥምቀት ማመን ነው፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ እጆቹን በኢየሱስ ራስ ላይ በመጫን ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወደ እርሱ ያስተላለፈ የመሆኑን እውነታ ስናምን በእርሱ ውስጥ እንጠመቃለን፡፡   
‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡›› (ገላትያ 3፡27) በአጥማቂው ዮሐንስ አማካይነት በእምነት ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ወደ ኢየሱስ ያስተላለፉ ሰዎች ሐጢያት አልባ የእግዚአብሄር ልጆች ይሆናሉ፡፡ 
‹‹የሥጋንም ሰውነት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፡፡›› (ቆላስያስ 2፡11) የሥጋን የሐጢያቶች ሰውነት በማስወገድ ከሐጢያት የመዳን መንገድ በእጅ ባልተደረገ መንፈሳዊ ግርዘት መገረዝ ነው፡፡ (በሮሜ 2፡29 ላይም ‹‹መገረዝም የልብ መገረዝ ነው›› ተብሎዋል፡፡) ያም ማለት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው በልባችን ውስጥ ያሉትን ሐጢያቶች መቁረጥ በሆነው በኢየሱስ ጥምቀት ማመን ነው፡፡  
‹‹ይህም ውሃ ማለት ደግሞ ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ የሰውነትን ዕድፍ ማስወገድ አይደለም፤ ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡›› (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21) ጥምቀት የሚያድነን ምሳሌ ነው፡፡ ቀድሞውኑም እንደምናውቀው በኖህ ዘመን ሰዎች በውሃ ባለማመናቸው ጠፍተዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን በኢየሱስ ቢያምኑም የሚጠፉ ዓመጸኛ ሰዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም ውሃ በሆነው የኢየሱስ ጥምቀት አያምኑምና፡፡
ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው ወንጌሉ ላይ እንዲህ ብሎ በመጻፍ ስለ ወንጌል ሁሉን ነገር ተናግሮዋል፡፡ ‹‹በውሃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ በውሃውና በደሙ እንጂ በውሃው ብቻ አይደለም፡፡ መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው፡፡›› (1ኛ ዮሐንስ 5፡6) ኢየሱስ እኛን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለማዳን በጥምቀቱና በመስቀሉ ወደ እኛ መጣ፡፡ ዮሐንስ እንዲህም ብሎዋል፡- ‹‹በምድር የሚመሰክሩት ሦስት ናቸው፤ እነርሱም መንፈሱ፣ ውሃውና ደሙም ናቸው፡፡ እነዚህም በአንድ ይስማማሉ፡፡›› (1ኛ ዮሐንስ 5፡8) ይህም የኢየሱስ ጥምቀት፣ መስቀሉና መንፈሱ ሁሉ በአንድ ላይ አንድ ፍጹም የሆነ ደህንነትን እንደሚያዋቅሩ ይነግረናል፡፡      
ኢየሱስ ኒቆዲሞስን እንዲህ አለው፡- ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› (ዮሐንስ 3፡5) እኛ ከውሃና ከመንፈስ ዳግም ተወልደናል፡፡ ለመዳንና መንፈስ ቅዱስን እንደ ስጦታ ለመቀበል የሚያስፈልጋችሁ ነገር ቢኖር በእርሱ የውሃ ጥምቀትና መስቀል ማመን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ‹‹ዳግም መወለድ›› የሚናገረው ይህንን ነው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ንስሐ ግቡ፤ ሐጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፡፡ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡38) የሐጢያቶችን ሁሉ ይቅርታና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለማግኘት በኢየሱስ ጥምቀት ከሙሉ ልባችሁ የማይናወጥ እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ ሌላ ምን ማለት እንችላለን? የእርሱ ጽድቅ ለደህንነታችን የሚሆን ወሳኝ ምግባር እንደሆነ ብዙ ምንባቦች የሚደግፉት መሆኑን አትካድ፡፡ ክርስትና ወደ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል መመለስ አለበት፡፡   
‹‹ስለዚህ የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል ትተን ወደ ፍጻሜ እንሂድ፡፡ መሰረትን ደግመን አንመስርት፡፡ እርሱም ከሞተ ሥራ ንስሐና በእግዚአብሄር እምነት፣ ስለ ጥምቀቶችና እጆችንም ስለ መጫን፣ ስለ ሙታንም ትንሳኤ፣ ስለ ዘላለም ፍርድም ትምህርት ነው፡፡›› (ዕብራውያን 6፡1-2) እዚህ ላይ የጥንቷን ቤተክርስቲያን እውነተኛ ወንጌል ለማግኘት ፍንጭ ማግኘት እንችላለን፡፡ እነርሱ ጥምቀቶችን፣ እጆችን መጫን፣ ከሙታን የመነሳትና ክርስቲያን የሆኑትም የሚገጥማቸውን የዘላለም ፍርድ ትምህርቶች አስተምረዋል፡፡ ሁላችንም ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደና በእግዚአብሄር የጽድቅ ሕግ መሰረት ለሐጢያቶቻችን ለመኮነን በመስቀል ላይ እንደሞተ በልባችን ማመን ይገባናል፡፡